“የዓባይ ግድብ በኢትዮጵያውያን ወዝና ላብ የተገነባ ነው”

-የግድቡ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት

አዲስ አበባ፡– የዓባይ ግድብ በኢትዮጵያውያን ወዝና ላብ የተገነባ መሆኑን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት አስታወቀ። ከግድቡ ጅማሬ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም ከ23 ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር በላይ ከህብረተሰቡ ተሰብስቦ ለግድቡ ግንባታ መዋሉንም ተጠቁሟል።

የጽህፈት ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍቅርተ ታምር የታላቁ ሕዳሴ ግድብ አስመልክቶ ትናንት ጽህፈት ቤቱ በሰጠው መግለጫ ላይ እንዳሉት፤ ግድቡ በህብረት ጀምረን ማጠናቀቅ እንደምንችል፣ ፕሮጀክት መቅረጽና መምራት፣ ሕዝብን በማስተባበር ለአንድ ዓላማ መቆም እና ጽናትን ለዓለም ያሳየንበት ነው። ግንባታውም ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያውያን ወዝና ላብ የተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

“እኛ ኢትዮጵያውያን የዓባይ ዘመን ትውልዶች 86 ነጥብ 5 የውሃ መጠኑ ከኢትዮጵያ ምንጭ በሆነው ዓባይ ላይ ዐሻራችንን ማስቀመጥ ከጀመርን 14 ዓመታት ተቆጥሯል ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ፤ ግድቡን ከመገንባት ባለፈ የቁጠባ ባህልን በማሳደግ፤ የሀገራችንን ገፅታ በመገንባት እና የአሸናፊነት ሥነ-ልቦና በማላበስ የአንድነታችንና ጽናታችን ማሳያ ነው። የእዚህ ትውልድ አዲስ የወል ትርክት ሆኖ የተመዘገበ የዘመናችን ዓድዋ ነው ብለዋል።

ፕሮጀክቱ በፋይናንስ በኩል በመንግሥትና ሕዝብ መቶ በመቶ በራስ አቅም ያለምንም የውጭ ዕርዳታም ሆነ ብድር የተገነባ መሆኑን ጠቁመው፤ ኢትዮጵያውያን በገንዘብ፣ በጉልበት፣ በዕውቀት፣ በፐብሊክ ዴፕሎማሲና በአካባቢ ጥበቃ በመረባረብ የተመዘገበው ስኬት በትውልድ የሚዘከር ህያው ድል መሆኑንም ጠቁመዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት እስከ ሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም አንድ ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ፣ ከአንድ ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ ተችሏል ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ፤ ግንባታው ከተጀመረበት ጊዜ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ ከ23 ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር በላይ ከህብረተሰቡ ተሰብስቦ ለግድቡ ግንባታ መዋሉንም ገልጸዋል።

የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት አንስቶ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም ከ84 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የጉልበትና የተፋሰስ ሥራ መሠራቱንም ጠቁመዋል።

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያን የልማት ጉዞ ለማደናቀፍና ውሃና አፈሩን በብቸኝነት ለመጠቀም የተለያዩ ሙከራዎች ሲደረጉ ቆይተዋል። አሁን ላይ የሚስተዋሉ ንግግሮችም ከዚህ ማዕዘን መታየት ይኖርባቸዋል። የዓባይ ግድብ ግንባታ በመንግሥት ጥረትና በሕዝብ ሁለተናዊ ንቁ ተሳትፎ የተገነባ ነው ብለዋል።

ማንም የኢትዮጵያ ተቃዋሚ የራሱን ትርክት በፈለገው መንገድ ሊያንሸራሽር ይችላል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ግድቡን እዚህ ደረጃ ያደረሰው ግን የመንግሥት ያላሰለሰ ጥረትና የሕዝብ ጠንካራ ተሳትፎ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ግድቡ የተጠናቀቀ ቢሆንም ሪቫን እስኪቆረጥ ድረስ ኢትዮጵያውያን የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል።

የዓባይ ግድብ በመጪው መስከረም እንደሚመረቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መግለጻቸው ይታወሳል።

በፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You