
የአትሌቲክስ ስፖርት ብዙ ውድድሮች ያለውና ከሌሎች ስፖርቶች ብዙ ሜዳሊያ የሚያስገኝ ዘርፍ ነው። ከአትሌቲክስ ስፖርት ውስጥ ደግሞ በጣም ፈታኙ የረዥም ሩጫና የመሠናክል ውድድር ነው። የመሠናክል ስፖርት 110 ሜትር፣ 400 እና በሦስት ሺ ሜትር መሠናክል የሚካሄድ ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ የሦስት ሺ ሜትር በጣም እልህ አስጨራሽና አድካሚ እንደሆነ በዘርፉ የተሳተፉ አትሌቶች ይናገራሉ።
የዛሬ ጽሑፋችን በእዚህ ስፖርት ስመጥርና አመለ ሸጋ ተብሎ በጓደኞቹና በሚያሠለጥናቸው አትሌቶች ዘንድ የሚነገርለት አሠልጣኝ አትሌት እሸቱ ቱራ ዙሪያ የሚያጠነጥን ይሆናል። መልካም ንባብ።
ሻምበል እሸቱ ቱራ በመላ ዓለም በተለይም በአፍሪካም ሆነ በእስያ እንዲሁም በአሜሪካ በርካታ ኢንተርናሽናል ውድድሮች ከማድረጉም በላይ በሚያስደንቅ ሁኔታ በተደጋጋሚ ጊዜ ድል የተቀዳጀ አትሌት ነው። የሚያኮራ ገድል ከፈጸሙ አትሌቶች ውስጥም የሚመደብ ነው። ሻምበል እሸቱ ቱራ ያስመዘገባቸውን ድሎች አንድ በአንድ ለማቅረብ ጊዜም ስለማይበቃ ዋና ዋናዎቹን ብቻ ለአንባቢያን ለማሳወቅ እንሞክራለን።
በእነ ሻምበል እሸቱ ቱራ ዘመን ኢትዮጵያ ለ6 ጊዜ በኦሎምፒክ ጨዋታዎች ተሳትፋለች። ከእነዚህ ውስጥ በመጀመሪያ የተሳተፈችበት የሜልቦርን ኦሎምፒክ ሲሆን፤ በእዚህ ወቅት ከተሳትፎ ውጪ ምንም ሜዳሊያ አላገኘችም። ከእዚህ በኋላ ባሉት ከሮም እስከ ሞስኮ አሎምፒክ ግን ጠንካራ ተሳትፎ ከማድረጓም ባሻገር 10 ሜዳሊያዎችን በማግኘት ጠንካራ ተፎካካሪነቷን እና አሸናፊነቷን አስመስክራለች። በአጠቃላይ ከተገኙት 10 ሜዳሊያዎች ውስጥም አምስት ወርቅ፣ አንድ ብር እና አራት ነሐስ ነበር። ከእነዚህ ውስጥ በሦስት ሺ ሜትር መሠናክል አንድዋ ነሐስ የሻምበል እሸቱ ቱራ ናት፡፡
ኢትዮጵያ በዓለም ሀገር አቋራጭ ሻምፒዮና መካፈል የጀመረችው በ1973 ዓ.ም (እ.እ.አ. 1981) ለዘጠነኛ ጊዜ ስፔን ማድሪድ ከተማ በተዘጋጀው ውድድር ላይ ነበር። ለአምስት ጊዜ በተከታታይ በቡድን በማሸነፍ ዓለምን አስደንቃለች።
የኢትዮጵያ አትሌቶችም አረንጓዴ ጐርፍ “Green flood” በመባል የተሰጣቸው ስያሜ በእዚሁ ውድድር ላይ ነበር። ስያሜ ከተሰጣቸው አትሌቶች መካከል ደግሞ ሻምበል እሸቱ ቱራ አንዱ ነው።
ሻምበል እሸቱ ቱራ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተወዳደረበት ሜዳ 44 ወርቅ፣ 17 ብር፣ 15 ነሐስ፣ 22 ዋንጫዎች ተሸልሟል። በሀገር ደረጃ ደግሞ በተለያዩ ሻምፒዮናዎች 55 ወርቅ፣ 7 ብር፣ 5 ነሐስ ሜዳሊያዎች አግኝቷል። ይህ ጀግናና አይበገሬ የመሠናክል ተወዳዳሪ በአጠቃላይ በሀገር ውስጥና በኢንተርናሽናል ደረጃ 99 ወርቅ፣ 24 ብር፣ 20 ነሐስ በአጠቃላይ 143 ሜዳሊያዎች በአንገቱ አጥልቋል፡፡
ሻምበል እሸቱ ቱራ የተወለደው በ1942 ዓ.ም በቀድሞ ሸዋ ጠቅላይ ግዛት ደብረ ብርሃን አውራጃ ቅንቢቢት ወረዳ አሌልቱ አካባቢ ነው። የተወለደው ገጠር በሆኑ በቅርቡ የመንግሥት ት/ቤት አልነበረም፡፡በመሆኑም ዕድሜው 13 ዓመት ሲሆነው ታላቅ እህቱ ያለችበት ወደ ሱሉልታ ወረዳ፣ ጫንጮ ከተማ አመራ። ብዙም ሳይቆይ በአካባቢው በሚገኘው ቄስ ትምህርት ቤት ከኔታ ጋር ፊደል ለመቁጠር ዕድል አገኘ።
በትምህርቱ ጥቂት እንደገፋ 22 ዓመት ሲሞላው ወታደር ለመሆን አለመ። በ1961 ዓ.ም የአካባቢውን ወጣቶች በመከተል ውትድርና ለመቀጠር አመልክቶ በቀድሞ ሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት በሚገኝ 4ኛ ክ/ጦር ተቀላቀለ። የአትሌቲክስ ስፖርት የጀመረውም በእዚሁ ጊዜ ነበር።
ሻምበል እሸቱ ቱራ የአትሌቲክስ ስፖርት ክፍል በሻምበል፣ በሻለቃ፣ በብርጌድ ደረጃ በደረጃ በመወዳደር አሸናፊ በመሆኑ በ4ኛ ክፍለ ጦር ደረጃ በተዘጋጀው ውድድር ላይም ከፍተኛ ውጤት አመጣ። በጥቂት ጊዜ ውስጥም የወደፊቱ የሀገሪቱ ተስፋ መሆኑን አሳየ።
በየጊዜው ዕድገት እያሳያ በመምጣቱ በ1964ዓ.ም በተዘጋጀው የመላ ኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች የስፖርት ውድድር የደቡብ ዕዝ ምርጥ አትሌት በመሆን ክፍሉን በመወከል ተካፈለ። በ1500 ሜትር በመወዳደር 3ኛ በመውጣት የነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆነ። ይህቺ ሜዳሊያ ለእሸቱ ቱራ የሞራል ስንቅ ሆነች።
በሚቀጥለው ቀን የ5ሺ ሜትር እና የሦስት ሺ ሜትር መሠናክል በሁለቱም አንደኛ በመሆን የወርቅ ሜዳሊያ አገኘ። የክፍሉንም የሜዳሊያ ቁጥር ከፍ አደረገ። የወከለው ክ/ጦርም ጀግናዬ ብሎ አዜመለት፣ አሞገሰውም። በእዚሁ ምክንያት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ የአትሌቲክስ ቡድን የመመረጥ ዕድል አገኘ።
እሸቱ ቱራ በ1966 ዓ.ም ለብሔራዊ አትሌቲክስ ቡድን በመመረጡም በሦስት የቻይና ከተሞች በተደረገው ኢንተርናሽናል ውድድር ሀገሩን ወክሎ ተሳተፈ። ከተሳትፎም አልፎ በሦስቱም ውድድሮች በብቃት አንደኛ በመሆን የሦስት ወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ሆነ። ከኢትዮጵያና ከአፍሪካ አህጉር አልፎ በዓለም ደረጃ ታወቀ።
ሻምበል እሸቱ ቱራ በነገሰበት ዘመን በወቅቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ አንድ ውድድር ይደረጋል። በእዚህ ውድድር ላይ አህጉራት የራሳቸውን ምርጥ አትሌቶች እንዲያቀርቡ ይጠየቃሉ። በእዚሁ መሠረት አፍሪካም አንድ ቡድን ለማዘጋጀትና ምርጥ አትሌቶች ለመምረጥ ሻምፒዮና ማዘጋጀት እንዳለበት የአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን ውሳኔ ያስተላልፋል።
በውሳኔው የተስማሙ ኮሚቴም የመጀመሪያ ሻምፒዮና ቱኒዚያ እንድታዘጋጅ መረጣት። ውድድሩ በተለያዩ መስፈርቶች አሸናፊ የሆኑ አትሌቶች ተመረጡ። ሻምበል እሸቱ ቱራ በውድድሩ ሦስት ሺ ሜትር መሠናክል አሸናፊ በመሆኑ አህጉሪቷን በመወከል በዓለም ሻምፒዮና ላይ ተሳተፈ። በውድድሩም ታሪክ በማሳየት በሚያስደንቅ ሁኔታ አሸነፈ። በእዚህ ውድድር ታዋቂው ጀግና ምሩፅ ይፍጠር አፍሪካን በመወከል በ10ሺ ሜትር ተወዳድሮ የሜዳሊያ ባለቤት መሆን የቻለበት ወቅት ነው።
ሻምበል እሸቱ ቱራ በሦስት ሺ ሜትር መሠናክል ከማሸነፉም በላይ በወቅቱ የዓለም ሦስት ሺ፣ 5ሺና 10ሺ ሜትር በከፍተኛ ደረጃ ለረጅም ጊዜ አሸናፊ በመሆን የተሞገሰውን እና የሪከርድ ባለቤት የነበረውን ኬንያዊው ሄኔሪ ሮናን በ6.78 ሰከንድ ቀድሞ በመግባት አይበገሬነቱን አሳይቷል። እንዲሁም በወቅቱ በምዕራብ ጀርመን በዱስል ዶርፉ ከተማ አፍሪካን በመወከል በሦስት ሺ ሜትር መሠናከል ሁለተኛ በመሆን የብር ሜዳሊያ ድል ተጎናጽፏል፡፡
በሌላም በኩል ሻምበል እሸቱ ቱራ ለመጀመሪያ ጊዜ በሴኔጋል ዋና ከተማ ዳካር በተዘጋጀው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በሦስት ሺ ሜትር መሠናክል ሁለተኛ በመሆን አሸናፊ መሆን ችሏል። በግብፅ ካይሮ በተደረገው ሦስት ሺ ሜትር ውድድር አንደኛ በመሆን አሸንፏል። በ5ሺ ሜትር ደግሞ ሁለተኛ በመሆን የብር ሜዳሊያ አግኝቷል።
ሻምበል እሸቱ ቱራ ካናዳ በተደረገው የሁለት ሺ ሜትር ውድድር ከማሸነፉም በላይ በወቅቱ የዓለም ሪከርድ ባለቤት በመሆን ተሸልሟል። የገባበት ሰዓት 8፡13.59 ሲሆን ይህ ሪከርድ በእሱ እጅ ለረጅም ጊዜ ቆይቷል።
በ1972 ዓ.ም ሞስኮ በተደረገው 22ኛው ኦሎምፒክ ሀገሩን ኢትዮጵያ በመወከል በሦስት ሺ ሜትር መሠናክል ተወዳድሮ የዓለም ታዋቂ አትሌቶችን በማስጨነቅ ያሸንፋል ተብሎ ሲጠበቅ ለጥቂት ተቀድሞ 3ኛ በመሆን የነሐስ ሜዳሊያ ለመጀመሪያ ጊዜ በእዚህ መስክ ለኢትዮጵያ አስገኝቷል፡፡
ይህች እሸቱ ቱራ ያገኛት ሜዳሊያ ለረጅም ዓመታት በታሪክ ተመዝግባ በሀገራችን የአትሌቲክስ ቤተሰብ ዘንድ ስትታወስ የምትኖር ናት።
ሻምበል እሸቱ ቱራ ውድድሩን ካቆመ በኋላ በመቻል ስፖርት ክለብ የአትሌቲክስ ስፖርት አምበል በመሆን አሠልጣኝም ነበር። በሀገር ውስጥም የተለያዩ ኢንተርናሽናል የአሠልጣኝነት ኮርሶች ተከታትሏል። ጀግናው እሸቱ ቱራ በኢንተርናሽናል የአሠልጣኝነት ኮርስ ላይ በውጤት ከመቶ ዘጠና ስምንት በማምጣት ብቃቱን አሳይቷል።
በጣም የሚገርመው የሻምበል እሸቱ ቱራ ጥንካሬ በሀገር ውስጥ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ የመሠናክል ስፖርት እያሸነፈ እንደሚያልፍ ሁሉ በየጊዜው ትምህርቱን በመከታተል የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በዳግማዊ ምኒልክ በመከታተል በቀለሙም መስክ ደማቅ ታሪክ ከጻፉ አትሌቶች አንዱ ነበር፡፡
ሻምበል እሸቱ ቱራ የብሔራዊ አትሌቲክስ አሠልጣኝ በነበረበት ጊዜ የታዳጊ ወጣቶችን ከማሠልጠኑም በላይ ፌዴሬሽኑ የመሠናክል ማቴሪያል እጥረት ስለ ነበረበት በአዲስ አበባ ስታዲየም ሠልጣኞቹን በማስተባበር በራሱ መዶሻ ጭምር ምስማር በመግዛት መሠናክል (ዝላዩን) እያዘጋጀ ያሠለጥን ነበር። እንዲሁም የተለያዩ ክለቦች በማደራጀት ሥልጠና በመስጠት ይታወቃል። በተለይም እንደ ቀስተደመና አትሌቲክስ ክለብ እና ሌሎች የግል ክለቦች በእነዚህ ዓመታት ታዋቂ የብሔራዊ አትሌቶቻችን በሻምበል እሸቱ ቱራ አማካኝት መድመቅ ችለዋል።
አመለ ሸጋው እሸቱ ቱራ በ1960ዎቹና በ70ዎቹ ውስጥ ከስመጥር አትሌቶች ከነሻምበል ምሩፅ ይፍጠር፣ ከበደ ባልቻ፣ ደረጀ ነዲና አሠልጣኝ ንጉሴ ሮባ ጋር ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል። በ1983 አዲስ የመንግሥት ለውጥ ተከትሎ የብሔራዊ አትሌቲክስ ቡድን ሲበተን እና ብሔራዊ አሠልጣኞች ሲባረሩ ለተወሰነ ጊዜ እቤቱ ከተቀመጠ በኋላ የውሃ ዋና ፌዴሬሽን ተመድቦ የፌዴሬሽኑ ጽ/ቤት ኃላፊ በመሆን ሠርቷል፡፡ይህ ታላቅ አትሌትና አሠልጣኝ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ ኮተቤ አካባቢ ይኖራል።
እኛም በእዚህ ለሕዝብና ሀገራቸው መልካም ያደረጉና በተሠማሩበት ዘርፍ ሁሉ የማይነጥፍ ዐሻራ ማኖር የቻሉ ግለሰቦች ታሪክ አንስተን ለአበርክቷቸው ክብር በምንሰጥበት የባለውለታዎቻችን አምድ እውቁን የ3ሺ መሰናክል አትሌት ሻምበል እሸቱ ቱራ ላበረከተው ዘመን ተሻጋሪ ሥራ አመሰገንን። ሰላም!
በተሾመ ቀዲዳ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 16 ቀን 2017 ዓ.ም