በባንግላዲሽ ጄት ተከስክሶ ቢያንስ 22 ሰዎች ሞቱ

የባንግላዲሽ አየር ኃይል ማሰልጠኛ ጄት በዋና ከተማዋ ዳካ በሚገኝ ትምህርት ቤት ግቢ ውስጥ ተከስክሶ ቢያንስ 22 ሰዎች ሲሞቱ ከ170 በላይ ሰዎች ቆሰሉ። አውሮፕላኑ በኡታራ አካባቢ ከሚገኘው የማልስቶን ትምህርት ቤት እና ኮሌጅ ባለ ሁለት ፎቅ ሕንጻ ጋር ከተጋጨ በኋላ ከፍተኛ እሳት እና ጭስ ታይቷል። የጦር ኃይሉ በፌስቡክ ገፁ ላይ በሰጠው መግለጫ ኤፍ-7 ጄት ሰኞ ዕለት ከቀኑ 7፡00 ሰዓት ለሥልጠና ከተነሳ በኋላ ችግር አጋጥሞታል። የአውሮፕላኑ አብራሪ በአደጋው ከሞቱት መካከል እንደሚገኝ የአየር ኃይሉ ጨምሮ ገልጿል።

ከ50 በላይ ሰዎች በእሳት ተቃጥለው ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል፤ ብዙዎቹ በአስጊ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ የብሔራዊ የቃጠሎ እና የፕላስቲክ ቀዶ ጥገና ሐኪም ተናግረዋል። ከሟቾቹ መካከል ብዙዎቹ አውሮፕላኑ በተከሰከሰበት ወቅት ከትምህርት ቤት እንዲወጡ የተደረጉ ተማሪዎች ናቸው። ከሟቾቹ ውስጥ 17ቱ ሕጻናት መሆናቸውን የሀገሪቱ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

በትምህርት ቤቱ ውስጥ የሚማሩት ዕድሜያቸው ከአራት እስከ 18 ዓመት መካከል መሆኑ ተገልጿል። የኮሌጁ መምህር ረዙል ኢስላም አውሮፕላኑ “በቀጥታ” ከሕንፃው ጋር ሲጋጭ መመልከታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሌላው መምህር ማሱድ ታሪክ ለሮይተርስ የዜና ወኪል እንደተናገሩት ፍንዳታ እንደሰማሁ “ወደ ኋላ ዞሬ ሳይ እሳትና ጭስ ብቻ ነው የተመለከትኩት… እዚህ ብዙ ተንከባካቢዎች እና ሕጻናት ነበሩ። “የ10 ዓመቱ የትምህርት ቤቱ ተማሪ ፈተናውን እንደጨረሰ ከሕንጻው መውጣቱን ተናግሮ፣ አውሮፕላኑ ከሕንፃው ጋር ሲጋጭ “ፊት ለፊት በዓይኔ አይቻለሁ” ብሏል። የቅርብ ጓደኛው አጠገቡ መሞቱንም ነው የገለጸው።

አብራሪው ሌተናንት ታውኪር ኢስላም የሜካኒካል ችግር ከገጠመው በኋላ አውሮፕላኑን ብዙ ሰዎች ወደሌሉበት አካባቢ ለመውሰድ እየሞከረ እንደነበር የአገሪቱ ጦር መግለጫ ያስረዳል። የጦር አውሮፕላኑ የተነሳው በዋና ከተማው ከሚገኝ የአየር ኃይል ማዘዣ ነው። መግለጫው አክሎም ጉዳዩን የሚያጣራ ኮሚቴ መቋቋሙን ገልጿል።

ከአደጋው በኋላ ከስፍራው የተገኙ ምስሎች በርካታ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች በተቃጠሉ ፍርስራሾች ውስጥ በሕይወት የተረፉ ሰዎችን ለማግኘት ሲሞክሩ ያሳያሉ። ተጎጂዎች በከተማው በሚገኙ ሰባት ሆስፒታሎች ሕክምና እየተደረገላቸው ነው ሲል የሀገሪቱ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

በኡታራ አዱኒክ ሜዲካል ኮሌጅ ሆስፒታል ተረኛ የሆኑት የሕክምና ባለሙያ እንደተናገሩት፤ አብዛኞቹ የተጎዱት ከ10 እስከ 15 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ሲሆን በርካቶቹ በጄቱ ነዳጅ የተቃጠሉ ናቸው። የዳካ ብሄራዊ የቃጠሎ እና የፕላስቲክ ቀዶ ጥገና ተቋም ደም ለመለገስ በመጡ በጎ ፈቃደኞች፣ ስለ ልጆቻቸው ለመጠየቅ በመጡ ወላጆች ተጨናንቋል።

የስምንት ዓመት የወንድሙን ልጅ የሚፈልግ አንድ ግለሰብ በህክምና ተቋሙ አካባቢ ሆኖ “የምወደው የወንድሜ ልጅ በአስከሬን ክፍል ውስጥ ነው” እያለ የታናሽ ወንድሙን፣ የልጁን አባት፣ ክንድ ተደግፎ ሲያለቅስ ይሰማል። የልጁ አባት “ልጄ የት አለ?” እያለ ደጋግሞ ይጠይቃል። የባንግላዲሽ ጊዜያዊ መንግሥት መሪ መሀመድ ዩኑስ የአደጋውን መንስኤ ለመመርመር እና “ሁሉንም አይነት ርዳታ መድረሱን ለማረጋገጥ”፤ “አስፈላጊ ርምጃዎች” እንደሚወሰዱ ተናግረዋል።

በኤክስ ገጻቸው ላይ “ይህ ለአገሪቱ ጥልቅ የኀዘን ጊዜ ነው። የተጎዱት በፍጥነት እንዲያገግሙ እመኛለሁ. . . “ ብለዋል። ባንግላዲሽ ማክሰኞ የሐዘን ቀን እንዲሆን በማወጇ የሀገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ በመላ ሀገሪቱ በግማሽ ዝቅ ብሎ ተውለብልቧል ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው።

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You