በሜልቦርን፣ በሮም፣ በቶኪዮ እንዲሁም በበርካታ አገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ የብስክሌት ውድድሮች ላይ ኢትዮጵያን ወክለዋል። በብስክሌት ስፖርት ፍቅር የተለከፉ ናቸው። ብስክሌት ሲታወስ እነሱ፤ እነርሱ ሲታወሱ ደግሞ የብስክሌት ስፖርት ሳይነጣጠሉ ይነሳሉ። ኤርትራዊያን። «በስፖርቱ ፍቅር መነደፋቸው ለምን?» የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ቀደምት ታሪኩን ለማስታወስ ስንሞክር ዘመናትን ወደኋላ መለስ ብለን መቃኘት የግድ ይለናል። ይህ ዘመን ወራሪው ፋሽስት ጣሊያንን የጥቁርን ክንድ ለማንበርከክ ድምበር ጥሶ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት የተዳፈረበት ነበር። ለእብሪቱ እና ለትቢቱ ማስታገሻ ጀግኖች አርበኞች በዱር በገደሉ እየመሸጉ ትንፋሽ አሳጥተው ወደመጣበት መልሰውታል።
መቼም ሁሉም ነገር መጥፎ አይሆንም። ወራሪ ወታደሮቹ ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ የጣሊያን ስሪት የሆኑትን እነ ቢያንኪሊ፣ ባርታሊ እንዲሁም ቦንሲት የሚል ስያሜ ያላቸው ብስክሌቶችን ይዘው ገብተው ነበር። ታዲያ እነዚህ ብስክሌቶች ፋሽስት በጀግኖች አርበኞች ድል ተደርገው ከኢትዮጰያ ጨርቃቸውን ጥለው ሲወጡ በምርኮነት አገር ውስጥ ቀርተው ነበር። ፋሽስት ጣሊያን በአምስት ዓመት የቆይታ ጊዜው ወታደሮቹ በአዲስ አበባ ብስክሌቶችን በጎዳናዎች ላይ በመጋለብ፣ ሰዎችን በማለማመድ እና ውድድር በማካሄድ የኢትዮጵያውያንን ልብ ለመማረክ ጥረት ያደርግ ነበር።
በወቅቱ በዓለም ላይ በተለይ በፈረንሳይ፣ ቤልጄም እንዲሁም ሆላንድ የመሳሰሉ አገራት ብስክሌት ተወዳጅ እና ቀዳሚው ስፖርት ነው። ለዚህ ስፖርት ኢትዮጰያውያኑ እንግዳ ቢሆኑም በቀላሉ እውቀቱን በመቅሰም ጥሩ ችሎታን አዳብረው ነበር። በጎዳናዎች ላይ እንደ ድንገት ከወራሪዎቹ ጣሊያኖች ጋር ሲገናኙ እንኳን በቀላሉ እያለፏቸው ይጓዛሉ። በዚህ ሁኔታ ላይ እንዳለ ጣሊያን ከአገሪቷ ሳይወድ በግዱ ተባረረ። የብስክሌት ስፖርት ግን በኢትዮጵያውያን እና ኤርትራዊያን ዘንድ ተወዳጅነቱ ቀጠለ።
በዚህ ወቅት ግን የብስክሌቶቹን ጥበብ ጠንቅቀው በመረዳት ከፈጣሪዎቹ ባልተናነሰ በስፖርቱ ላይ በመሰልጠን ከሌሎች ኢትዮጵያዊ ወንድሞቻቸው ጋር የሚታወቁ እጅግ በጣም በርካታ ኤርትራዊያን ነበሩ። የስፖርቱ ወዳጅ ከመሆን ባለፈ በሚሳተፉበት ውድድር ላይ ድል የሚያደርጉም ናቸው። ለባለ ሁለቱ ጎማ ተሽከርካሪ እንግዳ ከመሆን ይልቅ እንደ ባህል ይቆጥሩት ጀመር። በእነዚህ ዘመናት ኤርትራ የኢትዮጵያ አንድ አካል የነበረች ሲሆን፤ በተለይ በብስክሌት ስፖርት ከዚያ ክፍለ አገር የሚመጡ ስፖርተኞች ታዋቂ ነበሩ።
በዘመኑ እነ ካሳ ፈዲር፣ ካሳ ርእሶም፣ ሙሉጌታ ካሳ፣ታዬ ክፍሌ የሚባሉ ብስክሌተኞች ከአንዋር መስጊድ ፊት ለፊት እነ ኡስማን ኪኪያ ሱቆች አካባቢ እነ ራስ ሃይሉን የመሳሰሉ ታላላቅ መሳፍንት እና መኳንቶች በክብር ቦታቸው ላይ ተቀምጠው ውድድር ያደርጉ ነበር። የብስክሌት፣ የቦክስ እንዲሁም የአትሌቲክስ ስፖርት ቡድን በ1948 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አውስትራሊያ ሲያቀና ኢትዮጵያን በመወከል ኤርትራዊያንም ተሳታፊ ነበሩ። ጊዜው 1962 ነበር። በሮም ኦሎምፒክ ተሳትፎ ፈር ተቀዷል።
በድጋሚ ኢትዮጵያን ለመወከል በጋሽ ገረመው ደንቦባ የሚመራው እና አድማሱ መርጊያ፣ አላዛር ክፍሎም እና ጆቫኒ ማሶላን ያሳተፈው የሮም ኦሎምፒክ ላይ አሁንም ኤርትራዊያን ድርሻቸው ላቅ ያለ ነበር። በተለይ ታሪክን መለስ ብለው የሚያስታውሱን ጀግናው ብስክሌተኛ ጋሽ ገረመው ደንቦባ ኤርትራዊያን ስፖርተኞች ታዋቂና የማይበገሩ ነበሩ። በዛሬው የእሁድ ስፖርት ዝግጅታችን ያለፈውን ዘመን መለስ ብለን በመቃኘት ኤርትራዊያን ብስክሌተኞች በኢትዮጵያ የኦሎምፒክ እና አጠቃላይ የስፖርት ውድድሮች ላይ የነበራቸውን ሚና ለማንሳት የሞከርነው ያለ ምክንያት አልነበረም።
እንደሚታወቀው ኤርትራ ነፃ አገር መሆኗን ካወጀች እና እወቅናን ካገኘች ሶስት አስርት ዓመታት ሊቆጠሩ በጣት የሚቆጠሩ ዓመታት ቀርተዋል። ሆኖም በፖለቲካዊ ምክንያት በተፈጠረ አለመግባባት ማህበራዊ፣ ባህላዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ትስስሩ ተቋርጦ ወንድማማች ህዝቦች ተለያይተው ቆይተዋል። የዚህ ግንኙነት መቋረጥ ደግሞ ዛሬ ያነሳነውን ታሪካዊውን የብስክሌት ስፖርታዊ ውድድር ላይ ቀጥተኛ ተፅእኖ ያሳረፈ ነበር። በቅርቡ ግን ለሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች ብስራት የሚሆን ዜና መንግስታቱ ይፋ ማድረጋቸውን ተከትሎ ከታሰበው ፍጥነት በላይ የቀደመው ትስስር እየተጠናከረ ይገኛል።
ሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች በፖለቲካዊ ቀውስ በትስስር ከኖሩበት ህይወት ለ20 ዓመታት ተለይተው ቢቆዩም በቅርቡ ዳግም የተፈጠረውን ግንኙነት ምክንያት በማድረግ፣ የአገራቱንና የህዝቦቹን ወዳጅነት ይበልጥ ለማደስና ለማጠናከር ያለሙ በርካታ የግንኙነት መድረኮችም እየተፈጠሩ ነው። የሰላም ዘብ በመሆን ባላንጣ የሆኑትን የማቀራረብ እና እርቅ የመፍጠር ሚናው ጉልህ የሆነው ስፖርት በአገራቱ መካከል ተከፍቶ የነበረውን ሽንቁር ለመድፈን ሁነኛ መፍትሄ ሳይሆን አልቀረም። ለዚህም ይመስላል ከሳምንታት በፊት ስፖርቱ አሃዱ ብሎ ወንድማማች የሆኑትን ህዝቦች የማቀራረብ ሚናውን መወጣት የጀመረው። ይህን ጉዳይ ከቅርብ ቀናት በፊት የተደረጉ ሁነቶችን ያስታውሰናል። ሁለቱ አገራት እንደ አዲስ ግንኙነታቸውን ለማደስ ቃል ከገቡ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደው «የኢትዮ ኤርትራ የሰላም የአንድነትና የፍቅር ሩጫ» ነበር።
በፍቅር ተጀምሮ በሰላም የተጠናቀቀው ይህ ስፖርታዊ ሁነት በሺዎች የሚቆጠሩ የሁለቱ አገራት ዜጎች የተሳተፉበት ነበር። የውድድሩ አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን ታፈረ ጥቅምት 18 በተካሄደው ዝግጅት የኢትዮ ኤርትራ የፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት እንዲ ጎለብት መሰል መርሃ ግብሮች የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ ከፍተኛ እንደሆነ መግለፃቸው ይታወሳል።
ሌላኛውና ሁለቱን አገራት ግንኙነት የሚያጠናክረው ሁነት ህዳር 9 ቀን የተካሄደው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የጎዳና ላይ ውድድር ሲሆን፤ ለ18ተኛ ጊዜ በተካሄደው እና ከ44ሺ በላይ ተሳታፊዎች የተካፈሉበት ሁነት ላይ ታዋቂው ኤርትራዊ አትሌት ዘረሰናይ ታደሰ መገኘቱ እና ውድድሩን ማስጀመሩ ይናገራል። ኤርትራዊው ዘረሰናይ ታደሰ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣቱ መደሰቱን በዝግጅቱ ወቅት ይፋ ማድረጉን እና በይፋ ስፖርት የፍቅር መሰረትን መጣል የሚችል ዘርፍ መሆኑን አመላክ ቶበታል።
አትሌት ዘረሰናይ ታደሰ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2004 አቴንስ ኦሎምፒክ ቀነኒሳን እና ስለሺን ተከትሎ በ10ሺ ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ ያሸነፈ ነው። በረጅም ርቀት የትራክ፤ የአገር አቋራጭ እና የጎዳና ላይ ሩጫዎች ከኤርትራ አትሌቶች ከፍተኛውን ስኬት ያስመዘገበም ነው። ዘረሰናይ በተለያዩ የዓለም አትሌቲክስ ውድድሮች 6 የአሸናፊነት ሽልማቶች ያገኘ ሲሆን፤ አራቱን በግማሽ ማራቶን፣ አንዱን በ20 ኪሎ ሜትር እንዲሁም ሌላኛውን በ12 ኪሎ ሜትር እና የሞምባሳው የዓለም አገር አቋራጭ ላይ የተቀዳጃቸው ውጤቶች ናቸው። ምስራቅ አፍሪካን ከሚያኮሩ አትሌቶች መካከል የሚመደበው ይህ አትሌት ስፖርቱ የሰላም ድልድይ መስሪያ መሆኑን ከወንድሞቹ ጋር በመሆን አስመስክሯል።
አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ በበኩሉ፤ ስፖርት የሰላም መሳርያ መሆኑን ለማመልከት «ተመልከቱን ምንም ልዩነት የለንም፣ በሌላው ዓለም ኢትዮጵያውያንን ከኤርትራዊያን ለይቶ የሚመለከት የለም» ሲል ሁነቱን በሁለቱ አገራት መካከል የነበረው የጥላቻ ግንብ መፍረሱን ይፋ አድርጎበታል።
በመግቢያችን ላይ በስፋት ለመዳሰስ እንደሞከርነው በስፖርቱ በተለይ ደግሞ በብስክሌት እና በአትሌቲክስ ስፖርቶች ሁለቱ ወንድማማች አገራት ጠንካራ ማህበራዊ ትስስር እንዳላቸው አሳይተናል። ለዚህም ነው ከላይ የጠቀስነውን ሁነቶች በማሰናዳት ደብዝዞ የነበረውን ግንኙነት በአዲስ የፍቅር ቀለም ለማድመቅ ዋንኛ መሳሪያ የሆኑት። እስካሁን ከተደረጉት ስፖርታዊ ሁነቶች በተጨማሪ ደግሞ የአዲስ አበባ ብስክሌት ፌዴሬሽን አንድ ብስራት ይፋ አድርጓል።
ዛሬ ማለዳው ላይ በአዲስ አበባ ብስክሌት ስፖርት ጠንሳሽነት በኤርትራ የብስክሌት ፌዴሬሽን አጋርነት የታቀደ እና መዳረሻውን ኤርትራ አስመራ የሚያደርግ ልኡካን ቡድን መነሻውን ከመሃል ፒያሳ ጊዮርጊስ አደባባይ በማድረግ ጉዞውን ይጀምራል። በዚህም በርካታ አገር አቀፍ የብስክሌት ተወዳዳሪዎች የሁለቱን አገራት ወዳጅነት ያጠናክረዋል ተብሎ የታቀደው «የብስክሌት ቱር» ላይ ተሳታፊ ይሆናሉ።
የአዲስ አበባ ብስክሌት ስፖርት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ረዘነ በየነ በተለይ ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት መረጃ እንዳብራሩት፤ ወዳጅነትን ለማጠናከር ታስቦ ዛሬ በይፋ የሚጀመረው «የብስክሌት ቱር» መዳረሻውን አስመራ ያደርጋል። «የተጀመረውን የሁለቱን አገራት ወዳጅነት በተለይ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና በፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የተጀመረው ሰላም አስመልክቶ በስፖርቱ የበለጠ ለማጠንከር ታሳቢ አድርገናል» ብለዋል።
አቶ ረዘነ፤ በብስክሌት ስፖርት ሰፊ እውቅና ካላት ኤርትራ ልምድ ለማግኘት ሁነቱ ያግዘናል ብለዋል። ወደ ኤርትራ «በብስክሌት ቱር» የሚያቀናውን የልኡካን ቡድን የሚመሩት የስራ አስፈፃሚ እና የፌዴሬሽን አመራሮች ከዚህ ቀደም ወደ ኤርትራ በመጓዝ አገራዊ ትስስሩን የሚያጠናክር ሁነት ለማዘጋጀት መመካከራቸው የሚታወስ ነው። አዘጋጆቹ ይሄ ጉዞ ውድድር ሳይሆን በኢትዮጵያ እና በኤርትራ የተለያዩ ገጠራማ እና የከተማ አካባቢዎች ለሚገኙ ነዋሪዎች የልኡካን ቡድኑ የሰላም ጉዞ ወደኤርትራ እያደረገ መሆኑን ለማሳወቅ እና ግንኙነቱን ይበልጥ እንዲጠናከር ለማድረግ መሆኑን ነው ያሳወቁት።
መነሻውን ከመሃል ፒያሳ የሚያደርገው የልኡካን ቡድን በመጀመሪያ ቀን «የብስክሌት ቱር» መዳረሻውን ደብረ ብርሃን የሚያደርግ ሲሆን፤ ከፊት ለፊቱ የሚያገኛቸው ከተሞች ላይ እረፍት እያደረገ እና የሰላም ጉዞውን እያስተዋወቀ በሳምንቱ እሁድ አስመራ ይደርሳል። ከሰናፊ አዲቀዪ ከምትባል የኤርትራ ግዛት ደግሞ የአገሪቷ ተወዳዳሪዎች ኢትዮጵያውያን የልኡክ ቡድኑን በመቀላቀል በጋራ «ቱር» ያደርጋሉ። ከዚህ በተጨማሪም ቀደም ሲል ኢትዮጵያን ወክለው በብስክሌት ስፖርት ይወዳደሩ የነበሩ ኤርትራዊያን ከልኡካን ቡድኑ ጋር የሚገናኙ ይሆናል። የአዲስ አበባ ብስክሌት ፌዴሬሽን አስር ብስክሌተኞችን ይሳተፋሉ። የድሬዳዋ፣ ኦሮሚያ እንዲሁም የትግራይ ብስክሌት ፌዴሬሽኖች ጉዞው አገር አቀፍ ይዘት እንዲኖረው ከልኡካን ቡድኑ ጋር እንደሚቀላቀሉ ታውቋል።
የኢትዮ-ኤርትራ የሰላም የብስክሌት ቱር እውን እንዲሆን ከፌዴሬሽኑ ጋር በርካታ አካላት ሰርተዋል። ከእነዚህ ውስጥም በየዓመቱ ፌዴሬሽኑን በመደገፍ የሚታወቀው ኢስት አፍሪካን ቦትሊንግ «ኮካ ኮላ» ዋንኛው ነው። ይህ ኩባንያ በአገር ውስጥ በእግር ኳስ፣ አትሌቲክስ እና መሰል ስፖርቶችን በመደገፍ ማህበራዊ ኃላፊነቱን በተደጋጋሚ የሚወጣ መሆኑ ይታወቃል። ይህን በተመለከተ የዝግጅት ክፍላችን በአንድ ወቅት የካምፓኒው ዋና ማናጀር ሚስተር ዣቪ ሴልጋ አነጋግሮ ነበር።
በኢትዮጵያ ለተለያዩ ስፖርቶች እድገት እና መስፋፋት የግል ድርጅቶች ምን አይነት ሚና ሊወጡ ይገባል? በሚል ባነሳነው ሃሳብ ላይ ሚስተር ዣቪ፤ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ከመወጣቱ በፊት ከማህበረሰቡ ጋር ተቀራርቦ መስራት ዋነኛ ግቡ አድርጎ መንቀሳቀስ ይኖርበታል ብለዋል። «የእኛን አስፈላጊ ድጋፍ ለሚሹ ሁሉ በትብብር እንሰራለን፤ በአገር ውስጥ የማስተዳድረው ድርጅት ኮካ ኮላ ካምፓኒም ይህንን እንዲያደርግ አግዛለሁ» በማለት ተግባራቸውን እንደሚያከናውኑ ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ውስጥ ስፖርት እንዲያድግ የበኩላችንን አስተዋፆ ለማድረግ ወጣቱ የማህበረሰብ ክፍል ላይ ትኩረት አድርገው እንደሚሰሩም አስረድተዋል። የኢትዮ-ኤርትራ የሰላም የብስክሌት ቱር እውን እንዲሆንም የዚህ ካምፓኒ ድርሻ ጉልህ እንደሚሆን ይጠበቃል።