የፌዴራል መንግሥት ከትግራይ ሕዝብ ጋር በቀጥታ መነጋገር እንዳለበት ተገለጸ

አዲስ አበባ፡- የትግራይ ሕዝብ ጦርነት አክሳሪ እንደሆነ ከበቂ በላይ ስለተማረ የፌዴራል መንግሥት ከትግራይ ሕዝብ ጋር በቀጥታ ተገናኝቶ በመነጋገር ያሉትን ችግሮች ሊፈታ ይገባል ሲሉ የመቐለ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

የመቐለ ከተማ ነዋሪ እና የመንግሥት ሠራተኛ የሆነችው ወጣት በረከት ተዓረ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለፀችው፤ አሁን እንደ ሕዝብ ያለንበት ሁኔታ በአጭሩ ስገልፀው ‹‹እባብን ያየ በልጥ በረየ›› የሚለውን አባባል ያስታውሰኛል፤ ምክንያቱም ቀደም ሲል ያሳለፍነው የመከራ እና የስቃይ ጦርነት እንዲሁም ያንን ተከትሎ የመጣው የኑሮ መመሰቃቀል ሲደመር አሁን የክልሉ መሪዎች እየፈጠሩት ያለው ሁከት በፍራቻ እና ሰቀቀን ውስጥ አስገብቶናል።

የፌዴራል መንግሥት ከእኛ ከተበዳዮች እና ሰላም ፈላጊዎች ጋር በቀጥታ ተገናኝቶ ችግሮቻችንን ሊሰማን ይገባል ያለችው በረከት፤ በተለይም ከሴቶች፣ ከወጣቶች እና የመንግሥት ሠራተኞች ጋር በቀጥታ መገናኘት ሲገባው በሶስተኛ ወገን ተመካከሩ ተስማሙ እያለ እስከ አሁን ይህ ነው የሚባል ለውጥ ሳናገኝ ብዙ ጊዜ እየፈጀብን ነው፤ ይህም ወደ አላስፈላጊ አቅጣጫ እያመራ መሆኑን እና ሕዝቡም ፍርሃት ውስጥ እንደገባ ተናግራለች።

በክልሉ ከነገ ዛሬ ጦርነት ይጀመራል በሚል ስጋት አሁንም ከፍርሃት የመነጨ የሰላም እጦት መኖሩን ጠቁማ፤ በተለይ የመንግሥት ሠራተኛው በሁለንተናው እየተጎዳ እና ልጆቹን በሰላም እንዳያስተምር የኑሮ ውድነት እና የትምህርት ቤት ክፍያ ተደማምሮ አሁን ላይ የክልሉ መሪዎች በሚፈጥሩት አስፈሪ መግለጫ ጦርነት እንዳይቀሰቀስ ጭንቅ ውስጥ ገብተናል፤ በዚህም ምክንያት እንደ ሕዝብ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ እንገኛለን ብላለች።

በተለይ የክልሉ አመራሮች እና የጦር አዛዦች ከፌዴራል መንግሥት ጋር እያደረጉት ያለው አሉታዊ ግብረ መልስ፤ ወደ ጦርነት እንዳንገባ የሚል ከባድ ጭንቅ ውስጥ ነን ብላለች። የፌዴራል መንግሥት አካላት መቐለ ድረስ መጥተው በቀጥታ ከሕዝቡ ጋር በመገናኘትና በችግሩ ዙሪያ በመወያየት እፎይታ ሊሰጡ ይገባል ስትል ተናግራለች።

በመቐለ ሐድነት ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ዮሐንስ መብራህቱ በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት፤ ሕዝቡ በችግርና በድህነት መሰቃየቱ ሳያንስ አሁንም የክልሉ መሪዎች ወደ ከፋ ችግር ለማስገባት ከፌዴራል መንግሥት ጋር የሻከረ ግንኙነት እየፈጠሩ ዳግም ወደ ጥፋት ሊያስገቡን እየፈረዱ ነው።

ትግራይ እንደ ክልል ተወደደም ተጠላም በፌዴራል መንግሥት ስር ናት ያሉት አቶ ሐድነት፤ ሆኖም ግን የክልሉ አመራሮች ቅድሚያ ሊሠሩት የሚገባ የቤት ሥራ ሕዝቡን ማረጋጋት እና በኢኮኖሚ ማሻሻል ሲገባቸው ይህንን ወደ ጎን በመተው አሁንም የበፊቱን የጥፋት መንገድ እያሰፉ ሕዝቡን ወደ ፍርሃት እና ጭንቀት እየከተቱት ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ወጣት ጥዕማይ ገብረ በበኩሉ፤ በአሁኑ ጊዜ እንደሚባለው ዳግም ጦርነት ከተነሳ የትግራይ ሕዝብ ከባድ ችግር ላይ ይወድቃል፤ ምክንያቱም የሕዝብን ፍላጎት እና አቅም መረዳት እጅግ አስፈላጊ ነው ፤ እኛ እንደ ሕዝብ የተሻለ ኑሮ እና ዘላቂ ሰላም የሚሰጡን መሪዎች እንፈልጋለን፤ በጦርነት ከበቂ በላይ ተምረናል ፤ ይበቃናል ሲል ተናግሯል።

ሔርሞን ፍቃዱ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You