
የትግራይ ሕዝብ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ነፃነት መስዋዕትነት የከፈለ ሀገር ወዳድ ሕዝብ ነው። ኢትዮጵያን ሊወሩ በየዘመናቱ የመጡ ወራሪዎችን አሳፍሮ ሲመልስ የቆየና ለሀገሩ ነፃነትና ሉዓላዊነት ሲዋደቅ የኖረ ነው። የትግራይ ሕዝብ ከሌሎች ወንድም እህቶቹ ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን ለሀገሩ ዳር ድንበር የሚዋደቅ፤ ከራሱ በፊት ሀገሩን የሚያስቀድም፤ ቅኝ ገዢዎችንና ሌሎች ወራሪ ኃይላትን አሳፍሮ የመለሰ ጀግና ኢትዮጵያዊ ነው።
የትግራይ ሕዝብ የጀግንነቱን ያህል ሰላም ወዳድም ነው። በየትም ሥፍራ ቢኖር፣ የትኛውንም እምነት ቢከተል ለሰላምና አብሮነት ሰፊ ቦታን ይሰጣል። ከሰላም እጦት ብዙ ዋጋ የከፈለ ሕዝብ እንደመሆኑ ሰላም የዕሴቶቹ አንዱ መገለጫ ነው።
ይሁን እንጂ ከዚህ አኩሪ ከሆነው የትግራይ ሕዝብ ባህል ባፈነገጠ መልኩ ፍላጎታቸውን በነፍጥ ማሳካት የሚፈልጉ በስሙ የሚነግዱ ጽንፈኛ ቡድኖች እየተበራከቱ መጥተዋል። ጦርነት ናፋቂዎች እና ከውይይት ይልቅ ነፍጥ ማንሳት የሚቀናቸውና ሰላም ወዳዱን ሕዝብ የሚረብሹ፤ አብሮነቱን የሚያውኩ፤ የኢትዮጵያን መረጋጋትና ሉዓላዊነት የሚገዳደሩ ጽንፈኛ ቡድኖች በስሙ እዚህም እዚያም አቆጥቁጠዋል፡፡
እነዚህ ወገኖች በሚፈጥሩት ሁከትና ብጥብጥም ሀገር ብዙ ዋጋ ከፍላለች፤ ልማት ተደናቅፏል፤ የሰዎች ወጥቶ መግባት ተስተጓጉሏል፤ ምንም እንኳን በመላ ኢትዮጵያውያን አኩሪ ተጋድሎ ባይሳካም የሀገር ሕልውና አደጋ ላይ የሚጥል ተግባር ተፈጽሟል።
ሆኖም ዛሬም ሆነ ትላንት የትግራይ ሕዝብ ዋነኛ ፍላጎት ከተቀረው ወገኑ ጋር በሰላም፤ በእኩልነትና በፍትሐዊነት መኖር ነው። የትግራይ ሕዝብ ዋነኛ ጠላት ድህነት ነው። የትግራይ ሕዝብ ምኞት ኋላቀርነትና ብልሹ አሠራሮችን ማስወገድ ነው። የትግራይ ሕዝብ ዋነኛ ምኞት ንጹሕ የመጠጥ ውሃ፤ የኤሌክትሪክ አቅርቦት፤ መንገድና መሰል የመሠረተ ልማቶች መስፋፋት ነው። የትምህርትና የጤና አገልግሎት ማግኘት ነው።
የትግራይ ክልል ከደርግ ጊዜ ጀምሮ በጦርነት ሲታመስ የቆየ በመሆኑ ከሌሎቹ አካባቢዎች በባሰ መልኩ የመሠረተ ልማት እጥረት እና የመሠረታዊ ፍላጎቶች አለመሟላት የሚታይበት አካባቢ ነው።
በስሙ ሲነገድበት ቢኖርም ከደርግ ውድቀት በኋላም ቢሆን መፈታት የሚገባቸው ነገር ግን ያልተፈቱ በርካታ የልማት እና የሰላም ጥያቄ ያለበት ክልል ነው። የዘመናት የሕዝብ ጥያቄ የሆነው የንፁሕ መጠጥ ውሃ ፍላጎት ዛሬም በቂ ምላሽ አላገኘም። ወረዳዎችን ዞኖችን የሚያገናኙ መንገዶች ዛሬም በበቂ ሁኔታ አልተዳረሱም። በጦርነት የወደሙ ትምህርት ቤቶች እና የጤና መሠረተ ልማቶች መልሰው እንዲገነቡም ሕዝቡ ተደጋጋሚ ጥያቄዎችን እያቀረበ ነው።
የአካባቢ መራቆት እና የምርታማነት አለመጨመር ዛሬም የትግራይ አርሶ አደር ጥያቄ ነው። በሴፍትኔት የሚረዳውን ከፍተኛ ቁጥር ያለውን የትግራይ ሕዝብ ከተረጂነት ማላቀቅ የቤት ሥራ ሆኖ ዓመታትን ተሻግሯል።
ከዚሁ ባሻገር በቅርቡ በተደረጉ ጦርነቶች በርካቶች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ለአስከፊ ችግር ተጋልጠዋል። ሆኖም አንዳንድ አካላት ጉዳዩን ከሰብዓዊነት ይልቅ ፖለቲካ መልክ እንዲኖረው በማድረጋቸው ተፈናቃዮቹ አሁንም በከፋ ችግር ውስጥ እንዲማቅቁ ምክንያት ሆኗል።
ከዚሁ ጎን ለጎንም በጦርነቱ የተሳተፉ ወጣቶች በመልሶ ማቋቋም ወደ ሰላማዊ ሕይወታቸው እንዲመለሱ የሚደረገውንም ጥረት በእነዚሁ አካላት መስተጓጎል ገጥሞታል። የጦርነት አጋፋሪዎቹ የጦርነትና ግጭት ወላፈን እነሱን ስለማይነካ ጦር አውርድ ወሬዎች ላይ ተጠም ደው ውለው ያድራሉ።
ጽንፈኞቹ ከሁሉ በከፋ መልኩ ክልሉ ያለውን በጀት ለልማት ከማዋል ይልቅ ከፍተኛ ቁጥር ላለው ሠራዊት ደመወዝ እከፍላለሁ ብሎ መነሳቱ የሕዝቡ የልማት እና ሰላም ጥያቄዎች እንዳይመለሱ እንቅፋት ሆኗል። ይህ ደግሞ ለትግራይ ሕዝብ ተጨማሪ ሸክም የሚፈጠር ነው።
ስለዚህም እነዚህ የተሳሳቱ አካሄዶች ፈር ሊይዙ ይገባል። የትግራይ ሕዝብ ዋነኛ ፍላጎት ከተቀረው ወገኑ ጋር በሰላም፤ በእኩልነትና በፍትሐዊነት መኖር ነው። የትግራይ ሕዝብ ዋነኛ ጠላት ድህነት ነው። የትግራይ ሕዝብ ምኞት ኋላቀርነትና ብልሹ አሠራሮችን ማስወገድ ነው። የትግራይ ሕዝብ ዋነኛ ምኞት ንፁሕ የመጠጥ ውሃ፤ የኤሌክትሪክ አቅርቦት፤ መንገድና መሰል የመሠረተ ልማቶች መስፋፋት ነው።
በአጠቃላይ የትግራይ ሕዝብ ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ አካላት በሙሉ የትግራይን ሕዝብ የሰላም እና የልማት ፍላጎት ሊረዱ ይገባል። ትላንትም ሆነ ዛሬ የትግራይ ሕዝብ ፍላጎት ሰላም እና ልማት ብቻ ነው!
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 16 ቀን 2017 ዓ.ም