በብሔራዊ ደረጃ በኢትዮጵያ ከሚከበሩት የሙስሊም በዓላት መካከል አንዱ የነብዩ ሙሃመድ የልደት በዓል ወይም መውሊድ ነው:: የዘንድሮ 1493ኛው የመውሊድ በዓል ባሳለፍነው ማክሰኞ ተከብሯል። ስለሰዎች እና ባህላቸው ጥናት የሚያደርጉት/ኢትኖግራፒስት/ እና ጸሃፊው አፈንዲ መተቂ «መውሊድ፣ አሕባሽ እና እኛ» በሚለው ጽሁፋቸው ከንዳዳማው የዓረቢያ በረሃ ተነስቶ የዓለምን ታሪክ ለመቀየር የቻለው ታላቁ ሰው የተወለደበትን መውሊድን ልደት በዓል እኛ /ኢትዮጵያውያን/ ከጥንት ጀምሮ እናከብረዋለን በማለት ይገልፁታል።
ፀሃፊው፤ እኔ በተወለድኩባት ከተማ ገለምሶ በኢትዮጵያ ውስጥ ታላቁ የመውሊድ ማክበሪያ ስፍራ ይገኛል፡፡ በከተማዋ መውሊድ የሚከበረው ጥብቅ በሆነ እስላማዊ ባህል ነው፡፡ አንዳንዶች እንደሚሉት ሴትና ወንድ በጭራሽ ተቀላቅለው አያውቁም፡፡ የዚህን ብርቅና ድንቅ ሰው ክብርና ገድል በመንዙማ፣ በመዲህ፣ በቡርዳ እና በዚክሪ ይታወሳል፡፡ ወደፊትም በዓሉን እናከብረዋለን፤ የማታከብሩ ሰዎችም መብታችሁ ነው በማለት ሃሳባቸውን አስፍረዋል። በርካታ የአጃሚ እና የዓረብኛ ጥንታዊ ጽሁፍ መረጃዎች እንደሚያሳዩትም በኢትዮጵያ የመውሊድ በዓል በየመስጂዶቹ እና በተለያዩ የእስልምና ቦታዎች አያሌ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
ይህን ሁሉ ማለቴ እኔም መውሊድ በኢትዮጵያ በደማቅ ሁኔታ የሚከበሩባቸውና ብዙ ስላልተነገረላቸው ቦታዎች ለመጠቆም ነው። የአማራ ክልል የቀድሞው ባህልና ቱሪዝም ማስታወቂያ ቢሮ «የአማራ ክልል የቱሪስት መስህብ ሃብቶች አጭር ቅኝት» በሚል በ1991 ዓ.ም ባሳተመው መጽሀፍ ላይ እንደተገለጸው፤ በተለይ ወሎ እና አርጎባ ውስጥ የመውሊድ በዓል በአማረ ሁኔታ የሚከበርባቸው ሐይማኖታዊ ቦታዎች ይጠቁማል።
ጥሩ ሲና መስጂድ፣ በ14ኛው መቶ ክፍለዘመን የተገነባው የጎዜ መስጂድ፤ ኮምቦልቻ አካባቢ የሚገኘው የገታ መስጂድ፤ በአርጡማ ፉርሲ የሚገኘው የቆምበር የመቃብር ቦታ፤ የሾንኬ መንደር፤ ደቡብ ወሎ አልብኮ የሚገኘው ጀማ ንጉስ ከብዙ በጥቂቱ የእስልምና ታሪካዊ አሻራዎች ያረፉባቸው ጥንታዊ የሃይማኖት ትምህርት ማዕከላት ናቸው፡፡ ከዚህ ውስጥ የሾንኬ፤ የጥሩሲና እና የገታ መስጂዶች ደግሞ ዋነኛው የአካባቢው ታሪካዊ ሐይማኖታዊ ቦታዎችን ልንቃኛቸው ወደናል።
የሾንኬ መንደር
የሾንኬ መንደር አርጎባዎች መኖሪያ ነው። የሾንኬ መንደርና መስጂድ ልዩ የሚያደርገው በአካባቢው የሚገኙትን የኅብረተሰብ ክፍሎች የአርጎብኛ፣ የኦሮምኛ፣ የአማርኛ እንዲሁም ከፊል የዓረብኛ ቋንቋ መናገር መቻላቸው ነው። የአራት ቋንቋ ባለቤት በመሆናቸው እንግዳ በሚያጋጥማቸው ወቅት በፈለጉት ቋንቋ ማስተናገድ ይችሉበታል።
አርጎባዎች ከመውሊድ ጋር ተያይዞም ሆነ ለሌሎች የሃይማኖቱ ክንዋኔዎች እንደማዕከልነት ሆነው የሚያገለግሉ ታሪካዊ ቦታዎችን ገንብተዋል። «አርጎባ» ማለት «ዓረብ ገባ» ከሚለው ቃል ጋር ተመሳሳይ መሆኑ ይነገራል። በመሆኑም ከዓረብ አገራት የመጡ ናቸው ተብሎም ይታሰባል። አርጎባ ውስጥ በመጀመሪያ ነዋሪዎቹ ሲሰፍሩ እስከዓርባ የሚደርሱ መስጂዶችን ገንብተው ነበር። ይሁንና አብዛኛዎቹ በዘመናት ሂደት ከአሸዋ ስር እንደጠፉ ይነገርላቸዋል። የእድሜ ጫናን እና የተፈጥሮ እንዲሁም የሰው ልጅ ጥፋትን ተቋቁመው አሁን ላይ የተወሰኑት ቆመው ታሪክን ይመሰክራሉ።
ስለ ሾንኬ መንደር ካነሳን መንደሩ የት አካባቢ ይገኛል? የሚለውን ለመመለስ፤ በአማራ ክልል የኦሮሚያ ብሄረሰብ ልዩ ዞን ከሚሴ ከተማ በስተምስራቅ አቅጣጫ 23 ኪሎሜትሮች ርቀት ላይ ይገኛል። ዳገት ቁልቁለት የበዛበት መንደሩ ዙሪያ ገባውን በዕድሜ ጠገብ ዛፎች የተከበበ በመሆኑ መንፈስን የሚማርክ ይዘትን ተላብሷል። በመንደሩ ላለፉት 800 ዓመታት ጀምሮ የአርጎባዎች የባህልና የአኗኗር ትርኢት በየዕለቱ ይከወንበታል። በመንደሩ ውስጥ የሚገኘው ጥንታዊ መስጂድ ደግሞ የእስልምና ሃይማኖት ትምህርት ተቋም ማዕከል በመሆን ሲያገለግል የቆየ ታሪካዊ ቦታ ነው፡፡ የሾንኬ መንደር ውስጥ ደግሞ ታሪክን በጉያው ይዞ የኖረውና ሊጎበኝ የሚገባው የአርጎባዎች ሾንኬ መስጂድ ይገኛል። መስጂዱ በተለይ የመውሊድ በዓል አከባበርን አስመልክቶ በርካቶች ይጎበኙታል። በዓሉን ለማሳለፍ ጓዛቸውን ሰንቀው ለሳምንት እና አለፍ ላሉ ጊዜያት የሚቀመጡ አማኞች በሾንኬ መስጂጅ በየዓመቱ በቦታው ይገኛሉ።
የሾንኬ መንደርና መስጂድ ከገጠሪቱ ኢትዮጵያ የቤቶች አሠራር የተለየ ጥንታዊ የስነ-ህንፃ ጥበብ የሚታይበት ዲዛይን ይዟል። መንደሩና መስጂዱ የሚገነቡት ለብቻቸው ገለል ባሉ ተራራማ ስፍራዎች በመሆኑ ከሩቅ ሲታዩ የኮንሶን የእርከን ካቦች ያስታውሳሉ። የቤቶቹ አሠራር በነጫጭ ድንጋዮች የተካበ ነው። ጣሪያውም በእንጨት ርብራብ ተሠርቶ የውጭ ጣሪያው በነጭ አሸዋና በአፈር የተደለደለ እና ከላይኛው የኮረብታ አካል ጋር የተገናኘ ወለል እንዲኖረው ይደረጋል። የአርጎባ እናቶች እህል ለማስጣት እና ልብስ ለማደራረቂያነት ይገለገሉበታል። አለፍ ሲልም አንዳንዶች የአካባቢውን ሁኔታ እየቃኙ ለመናፈሻነት ይጠቀሙበታል።
የሾንኬ መንደርና መስጂድ ለየት ያለ የስነ-ህንፃ ውበት ከታችኛው የተራራው አካል እስከ ጫፍ ድረስ የተገነቡ በመሆናቸው ጎበዝ መሃንዲስ እንደገነባቸው ውበታቸው ማራኪ ነው። በሾንኬ መንደር ውስጥ ሦስት ጥንታዊ መስጂዶች ይገኛሉ። ሁለቱ አነስተኛ መስጂዶች ናቸው። በጁምአ (ዓርብ ዕለት) ሀሉም በአንድ ላይ ለፀሎት የሚገናኙበት መስጂድ ደግሞ በመንደሩ ተራራ ጫፍ ላይ የሚገኘው ዋናውና ትልቁ መስጂድ ነው፡፡
የሾንኬ ዋናው መስጂድ በአራት ማዕዘን ቅርጽ የተሰራ ነው። ጣሪያው በትላልቅ ጣውላዎች፣ በጭቃና በአሸዋ የተያያዘ ነው። ግድግዳዎቹ ደግሞ ባልተጠረቡ እና በአካባቢው ከሚገኙ ነጫጭ ድንጋዮች ተያይዞ ተገንብቷል። ምሰሶዎቹ ትላልቅና ተጠርበው የተዘጋጁ እንጨቶች ናቸው። ለረጅም ዘመናት ዋልታ በመሆን የመስጂዱን የላይኛውን ክፍል ይዘው ሲታዩ «ታሪክን አላፈርስም ብለው እንደሚጠብቁ ዘቦች ይመስላሉ» በማለት ያይዋቸው ይመሰክሩላቸዋል።
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ የሾንኬ መስጂድ እና ሰፈሮች በሙሉ በቅርስነት ተመዝግበዋል። መስጂዱ ደግሞ ቁመቱ ሦስት ሜትር እና ስፋቱ ደግሞ 289 ሜትር ነው። በሩ የተሰራበት ጣውላ 40 ሳንቲሜትር ውፍረት አለው። የውስጥ ምሰሶዎቹ 28 ይደርሳሉ። ህንጻው ምንም አይነት የፋብሪካ ውጤት የማይታይበት መስጂድ ሆኖ እናገኘዋለን።
በመስጂዱ ውስጥ ከመካ ከተሰደዱ ሰዎች ጋር አብረው እንደመጡ የሚነገርላቸው ቅርሶች ይገኛሉ። ከመካ መጥተዋል የሚባሉ ትላልቅ በርሜሎች፣ ጀበናዎች እና የመመገቢያ ዕቃዎችን ናቸው። በርሜሎቹ እና ሰሃኖቹ ደግሞ በቶሎ ከማይበሰብስ እንጨት ተቀርፀው የተሰሩ ናቸው። በርካታ አጥኚዎችም አመጣጣቸውን እና የወቅቱን የአኗኗር ሁኔታ በሚገባ ሊመሰክሩ የሚችሉ ቅርሶች መሆናቸውን መስክረውላቸዋል።
የታሪክ ማስረጃዎች እንደሚያሳዩት፤ አሁን አሁን እምብዛም ትኩረት ያልተሰጠው ቦታ ቢሆንም ከሀገር ውስጥ ጎብኚዎችን የሾንኬ መስጂዶችን ይጎበኙ ነበር። ከሀረር፣ ከጅማ፣ ከአርሲና ከደቡብ እና ከሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች በተለያየ በጊዜ ወደመስጂዶቹ መጥተው ጸሎት የሚያደርሱ ሙስሊሞችም በዙዎች ነበሩ። ከውጭ ሀገራት ደግሞ በተለይ ከየመን የሚመጡ የእስልምና አስተምህሮ ተማሪዎች እንደነበሩ ይነገራል።
ለሾንኬ መስጂድና መንደር አመሰራረት ዋነኛ ምክንያት ነው ተብሎ በታሪክ አጥኚዎች ዘንድ የሚታመነው በአቅራቢያው ያለው የጦለሀ መንደር ምስረታ ነው። የጦለሀ መንደር ከሾንኬ አካባቢ በስተምሥራቅ ስድስት ኪሎሜትሮች ርቀት ላይ ይገኛል። በጦለሀ መንደር ደግሞ በግምት ከዛሬ ዘጠኝ መቶ ዓመት በፊት እንደተመሰረተ በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ ይታመናል። ከዚያም ከ34 ዓመታት በኋላ አርጎባዎቹ ሾንኬ መንደርን ለመመስረት የሚያመች አካባቢ በማግኘታቸው በዚያው ሰፍረው እንደቆዩ የአፈታሪክ ማስረጃዎች ዋቢ ናቸው።
የጦለሀን መስጂድ የመሠረቱት ኩሉባስ የተባሉ ግለሰብ እንደሆኑና ከእርሳቸው ጋር ደግሞ ፈቂ አህመድ የተባሉ ሼህ አብረው ይኖሩ እንደነበር ይነገራል፡፡ ሁለቱ ሰዎች ከአርጎባ ብሔረሰብ የወጡና የእስልምና ኃይማኖት ተከታይ በመሆናቸው በአሁኑ ሾንኬ መንደር ይኖሩ ከነበሩ የሌላ ብሔረሰብ አባላት ጋር በመሬት ጉዳይ በየጊዜው ግጭቶች ይፈጠሩ እንደነበር የአርጎባ አዛውንቶች በተደጋጋሚ ገልጸውታል።
ግጭቶቹ ደግሞ እየጠነከሩ ሲመጡ ከብዙ ሙከራዎች በኋላ በሾንኬ አካባቢ ይኖሩ የነበሩት ጎሳዎች ጦለሀን በማጥቃት ኩሉባስን ገደሏቸው፡፡ በዚህን ጊዜ ጦለሀ ውስጥ ሸህ ፈቂ አህመድ ብቻቸውን የአካባቢያቸው መሪ እንደሆኑ ይነገራል። እንደ አዛውንቶች አነጋገር ሼሁ ጥቃት ያደረሱባቸውን ሰዎች ከመከላከል ባሻገር የኩሉባስን ደም ለመመለስ አስፈላጊውን የጦር ዝግጅት ያካሂዱ ጀመር።
ሼሑም አስፈላጊውን ዝግጅት ካጠናቀቁ በኋላ ወደ ሾንኬ አካባቢ በመዝመት የኩሉባስ ገዳዮች የሆኑትን ጎሳዎች አጠቋቸው። በጥቃዋቱም ሼሕ ፈቂ ድል ቀናቸውና ሾንኬን አስለቅቀው መያዝ ቻሉ። በዚህም መሰረት አሁን ላይ የሾንኬ መንደርና መስጂድ ለመመስረት ተቻለ፡፡
መስጂዱ በተለይ በመውሊድ በዓል እና በእስልምና በዓላት ወቅት በርካታ ሰዎች ፀሎት ያደርሱበታል። በየበዓላቱ ሐይማኖታዊ ክንውኖች ተካሂደው ችግረኛ የማብላት ስርዓት ይካሄዳል። አካባቢው የተረጋጋ እና መንፈስን ለማደስ የሚመች በመሆኑ የእስልምና ሐይማኖት ተከታዮች የሾንኬን መስጂድ በመውሊድ ወቅት ይመርጡታል። ይሁንና የውጭ አገራት በተለይም የዓረቡን ዓለም ጎብኚዎች መሳብ የሚችል ቦታ በመሆኑ ሊሰራበት ይገባል።
ገታና የገታ አንበሳ
ሌላው ታሪካዊ የእስልምና ሐይማኖት ቦታ፤ የመውሊድ በዓል አከባበር የሚታወቀው ኮምቦልቻ ዙሪያ የሚገኘው ገታ መሆኑን የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም መስህብ ቅኝቶች ላይ ያተኮረው መጽህፍ ይጠቁማል። ገታ ከአዲስ አበባ 375 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ በምትገኝው ኮምቦልቻ አካባቢ ጨቆርቲ እንዳለፉ ይገኛል። የጨቆርቲን መንደር ትተው ወደግራ አራት ኪሎሜትሮችን እንደተጓዙ ደግሞ በእስልምና ሐይማኖት ተከታዮች ዘንድ ከፍተኛ ክብር ያለውን የገታ ቅዱስ ቦታና ጥልቅ የታሪክ ፍተሻ የሚያስፈልገውን የገታ አንበሳን ያገኙታል።
ገታ መውሊድን ምክንያት በማድረግ በየዓመቱ ደማቅ ክብረ በዓል የሚደረግበት ስፍራ ሲሆን በብዙ ሺህ የሚቆጠር ህዝብ ከተለያየ የአገሪቱ ክፍሎች እና ከዓረቡ ዓለም ሳይቀር ወደገታ የእስልምና ቅዱስ ስፍራ ይጎርፋል። ገታን ያቀኑት ቀደምት የሃይማኖቱ መሪዎች አጽም በአንድ ክፍል ውስጥ በክብር ተቀምጦ ይገኛል::
ከገታ ጊቢ ጥቂት ርቀት ላይ የሚገኘው ከአንድ ወጥ ድንጋይ ተፈልፍሎ የተስራው የአንበሳ ምስል ሌላው ትኩረትን የሚስብ ቅርስ ነው:: ይህ የአንበሳ ምስል በከፊል አየር ላይ የተንጠለጠለ ሲሆን አብዛኛው የሰውነት ክፍሉ ከዋናው አለት ጋር የተያያዘ ነው:: ከአንድ ወጥ ድንጋይ ተፈልፍሎ ተሰርቷል። አንበሳው ፊት ላይ የመስቀል ምልክት አለ፡፡ በተጨማሪም በሳባውያን ፊደላት የተጻፉ ሆሄያትን ይመለከታሉ፡፡ ከዚህ በመነሳት ብዙዎች አካባቢው ብዙ ዘመን ያስቆጠረ እንደሆነ ይመሰክራሉ። ምክንያቱም አሁን ላይ አካባቢው የሙስሊሞች ቅዱስ ስፍራ ሲሆን ቀደምት ጊዜ ደግሞ ክርስቲያኖች ይኖሩበት እንደነበረ የገታው አንበሳ መስቀል ምልክት እማኝ መሆኑን ይመሰክራሉ። ይህ ቅርስ ለታሪክ ተመራማሪዎች ብዙ ፍተሻ እንዲያደርጉ የሚጋብዝ ሆኖ እናገኘዋለን።
ገታ ምን ያክል ዘመን ያስቆጠረ እንደሆነ ግን ዛሬም ድረስ ጥናት ባለመደረጉ አብዛኛው በመላምት የሚነገር ነው። በሐይማኖታዊው አስተምህሮ በቦታው የቅድስና ታላቅ ተግባር ፈጽመዋል የሚባሉት ሰይድ ቡሽራ የተባሉ ሰው ናቸው። የሰይድ ቡሽራ ገታ መውሊድ ታህሳስ 29 ቀን በየዓመቱ በቦታው ይከበራል።
በገታ መውሊድ በዓል ወቅት እጅግ ብዙ ሰው ይገኝበታል፡፡ የገታ መውሊድ ከነብዩ መሃመድ መውሊድ በዓል ባልተናነሰ ገናና ነው፡፡ ይሁንና ዋናው መውሊድ በገታ ዓመት ጠብቆ የሚመጣና ተናፋቂ በመሆኑ የሚታደሙት ብዙዎች ናቸው፡፡ ገታ ስዕለት ይሰማል ብለው በሙሉ ልብ የሚናገሩ ሰዎች ቁጥርም ብዙ ነው፡፡
መሐመድ ነሲም የተባሉ ሰው በጽሁፍ እንዳሰፈሩት፤ የገታ መስጂድ ከሁለት መቶ ዓመት በላይ እድሜ ያስቆጠረ ጥንታዊ የእስልምና ሃይማኖታዊ ተቋም ነው። የገታ መስጂድ መስራች ሐጂ ቡሽራ አይ መሀመድ ይባላሉ። ሐጂ ቡሽራ በሸዋ ክፍለ ሀገር በቀድሞው ኢፋት አውራጃ ልዩ ስሙ ላንቱ ከሚባለው መንደር በ1753 ዓ.ም ነው የተወለዱት።
እንደ ጸሃፊው፤ ሸህ ቡሽራ እውቀትን ፍለጋ ከኢትዮጵያ አልፎ ሱዳን ብሎም እስከ ሳዑዲ ዓራቢያ ድረስ ተዘዋውረዋል። በሱዳን የሐይማኖት መምህር ሆነው ሲያገለግሉ «አወል ፈይድ» የሚል ስም ተሰጥቷቸው ነበር፡፡ ሐጂ ሰይድ ቡሽራ በሳዑዲና በሱዳን የ25 ዓመታት ቆይታ በኋላ በ1770 ዎቹ መጨረሻ ወደ ኢትዮጵያ ይመለሳሉ። ከዚያም በሼህነታቸው ወደተሾሙበት ቃሉ ወረዳ ገታ ከሚባለው ተራራማ ቦታ ይመደባሉ። በገታም መስጂድ አሰርተው በመቀመጥ የአካባቢውን የሐይማኖት መሪና አስተማሪ በመሆን የእስልምና ሃይማኖትን በማስተማርና በማስፋፋታቸው ይታወቃሉ።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በዚሁ በገታ የነብዩ መሐመድን የመውሊድ በዓል በታላቅ ድምቀት በማክበር እስከአሁን በእሳቸው የተጀመረው የመውሊድ በዓል እየተከበረ እነሆ ለአሁኑ ዘመን ደርሷል። አሁንም ገታ የመውሊድ በዓል አከባበር ዋና መናኸሪያ ሆኖ ቀኑን በድቤ፣ በዝየራ እና በምስጋና እየተከበረ ይውላል። ውብ አስረቅራቂ ድምጽ ያላቸው ሰዎች በዜማ የታጀቡ ግጥሞችን እያወጡ ቀኑን በምስጋና ያሳልፋሉ። ይህን ቀን በገታ ማሳለፍ የሚመኙ በርካታ ሙስሊሞች በዕለቱ የኮምቦልቻን መንገድ አቋርጠው በቦታው ሲያሳልፉ ይስተዋላል።
የጥሩሲና መስጂድ
በአማራ ክልል የኦሮሚያ ብሄረሰብ ልዩዞን የባህልና ቱሪዝም መምሪያ መረጃ መሰረት ሌላው የእስልምና ታሪካዊ ቦታ የጥሩ ሲና መስጂድ ነው። ከከሚሴ ከተማ ወደ ኮምቦልቻና ደሴ በሚወስደው መንገድ ላይ 11ኪሎ ሜትሮችን ከተጓዙ በኋላ እንደገና በስተምስራቅ አቅጣጫ የ30 ደቂቃ የእግር ጉዞ ታሪካዊውን የጥሩ ሲና መስጂድን ያገኙታል። የጥሩ ሲና መስጂድ ልዩ የሚያደርገው ምክንያት ዋነኛው የሴት ገዳማውያን መናኞች መቀመጫ በመሆኑ ነው። ከዋናው ጥሩሲና መስጂድ አቅራቢያ በተገነባ መለስተኛ መስጂድ ሴቶች ፀሎት እያደረሱ ምድራዊውን ዓለም ንቀው፤ ከወንድ ጋር ሳይገናኙ እስከዕለተ ሞታቸው ይኖሩበታል።
የቅርብ ጊዜ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ ባለፈው ዓመት ብቻ 150 ሴቶች በገዳማዊ ስርዓት በመስጂዱ ይኖሩ ነበር። ከመናኞቹ መካከል አብዛኛዎቹ ቁርዓን የሚቀሩ እና ኪታብ የሚያዘጋጁ ናቸው፤ ሌላ ስራ የላቸውም። እነርሱ በገዳሙ እያሉ ማንኛውም ህፃን ልጅም ቢሆን ወንድ ከሆነ ወደውስጥ መግባት አይፈቀደለትም። በርካታ ዓመታትን ያስቆጠረው ትልቁ መስጂድ አሰራሩ ውብ እና የአባቶቻችንን የቤት አሰራር ብቃት የሚያስመሰክር ነው። በተለይ የጣራው አሰራር ጥበብ በተለያዩ የእንጨት ጌጦች ያሸበረቀ በመሆኑ ያዩት ሁሉ አድናቆታቸውን ይቸሩታል።
ሌላው ግርምት የሚጭሩት የመስጂዱ ምሶሶዎች ብዛት እና ውፍረት ነው። የእያንዳንዱ ቋሚ እንጨት ውፍረት ሁለት ሰዎች እጅለእጅ ተያይዘው ሊያቅፉት ቢሞክሩ እንኳን አይቻላቸውም። ከዚህ በላይ የምሰሶዎቹ ቁመት ረዥም በመሆኑ በሰው ልጅ ኃይል መተከላቸውን የሚጠራጠሩ ብዙዎች ናቸው። በክብ ቅርጽ የተሰራው መስጂዱ ግድግዳዎቹ በአግድም እና በቁመት የተረበረቡ እንጨቶች ናቸው። ኮርኒሶቹ ደግሞ የስፌት ምስል ያላቸው ሰፋፊ ቃጫዎች እና ስንደዶዎች ተገምዶ የተሰራ ነው። መስጂዱን ልዩ የሚያደርገው ሌላው ነገር በቅጥር ጊቢው ውስጥ የተለያዩ አገልግሎቶችን የሚሰጡ የስጋ ቤት፣ የቡና ማፍሊያ ቦታ፣ የማር ብርዝ ማዘጋጃ ቤት በውስጡ ማካተቱ ነው። አያንዳንዱ ቤት የእራሱ ሰው የተመደበለት ሰራተኛ አለው።
በመስጂዱ የግምጃ ቤት ውስጥ ደግሞ የተለያዩ እድሜ ጠገብ የሆኑና የአሰራር ጥበባቸው በእጅጉ ውበትን የተላበሱ የባህል እቃዎች ማለትም ከእንስራ ያልተናነሱ ጀበናዎች፣ ግዙፍ የቡና መውቀጫዎች ይገኛሉ። ከአንድ እንጨት ተፈልፍለው የተሰሩ በርካታ በርሜሎች፣ ቁጥራቸው ከ500 በላይ የሆኑ ሲኒዎች፣ በእንጨት ተፈልፍለው የተሰሩ የሲኒ መደርደሪያ ረከቦቶች እና ሌሎችም እድሜ ጠገብ ውብ የባህል ቅርሶች ነበሩት። በጥሩሲና መስጂድ የተለያዩ መንፈሳዊ ከንውኖች ቂርአቶችና ደርሶች የሚሰጡበት ቢሆንም በዋናነት ግን የነቢዩ መሃመድ የልደት በዓል (መውሊድ) በሰፊው ይከበርበታል።
ለበዓሉም ድምቀት ከ20 በላይ ግመሎች እና በርካታ በሬዎች ታርደው ለታዳሚዎች መስተንግዶ ይውሉ እንደነበር የታሪክ መረጃዎች ያስረዳሉ። በዓሉን የታደመው ሁሉ የሚያጋጥመው ልዩ ነገር ደግሞ ሌሊት ላይ ለጋ የማር ብርዝ ተዘጋጅቶ በክቡር ዘበኛ መጠጫ በሰልፍ በሰልፍ በሚመጡ ታዳሚዎች የሚታደልበት ስርዓት ነው። በአንድ ትርንጎ ላይ ከ ዘጠና እስከ አንድ መቶ ሰንደሎች ተሰክተው ህዝቡን በመልካም መዓዛ ያውዱታል። በርካታ የእስልምና መምህራንን ያፈራ ቦታ መሆኑም ይነገርለታል።
ትልቁ የጥሩሲና መስጂድ በ2009 ማብቂያ ወር ላይ በመብረቅ ጉዳት ደርሶበታል። በመብረቁ አማካኝነት በተነሳ እሳትም መስጂዱ ተጎድቷል። ዳግም የቦታውን ታሪካዊነት በጠበቀ መልኩ መስጂዱን ለመገንባት ጥረት ተጀምሯል። በመሆኑም ታሪኩን ለመቋደስ ጉብኝት ማድረግ ያስፈልጋል። በጎብኝቱ የሚገኘውን ገቢ ጥሩሲናን በማሳደስ ለትውልድም የሚተርፍ ቅርስ ለማስተላለፍ ይረዳልና ቦታውን በመጎብኘት ተጨማሪ መረጃዎችን እንድታገኙ እንጋብዛለን።
ጌትነት ተስፋማርያም