ኧረ ጎበዝ የእኛ ነገርስ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰበት መጣ! አንዳንድ ነገሮች እኮ ፈጽሞ የማይደረጉ እየመሰሉን ነው። ራሳችን እናርቃቸዋለን፤ ራሳችን ደግሞ እናደንቃቸዋለን። እኛው ገፍተን ያራቅናቸውን ነገሮች እንደገና ዳግም እንናፍቃቸዋለን። አንድ ምሳሌ ላንሳላችሁማ! ባለፈው ሰሞን ማህበራዊ ድረ ገጽ ላይ አንድ ሙስሊም ሽማግሌ የመነኩሴ ቆብ ሲሰፉ የሚያሳይ ፎቶ ሰዎች ብርቅ ሆኖባቸው ሲቀባበሉት ነበር። መጀመሪያ ትኩረት አልሰጠሁትም ነበር። አንድ እንደኔ ነገሩ ዘግይቶ የገባው ጸሐፊ ግን ስለዚያ ጉዳይ ጥሩ አድርጎ ጽፎ አገኘሁ። አሁን የእኔን ሳይሆን እሱ የጻፈውን ልንገራችሁ (ቃል በቃል አይደለም)።
‹‹እዚህ መንደር አንድ ፎቶ ሲመላለስ አየሁ። መጀመሪያ ሰውዬው በዚህ ዕድሜያቸው ልብስ እየሰፉ መሆኑ ገርሟቸው ነው ብዬ ትኩረት ሳልሰጥ አለፍኩት፤ በኋላ ሲደጋገምብኝ ምንድነው ብዬ ሳይ ግን ሰውዬው ሙስሊም ሆነው የመነኩሴ ቆብ እየሰፉ ነው። ኧረ ጎበዝ እንዴት ዘቅጠናል ግን?›› እያለ ጸሐፊው ይቀጥልና በቀልድ ይነግረናል። እኛ ዛሬ በብሄርና በሃይማኖት ጥላቻ ዘቅጠን እንጂ አባቶቻችን እኮ ይህን አያውቁትም። እንግዲህ እንደ እኛ የዘቀጠ አስተሳሰብ ቢሆን ኖሮ ሰውዬው ማለት የነበረባቸው ‹‹አይ ዞር በይ! የምበላው አጥቼ ጾሜን ተደፍቼ አድራለሁ እንጂ የመነኩሴ ቆብማ አልሰፋም!›› ማለት ነበረባቸው። እንግዲህ ሙስሊም ሆነው የመነኩሴ ቆብ መስፋታቸው ከገረመን የማይገርመን ‹‹ጾሜን አድራለሁ እንጂ የመነኩሴ ቆብማ አልሰፋም›› ቢሉ ነበር አይደል?
አንዳንድ የራሳችን የሆኑ ነገሮች ብርቅ እየሆኑብን ነው። ሙስሊምና ክርስቲያን በአንድ ማዕድ በበላበት፣ በአንድ ዕድር አብሮ በሚረዳዳበት አገር ውስጥ ነው ያ የሙስሊም ሰውዬ የመነኩሴ ቆብ መስፋት ብርቅ የሆነብን። እንዲያውም አንዱ የሰጠው አስተያየት ብዙ ሰው የወደደው ነበር። ‹‹እኚህን ሽማግሌ እኮ አንድ ሰው ሄዶ ‹የመነኩሴ ቆብ እየሰፉ ነው?› ቢላቸው ‹ዞር በል ከዚህ! ሥራ ፈት!› ነበር የሚሉት›› ብሏል። ትክክለኛ አስተያየት ነው። የምር ይህን እንዲህ የገረመንን ነገር ለእኒህ ሽማግሌ ብንነግራቸው ይስቁብን ነበር።
እውነትም ‹‹ሥራ ፈት!›› ማለታቸው አይቀርም ነበር፤ ይሄ እኮ እርሳቸው ዕድሜ ዘመናቸውን የኖሩበት ነው። እኛ ቆብ መስፋታቸው ሲገርመን እርሳቸው እኮ ከመነኩሴዋ ጋር አብረው በልተው ይሆናል። ወደ ተነሳሁበት ሀሳብ ልመለስ። አንዳንድ የማይቻል የሚመስሉን ነገሮች አሉ። የማይቻል የመሰሉን ራሳችን ስላራቅናቸው ነው። ጎበዝ እኔ እኮ የዩኒቨርሲቲ ምርቃት ሰሞን (አጭር ቀሚስ) ሚኒስካርትና ሱፍ መልበስ ግዴታ ይመስለኝ ነበር(የዋህነቴ!)። የምር የዩኒቨርሲቲው አስገዳጅ ህግ ሁሉ ይመስለኝ ነበር።
እንዲያውም የተመረቅሁ ዓመት ግቢው ውስጥ አንዲት ሴት በጣም ሹል ጫማ አድርጋ ስትሄድ ወድቃ ተስቆባት ነበር። በዚያ ላይ የለበሰችው ልብስም ከፊል ራቁት ስለነበር ለወጣቶች መሳለቂያነት የመዳረግ ዕድሏ ከፍተኛ ነበር፤ ያኔ በጣም ነበር ያዘንኩት። እንዲህ ከሚሆን የዚህ ህግና ደንብ ቢቀርስ? ብዬ ነበር (ለካ ግዴታ አልነበረም)።
ከሰሞኑ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ተማሪዎች ያሳዩት ነገር አንጀቴን ነው ያራሰው! ለምን መሰላችሁ? በአገራቸው ባህል መኩራታቸው አይደለም፤ የፈረንጅ አምላኪን ሁሉ ማሳፈራቸው ነው ያስደሰተኝ። ማድረግ እንደሚቻል ማሳየታቸው ነው ያስደሰተኝ። እንዲያውም አንዳንድ ከገጠር አካባቢ የሚመጡ ልጆች የምረቃ ሰሞን ባለመዱት ጫማ እና ባለመዱት አጭር ቀሚስ መሄድ ጭንቅ የሚሆንባቸውም ነበሩ። ይሄ ማለት ግዴታ ይመስላቸው ነበር ማለት ነው።
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በራስ መተማመን ግን አስደሳች ነው። በእውነት ይሄ ከፍተኛ በራስ የመተማመን አቅሙ እንዳላቸው የሚያሳይ ነው። በብዙ ነገሮች የተቸገርነው በራስ መተማመን በማጣት ይመስለኛል። በተለይም በአገር ባህል ላይ ትልቁ ችግራችን ይሄ ነው። እሺ ፈረንጅ ሰራሽ ጫማ እና ከፈረንጅ የተኮረጀ ከፊል ራቁትነት በራስ መተማመን ማጣት አይደለም? ይህን አለማድረግ የሆነ የበታችነት እንዲሰማን ስለሚያደርገን እኮ ነው።
በአገራችን ከ40 በላይ ዩኒቨርሲቲዎች ያሉ ሲሆን፤ በሰኔ ወር መጨረሻና በሐምሌ ወር መጀመሪያ አካባቢም ተማሪዎቻቸውን ያስመርቃሉ። ስለዚህም ዩኒቨርሲቲዎቹም ሆኑ ከተሞቹ በሰዎች ብዛት ይጥለቀለቃሉ። በእርግጥ በቴሌቪዥን የምናየው በብዛት በጋዋን የተሸፈነ ሰውነት ነው። ጋዋን ደግሞ ግዴታ ነው፤ ማዕረግም ነው። እያወራን ያለነው ግን ከምርቃት በፊትና በኋላ ስለሚኖሩ ዝግጅቶችና አለባበሳቸው ነው።
ከምርቃት በፊት ብዙ ዝግጅቶች አሉ(እንዲያውም የምርቃቱ ቀንማ መጨረሻው እኮ ነው)። በግቢው ውስጥ የሚከበሩ ብዙ ነገሮች አሉ፤ በእነዚህ ዝግጅቶች ላይ ታዲያ የሚለበሱ ልብሶች ሁሉ ፈረንጅኛ አለባበስ ናቸው። ምናልባት አልፎ አልፎ ግን የባህል ቀን በሚከበር ዕለት የባህል ልብስ ይለበስ ይሆናል።
እንግዲህ እንደ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እንዲህ በራስ መኩራት፣ በራስ መተማመን ይቻላል ማለት ነው። በፎቶው ላይ እንደምታዩት ሴቶች በባህል ቀሚስ ፣ ወንዶች በጃኖ እንዲህ ሽብርቅ ብለዋል። ይሄ የባህል ልብስ ዋጋው ቀላል እንዳይመስላችሁ! ከሱፍና ከአጭር ቀሚስ በላይ ነው። በነገራችን ላይ ከተማሪዎች ጠይቄ እንዳጣራሁት ሁሉም የትምህርት ክፍሉ ተማሪዎች አይደሉም፤ ይህን የባህል ልብስ ያልገዙም አሉ። እንዲህ ማድረጉን የተስማሙ ገዙና ተዋቡበት፤ ሱፍና አጭር ቀሚስ ወይም ሌላ ምርጫ የፈለጉትም የራሳቸውን ፍላጎት ተከተሉ።
አሁን ሁሉም የባህል ልብስ ይልበሱ ማለቴ አይደለም(እሱ እንደ ፍላጎታቸው ነው) ግን የሚያስደስተው በውጭ ባህል ተወሯል እየተባለ ከሚታማው ወጣቱ ውስጥ እነዚህ መገኘታቸው ነው። በተለይም ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ደግሞ ይሄ የተለመደ አይደለም። እኔ ራሴ እኮ ብርቅ አደረኩት አይደል? እንዳትፈርዱብኝ ጎበዝ ይሄስ ብርቅ ነው! ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ፈረንጅኛ ነገር የግዴታ መስሏል። ከሥርዓተ ትምህርቱ ጀምሮ አገርኛ ነገርን ያስረሳል። ቋንቋው የውጭ፣ የትምህርቱ ይዘት የውጭ፣ ፋሽኑ የውጭ፤ ታዲያ በዚህ ውስጥ የፈረንጅ ልብስ ግዴታ ቢመስላቸው ይፈረዳል?
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን የባህል ልብስ ‹‹ምን የማይቻል የሚመስል እያልክ ታካብዳለህ! ይሄ ቀላል አይደል እንዴ!›› የሚል ይኖር ይሆን? ብዬ አሰብኩ። የሚል ካለ በእውነቱ ጥሩ ጥያቄ ነው። ግን የማይቻል የሚመስላቸው ብዙዎች ናቸው። የማይቻል የሚመስለው እኮ መግዛቱ ወይም መልበሱ አይደለም፤ አስተሳሰቡ ነው። አስተሳሰባችን ተጨቁኗል፤ ነፃነቱን አጥቷል። የምርቃት ሰሞን ሱፍና ከራቫት ወይም አጭር ቀሚስ ግዴታ በመሰለበት ሁኔታ ሙሉ ቀሚስ ወይም ለወንዶች የወንድ የባህል ልብስ መልበስን ማሰብ ትልቅ በራስ መተማመን ይጠይቃል። የሆነውስ ሆነና ግን ይሄን ነገር መምህራንስ ያበረታቱ ይሆን? ይህን ያልኩበት ምክንያት አለኝ። እንደመደምደሚያም ይሁንና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሆነ የተባለ ታሪክ ልንገራችሁ።
ተማሪዎች የመመረቂያ ጥናት ሲያቀርቡ ነው። ሁሉም የሚያቀርቡት(መምህራንም የለመዱት) ወንዶች ሱፍ ለብሰው ነው። አንደኛው ተመራቂ የአካባቢውን የባህል ልብስ ለብሶ ገባ። መምህሩ ‹‹እንዲህ ሆነህ አታቀርብም›› አለው። በዚህም አለመግባባት ተፈጠረ። በኋላ ግን ተማሪዎችም መምህራንም የከለከለው መምህር ላይ ፈረዱበት። ‹‹እንዲህ አይነት ነገር መበረታታት ሲገባው እንዴት እንዲህ ትላለህ!›› ብለው ሲፈርዱበት ክልከላውን ተወው፤ ተማሪውም ተመረቀ፤ አሁን በሥራ ላይ ይገኛል። እስኪ እንዲህ በራሳችን እንተማመን!
ዋለልኝ አየለ