የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ጅማሮ

የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ፤ የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ሽያጭ፣ ግዥ እና ልውውጥ በቋሚነት የሚደረግበት ቦታ እንደሆነ የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ። ገበያው ለተቋማት የገንዘብ ምንጭ እና ማደግ፣ ለሀገር ውስጥ ጠቅላላ ምርት (ጂዲፒ) መጨመር፣ ለተሳለጠ የግብይት ሥርዓት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለውም በብዙ ተነግሮለታል።

የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ፤ የሀገር ውስጥ ካፒታልን ለማሳደግ፣ የፋይናንስ አካታችነትን ለማስፋፋት እንዲሁም የረጅም ጊዜ የኢኮኖሚ ዕድገትን ለመደገፍ ትልቅ አቅም አለው። ታዲያ ይህን ገበያ በኢትዮጵያ ተግባራዊ ማድረግ እንዲቻል ባለፉት ጥቂት ዓመታት ሰፊ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱ ይታወሳል። ለዚህም መንግሥት ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ የካፒታል ገበያ ሥነ-ምኅዳርን ለማስፋት ደረጃ በደረጃ የታቀዱና በሪፎርም የተደገፉ እንቅስቃሴዎችን ሲያከናውን ቆይቷል።

የሥትራቴጂ አቅጣጫውም በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ ላይ የተመሰረተ ሆኖ የሕግ ማሕቀፎችን፣ አስፈላጊ ተቋማትን እና ዘመናዊ የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማትን የመገንባት እንቅስቃሴዎች ላይ በትኩረት ሲሠራ ቆይቶ፤ አሁን ላይ የተግባር እንቅስቃሴውን ‹‹ሀ›› ብሎ ጀምሯል። ሰፊ ዝግጅት ሲደረግበት የቆየው የኢትዮጵያ የሰነደ መዋዕለ ንዋዮች ገበያ አሁን ላይ የመንግሥት የግምጃ ቤት ሰነዶችን እና ሌሎች የሰነደ ሙዓለ ንዋዮችን በይፋ ማገበያየት ጀምሯል። የግብይቱን በይፋ መጀመር አስመልክቶ የብሔራዊ ባንክ ገዢ አቶ ማሞ ምህረቱን ጨምሮ የተለያዩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ እስማዔል ጥላሁን (ዶ/ር) ገበያው በይፋ መጀመሩን አስመልክተው ሲገልጹ፤ የገበያው በይፋ መጀመር የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያን ለማጠናከር ለሰሩ ባለድርሻ አካላት የልፋታቸው ውጤት ትልቅ ማሳያ ነው። የመንግሥት የዕዳ ሰነዶች በገበያው መመዝገብ እና በግብይት መድረኮች ላይ ለግብይት መቅረብ መቻላቸው ለኢትዮጵያ የዕዳ ሰነዶች ገበያ አዲስ ምዕራፍ ከፋች እንደሆነም አመላክተዋል።

በተመሳሳይ የአክሲዮን ግብይት ጅማሮ ዘመናዊ ገበያ መሰረተ ልማት ለመገንባት የተሠሩ ሥራዎች ውጤታማነት ማረጋገጫ መሆኑን ጠቅሰው፤ ገበያው በዚህ የለውጥ ሂደት ውስጥ የመሪነት ሚና በመጫወት ለሀገሪቷ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚችል አብራርተዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ ገበያው ዛሬ ላይ ለመድረሱ ከተለያዩ ተቋማት የብዙ ዓመታት ጥረትን ጠይቋል። ለአብነት የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም፣ የተቋማት ግንባታ፣ የሕግ ዝግጅት፣ የሰው ኃይል ሥልጠናና የተሳታፊዎች በአንድ ላይ መተባበርን ጨምሮ ከተመዘገቡት ኩባንያዎች ጎን ለጎን የሲቢኢ ካፒታልና የወጋገን ካፒታል ሁለት ኢንቨስትመንት ባንኮች በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ፈቃድ ተሰጥቷቸው ወደ ሥራ ገብተዋል።

የመንግሥት የግምጃ ቤት ሰነድ ግብይት በገበያው በቀዳሚነት ተመዝጋቢ ሆነው መገበያየት የጀመሩት የወጋገን እና የገዳ ባንክ ናቸው። ባንኮቹ በአሁን ወቅት አክሲዮኖቻቸውን በይፋ ማገበያየት የጀመሩ ሲሆን ማንኛውም ዜጋ አቅሙ በፈቀደው ልክ ወደ እነዚህ ባንኮች በመሄድ አክሲዮን መግዛት ይችላል።

በቀጣይም ግለሰቦችና የተለያዩ ድርጅቶች የግምጃ ቤት ሰነዶችንና አክሲዮኖችን በቀላሉ አገናኝ አባላቶችና ኢንቨስትመንት ባንኮች ጋር የፋይዳ መታወቂያቸውን ይዘው በመሄድና በመደወል ኢንቨስት ማድረግ ይችላሉ። እንዲሁም ባሉበት ቦታ ሆነው በቀላሉ ኢንቨስት ማድረግ የሚችሉባቸውን ዕድሎች ለማስፋት የሞባይል መተግበሪያዎችንና ሌሎች የትምህርትና የስልጠና ዝግጅቶችን የሚከታተሉ ይሆናል፡፡

ግለሰቦችና ድርጅቶች የግምጃ ቤት ሰነድ መግዛት ሲፈልጉ፤ በቀላሉ የፋይዳ መታወቂያቸውን በመስጠት ኢንቨስትመንት ባንኮቹ ጋር መመዝገብ እንደሚችሉ ያነሱት እስማኤል ጥላሁን (ዶ/ር)፤ ግለሰቦች ገንዘብ አስገቡ በሚባሉበት አካውንት በማስገባት ይግዙልኝ ወይም ይሽጡልኝ በሚለው መስፈርት መገበያየት እንደሚችሉም አስረድተዋል።

ከዚህ ውጭ ግብይቱን ተግባራዊ ለማድረግ አስቸጋሪ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን እንዲረዱና እንዲጠቀሙ የሚገደዱበት ምክንያት እንደሌለም ጠቅሰዋል። ይሁንና በቀጣይ ለመተግበር ቀላል የሆነና ገበያው ላይ መሳተፍ የሚያስችሉ ቀለል ያሉ የሞባይል መተግበሪያዎች እንደሚኖሩ አመላክተው፤ ይህም ቀልጣፋ ፈጣንና ተዓማኒነት ያለው አገልግሎት ለመስጠት ያግዛል ብለዋል።

የመንግሥት ግምጃ ቤት ሰነድን ለገበያ ክፍት የማድረግና የግሉ ዘርፍ የሰነድ ሙዓለ ንዋዮች ግብይት ጅማሮ የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ውጤታማነት ማሳያ ነው ያሉት የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሺዴ ናቸው። እሳቸው እንዳሉት፤ ግልጽ፣ ፍትሃዊና ተዓማኒ የካፒታል ገበያ ለመገንባት፣ የፋይናንስ አቅርቦትን ለማሻሻልና የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለማስፋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። የግብይት ሂደቱ የመንግሥት የግምጃ ቤት ሰነድን በዘመናዊ መልኩ ለገበያ ክፍት በማድረግ አማራጭ የፋይናንስ አቅም ሆኖ ያገለግላል።

ገበያው በይፋ ሥራ በጀመረበት በዚህ ወቅት የመንግሥት የግምጃ ቤት ሰነዶች (የመንግሥት ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች) በገበያው ተመዝግበዋል። በመሆኑም ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የግምጃ ቤት ሰነዶቹን መግዛት ይችላል። ሚኒስትሩ መንግሥት ለ2018 በጀት ዓመት አንድ ነጥብ ዘጠና ሶስት ትሪሊዮን ብር በጀት ማጽደቁን አስታውሰው፤ ከዚህ ውስጥ 80 በመቶ ያህሉ ገንዘብ የሚሸፈነው ከሀገር ውስጥ ገቢና በሀገር ውስጥ ብድር እንደሆነ ገልጸዋል።

አጠቃላይ ከ2018 በጀት ውስጥ 188 ቢሊዮን ብር ያህሉ የተጣራ የበጀት ጉድለት መኖሩን ሚኒስትሩ ጠቅሰው፤ ከዚህ ከተጣራ የበጀት ጉድለት ውስጥ 173 ቢሊዮን ብር ያህሉ የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያን በመጠቀም በሀገር ውስጥ ብድር ለመሸፈን መታቀዱን አንስተዋል። ከዚህ በፊት የነበረው የመንግሥት የግምጃ ቤት ሰነድ ገበያ፤ ከገበያው በታች በሆነ ወለድ የሚመራ የነበረ በመሆኑ ኢንቨስተሮችን የሚጋብዝ እንዳልነበረ አስታውሰው፤ በዚህ ምክንያትም በግምጃ ቤት ሰነድ ግብይት የሚሳተፉ ባንኮች ተጠቃሚ አልነበሩም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሃና ተልህቁ በበኩላቸው እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮችና የመንግሥት የግምጃ ቤት ሰነዶች ግብይትን ለማስጀመር ሰፊ ዝግጅት ሲደረግበት ቆይቶ መገበያየት መጀመሩ ትልቅ ስኬት ነው። መንግሥት የግምጃ ቤት ሰነዶችን በገበያው ማስመዝገቡ ኮርፖሬት ኩባንያዎች በገበያው ተማምነው ሰነደ ሙዓለ ንዋዮቻቸውን እንዲያስመዘግቡና እንዲገበያዩ በር ከፋች ነው በማለት በገበያው ላይ ያላቸውን ዕምነት ገልጸዋል።

አሁን ላይ በይፋ የተጀመረው የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ በሀገሪቷ ኢኮኖሚ ውስጥ የተከናወኑ የልማት ውጤቶች የሚታዩበትና በፋይናንስ ዘርፍ ላይ ትልቅ አሻራ የሚያሳርፍ አዲስ ምዕራፍ መሆኑን ጠቅሰዋል። ለመጀመሪያ ጊዜ ክፍት የሆነው የመንግሥት የግምጃ ቤት ሰነዶችና የድርጅት ሙዓለ ንዋይ ሰነዶች ግብይት ኢንቨስተሮች በገበያ ላይ በንቃት መሳተፍ የሚችሉበትን ሰፊ ዕድልና ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር እንደሆነም አብራርተዋል።

ይህ ታሪካዊ ምዕራፍ የተከፈተው ኢትዮጵያ በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርም እያካሄደች ባለችበትና ሁሉን አቀፍ፤ ጠንካራና ገበያ መር ኢኮኖሚ ግንባታ ውስጥ ሆና ነው ብለዋል። ገበያው የመንግሥት የእዳ አስተዳደርን የማዘመን ጉዞ ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። ይህ ሲባል ለመንግሥት የፋይናንስ አማራጭ ከመሆን ባለፈ የፊስካልና የገንዘብ ፖለሲዎች ውጤታማነት ተገማችነትን ያጠናክራል። በመሆኑም ይህን እድል የበለጠ ለማጠናከርና ለማስፋት የካፒታል ገበያ ድርሻ እጅጉን የጎላ ነው።

የካፒታል ገበያ ገበያውን ቀልጣፋ፣ ግልጽና ተዓማኒ ከማድረግ ባለፈ ኢንቨስተሮች ወደ ገበያው በቀላሉ መግባትና መውጣት እንዲችሉ መንገድ የሚፈጥር ነው። ከዚህ ባለፈ ቁጠባን ወደ ኢንቨስትመንት በመቀየር ፈጣን የኢኮኖሚ እድገትን ያመጣል። ገበያው ለግል ኩባንያዎችም ትላልቅ ዕድሎችን ይዞ የመጣ በመሆኑ፤ ኩባንያዎች ከሕዝብ ገንዘብ በማሰባሰብ የቢዝነስ ሥራዎቻቸውን ማስፋፋት ብቻ ሳይሆን፤ በገበያው ዘንድ ያላቸውን ዕይታ ከፍ በማድረግ የፋይናንስና ድርጅት አስተዳደራቸውን ግልጽ በማድረግ በባለሀብቶች ዘንድ ዕምነት መፍጠር ያስችላቸዋል። ለዚህም የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ምዝገባ ወሳኝ ነው ሲሉ አስረድተዋል።

በአዋጁ መሰረት የሕዝብ ኩባንያዎች ሲመዘገቡ ግልጽና ተዓማኒ በሆነ መረጃ በደንበኛ ሳቢ መግለጫ በኩል ለኢንቨስተሮች በማሳወቅ ገበያውን መቀላቀልና ገንዘብ ማሰባሰብ እንደሚቻል ያነሱት ዋና ዳይሩክተሯ፤ በአሁን ወቅት በሀገሪቱ የመጀመሪያ በሆነው የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ቀዳሚ ሆነው መገበያየት የጀመሩት ባንኮቹ በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣንና በሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ በመመዝገብ የመጀመሪያዎቹ የሕዝብ ኩባንያዎች መሆን እንደቻሉም ተናግረዋል።

ግልጽና ተዓማኒነት ያለው የካፒታል ገበያን መገንባት ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወሳኝ ነው ያሉት የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ ናቸው። እሳቸውም መንግሥት ሀገሪቷ የገጠሟትን የኢኮኖሚ ስብራቶች በመለየትና ደረጃ በደረጃ በመፍታት ኢኮኖሚውን ወደ ተረጋጋና ዘላቂ ወደ ሆነ ዕድገት መመለስ የሚያስችል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ቀርጾ ወደ ተግባር መግባቱን አስታውሰዋል።

ከእነዚህም መካከል ግልጽና ተዓማኒነት ያለው የካፒታል ገበያ መገንባት አንዱ ነው። ያሉት ማሞ ምህረቱ፤ በዚህ ረገድ አኮኖሚው ለሚያስፈልገው የካፒታልና የፋይናንስ ምንጭ በዘላቂነት ለማመንጨትና ዘላቂ ሃብት ለማምጣት በተለመደው መንገድ ማለትም የታክስ ገቢዎችን፣ ብድርና እርዳታን ብቻ መመርኮዝ በቂ እንዳልሆነ ጠቅሰዋል። ለዚህም የብሔራዊ ባንክ ፈር ቀዳጅ ሚና በመጫወት ከዛሬ አምስት ዓመታት በፊት የካፒታል ገበያን ወደ ሥራ ማስገባት መቻሉን ተናግረዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ የካፒታል ገበያ በዘመናዊ መንገድ መደራጀት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ላስቀመጣቸው ዋና ዋና ስትራቴጂካዊ ዕቅድ መሳካት ወሳኝ ሚና ይጫወታል። በዋናነት የዋጋ መረጋጋትን ለማምጣት፣ የገንዘብ ፖሊሲ መሳሪያውን ውጤታማነት ለማሳደግና አሰራሮችን ለማዘመን ለሚደረገው ጥረት አጋዥ መሳሪያ ነው። በተለይም መንግሥት የተለያዩ ሀገራዊ የልማት ዕቅዶችን ለማሳካት በሚያደርገው ጥረት መሰረት የሚገጥሙ የበጀት ጉድለቶችን ገበያ መር በሆነና የዋጋ ግሽበትን በማያስከትሉ ዘዴዎች ለመጠቀም ዕድል ይሰጣል።

የረዥም ጊዜ የፋይናንስ አገልግሎት መጠንን ለመገመትና ለመቆጣጠር መሳሪያ ሆኖ ያገለግላል። ግልጽ በገበያ የሚመራ፤ የዳበረና የሰላ የካፒተል ገበያ የመንግሥት የግምጃ ቤት ሰነዶች የሚሸጡበት ሁለተኛ ገበያ ሲሆን፤ የብሔራዊ ባንክ የፖሊሲ ተመን ትርጉም ባለው መልኩ ወደ ኢኮኖሚው እንዲቀላቀል ትልቅ አስተዋጽኦ አለው። የካፒታል ገበያ ሥርዓት ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት አማራጭ ፋይናንስ ምንጭ ሆኖ የሚያገለግል እንደሆነ ማሞ ምህረቱ ገልጸዋል።

በመጨረሻም የካፒታል ገበያ ሥርዓት እንዲያድግና ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት አማራጭ ፋይናንስ ምንጭ ሆኖ ያገለግላል። የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ቀልጣፋ በሆነ መንገድ ፈጠራን በማበረታታት የንግድ ተቋማት የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴያቸውን እንዲያሻሽሉ፣ አዳዲስ ምርቶችን እና ቴክኖሎጂዎችን እንዲያዳብሩ፣ ተለዋዋጭ ከሆነው ዓለም አቀፋዊ አስተሳሰብ ጋር አብረው እንዲራመዱ፣ ተለዋዋጭ የገበያ ሁኔታዎችን በመመልከት ተወዳዳሪ ሆነው እንዲቀርቡ እድሉን ያመቻቻል ብለዋል።

ከንግድ ድርጅቶች መስፋፋት ጋር ተያይዞ የሚመጣን የሥራ እድል ፈጠራ እንዲሁም ሥራ ፈጣሪነትን በማበረታታት ለአንድ ሀገር የምጣኔ ሃብት ዕድገት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አመላክተው፤ በቅርቡ ግብይቱን በይፋ የጀመረው የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ትልቅ አበርክቶ እንደሚኖረው ጽኑ እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You