አዲስ አበባ ፡- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ባለሥልጣን ከቀድሞው የፌዴራል ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ሥር ወጥቶ ራሱን ችሎ በተቋቋመ በስድስት ወራት ውስጥ 18 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰብ መቻሉን አስታወቀ፡፡ ገቢው የእቅዱን 95 በመቶ መሆኑን ገለጸ፡፡
የባለሥልጣኑ የታክስ ጉዳዮች ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮሴፍ ግርማ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፤ ባለስልጣኑ ባለፉት ስድስት ወራት 19 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 18 ነጥብ 9 ቢሊየን ብሩን ገቢ ስብስቧል፡፡ በዚህም የዕቅዱ 95 በመቶ ማሳካት ችሏል፡፡ አፈጻጸሙም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ብልጫ አለው።
ገቢው ከታክስ፣ ቀጥተኛ ካልሆኑ ታክሶች ከማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች የተሰበሰበ መሆኑን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ጠቅሰው፣ ለገቢ አሰባሰበቡ ስኬታማነት የእያንዳንዱ የግብር ከፋይ ፣ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ሠራተኛ እና የግብር ከፋዩ አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል።
እንደ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ በከተማዋ ከ 380 ሺ በላይ ግብር ከፋይ የሚገኙ ሲሆን፣ እነዚህን አገልግሎት ፈላጊዎች በተገቢው ሁኔታ ለማስተናገድና ግብሩን በአግባቡ ለመሰብሰብም ያለፈውን አሠራር የመገምገም፣ ዕቅድ የማፅደቅ፣ ለሁሉም ሠራተኞች እንዲሁም ለ 900 ከፍተኛ ኦፊሰሮች ሥልጠና ተሰጥቷል ።
ባለፉት ስደስት ወራትም ሕገወጥ ንግድ (ኮንትሮባንድ) ፣ ታክስ መሰወር እና የመሳሰሉት ህገወጥነቶች መታየታቸውን ጠቅሰው፣ እንደዚያም ሆኖ በአዲስ አበባ ያለው አፈፃፀም የተሻለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በኮንዶሚኒየም ቤቶች ኪራይ ገቢ ግብር ዙሪያ፣ የሪል ስቴት ባለሀብቶች የሊዝ ገቢ ከመክፈል አንፃር ከፍተኛ የሆነ ክፍተት መኖሩንም ጠቅሰዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 19/2011
በኃይለማርያም ወንድሙ