የጥበብ ፍቅር እንዲህ ያደርጋል፡፡ ይቺ ድምጻዊት በፋርማሲ የትምህርት ክፍል ብትመረቅም መክሊቴ ነው ያለችው ሙዚቃ ሆነ፡፡ ድምጻዊቷ ወደ ሙዚቃው የመጣችው ለእንጀራ ሳይሆን የጥበብ ፍቅር አሸንፏት ነው ማለት ነው፡፡ የመድሃኒት ቀማሚ፣ ምርጥ የፎቶ ባለሙያ፣ ሞዴሊስት፣ ተዋናይ … የእነዚህ ሙያዎች ሁሉ ባለቤት መሆን እየቻለች ሙዚቃን መርጣለች፡፡ የብዙ መክሊት ባለቤት ብትሆንም እርሷ ግን ከሙዚቃው ውጭ ያለው ሁሉ ምርጫዋ ሊሆን አልቻለም፡፡ ለምንና እንዴት? ለሚለው ከድምጻዊቷ ጋር ቆይታ አድርገናል፤ መልካም ንባብ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ብዙ ቀጠሮ ሰርዘሽብኝ ነው የተገናኘነው፤ ይህን ያህል ምን እየሰራሽ ቢሆን ነው?
ሳራ፡- የቀረጻ ሥራዎች ነበሩብኝ፤ በዋናነት ደግሞ አሁን አዲስ የባህል ዘፈን እየሰራሁ ነው፤ በእነዚህ ምክንያቶች ስላልተመቸኝ ነው እንጂ ቃለ መጠይቅ ላለመስጠት ብዬ አይደለም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ስለአዲሱ ዘፈንሽ ገና ብዙ እናወራለን፡፡ በመጀመሪያ እስኪ ራስሽን አስተዋውቂ!
ሳራ፡- ሳራ ቲ እባላለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡- የአባትሽ ስም «ቲ» ነው?
ሳራ፡- ሳራ ታደሰ ነው (ሳቅ) ግን አርቲስት ስትሆን ቶሎ በሰው ጆሮ ውስጥ የሚገባ ነገር ትፈልጋለህ፡፡ ከተለመደው አጠራር ወጣ ያሉ የቅጽል ስሞች የተለመዱ ናቸው፡፡ ብዙ ጊዜ የሚመረጡትም ለመያዝ የሚያመቹና አጭር የሆኑ ስሞች ናቸው፡፡ የእኔን ወንድሜ ነው ያወጣው፡፡ በዚያው እኔም እንደመጠሪያ ቆጠርኩት፡፡ ዘፈኖቼ ላይም ሳራ ቲ ተብሎ ነው የሚጻፈው፡፡
አዲስ ዘመን፡- የት ተወለድሽ? የትስ አደግሽ?
ሳራ፡- የተወለድኩት ሻሸመኔ ነው፤ ያደኩትም ሻሸመኔ ነው፡፡ ትምህርቴን እስከ 10ኛ ክፍል ድረስ ሻሸመኔና ሀዋሳ ነው የተማርኩት፡፡ ከ10ኛ ክፍል በኋላ ያለውን አዲስ አበባ ነው የተማርኩት፡፡ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቴንም ሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ አዲስ አበባ ካምፓስ በፋርማሲ ነው የተመረቅኩት፡፡
አዲስ ዘመን፡- አሁን በተመረቅሽበት ሙያ ምን እየሰራሽበት ነው?
ሳራ፡- በፋርማሲው ምንም እየሰራሁበት አይደለም፡፡ እኔ ከልጅነቴ ጀምሮ ፍላጎቴ ሁሉ ያለው ሙዚቃ ላይ ነው፡፡ ምኞቴም ከልጅነቴ ጀምሮ ዘፋኝ እንደምሆን አውቅ ነበር፡፡ ይህ የሆነው ሙዚቃ በጣም ከመውደዴ የተነሳ ነው፡፡ አሁንም ሙሉ ትኩረቴ ያደረኩት ሙዚቃ ላይ ነው፡፡ የፋርማሲነት ሥራ ደግሞ ወዲያና ወዲህ እያሉ የሚሰራ ሥራ አይደለም፡፡ ከፍተኛ ትኩረት የሚፈልግ ሥራ ነው፡፡ እኔ የሙዚቃው ፍቅር በለጠብኝና ትኩረቴን በዚህ በኩል ማድረግ ፈለኩኝ፡፡ ምናልባት ወደፊት ወደ ፋርማሲስትነት መመለስ ከፈለኩም በቂ ትኩረት ሰጥቼ ነው፤ አሁን ባለኝ ፍላጎት ግን የምቀጥለው በሙዚቃው ብቻ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ፋርማሲ ለመግባት እኮ ከፍተኛ ውጤት ያስፈልጋል፤ ጎበዝ ተማሪ ነበርሽ ማለት ነው?
ሳራ፡- ጥሩ ውጤት ነበረኝ፤ ፋርማሲ የገባሁትም ፈልጌው እና መግባት የሚያስችል ውጤት ኖሮኝ ነው፡፡ በዚህ በኩል ኅብረተሰቡን ማገልገል ምኞቴ ነበር፡፡ ሰዎች ለአንድ መድሃኒት ከፍተኛ ዋጋ ሲከፍሉ ይህ ይቆጭኝ ነበር፡፡መድሃኒት የሕይወት ጉዳይ ነው፡፡ መድሃኒት ማዘጋጀት ማለት የሰውን ልጅ ህይወት ማዳን ነው፡፡ በዚህ በኩል ኅብረተሰብን ማገልገል እፈልግ ነበርና እሱን መማር ፈለኩ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ታዲያ የልጅነት ምኞትሽ የትኛው ነበር እንበል?
ሳራ፡- የልጅነት ምኞቴ ሙዚቃው ነው፡፡ ፋርማሲው ከዚያ ጎን ለጎን አስበው የነበረው ነው፡፡ ትምህርት ላይም ያመጣሁት ውጤት ጥሩ ስለሆነ ነው፡፡ መደበኛውን ትምህርት እየተማሩ መደበኛው ትምህርት ከሚያስገኛቸው መስኮች አለመመኘት አይቻልም፡፡ ሙዚቃው በተፈጥሮ ተሰጥኦና በፍላጎት የሚሄድ ነው፡፡ ይሄኛው ግን በትምህርት የሚገኘው ነው፡፡ ከልጅነት ፍላጎቶችሽ አንዱን ምረጭ ከተባልኩ ሙዚቃው ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- እንዴት ወደ ሙዚቃው ገባሽ?
ሳራ፡- እንደነገርኩህ ከልጅነቴ ጀምሮ ነው የሙዚቃ ፍቅር ያደረብኝ፡፡ ከመዋዕለ ሕጻናት ጀምሮ ትምህርት ቤት እዘፍናለሁ፡፡ ቤት ውስጥ ባገኘሁት አጋጣሚ ሁሉ አንጎራጉር ነበር፡፡ በተለይም ዝናብ ሲሆን፣ ቤት ውስጥ መብራት ሲጠፋ ደግሞ መዝፈን በጣም ነበር የምወደው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ብዙ ዘፋኞች ዘፈን ሲጀምሩ ከቤተሰብ ቁጣ የሚያጋጥማቸው አሉ፤ ይሄ አንቺ ጋ እንዴት ነበር?
ሳራ፡- ይሄ ነገር እኔ ጋ በፍጹም አልነበረም፡፡ ቤተሰቦቼ በደንብ ነበር የተቀበሉኝ፡፡ እንዲያውም ድምጼ እንደሚያምርና ዘፋኝ መሆን እንደምችል እየነገሩኝ ነው ያሳደጉኝ፡፡ ስለዚህ በቤተሰብ በኩል ዘፋኝነቴን የሚያበረታታ እንጂ ምንም የሚነቅፍ ነገር አጋጥሞኝ አያውቅም፡፡ቤተሰቦቼ ስለሚያበረታቱኝም ሙዚቃን የጀመርኩት ተማሪ እያለሁ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ሙዚቃ ለመስራት ስትፈልጊ ምን አደረግሽ? ወዴትስ ሄድሽ?
ሳራ፡- መጀመሪያ ለሙዚቃ አቀናባሪው ለሁንአንተ ሙሉ ደወልኩለት፡፡ ይህን ሳደርግ ከቤተሰቦቼ ጋር አውርቼበትና አስቤበት ሙዚቃ ለመስራት ብዬ ነው፡፡ ሁንአንተ ሙሉ ስደውልለት ‹‹ነይ እና ልስማሽ›› አለኝ፤ ይህን ሲለኝ በቀጥታ ሄድኩና ዘፈንኩለት፡፡ ዘፈኔን ሲሰማ ደስ አለውና በቃ ዘፋኝ ሆንኩ(ሳቅ)
የመጀመሪያ ሙዚቃዬንም ‹‹አላምን አለኝ›› የሚለውን ከኤም ሲ ሲያምረኝ ጋር ነው የሰራሁት፤ ሙዚቃውን ሁንአንተ ሙሉ አቀናበረው፡፡ በሰዓቱ በጣም ጥሩ ተቀባይነት ነበረው፡፡ የመጀመሪያ ሙዚቃዬም የወጣው በ2003 ዓ.ም ሲሆን በ16 ዓመቴ ነው የሰራሁት፤ የወጣውም በሲዲ ነበር፡፡ «ምን ላርግልህ»፣ «አላምን አለኝ»፣ «የሕይወቴ አበባ» እና «ዘረኝነት» የተሰኙ ሙዚቃዎችን ሰርቻለሁ፡፡ ሁሉም ነጠላ ዜማዎች ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ሌላስ ከእነማን ጋር ሰርተሻል?
ሳራ፡- በአጃቢነት(ፊቸሪንግ) ከብዙ ድምፃውያን ጋር ሰርቻለሁ፡፡ ከኤም ሲ ሲያምረኝ፣ ከሳሚ ካሳ፣ ከታደለ ሮባ እና ከልጅ ሚካኤል ጋር የሰራኋቸው ዘፈኖች አሉ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ዘፈኖችሽ ከየትኛው የሙዚቃ ዘውግ ውስጥ የሚመደቡ ናቸው?
ሳራ፡- ማለት?
አዲስ ዘመን፡- የባህል ዘፈን ነው? ዘመናዊ ነው? ራፕ ? ወይስ… ምንድነው ብለን ነው የምንጠራው?
ሳራ፡- አሁን እየመጣሁ ያለሁበት የሙዚቃ መንገድ ‹‹ሲክስ ኤይት›› ላይ ያሉት ናቸው፡፡ ይሄ ማለት ቺክቺካ እንደሚባሉት አይነት ዘፈኖች ማለት ነው፡፡ እነዚህ ሙዚቃዎች የአገራችንን ሙዚቃ በደንብ ነው የሚያስተዋውቁት፡፡እነዚህ ዘፈኖች የአገራችን ዘፈኖች የሚዘፈንባቸው ስልቶች ናቸው፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ህዝቡ ሊገባውና ሊደሰትበት ይችላል ብዬ በማስበው በራሴ መንገድም እሰራለሁ፡፡ አዳዲስ ነገሮችን ይዞ መምጣት በአድማጩና ተመልካቹ ዘንድ ያስደስታል፡፡ አዲስ ነገር አለው ብዬ ያሰብኩበትን እዘፍናለሁ፡፡ ወደ ባህላዊው ጉዳይ እየገባሁ እንዳለ ነው የማምነው እንጂ «ራፕ ዘፋኝ» አይደለም፡፡ በተለይም ከዚህ በኋላ በሚመጡት ሥራዎቼ ባህላዊ ናቸው፤ ለዚህም አሁን እየሰራሁት ያለው ማሳያ ይሆናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- አሁን ወደባህሉ ለመምጣት አስበሻል፤ እስካሁን በሰራሻቸውም ቢሆን ከአገራችን ባህል ውጭ ያሉ ዘፈኖችን መስራት የሚያስኬድ ይመስልሻል?
ሳራ፡- በጣም ነው የሚያስኬደው! ወደ ባህል የመጣሁት ያ መንገድ አላስኬደኝ ብሎኝ አይደለም፤ በጣም እንደተወደዱ፣ ብዙ አድናቂዎች እንደነበሩት አምናለሁ፤ አይቼዋለሁም፡፡ ወደ ባህል ዘፈን መምጣት ያሰብኩት የአማርኛ ዘፈንን በጣም እየለመድኩት ስመጣ የባህል ዘፈን ሊያስደስት እንደሚችል ስለገባኝ ነው። የባህል ዘፈን መዝፈንን ስሜቴ ስላዘዘኝ ነው፡፡ ብዙ የባህል ዘፈኖች ቢኖሩም ገና ብዙ ደግሞ ያልወጣ ባህል አለን፤ ብዙ ያልታየ የአገራችን ቱባ ባህል አለን፤ ያ ገና አልተሰራበትም፡፡ እኔም በሙዚቃው ገና ብዙ ስላልሰራሁ አሁን በሚያስደስተኝ ነገር መሥራት እፈልጋለሁ፡፡ የሚያስደስተኝና ሰራሁ ብዬ የማስብበትን ደግሞ ሳስበው የባህሌን ነገር ይዞ መነሳት ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- «ድምጿ ለባህል ዘፈን ነው የሚሆነው» የሚል አስተያየት ሰምቻለሁ፤ «አንቺ እኮ የባህል ዘፋኝ ነው መሆን ያለብሽ» ተብለሽ አታውቂም?
ሳራ፡- ይሄንን ከአንተ ሰማሁ (ሳቅ) መድረክ ላይም ስጫወት እስካሁን የእንግሊዘኛ ዘፈኖችን ነበር የምጫወተው፡፡ የእስካሁን ሥራዎቼም በልጅነት ድምጽ የተሰሩ ናቸው፡፡ ምናልባት ከዚያ ተነስቶ የልጅነት ድምጽ ስለሆነ በትክክል እዚህ ጋ ነው ማለት ያስቸግር ይሆናል፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ሲሰሙት ‹‹ይሄማ ለባህል ነው የሚሆነው›› ይሉ ይሆናል፡፡ ጥሩ እንደሆነ ግን ብዙ አስተያየት እሰማለሁ፤ የባህል ዘፈን ነው መዝፈን ያለብሽ ግን አልተባልኩም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ወጥ የሆነ የእንግሊዘኛ ሙዚቃ ለማዜም አላሰብሽም?
ሳራ፡- አልገባኝም!
አዲስ ዘመን፡- ወጥ የሆነ የእንግሊዘኛ ሙዚቃ ማለት ከአማርኛ ጋር እየቀላቀልሽ ሳይሆን በእንግሊዘኛ ብቻ ማለት ነዋ!
ሳራ፡- እንደዚያ ያሰብኳቸው ሙዚቃዎች አሉኝ፤ አሁንም በመሥራት ላይ ነኝ፡፡ የእንግሊዘኛ ዘፈኖቼ ግን ከኢትዮጵያ ውጭ አድማጭ እንዲኖራቸው ታስበው የተሰሩ ናቸው፡፡ ስለዚህ በእንግሊዘኛውም ቢሆን ሥራዎች አሉኝ፡፡
አዲስ ዘመን፡- «የሕይወቴ አበባ» የተሰኘው ዘፈንሽ የሰርግ ዘፈን ነው፤ የሰርግ ዘፈን ደግሞ ብዙ ጊዜ በባህላዊ አዘፋፈን ስልት ነው፡፡ አንቺ እንዴት ለሰርግ አሰብሽው?
ሳራ፡- የሕይወቴ አበባን በአዲስ መልክና በተረጋጋ አዘፋፈን ነው የሰራሁት፡፡ በዚያ መልክ መሰራት አለበት ብለን አምነንበት አወጣነው፡፡ በእንዲህ አይነት ረጋ ባለ አዘፋፈንም የሰርግ ዘፈን መሥራት እንደሚቻልም አሳይተንበታል።
አዲስ ዘመን፡- በባህል ዜማ የምትመጪበት አዲሱ ዘፈንሽ ምን ደረጃ ላይ ነው?
ሳራ፡- ከሁለት ወር በኋላ ይወጣል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ዘፈኖችሽ ላይ ያለው ቪዲዮ በአገራችን ከተለመዱት የዘፈን ቪዲዮዎች ወጣ ያለ ነው፡፡ መቸቱም ቶሎ ቶሎ የሚቀያየርና ውድ የሆነ አካባቢዎች የሚታዩበት ነው፡፡ እንዲህ አይነት ቪዲዮ መሥራት አስቸጋሪ አልሆነብሽም?
ሳራ፡- በጣም ውድ ነው፡፡ ጥሩ ነገር ለመሥራት ጊዜም፣ ገንዘብም ኃይልም አጥፍቶ ነው፡፡ ለዚያ ዘፈን የሚያስፈልገው አይነት ቪዲዮ ነው የተሰራው፡፡ በሥራዎቼም ጥሩ ነገር ማሳየት ነው የምፈልገው፡፡ ቪዲዮውን ለመሥራት ከፍተኛ ወጪ ነበረው፤ ግን ከፍተኛ አቀባበል ነው ያገኘሁበት፡፡ ስለዚህ ቪዲዮውን በቂ ጊዜና ገንዘብ አውጥቼ በመሥራቴ ተወዳጅ አድርጎኛል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኤም ሲ ሲያምረኝን ደጋግመሽ ጠቅሰሽዋል፤ ከእርሱ ጋር ምን ዓይነት ሙዚቃ ነው የሰራችሁት?
ሳራ፡- ቀደም ሲል እንዳልኩህ ሙዚቃ ለመሥራት አስቤ ሁንአንተ ሙሉ ጋ ስመጣ ኤም ሲ ሲያምረኝ ደግሞ ፊቸሪንግ የምትገባለት ሴት ዘፋኝ ይፈልግ ነበር፡፡ ሁንአንተ ሙሉ ለምን አብረሽው አትሰሪም የሚለውን ሀሳብ አመጣና ከኤም ሲ ሲያምረኝ ጋር አስተዋወቀን፡፡ እኔ ለመሥራት ፍላጎቱ ስለነበረኝ እዚህ ዘፈን ላይ መግባት አለባት የሚባለው ላይ እየገባሁ መሥራት ጀመርኩ፡፡ ከዚያ በኋላ ነው የፊቸሪንግ ሥራዎችንም መሥራት የጀመርኩት፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከታደለ ሮባ ጋርስ?
ሳራ፡- ከታደለ ሮባ ጋር አብረን ሰርተናል፡፡ «ሰምተሻል» የሚለው ዘፈኑ ላይ አንድ የራፕ ክፍል አለ፤ እሱ ክፍል የኔ ነው፡፡ እሱንም የሰራሁት ሁንአንተ ስቱዲዮ ውስጥ ሆኜ ነው፡፡ ታደለ ሮባ ሰው ይፈልግ ነበር፤ ሰው ሲመረጥ አንዷ ተመራጭ እኔ ሆንኩ ማለት ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ሁንአንተ በጣም ጎበዝ ፕሮዲዩሰር ነው፡፡ ሰዎች እንዲያድጉ የሚፈልግና የሚያበረታታ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከዘፈን ውጭ በምንድን ነው ወደ ህዝብ መድረስ የምትፈልጊው?
ሳራ፡- ማለት?
አዲስ ዘመን፡- አርቲስቶች ብዙ ሥራዎችን ሲሰሩ እናያለን፡፡ ማስታወቂያ ይሰራሉ፣ ፊልም ይሰራሉ፤ ሞዴል ሆነው ይሰራሉ፤ አንቺ ከእነዚህ ውስጥ አለሁበት የምትይው የለም?
ሳራ፡- ህዝቡ ጋ መድረስ የምፈልገው በሙዚቃዬ ነው፡፡ ልቤ ውስጥ ያለው እሱ ነው፡፡ ለፊልም በጣም ብዙ ስክሪፕት ነበር የመጣልኝ፤ ግን ፈቃደኛ አልነበርኩም፡፡ አንዳንድ የማስታወቂያ ሥራዎችን ግን ሰርቻለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡- የፊልም ስክሪፕት መጥቶልሽ ለምንድነው ፈቃደኛ ያልሆንሽው?
ሳራ፡- ሙሉ በሙሉ ፊልም የሚባል ነገር አልሰራም ብዬ አይደለም፤ ለአሁኑ ግን ልቤ ውስጥ ያለው ሙዚቃው ስለሆነ ነው፡፡ ምናልባት ወደፊት ልሰራው እችል ይሆናል፤ አሁን ላይ ግን የሙዚቃ ሥራው ሙሉ ጊዜ የሚፈልግ ስለሆነብኝ ነው፡፡
ጭፈራ ላይ ግን በጣም ጎበዝ ነኝ(ሳቅ)፡፡ ሥራዎቼ ላይም ላይቭ ስጫወት ጭፈራ እችልበታለሁ፡፡ ግን ለብቻው ጨፋሪ መሆን አልፈልግም፡፡ ዘፋኝ ሲኮን ይጨፈራል፤ ያንን ነው የምጠቀምበት እንጂ ስለቻልኩበት ብዬ ጨፋሪ ለመሆን ፍላጎቴም አይደለም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ዘፋኝነትን ሥራዬ ብለሽ ይዘሽዋል፤ በዘፋኝነትሽ ምን አደረግሽ? አሁን ላይስ ምን እየሰራሽ ነው?
ሳራ፡- አሁን ላይ ሸራተን አዲስ ነው እየሰራሁ ያለሁት፡፡ ኦፊስ ባር ውስጥ በሳምንት ሁለት ቀን እሰራለሁ፡፡ እዚያ መሥራት ከጀመርኩኝ ሦስት ዓመት ሆኖኛል፡፡ በቀጥታ (ላይቭ) ነው የምጫወተው፡፡ በየሳምንቱ ሐሙስ እና ቅዳሜ መደበኛ ሥራዬን ነው፡፡ የምንሰራው በባንድ ነው፤ ሌሎች አርቲስቶችም አሉ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከኢትዮጵያ ውጭ የሄድሽባቸው አገራት አሉ?
ሳራ፡- አዎ! በሙዚቃ ሥራ በብዙ የአውሮፓም ሆነ የአፍሪካ ሀገራት ሄጃለሁ፡፡ በሄድኩባቸው አገራትም ጥሩ ልምድ ነበረኝ፤ ጥሩ ሥራዎችን አቅርቤያለሁ፡፡ አሁን ደግሞ ኮንሰርት ለማቅረብ ገና እየተነጋገርኩ ነው፤ እሱ ገና በሂደት ላይ ስለሆነ ስለሙሉ ዝግጅቱ አሁን ላይ እንዲህ ነው ማለት አልችልም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ስለሙዚቃ አንድ ተደጋግሞ የሚነሳ ነገር አለ፤ ዘፋኝ ነሽና ይህን ጥያቄ አንቺንም ይመለከትሻል፡፡ በአንቺ ዕይታ ይሄ ዘመን ለሙዚቃ ምቹ ነው?
ሳራ፡- ዘመኑ ለሙዚቃ አስቸጋሪ ነው ብዬ አላምንም፡፡ የሙዚቃን ተደራሽነት ፈጣንና ቀላል አደረገ እንጂ ምን ችግር አለው? እርግጥ ነው በውስጡ ብዙ ጥሩ ያልሆኑ ነገሮች አሉ፤ ግን ደግሞ እንደዘመኑ ነው መሄድ ያለብን፡፡ ኪነ ጥበብ እኮ እንደኪነጥበብነቱ ከሆነ መታየት ያለበት የሥራው አድማጭ ጋ መድረስ ነው የሚፈለገው። ትኩረት መደረግ ያለበት ሙዚቃው አድማጭ ጋ ደርሶ መሰማቱን ነው፡፡ ከሽያጭና ከገቢ አንጻር ከሆነ የሚታየው ደግሞ ይሄ እንደ ኪነጥበብነቱ ሳይሆን ቢዝነስነቱ ነው የታየው ማለት ነው፡፡
ከእውቅና አንጻርም ከሆነ ያየነው የድሮዎቹ ታዋቂ የሆኑት በሥራቸው ነው፡፡ እነ ጥላሁን ገሠሠን፣ እነ አስቴር አወቀን እናደንቃለን አይደል? እነዚህ ሰዎች እኮ በካሴት ዘመን ስለሆኑ ብቻ ሳይሆን ችሎታ ስላላቸው ነው፡፡ በእነ አስቴርና ጥላሁን ዘመን አብረው ዘፍነው እኮ ማንም ሳያውቃቸው የቀሩ አሉ፡፡ በዚያን ዘመንም ሥራቸው ሳይወጣ ተደብቆ የቀረ ብዙ ናቸው፡፡
በዚህኛው ዘመንም ጎልተው የወጡ አሉ፤ ተደብቀው የቀሩም አሉ፡፡ እንዲያውም በዚህኛው ዘመን እኮ ዘፋኝ ይበዛል፤ ዘፋኝ ሲበዛ ደግሞ ውድድሩ ይጠነክራል፡፡ ውድድሩ በጠነከረ ቁጥር እንግዲህ የአሁኖቹ የቀድሞዎቹን ያህል የማይሆኑ ይመስላል፤ በሌላ በኩል ዘፋኝ ሲበዛም ልብ ያለመባል ነገርም ያጋጥማል፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ ለዘፈኑም እኮ ቫራይቲ (የተለያየነት) መኖር አለበት፡፡ ሁሉም ህዝብ አንድ አይነት ዘፈን አይደለም የሚወደው፡፡
አዲስ ዘመን፡- እንግዲህ የአርቲስት ሕይወት የህዝብ ነውና ስለግል ሕይወትሽም ልጠይቅሽ ነው፡፡ ያገባች ወይስ ያላገባች?
ሳራ፡- አላገባሁም፤ ቦይ ፍሬንድም የለኝም(ሳቅ)፤ ለጊዜው ያለሁት ከሙዚቃው ጋር ብቻ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ምነው ከሙዚቃ ሥራ ጋር አብሮ አይሄድም?
ሳራ፡- እንደዚያ ብዬ አይደለም፤ ፍቅር ከምንም ነገር ጋር አብሮ ይሄዳል፡፡ ከታሰበበት ፍቅር የማይሰራበት ቦታ የለውም፡፡ ግን ደግሞ እንደዚህ አይነት ጉዳይ ፈልጎ በማምጣት የሚሆን ነገር አይደለም፡፡ ይሄ ከእግዚአብሔር የሚሰጥ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ፡፡
ሳራ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
ዋለልኝ አየለ