
‹‹ፖሊቲክስ›› የሚለው ቃል የጥንታዊ ግሪክ ቃል ነው። ቀጥተኛ ትርጉሙ ‹‹የዜጎች ጉዳይ›› ማለት ነው። ዘርዘር ሲደረግ፤ የጋራ ውሳኔ፣ የኃላፊነት መጋራት፣ የሀብት መጋራት፣ ለሕዝብ ተገቢ ነገር ማድረግ፣ የመንግሥት አስተዳደር…. የሚሉ ማብራሪያዎች አሉት። የማኅበራዊ ሳይንስ ዘርፍ ወጥ የሆነ ትርጉም እንዲኖረው አይጠበቅም። ምሁራን እና ግለሰቦች የየራሳቸው ብያኔ ሊሰጡት ይችላሉ፤ ያም ሆኖ ግን የጋራ የሆነ ትርጓሜም ይኖረዋል። በተለያዩ ምሁራን የሚሰጡት ብያኔዎችም ሲጠቃለሉ ተመሳሳይ ይዘት ይኖራቸዋል።
የሀገራችንን ልማዳዊ የፖለቲካ አመለካከቶች ልብ እንበል። ‹‹ፖለቲካ ቆሻሻ ነው!›› የሚለው ተገቢ ያልሆነ እና አስደንጋጭ ቃል ሁሌም ይገርመኛል። ‹‹ፖለቲካ እና ኤሌክትሪክን በሩቁ›› የሚለውም ለረጅም ጊዜ የቆየ የተዛባ ስብከት ነው። ይሄ ማለት ሰዎች በፖለቲካዊ ጉዳይ እንዳይሳተፉ ማስፈራራት ማለት ነው። በሌላ በኩል አገር ተረካቢ እንዳይኖር ማድረግ ማለት ነው።
‹‹ፖለቲካ ቆሻሻ ነው›› ማለት አላዋቂነት ነው። ይህን የሚሉት ለእውቀት በጣም ሩቅ የሆኑ ሰዎች ናቸው። ‹‹ፖለቲካ ቆሻሻ ነው›› የሚሉበት ምክንያት ማታለል፣ ማጭበርበር፣ ሴራ፣ ክህደት…. ሲፈጸም በማየት ነው። በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ባለ ሴራ እና ክህደት በሚበዛበት አገር ክህደት በተፈጸመ ቁጥር አንዳንድ ሰዎች ‹‹ፖለቲካ ግን ቆሻሻ ነው!›› ይላሉ።
ቆሻሻ የሆነው ፖለቲካ በራሱ አይደለም፤ ቆሻሸ የሆኑት ክህደት የፈጸሙት ሰዎች ናቸው፣ ማጭበርበርና ማታለል የፈጸሙት ናቸው። ደፋር የሆነ ሰው ‹‹እገሌ እና እገሌ ቆሻሻ ናቸው›› ማለት ነው እንጂ ያለበት፤ ፖለቲካን በራሱ ቆሻሻ ነው ማለት አይደለም። ፖለቲካ ቆሻሻ ነው ማለት እኮ ሳይንሱ በራሱ ቆሻሻ ነው እንደማለት ነው። ማንኛውም ሰው ፖለቲካ ውስጥ ሲገባ አታላይ፣ አጭበርባሪ፣ ውሸታም እና ከሃዲ መሆን ይጠበቅበታል እንደማለት ነው። ለዚህም ነው የሆነ ተመስጋኝ እና ተወዳጅ የሚባል ሰው ፖለቲካ ውስጥ ሲገባ አንዳንድ ሰዎች ‹‹እገሌም ተበላሸ?›› የሚሉት። በእነርሱ እምነት ፖለቲካ ውስጥ መግባት መበላሸት ማለት ነው፤ ውሸታም ለመሆን መዘጋጀት ማለት ነው።
በሀገራችን የምናስተውላቸው የፖለቲከኞች ጥፋቶች የሰዎቹ እንጂ የሳይንሱ ባህሪ አይደለም። ያልሰለጠኑ ስለሆኑ የተፈጠረ እንጂ ፖለቲካ በባህሪው እንደዚያ ሆኖ አይደለም። የሚዋሹትና የሚያታልሉት ለአገር የማያስቡ፣ የግል ጥቅም እና ክብር የሚያስበልጡ ስለሆኑ እንጂ የፖለቲካ ባህሪ ሆኖ አይደለም። ስለዚህ ፖለቲካ ቆሻሻ ነው ከማለት ይልቅ ተዋናዩን በግልጽ መናገር ይልመድብን።
ፖለቲካ ማለት የዜጎች ጉዳይ ማለት ነው። ማንም ሰው ሊሳተፍበት የሚችል እና እንዲያውም ሊሳተፍበት ግዴታ የሆነ ማለት ነው። አንድ ዜጋ በሀገሩ ውስጥ ሲኖር ብዙ ነገር ይመለከተዋል፤ ፖለቲካ ማለት ያ ጉዳይ ማለት ነው። ብዙ ሰዎች ‹‹ፖለቲካ አታነካካኝ›› ሲሉ ይሰማል። እነዚህ ሰዎች ፖለቲካ የሚሉት ተደብቆ መንግሥትን መውቀስ(ሀሜት) ስለሆነ ነው። ፖለቲካ ማለት ግን መንግሥትን መውቀስ ወይም መንግሥት ማወደስ ማለት አይደለም፤ ምናልባት እሱ አንዱ ሊሆን ይችላል። ፖለቲካ ማለት ግን በአገር ጉዳይ ላይ (የሰፈርም ይሁን የድንበር ጉዳይ) ሀሳብ መስጠት፣ በቻሉት መጠን መሳተፍ ማለት ነው። ፖለቲካ ማለት በመንግሥታዊ አስተዳደራዊ ጉዳይ ውስጥ ገብቶ መሳተፍ ማለት ነው። ወይም መንግሥት በሚሰራቸው ጉዳዮች ላይ መሳተፍ ማለት ነው። ይህ ሲሆን ነው መንግሥት ማለት ሕዝብ ማለት ነው የሚለው ገለጻ በትክክል የታሰበለትን ትርጓሜ የሚይዘው።
በኢትዮጵያ ዓውድ ግን ፖለቲካ ማለት የግድ ለሥልጣን መታገል ማለት መስሏል። በውሃ ቀጠነ ምክንያት ሀገር እያስተዳደረ ያለውን መንግሥት መቃወም ወይም ሀገር እያስተዳደረ ያለውን መንግሥት ቅዱስ አድርጎ ማወደስ ብቻ መስሏል። ፖለቲካ ማለት ግን መንግሥትን ከመቃወም ወይም መደገፍ ጋር ሳይሆን ከሀገር ጉዳይ ጋር የሚያያዝ ጉዳይ መሆን አለበት። ፖለቲከኛ ሲባል የፓርቲ አመራር ወይም የፓርቲ አመራር ባይሆንም በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ በቋሚነት የሚሳተፍ ነው። ፖለቲካ ሲባል ግን(ሀሳቡ ማለት ነው) የማንኛውም ሰው ጉዳይ መሆን ይችላል።
የፖለቲካ አረዳዳችን የተዛባ ስለሆነ ይመስላል ፖለቲካን ከሰላማዊ መንገድ ይልቅ ወደ አስፈሪ ገጽታ የወሰድነው። በኢትዮጵያ ዓውድ ፖለቲካ ሲባል መታሰር እና መገደል ያለበት፣ መሰደድ እና መንገላታት ያለበት ተደርጎ ይታሰባል። መታሰር የፖለቲካ ጉዳይ ሳይሆን የህግና ደንብ መተላለፍ ጉዳይ ነው፤ አለፍ ሲልም የወንጀል ጉዳይ ነው። የፖለቲካ ልማዳችን ኋላቀር ስለሆነ መንግሥት ላይ ተቃውሞ ያላቸው ሰዎች በሰለጠነ መንገድ ከመጠየቅ ይልቅ የድብቅ ሴራ እና ተንኮል ያበዛሉ፤ ሀገር እያስተዳደረ ያለው መንግሥትም የዚሁ አይነት የፖለቲካ ባህል አካል ነውና ተጠራጣሪ ስለሚሆን ንቆ ማለፍ አይችልም፤ ያስቸግሩኛል በሚል ስጋት ሊያስራቸው ይችላል። በእነዚህ ምክንያቶች ፖለቲካ አስፈሪ እንዲሆን ተደረገ።
ፖለቲካ ማለት የግድ ተቃዋሚ ፓርቲ መስርቶ መታገል፤ ወይም በገዥው መንግሥት ውስጥ ገብቶ ሥልጣን መያዝ ማለት ብቻ አይደለም። በኢኮኖሚ ፖሊሲ ላይ መሳተፍ ፖለቲካ ነው። አንድ ገበሬ ማዳበሪያ በወቅቱ አልደረሰልኝም ቢል ፖለቲካ ነው። አንድ ሐኪም የጤና ፖሊሲ ላይ ጥያቄ ቢያነሳ ፖለቲካ ነው፣ አንድ አርቲስት የፊልም ፖሊሲ ላይ ጥያቄ ቢያነሳ ፖለቲካ ነው። ችግሩ ግን ‹‹ፖለቲካ ነው!›› ሲባል ጭንቅላታችን ውስጥ የተቀረጸው አስፈሪ ነገር ስለሆነ ማዳበሪያ እንዴት ፖለቲካ ይሆናል? ፖለቲካ ማለት የዜጎች ጉዳይ ከሆነ፤ ማዳበሪያ የዜጎች ጉዳይ ነው። ስለዚህ በግብርና ሥራ የሚተዳደሩ ዜጎች የማዳበሪያ ጉዳይ ሲያነሱ የሚያስተዳድራቸውን መንግሥት አቅርብልን እያሉ ነው። ስለዚህ ፖለቲካ ነው ማለት ነው።
ፖለቲካን በዚህ ልክ ማክበድ እና አስፈሪ ማድረግ ተተኪ እንዳይኖር ያደርጋል። ፖለቲካችንም እንዳይሻሻል እና የሰለጠነ እንዳይሆን ያደርጋል። ሥልጣን እና ጥቅም የሚፈልጉ ሰዎች ብቻ የሚገቡበት ያስመስለዋል። እንዲያውም በሰለጠኑት ሀገራት በኢኮኖሚ ራሳቸውን የቻሉ ሰዎች የሚገቡበት ነው።
ሰላም፣ ፍትሕ፣ ሰብዓዊ መብት… የሚባሉት ነገሮች ለሰው ልጅ መሠረታዊ የሆኑ ነገሮች ናቸው። ማንም ሰው ሰላም ይፈልጋል፣ ፍትሕ ይፈልጋል፣ ሰብዓዊ መብቱ እንዲከበር ይፈልጋል፤ እነዚህ ነገሮች የዜጎች ጉዳዮች ናቸው። ስለዚህ ፓርቲ ወይም ድርጅት ውስጥ ገብቶ ለሚታገል ብቻ ሳይሆን ለማንም ሰው ጉዳይ ናቸው ማለት ነው። ፓርቲ ውስጥ ገብቶ መታገል አንዱ አማራጭ ነው፤ እኔ ሥልጣን ይዤ ላስተካክለው ብሎ መጠየቅ የፖለቲከኞች ድርሻ ነው። ዳሩ ግን በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ለመሳተፍ ፓርቲ ውስጥ መግባት የግድ አይደለም።
በአጠቃላይ ፖለቲካ የዜጎች የጋራ ጉዳይ እንጂ ቆሻሻ ነገር አይደለም!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 16 ቀን 2017 ዓ.ም