የተስፈኛው ወጣት አትሌቲክስ ቡድን አበረታች ጅምር

እንደ ኦሊምፒክና የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ባሉ መድረኮች ሀገርን በድል ሊያስጠሩ የሚችሉ ምርጥ አትሌቶችን ለማፍራት ታዳጊና ወጣት አትሌቶች ላይ ማተኮር አስፈላጊ መሆኑ ግልጽ ነው። በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታም ታዳጊዎችን ከትምህርት ቤቶች በመመልመል፤ በፕሮጀክቶች እና ማሰልጠኛ ማዕከላት አልፈው ለክለቦችና ብሄራዊ ቡድኖች እንዲበቁ የማድረግ ሂደት ተግባራዊ ይደረጋል። ይሁንና በትክክለኛው ዕድሜ ታዳጊዎችን ከማፍራት አንጻር ክፍተቶች መኖራቸው ተደጋግሞ ተነግሯል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም በዚህ ምክንያት በተደጋጋሚ ሲወቀስ የቆየ ቢሆንም ዘንድሮ በወሰደው ቁርጠኛ ርምጃ በተገቢው ዕድሜ የወጣት ቡድኑን በመምረጥ አበረታች ጅምር አሳይቷል። በህክምና ምርመራ ዕድሜያቸው ተረጋግጦ በናይጄሪያው አህጉር አቀፍ ቻምፒዮና የተሳተፈው የወጣት ቡድን ወደ ሀገሩ ሲመለስም አባላቱን ለማትጋት የሚያስችል የሽልማትና ዕውቅና መርሃ ግብር አከናውኗል።

ከሰሞኑ በናይጄሪያ አቡኩታ ከተማ ሲከናወን በቆየው የአፍሪካ ከ18 እና 20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ቻምፒዮና ሀገሩን የወከለው ቡድን ትናንት የማበረታቻ ገንዘብ ሽልማት ተበርክቶለታል። በሁለቱም የዕድሜ ምድብ 28 አትሌቶችን ያካተተው ቡድን 2 የወርቅ፣ 3 የብር እና 5 የነሃስ በጥቅሉ 10 ሜዳሊያዎችን ማስመዝገቡ የሚታወስ ነው።

ቡድኑ በናይጄሪያ ቆይታው የነገው አትሌቲክስ ተረካቢ መሆኑን በማስመስከሩ ደማቅ አቀባበልና የዕውቅና መድረክ በፌዴሬሽኑ ተዘጋጅቷል። ሰንደቃቸውን ለማውለብለብ የበቁት ታዳጊና ወጣት አትሌቶች የተደረገላቸውን አቀባበል ተከትሎ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ከ18 ዓመት በታች ቡድን በ800 ሜትር የወርቅ እንዲሁም በ1 ሺህ500 ሜትር የብር ሜዳሊያ ያጠለቀችው ወጣቷ አትሌት ኤልሳቤጥ አማረ፤ በናይጄሪያ የነበራቸው ቆይታ አስቸጋሪ ቢሆንም የተሰጣቸውን አደራ ለመወጣት የቡድኑ አባላት ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸውን ገልጻለች። ይህ ጅማሬ እንደመሆኑ የተገኘውን ልምድ በማዳበር በቀጣይ ሀገርን ለመወከል ጥረት እንደሚደረግም ጠቁማለች።

በብሄራዊ ቡድኑ የረጅም ርቀት አሰልጣኙ መሠረት መንግሥቱ፤ ውድድሩ ከባድ ቢሆንም በትክክለኛው መስፈርት መሠረት ተሳትፎ የተደረገበት በመሆኑ ራስን ለማየት የሚጠቅም መሆኑን ያመላክታል። የነበሩት ተጽእኖዎች ውድድሩን ፈታኝ በማድረጋቸው በሚጠበቀው ልክ ባይሆንም ተስፋ ሰጪ ነው። በመሆኑም በተጀመረው ሁኔታ ዕድሜን ችግር እየቀረፉ በመሄድ ተገቢዎቹ ታዳጊዎች ላይ መሥራትና ትኩረት ማድረግ ይገባል። ኢትዮጵያ ተተኪዎችን የማፍራት ሰፊ አቅም ያላት ሀገር እንደመሆኗ በኬንያ እና ዩጋንዳ የታዩትን ሰፊ ልዩነቶች ለማጥበብ የሚቻልበትን ሁኔታ ላይ ልምድ የተገኘበት ቻምፒዮና መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የወጣት ቡድኑን እየመሩ ወደ ናይጄሪያ ያቀኑት የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ኢንስትራክተር አድማሱ ሳጂም፤ የቡድኑን ቆይታ አብራርተዋል። በናይጄሪያ በነበረው ከባድ ሙቀት፣ የምግብ አቅርቦት ችግር፣ የትራንስፖርት አቅርቦት አለመኖር እንዲሁም ቡድኑ ካረፈበት ስፍራ ውድድሩ እስከሚካሄድበት ስታዲየም ለመድረስ የአንድ ሰዓት ጉዞ ማድረግ እጅግ ፈታኝና በርካታ አትሌቶችን ለህመም የዳረገም ነበር። ይሁንና አትሌቶቹ በነበራቸው ቁርጠኝነት ለችግሮቹ እጅ ባለመስጠት እንዲሁም ባለሙያዎች በአንድነት በሠሩት ሥራ ሜዳሊያዎች ሊመዘገቡ ችለዋል። ተተኪ አትሌቶችን ፍትሃዊ ተሳትፎ ማረጋገጥ ፍሬ ሊያፈራ የሚችል መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው። በተጨማሪም ቀድሞ ኢትዮጵያ ትታማበት የነበረውን የዕድሜ ማጭበርበር ችግር ለመፍታት ፌዴሬሽኑ የወሰደው ርምጃ በአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን ጭምር የተወደሰ እንደነበርም ነው በመድረኩ ላይ ያመላከቱት።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር ስለሺ ስህን፤ ከዕድሜ ጋር በተያያዘ ፌዴሬሽኑ ጥብቅ ውሳኔ ላይ መድረሱን ተከትሎ ቡድኑ ይህን ያህል ውጤት ያስመዘግባል ተብሎ ባይጠበቅም ሀገርን ያከበረ ውጤት በመመዝገቡ ለቡድኑ አባላት ምስጋናውን አቅርቧል። ከውጤት ባልተናነሰ አትሌቲክሱ መስመር መያዝ አለበት የሚለው የሥራ አስፈጻሚው አቅጣጫ በመሆኑ ከዚህም በኋላ በተመሳሳይ በዕድሜ ተገቢነት ላይ ጠበቅ ያለ ርምጃ ይወሰዳል። ተገቢ አትሌቶች የሚገባቸውን ሲያገኙ ውጤት የሚገኝ እንደመሆኑ በዚህ ሂደት ተሳታፊ የነበሩ አካላት በሙሉ ሊመሰገኑ ይገባል።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You