በዞኑ ዘንድሮ በአረንጓዴ ዐሻራ 750 ሄክታር መሬት በአቮካዶ ችግኝ ይሸፈናል

ሞጆ፡- በኦሮሚያ ክልል የምስራቅ ሸዋ ዞን በዘንድሮ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀግብር 750 ሄክታር በአቮካዶ ችግኝ ለመሸፈን መታቀዱን የዞኑ ግብርና ፅህፈት ቤት አስታወቀ። በሰባተኛው ዙር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር እስካሁን 250 ሄክታር መሬት በአቮካዶ ችግኞች ለመሸፈን መቻሉ ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ትናንትና በኦሮሚያ ክልል የምስራቅ ሸዋ ዞን ሎሜ ወረዳ የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር አካሂዷል።

በእለቱም ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ቆይታ ያደረጉት በኦሮሚያ ክልል የምስራቅ ሸዋ ዞን የግብርና ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መስፍን ተሾመ፤ ከዚህ ቀደም በአረንጓዴ ዐሻራ ልማት መርሀግብር የተራቆቱ ጋራዎችን ማልማት የተለመደ መሆኑን ተናግረዋል። ከሶስት ዓመታት በፊት ጀምሮ የፍራፍሬ ችግኞችን በወረዳዎች እየተከሉ እንደሚገኙ ገልፀዋል። ዘንድሮም በኦሮሚያ ክልል የምስራቅ ሸዋ ዞን በአረንጓዴ ዐሻራ መርሀግብር 750 ሄክታር በአቮካዶ ችግኝ ለመሸፈን መታቀዱን አመልክተዋል።

ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬ ችግኞች የአካባቢን አፈር ለምነት ለማስጠበቅ፣ የተበከለ አየርን ከመቀነስ ባለፈ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸው የላቀ እንደሆነም ኃላፊው ገልጸው፤ በዞኑ በዘንድሮ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀግብር ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬ ችግኞችን በሰፊ መሬት ላይ በኩታ ገጠም እየተተከለ እንደሚገኝ እና አስካሁንም የአቮካዶ ችግኝ በ250 ሄክታር ላይ መተከሉን ገልፀዋል።

እንደ ኃላፊው ገለፃ፤ ዞኑ ለአቮካዶ ምርት የአፈር፣ ምድራዊ አቀማመጥ እና የአየር ሁኔታው ምቹ ነው። ችግኞቹ በተተከሉበት ቦታም የሚያልፍ የመስኖ ውሃ በመኖሩ ከእዚህ ቀደም የተተከሉ የአቮካዶ ችግኞች ፍሬ አፍርተው ለውጭ ገበያ በመቅረባቸው ከፍተኛ ገቢ ለሀገሪቱ ማስገኘት ችለዋል።

በዞኑ ከዚህ ቀደም በአንድ ሄክታር መሬት ላይ ከ13 እስከ 14 ኩንታል ብቻ ጤፍ እንደሚመረት የተናገሩት ኃላፊው፤ በአቮካዶ ምርት ግን ከ200 እስከ 250 ኩንታል በማምረት በሚሊዮን የሚቆጠር ብር ገበሬው እንደሚያገኝ አስረድተዋል።

ችግኞቹ ከፍተኛ እንክብካቤ እና ትኩረት የሚፈልጉ በመሆናቸው ለገበሬዎቹ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ መሠራቱንም ኃላፊው ተናግረዋል።

የአቮካዶ ምርትን በዞኑ ከሶስት ዓመታት በፊት ሲጀመር ለገበሬው አዲስ በመሆኑ እምብዛም ተቀባይነት እንዳልነበረው ያስታወሱት አቶ መስፍን፤ በአሁኑ ጊዜ ግን በተሠራው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እና ቀድመው ተጠቃሚ የሆኑ የአርሶ አደሮች ምስክርነት በዞኑ ችግኞቹን የመትከል ፍላጎት መጨመሩን አብራርተዋል።

በዞኑ የሚተከሉት ችግኞችም ከፍተኛ ምርት የሚያስገኙ የተመረጡ የአቮካዶ ችግኞች ሲሆኑ፤ተተክለው ሶስት ዓመት እስኪሞላቸው ድረስ በዓመት አንድ ጊዜ የሚያፈሩ ይሆናል። ከሶስተኛ ዓመት በኋላ ግን በዓመት ሁለት ጊዜ ፍሬ በማፍራት ምርቶቹን ኤክስፖርት ለማድረግ እንደሚቻልም ተናግረዋል።

አቶ መስፍን በቀጣይም ሙዝ፣ ፓፓያ፣ ብርቱካን እና ሎሚ በክላስተር ለመትከል መታቀዱን ገልጸው፤ ከፍተኛ የሎሚ ምርት ፍላጎት ያለ በመሆኑ፤ ከህንድ የሎሚ ችግኞችን በማስመጣት በአንድ ወረዳ ላይ የተከላ መርሀግብር መካሄዱን ገልፀዋል።

መክሊት ወንድወሰን

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You