የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለአሉቶ እንፋሎት ጉድጓድ ቁፋሮ ፕሮጀክት የቁፋሮ መሳሪያ ለማቅረብ እና የቁፋሮ ስራውን ለማከናወን ከሁለት የቻይና እና ከአንድ የኬንያ ኩባንያዎች ጋር ስምምነት ተፈራረመ፡፡
ስምምነቱ የተካሄደው ለፕሮጀክቱ ጉድጓድ ቁፋሮ አገልግሎት የሚሰጡ የመቆፈሪያና ሌሎች ከዚህ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን መሳሪያዎችን ለማቅረብ እና 8 ጉድጓዶችን ለመቆፈር እንደሆነ በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ወቅት ተገልጿል፡፡
ይህን ስራ ሦስቱም ስራ ተቋራጮች በጥምረት እንደሚያከናውኑት ታውቋል፡፡
የፊርማ ስነ-ስርዓቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር አብርሃም በላይ እና የሶስቱም ኩባንያ ተወካዮች ተፈራርመዋል፡፡
ዶ/ር አብርሃም በፊርማ ስነ- ስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት የፕሮጀክቱን ስራ ለማከናዎን ከአመታት በፊት እንቅስቃሴ እንደተጀመረ ጠቁመው ስራውን አንዱ ወደ አንዱ ሳይገፋ የሶስቱም ስራ ተቋራጮች በጋራ በመሆን የፕሮጀክቱን ስራ እዉን ማድረግ እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡
እንደ ዶ/ር አብርሃም ገለፃ ዘርፉ ከባድና ዘመናዊ መሳሪያዎችን መጠቀም ስለሚፈልግ ብቃት ያላቸው ባለሙያዎችን በመጠቀም ተቋራጮቹ እንዲሰሩ አሳስበዋል፡፡
የፕሮጀክቱን ስራ እውን ለማድረግም ተቋሙ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የጅኦተርማል ልማት ዘርፍ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ አቶ ፍቅሩ ወልደርያም እንደገለፁት ስምምነቱ የተካሄደው ዕቃዎችን በመፈብረክ በ8 ወራት ውስጥ ለማቅረብ እና እቃው ከቀረበ በኋላ የጉድጓድ ቁፋሮውን በ1 አመት ውስጥ አጠናቆ ለማስረከብ ነው፡፡
በአሉቶ ፕሮጀክት ላይ 22 ጉድጓዶችን ለመቆፈር እንደታሰበ የተናገሩት አቶ ፍቅሩ በዚህ ስምምነት የተካሄደው የቁፋሮ ስራ ውጤታማ ከሆነ የቁፋሮ ስራዉ እንደሚቀጥል አስረድተዋል፡፡
ከሶስቱ ስራ ተቋራጮች ጋር የተካሄደው ስምምነት ከአለም ባንክ በተገኘ ብድርና ዕርዳታ የሚሸፈን የ76 ነጥብ 8 ሚሊዬን ዶላር እና የ96 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር እንደሆነም አቶ ፍቅሩ ገልፀዋል፡፡
ምንጭ ፡-የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል