
የአዲስ አበባ ከተማን መስፋፋትና እድገት ተከትሎ የትራንስፖርት አገልግሎት ፍላጎቱም በየጊዜው ሲጨምር፣ ይህን ፍላጎት ለመመለስም እንዲሁ የተለያዩ ጥረቶች ሲደረጉ ኖረዋል:: ከተማ አስተዳደሩ በተለይ በብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት በኩል ዘመኑን የዋጁ አውቶብሶችን ከውጭ በማስመጣት፣ በሀገር ውስጥ እንዲገጣጠሙ በማድረግ አገልግሎቱን እንዲቀላቀሉ ሲያደርግ ቆይቷል::
የከተማዋን ቀላል የባቡር መሰረተ ልማት በመዘርጋትም የትራንስፖርት አገልግሎቱ የተሳለጠ እንዲሆን ለማድረግ የከተማዋ አስተዳደር ጥረት አድርጓል:: የግሉ ዘርፍ በከተማ አውቶብስ አገልግሎት እንዲሰማራ ምቹ ሁኔታ ፈጥሮም እንደነበር ይታወቃል:: የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋት መስራቱን ቀጥሏል::
ዘመኑን የዋጁ የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎቶችን ወደ ከተማዋ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የማምጣቱ ስራ ቀጥሎም በኤሌክትሪክ የሚሰሩ የከተማ አውቶብሶች ወደ አገልግሎቱ እንዲገቡ ተደርጓል::
እንደሚታወቀው፤ መንግስት በኤሌክትሪከ ለሚሰሩ ተሽከርካሪዎች የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ ተከትሎ በከተማ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ የቤት መኪናዎችና ሚኒባሶችን በጎዳናዎች ላይ በብዛት መመልከት ከተጀመረ ቆይቷል፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ለሰርቪስ አገልግሎት የሚሰጡ ሚዲባሶች በከተማዋ ጎዳናዎች በብዛት ይታያሉ:: በኤሌክትሪክ የሚሰሩ የከተማ አውቶብሶችም እነዚህን ተሽከርካሪዎች ነው የተቀላቀሉት::
በኤሌክትሪክ የሚሠሩ የከተማ አውቶብሶች የከተማዋን የህዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት አገልግሎት በይፋ የተቀላቀሉት የከተማዋ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በተገኙበት በቅርቡ በመስቀል አደባባይ በተካሄደ ሥነ-ሥርዓት ነው:: ወደ አገልግሎቱ የገቡት 100 በኤሌክትሪክ የሚሠሩ የከተማ አውቶቡሶች ሲሆኑ፣ በከተማዋ የትኛውም ክፍል አገልግሎት እየሰጡም ይገኛሉ::
የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ያብባል አዲስ አውቶቡሶቹ በይፋ ሥራ እንዲጀምሩ በተደረገበት ወቅት እንደተናገሩት፤ የአውቶብሶቹ ወደ ሥራ መግባት መንግሥት በትራንስፖርት ዘርፍ ከግሉ ዘርፍ ጋር ለመሥራት ያሳለፈው ውሳኔ አንድ ማሳያ ነው።
የከተማ አስተዳደሩ ከለውጥ ማግስት እና በኮሪደሩ ልማት ከፍተኛ ትኩረት ከሰጣቸው ጉዳዮች አንዱ የትራንስፖርት ዘርፍ መሆኑን ጠቅሰው፣ የከተማ አስተዳደሩ የከተማዋ ትራስፖርት የብዙኃን ፍላጎት አቅርቦት እና ፍላጎት አለመመጣጠን፣ የከተማዋ ትራፊክ መጨናነቅ የዘርፉ ዋና ዋና ችግሮች መሆኑን በመረዳት ሲሠራ መቆየቱን ገልጸዋል። ባለፉት የለውጥ ዓመታት ችግሮቹን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ለዘርፉ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ማውጣቱንም አመልክተዋል።
እንደ እሳቸው ማብራሪያ፤ የከተማ አውቶቡስ ትራንስፖርት ዘርፉን ለማሳደግ ከለውጡ በኋላ የሸጎሌ እና የቃሊቲ አውቶቡስ ዲፖዎች የመርካቶ አውቶብስ ተርሚናል በአዲስ መልክ ተሰርተዋል። ዘመናዊው የአድዋ ድል መታሰቢያ የአውቶቡስ ተርሚናልም ተገንብቷል:: በመጪዎቹ ዓመታት የኤሌክትሪክ አውቶቡሶችን ቁጥር ለመጨመር እቅድ ታቅዷል::
የከተማ አስተዳደሩ ከለውጡ በፊት 610 አውቶብሶች ብቻ እንደነበሩት አስታውሰው፣ በየዓመቱ በተሰራው ሥራም 827 አውቶቡሶችን መጨመር መቻሉን ገልጸዋል:: አሁን በቀን ከአንድ ሺ 170 በላይ አውቶቡሶችን በማሰማራት የብዙኃን ትራንስፖርት አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን አስታውቀው፤ በዚህም በቀን አንድ ነጥብ አንድ ሚሊየን ህዝብ ማጓጓዝ መቻሉን አመላክተዋል።
ኃላፊው እንዳስታወቁት፤ በለውጥ ዓመታቱ የመንገድ፣ የተርሚናል፣ የመኪና ማቆሚያ፣ የታክሲ እና የአውቶቡስ መጫኛና ማውረጃዎች፣ የእግረኛና የብስክሌት መንገድ መሰረተ ልማቶች በስፋት ተገንብተዋል:: በኮሪደር ልማት ከአምስት ሺህ በላይ መኪናዎችን ማቆም የሚችሉ ትልልቅ የፓርኪንግ ቦታዎች ተሰርተዋል።
ከመንገድ፣ ከዴፖ፣ ከተርሚናል እና ከመኪና ማቆሚያ መሰረተ ልማቶች በተጨማሪ የትራፊክ መብራቶችን በማስፋፋት፣ አደባባዮችን በመሸጋገሪያዎች በመቀየር፣ ማቋረጫ መንገዶችን በመሬት ውስጥ መተላለፊያዎች በመቀየር፣ የመንገድ ምልክት ስራዎችን ማሳደግ ተችሏል። የትራፊክ ቁጥጥር ሥራውንም በማሳደግ የከተማዋን የትራፊክ መጨናነቅ ለመቀነስ ጥረት ተደርጓል።
የከተማ አስተዳደሩም የትራንስፖርት አገልግሎትን ለማሻሻል እና የትራፊክ መጨናነቅን ለመቀነስ ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን መሥራቱን ጠቅሰው፣ አሁንም የከተማዋ እና የመሰረተ ልማት እድገቱ የትራንስፖርት አቅርቦቱ የተመጣጠነ አይደለም ሲሉም ተናግረዋል። በመሆኑም የትራንስፖርት አገልግሎት እና የትራፊክ እንቅስቃሴው ዛሬም የተፈለገውን መሻሻል አላመጣም ብለዋል።
ኃላፊው እንዳብራሩት፤ የከተማ አስተዳደሩ የብዙኃን ትራንስፖርት አገልግሎትን በመንግሥት ብቻ ማሟላት እንደማይቻል አምኖ በመንግሥት እና በግል አጋርነት የትራንስፖርት አገልግሎቱን ችግሮች ለመፍታት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል:: በዚህም የግል ባለሀብቱ ተሳትፎ እንዲጠናከር ለማደረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመልክተው፣ የከተማ አስተዳደሩ ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመመካከር የግል ባለሀብቱ በከተማዋ የብዙኃን ትራንስፖርት አገልግሎት ዘርፍ በስፋት እንዲሰማራ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አስታውቀዋል።
ለእዚህም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመጀመሪያ እርምጃ መውሰዱን ጠቅሰው፣ የከተማዋን የብዙሃን ትራንስፖርት በየዓመቱ የማስፋፋት እቅድ አካል የሆነው የ100 የኤሌክትሪክ አውቶቡሶች ግዢ በመንግሥት በጀት መፈፀሙን አመላክተዋል።
የ100 የኤሌክትሪክ አውቶቡሶች አቅርቦት የትራንስፖርት አገልግሎቱን ከማሻሻል በዘለለ ለከተማዋ ጭስ አልባ የብዙኃን ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ መሆናቸው ልዩ ያደርጋቸዋል።
የከተማ አስተዳደሩም እነዚህ አውቶቡሶች በበብቃት ለማስተዳደር እና በቴክኖሎጂ የተደገፈ፣ የተሻለ እና የዘመነ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት እንዲቻል የማስተዳደር ኃላፊነቱ በመንግሥት እና በግል አጋርነት እንዲሆን ወስኖ ወደ ተግባር ገብቷል። በዚህም መንግሥት አውቶቡሶቹን ያቀረበ ሲሆን፣ አውቶቡሶቹን በብቃት ለማስተዳደርና የብዙኃን ትራንስፖርት አገልግሎትን ለመስጠት የሚያስፈልገውን የዴፖ ልማት፣ የቴክኖሎጂ አቅርቦት፣ የወርክሾፕ አቅርቦትና የሰው ኃይል አቅርቦት በግል ባለሀብቱ እንደሚሸፈን አስታውቀዋል።
የበላይነህ ክንዴ ግሩፕ የመንግሥት እና የግል አጋርነት የትራንስፖርት ኦፕሬተር እንዲፈጠር ፈር ቀዳጅ ባለሀብት ሆኖ መገኘቱን ጠቁመዋል። የመኪና መገጣጠሚያ በመክፈት እና በአዲስ አበባ ከተማ የቬሎሲቲ የትራንስፖርት ኦፕሬተር በመፍጠር የአውቶቡስ እና የታክሲ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት አስቀድሞ በዘርፉ የተሰማራ ባለሀብት መሆኑን አስታውቀዋል።
አሁን ደግሞ በመንግሥት እና በግል አጋርነት ለመስራት 100 የኤሌክትሪክ አውቶብሶችን ይዞ ለመስራት ብቻ ሳይሆን በተወሰኑ ዓመታት የኤሌክትሪክ አውቶቡሶችን ቁጥር በከፍተኛ መጠን የመጨመር ራዕይ ይዞ የመጣ ድርጅት መሆኑን ጠቅሰዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፤ በመዲናዋ ጠዋትና ማታ የሚታየውን ከፍተኛ ሰልፍ እና እንግልት መመልከት ሲያሳቅቀን ቆይቷል ሲሉ ጠቅሰው፣ መንግሥት በአካባቢ ላይ የአየር ንብረት ሊያስከትሉ የሚችሉ ችግሮችን ለመከላከል እያከናወነ ካለው ተግባርና ከውጭ የሚገባው ነዳጅ አገሪቷን ለከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወጪ እየዳረገ ያለበትን ሁኔታ ለመቀነስ በሚያደርገው ጥረት የከተማ አስተዳደሩ ይህን ፈር ቀዳጅ እርምጃ መውሰዱን አስታውቀዋል::
ከስድስት ወራት በፊት 150 የኤሌክትሪክ ሚኒባሶች ተገዝተው የአየር ንብረት ብክለት መቀነስንና ነዳጅ ቁጠባን በሚያግዝ መልኩ የመዲናዋን የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲቀላቀሉ መደረጉን አስታውሰዋል። በእነዚህ ሥራዎች ዋነኛና መሰረታዊ ትኩረት ተደርጎ የተወሰደው በከተማዋ በነዋሪዎች ላይ የሚታየውን የትራንስፖርት እንግልት መቀነስ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
እሳቸው እንዳስታወቁት፤ ከለውጡ ወዲህ የአውቶቡስ ቁጥር ማሳደጉ ብቻውን በቂ አለመሆኑ ታምኖበት ስምሪቱንና አገልግሎት አሰጣጡንም ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። ይሄንንም ለማሻሻል የሚያስችሉ የቴክኖሎጂና የሥነ-ምግባር ሥልጠናዎችን ተሰጥተዋል፤ መሰረተ ልማቱንም በመዘርጋት በኩል ጉልህ እርምጃዎች ተወስደዋል።
በተለይም ከኮሪደር ልማት ጋር ተያይዞ ብልህ የትራንስፖርት ሥርዓት በመዘርጋት ቴክኖሎጂን መጠቀም የሚያስችሉ ስልጠናዎችን በመስጠት የትራንስፖርት ስምሪቱን ቀልጣፋና ፈጣን የማድረግ ተግባሮች መከናወናቸውን ተናግረዋል።
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሩ አቶ አለሙ ስሜ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ በኤሌክትሪክ የሚሰሩት አውቶብሶች ወደ ሥራ የገቡበት ሁኔታ መዲናዋ አሁን ያላትን ዕድገት በትራንስፖርት ዘርፉም እውን ለማድረግ በአቅርቦት ብቻ ሳይሆን ከአካባቢ ጋር የሚስማማ ቴክኖሎጂ እንዲሁም ዘርፉ እንዲሰፋ ማድረግ የሚያስችለው የግል ባለሀብቱ ተሳትፎ እውን የሆነበት ነው። ኢትዮጵያ በፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ ትገኛለች። ይሄንን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ለማረጋገጥ የትራንስፖርት ዘርፉ ሚናውን መወጣት ይኖርበታል።
የመዲናዋ መንገዶች እንዲሰፉ እየተደረገ ይገኛል፤ አዳዲስ አማራጭ መንገዶች እየተከፈቱ ናቸው፤ የእግረኛና ተሽከርካሪ መንገድ በሚገባ እየተለየ ነው። ይህ ሁሉ የመንገድ መሰረተ ልማት ቅልጥፍናን ያሳድጋል።
ዜጎች በትራንስፖርት እጥረት እንዳይቸገሩ በርካታ የትራንስፖርት አማራጮች እየቀረቡ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ አዲስ አበባ ውስጥ ህዝብ ያሳፈረ እንዲሁም እቃ የጫነ ተሽከርካሪ የሚቆሙበት ኬላ ሳይኖራቸው መቆየቱን ጠቅሰው፣ ይህን ችግር ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል:: ይህን ሁሉ በማድረግ የከተማዋ እንቅስቃሴ እንዳይቋረጥ የአርአያነት ሚና እየተጫወተች መሆኑንም አስገዝበዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) ግንባር ቀደም መሪነት ኢትዮጵያን ማበልፀግ ብቻ ሳይሆን አየሯንም ማበልፀግ ላይ በትኩረት እየሰራች መሆኑን ሚኒስትሩ ጠቁመው፣ ባለፉት ዓመታት ለእዚህ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ 40 ቢሊየን ችግኞች መተከላቸውን ጠቅሰዋል።
ከተሽከርካሪዎቹ የሚወጣውን በካይ ጋዝ እንዲቀንሱ፤ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ተሽከርካሪዎች በተቻለ አቅም የአካባቢ የአየር ንብረትን የማይጎዱና ታዳሽ ኃይል (የኤሌክትሪክ ኃይል) የሚጠቀሙ እንዲሆኑ አቅጣጫ መቀመጡንም ገልጸዋል።
በዚህም በኢትዮጵያ ታዳሽ ኃይልን የሚጠቀሙ የኤሌክትሪክ መኪናዎች በስፋት የማስገባት ሥራ እየተሰራ ነው መሆኑን ጠቅሰው፣ 100ዎቹ የኤሌክትሪክ አውቶቡሶችም የዚህ ፖሊሲ መፈፀሚያ መሆናቸውን አመላክተዋል። አውቶብሶቹ የብዝኃን ትራንስፖርት እጥረት እና የነዋሪዎችን እንግልት የሚቀንሱ ዘመናዊና ተደራሽ መሆናቸውን ተናግረዋል::
በመንገድ ላይ የሚጠፋው ጊዜ ማጠር አለበት። መንግሥት ለነዳጅ የሚያወጣውን ወጪ ለመቀነስ እየሰራ ነው። ከውጭ የሚመጡ መኪኖች በታዳሽ ኃይሎች የታጠቁ መሆን አለባቸው ሲሉም አስታውቀዋል:: አቶ በላይነህ ክንዴ በኢንዱስትሪው ያመጡትን የፈር ቀዳጅነት ሚና ሌሎች ባለሀብቶች በታዳሽ የትራንስፖርት ዘርፉ በመሰማራት እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል። ለእዚህም መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
አቶ ተሻለ አንማው በከተማ አውቶቡስ አሽከርካሪነት ለ11 ዓመታት አገልግለዋል፤ በቅርቡም የፐብሊክ አውቶቡስ ሹፌር ሆነው ሰርተዋል። ከድርጅቱ በጡረታ ከተገለሉ በኋላ ደግሞ አዲሱን የኤሌክትሪክ አውቶቡስ /ቬሎሲቲ/ ድርጅት ተቀላቅለዋል::
በቬሎሲቲ የኤሌክትሪክ አውቶቡስ አገልግሎት ላይ በተሰጣቸው ስልጠና እና መመሪያ መሰረት አገልግሎቱን በተገቢው ጥንቃቄ እንደሚያከናውኑም ይናገራሉ:: በአውቶቡስ አገልግሎት ድሮና ዘንድሮ ሰፊ ልዩነት መኖሩን ጠቁመው፤ አሁን በኤሌክትሪክ በሚሰሩ አውቶቡሶች አገልግሎት በምንሰጥበት ጊዜ ልብሳችን በግሪስ ወይም በዘይት አይቆሽሽም ይላሉ። በሹፌርነት ከሰሩባቸው 36 ዓመታት የአሁኑ የተሻለ የአገልግሎት ዘመናቸው እንደሚሆን ተስፋ እንዳላቸውም ገልጸዋል።
አሽከርካሪውም በነዳጅ የሚሰራው አውቶብስ የነዳጅ መጠን እንደሚጠበቅ ሁሉ ለዚህኛውም የኤሌክትሪክ ሲስተሙን መጠበቅ ከቻለ ምንም ዓይነት ችግር እንደማይገጥመውም ነው የተናገሩት።
በከተማ ትራንስፖርት አውቶቡስ ላይ ለ26 ዓመታት ያገለገሉት አቶ ደረጀ እጅጉ በበኩላቸው፣ ቬሎሲቲ የኤሌክትሪክ አውቶቡስ በስራ ላይ ካሉትም ከቀደሙትም አውቶቡሶች አኳያ ሲታይ ሥራ እንደሚያቀል ይናገራሉ። በነዳጅ የሚሰሩ አውቶቡሶች በቀን ከ100 ሊትር ያላነሰ ነዳጅ እንደሚወስዱ ጠቅሰው፣ ይህም በኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጫና እንደሚያሳድር ገልጸዋል::
በአዲሶቹ ዘመናዊ የኤሌክትሪክ አውቶቡሶች የድምጽ ብክለት እንደማይኖር ተናግረው፣ ነዳጅ የማይጠቀሙና ታዳሽ ኃይል ምንጭ የሚጠቀሙ መሆናቸው የአየር ብክለት እንደማያስከትሉም እሳቸውም ይናገራሉ። ለህዝቡ ጤንነት የላቀ እገዛ እንደሚያደርጉም አመልክተዋል:: ድምፅም የሌላቸው በመሆናቸው፣ ተገልጋዩ በአውቶቡሱ ውስጥ ለመደማመጥ እንደማይቸገርም አመልክተዋል። አቶ ደረጀ ተገልጋዩ አውቶብሶቹን ሲገለገል እንደ ራሱ ንብረት በመመልከት በአግባቡ ሊጠቀምባቸው እንደሚገባም አሳስበዋል።
ሌላዋ የአውቶብሱ አሽከርካሪ ወይዘሮ ሐረገወይን ብስራት አውቶቡሶቹ የአየር ብክለትን በመቀነስ የጎላ ሚና እንዳላቸው፣ በነዳጅ ሳቢያ በሀገሪቱ ላይ የሚደርሰውን የወጪ ጫና እንደሚያቃልልና የትራንስፖርት መሰረተ ልማቱንም እንደሚያሳድግ ጠቁመዋል::
በኃይሉ አበራ\
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 4 ቀን 2017 ዓ.ም