የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጅማ አባጅፋር እግር ኳስ ክለብን ፌዴሬሽኑ ከሚያዘጋጃቸው ማንኛውም የእግር ኳስ ውድድሮች ማገዱን አስታወቀ።
በኢትዮጵያ ፕሪሚሪር ሊግ እየተሳተፈ የሚገኘው የጅማ አባጅፋር እግር ኳስ ክለብ ከውድድር የታገደው ለተጫዋች ደሞዝ ባለመክፈሉ መሆኑን ፌዴሬሽኑ በመግለጫው አመልክቷል።
አብዱልፈታህ ከማል ከክለቡ ጋር ውል እያለው ከመስከረም 2010 ዓ.ም ጀምሮ ውሉ በክለቡ በመቋረጡ ምክንያት ተጫዋቹ ለፌዴሬሽኑ ስነ ምግባር ኮሚቴ አቤቱታ አቅርቧል።
አብዱልፈታህ ባቀረበው አቤቱታ መሰረትም የካቲት 12 ቀን 2011 ዓ.ም ጅማ አባጅፋር ለተጫዋቹ ደሞዙን በአምስት ተከታታይ ቀናት እንዲከፍል በፌዴሬሽኑ የስነ ምግባር ኮሚቴ በኩል ውሳኔ ተሰጥቶ ነበር።
ይህ ካልሆነ ግን ፌዴሬሽኑ በክለቡ ላይ የቅጣት እርምጃ እንደሚወስድ ቢያሳውቅም ጅማ አባ ጅፋር ይህን ውሳኔ ተግባራዊ እንዳላደረገ ተገልጿል።
ክለቡ የተጫዋቹን ደሞዝ ባለመክፈሉም ከየካቲት 29 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ከሚያዘጋጃቸው ማንኛውም የእግር ኳስ ውድድሮች ማገዱን የስነ ምግባር ኮሚቴው አስታውቋል።
እንደ ኢዜአ ዘገባ የጅማ አባ ጅፋር እግር ኳስ ክለብ የስፖርት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አጃኢብ አባመጫ በበኩላቸው ክለቡ ፌዴሬሽኑ የእግድ ደብዳቤ ደርሶታል ብለዋል።
በጉዳዩ ዙሪያ የክለቡ ቦርድ አስቸኳይ ስብሰባ በማድረግ በውሳኔው ላይ ያለውን አቋም በቀጣይ እንደሚያሳውቅም ገልጸዋል።
ጅማ አባ ጅፋር በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እስካሁን ባደረጋቸው 14 ጨዋታዎች 21 ነጥብ ሰብስቦ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።