በሚቀጥለው የበጀት ዓመት ትኩረት ከሚፈልጉ ዘርፎች መካከል አንዱ በሆነው የመስኖ ልማት ግብርናውን እያዘመኑ ምርትና ምርታማነት ማሳደግ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቅርቡ ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡ የዘርፉ ባለሙያዎችም ግብርናውን በማዘመን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የመስኖ ልማት ወሳኝ መሆኑን ይገልጻሉ።
የግብርና ተመራማሪው ዶክተር ብርሃኑ አምሳሉ፣ መንግሰት እስከ አሁን ለመስኖ ልማት ትኩረት እንዳልሰጠ በመጥቀስ፤ ‹‹ያለንን የውሃና የመሬት ሀብት በአግባቡ መጠቀም ችለን ቢሆን ኖሮ ከራሳችን አልፈን ሌሎችንም መመገብ እንችል ነበር›› ሲሉም ይናገራሉ።
‹‹ዝናብ ብቻ ጠብቀን እያመረትን ነው›› ያሉት ዶክተር ብርሃኑ፣ የሀገሪቱ አመራረት የምግብ እህል ፍላጎቷን በሚገባ ማረጋገጥ እንዳላስቻላት፣ አርሶ አደሩም ማግኘት የሚገባውን ጥቅም እያገኘ አለመሆኑን እንዲሁም ሀገሪቱ ወደ ውጭ መላክ ከሚኖርባት ምርት እጅግ ያነሰውን እየላከች መሆኗን ያብራራሉ፡፡ ‹‹ይህንን ማጣት ደግሞ እድገታችንን ጎትቶታል›› ይላሉ።
በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የሰብል ምርምር ዳይሬክተር ዶክተር ታዬ ታደሰ፣ የመስኖ ልማት ትኩረት ሳይሰጠው መቆየቱን በመጥቀስ የዶክተር ብርሃኑን ሃሳብ ያጠናክራሉ፡፡ በመስኖ ሊለማ የሚችል መሬትም የመስኖ አቅሙም እንዳለ ጠቅሰው፤‹‹እኛ ግን አልተጠቀምንበትም፡፡›› ሲሉም ያብራራሉ።
በአገር ደረጃ በመስኖ ልማት ስንዴን ጨምሮ የተለያዩ ሰብሎችን የማምረት ስራ በመንግስት ድጋፍ እየተከናወነ መሆኑን ዶክተር ታዬ ጠቅሰው፤ በዚህ ዓመት ብቻ ወደ 3 ሺ 300 ሄክታር አካባቢ መሬት በመስኖ ለማልማት በሙከራ ደረጃ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ይህ ግን ከልማቱ ፋይዳ አኳያ ዝቅተኛ እንደሆነ ነው ዶክተር ታዬ የሚገልጹት፡፡
በመስኖ ልማቱ እየተከናወነ ያለውን ይህን ተግባር ማስፋትና ወደ መላ አገሪቱ የሚዳረስበትን መንገድ ማመቻቸት አገሪቱ በምግብ እህል ራሷን ለመቻል የምታደርገውን ጥረት እንደሚያግዝና በውጭ ምንዛሬ እየተገዛ የሚመጣውንም ስንዴ ለማስቀረት እንደሚረዳ ያብራራሉ።
ዶክተር ብርሃኑ፣ የሀገሮችን ልምድ የመቅሰም አስፈላጊነትን ይጠቅሳሉ፡፡ ግብጽና ሌሎች አገሮች በመስኖ እያለሙ የት እንደደረሱ ማየትና ከእነሱም ልምዶችን ወስዶ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባም ያመለክታሉ።
ለመስኖ ልማት ምቹ የሆኑ አካባቢዎችን መለየትና በስፋት ትርጉም በሚሰጥ መልኩ ወደ ማምረቱ ስራ መግባት እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ፤ይህን ለማድረግ ግን ከፍተኛ ሀብት እንደሚጠይቅም ያመለክታሉ፡፡ በጥናት ላይ ተመስርቶ ኢንቨስት ማድረግም ሌላው መከናወን ያለበት ተግባር መሆኑን ይገልፃሉ።
‹‹ለእኛ የሚያስፈልገን እንደ ላይኛው አዋሽ ያሉ የመስኖ ፕሮጀክቶችን በማስፋፋት ዘላቂ የሆነ ተግባር ማከናወን ነው›› ያሉት ዶክተር ብርሃኑ፤ ይህን መሰሉን ስራ ለመስራት ግን የመንግሰት ቁርጠኝነት እጅግ በጣም ወሳኝ መሆኑን ያስገነዝባሉ። ቁርጠኝነቱንም በቂ ጥናት እንዲካሄድ በማድረግ በቂ ሀብት በመመደብ የሰው ኃይል በማሰልጠን ማሳየት እንደሚገባውም ያመለክታሉ።
ዶክተር ታዩ እንደሚሉት፤መንግሰት ያለማቸውን የመስኖ መሬቶችን በሚገባ ከመጠቀም ባሻገር ሌሎች የመስኖ ልማት ሊሰራባቸው የሚችሉ መሬቶችን መለየት ይኖርበታል፡፡ የመስኖ ልማቱን ማዘመንና ማስፋፋትም ያስፈልጋል፡፡ በዚህም ከአገሪቱ ያለፈ ሌሎችን ለመመገብ የሚያስችል አቅም ማዳበር ይቻላል፡፡
መንግስት በትምህርት ሴክተሩ ተደራሽነት ላይ ያከናወነውን ተግባርና ያሳየውን ቁርጠኝነት ያደነቁት ዶክተር ታዬ፣ በመስኖ ልማቱ ላይም ይህንን ቁርጠኝነት መድገም እንዳለበት ያስገነዝባሉ፡፡ በዚህም ስትራቴጂዎችን መቀየስ፣ የመስኖ መዋቅር መስራት፣ በጀት መመደብ፣ የሰው ኃይል ማብቃት እንደሚኖርበት ያመለክታሉ፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት መምህር ዶክተር መብሩክ መሀመድ፣ መንግስት ለመስኖ ልማቱ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ለዚህም አሁን ያለውን የመስኖ ወይም የእርሻ ልማት ሥርዓት የሚያሻሽል ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀቱን ይገልጻሉ፡፡
በፍኖተ ካርታ ዝግጅቱ ላይ የተሳተፉት ዶክተር መብሩክ፣ ፍኖተ ካርታው አገሪቱ በ3ኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መገባደጃ ላይ በመስኖ ልማት የት መድረስ አለባት የሚለውን ራእይ የሰነቀም እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
የኢትዮጵያን ሁኔታ የሚዳስስ ጥናት መደረጉን፣ በአሁኑ ወቅት በውጭው ዓለም ላይ አሉ የተባሉት የዘርፉ ቴክኖሎጂዎች ምን ላይ ደርሰዋል የሚለውም መዳሰሱን፣ የአገሪቱን የውሃ ሀብትስ በምን መልኩ ነው ለመስኖ ልማት ልናውለው የምንችለው የሚሉትን መመልከቱን ይገልጻሉ። ፍኖተ ካርታው እስከ 3ኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ማብቂያ ድረስ በስራ ላይ እንደሚውልም ይጠቁማሉ፡፡
ዶክተር መብሩክ እንዳሉት፤በመስኖ ልማቱ የታሰበው ግብ ላይ ለመድረስ ምን ዓይነት ማነቆዎች ያጋጥማሉ የሚለው ታይቶም ስድስት የትኩረት ነጥቦች ተቀምጠዋል፡፡ ያለ ሰው ኃይል ልማት ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም አስቸጋሪ እንደሚሆን በፍኖተ ካርታው መታየቱን ይገልጻሉ፡፡
የቴክኖሎጂ ደረጃና አይነትን መለየት፣ ቴክኖሎጂን ሁሌም ከውጭ ማስመጣት እንደማይቻልና በሀገር ውስጥ በማላመድ ማምረት እንደሚያስፈልግ መዳሰሱን ለእዚህ ደግሞ በውሃ ልማትና ማህበራዊ ዘርፎች ያሉ የምርምር ተቋማት ተጠናክረው መስራት እንደሚኖርባቸው መመልከቱን ያብራራሉ፡፡
ሌላው ፍኖተ ካርታ የተመለከተው የመሰረተ ልማት ጉዳይ መሆኑን ዶክተር መብሩክ ጠቅሰው፤በዚህ ከውሃ ማሰባሰብ አንስቶ እስከ መስኖ ተጠቃሚው ድረስ ያሉ የመሰረተ ልማት ሰራዎች እንደሚያስፈልጉ፣ከዚህ አንጻር ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተግዳሮቶች መለየታቸውን አብራርተው፤ ለእነዚህ ለሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች መፍትሄ እየተቀመጠ ከተሰራ በመስኖ ልማቱ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ነው ዶክተር መብሩክ ያመለከቱት፡፡
‹‹የመስኖ ልማቱ ሰፊ ሀብት ይጠይቃል›› ሲሉ ዶክተር ብርሃኑ የጠቀሱን ሀሳብ ዶክተር መብሩክ ያጠናክራሉ፡፡ ለእዚህ ስራ ሊውል በሚችለው ሀብት ምንጭ ላይ በፍኖተ ካርታው ዝግጅት ወቅት ሰፊ ውይይት መደረጉን ጠቅሰው፤ዋና ጉዳይ መሆን ያለበት ለመስኖ ልማት ትኩረት መስጠት መሆኑንም ይገልጻሉ፡፡
ለመስኖ ልማት የሚውል ገንዘብ ራሱን እንደሚተካም በመጥቀስ፤ ‹‹ተገቢውን ትኩረት ሰጥተን ወጪ የምናደርግ ከሆነ የመስኖ ልማቱ አዋጭነቱ አያጠራጥርም›› ሲሉም ነው የተናገሩት፡፡
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ በኢትዮጵያ ከ3 ነጥብ 7 እስከ 4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር በመስኖ ሊለማ የሚችል መሬት ይገኛል፡፡ ከዚህ ውስጥ በመስኖ እየለማ ያለው 7 እስከ 10 በመቶው ብቻ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በተደጋጋሚ እንዳስገነዘቡት፤ ግብርናውን በማዘመን በኢኮኖሚ ውስጥ ተገቢ ሚናውን እንዲወጣ ማድረግ ይገባል፡፡ ሀገሪቱ ወንዞቿን በመጠቀም በረሃዎቿን ገነት ማድረግ እንዳለበትም በተደጋጋሚ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገው ሽግግር ገና ረጅም ጊዜ ይፈልጋል፡፡ በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ግብርና ያለው ሚና በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ እያደገ ካለው ኢኮኖሚ አንጻር ሲታይ ለኢንዱስትሪው የሚያደርገው አስተዋጽኦ የሚጠበቀውን ያህል አይደለም፡፡
መንግስት በተለያዩ መስኮች በቁርጠኝነት ሰርቶ ለውጥ ያመጣውን ያህል በመስኖ ላይ ለውጥ ለማምጣት የመስኖ አካባቢዎችን መለየት፣ከፍተኛ በጀት መመደብ፣ የሰው ኃይል አሰልጥኖ ማሰማራት፣ በመስኖ ያደጉ ሀገሮችን ተሞክሮ መቅስምና ተግባራዊ ለማድረግ ቁርጠኛ ሆኖ መገኘት ይኖርበታል፡፡ ይህንንም ከቃል ባለፈ በተጨባጭ ማሳየት ይገባል፡፡ ለእዚህም እንዲሆን ያዘጋጀውን የመስኖ ልማት ፍኖተ ካርታ በአስቸኳይ መሬት ላይ በማውረድ በትኩረት መሰራት ይኖርበታል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 19/2011
በእፀገነት አክሊሉ