
ፀረ-ተህዋስያን መድኃኒቶች የሚባሉት በበሽታ አምጪ ተህዋስያን አማካኝነት በሰውና በእንስሳት ላይ የሚደርስ ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከልና ለማከም የምንጠቀማቸው መድኃኒቶች ናቸው::
እነዚህ መድኃኒቶች በዓይነት፣ በይዘታቸውና በአጠቃቀማቸው የተለያዩ ሲሆኑ፤ መድኃኒቶቹ የተፈለሰፉት ከዛሬ 80 ዓመት በፊት እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ:: ዘመኑ ደግሞ አዳዲስ መድኃኒቶች የሚመረቱበት በመሆኑ እነዚህ፤ እነዚህ ናቸው ብሎ በዝርዝር ለማስቀመጥ አስቸጋሪ ይሆናል:: እናም ከዚያ ይልቅ ለእኒዚህ መድኃኒቶች መፈጠር ምክንያት የሆነው ምንድነው የሚለውን ብናነሳ ይበጃል::
ከላይ እንደተጠቆመው እነዚህ መድኃኒቶች የተለያየ አገልግሎት እንዳላቸው ታሳቢ ተደርጎ የተፈበረኩ ናቸው:: በተለይም የሰው ልጆች ጤና ላይ እየደረሰ ያለው በተህዋስያን የሚመጣው በሽታ አደገኛ በመሆኑ የግድ ፀረ ተህዋስያን መድኃኒቶችን ማምረት አስፈልጓል:: በዚህም የሰዎችን ጤና በከፍተኛ ሁኔታ በመጠበቅ እፎይታን መስጠት ተችሏል::
እነዚህ መድኃኒቶች ዓለም ከደረሰባቸው ትልልቅ የሳይንስ ውጤቶች ውስጥ እጅግ ጠቃሚ በመሆን ውስጥ ተካተው የሚገኙ ሲሆኑ፤ የሰው ልጆችና እንስሳት ከሚደርስባቸው ስቃይና ሞት ታድገዋል በሚል ተለይተዋል:: በኢትዮጵያም ቢሆን አብዛኞቹ በሽታዎች ተላላፊ በመሆናቸው ለማከምና ለመከላከል የፀረ-ተህዋስያን መድኃኒቶች ቁልፍ ሚናን ይጫወታሉና ወሳኝነታቸው ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም::
የፀረ-ተህዋስያን መድኃኒቶች በከፍተኛ ደረጃ ተላላፊ በሽታዎችን መከላከልና ማከም በመቻላቸው ምክንያት በስፋት ጥቅም ላይ ይውላሉ:: በዚህ የተነሳ ደግሞ የመለመዳቸው ሁኔታ ሰፊ ነው:: በተጨማሪም አግባብ ባልሆነ ሁኔታ ጥቅም ላይ የመዋላቸውም ሁኔታ ከፍተኛ ነው:: ይህ ደግሞ መድኃኒቶቹን በበሽታ አምጪ ተህዋስያን በቀላሉ እንዲለመዱ ያደርጋቸዋል:: ከዚህ አንጻር ነው የፀረ ተህዋስያን መድኃኒቶች በጀርሞች መለመድ የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ የመጣው።
ይሄ ጉዳይ እንደ ሀገር ከፍተኛ ችግር እያስከተለ በመሆኑ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ አራተኛ መንግሥት እየተባለ ለሚጠራው መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አዘጋጅቷል:: ስለ ሁኔታው አውቀው ለማኅበረሰቡ እንዲያስገነዝቡም ማሳሰቢያ ጭምር አስተላልፏል::
በወቅቱ እንደተባለውም፤ የፀረ-ተህዋሲያን መድኃኒቶች በጀርሞች መለመድ Antimicrobial resistance (AMR) በሰው፣ በእንስሳትና በአካባቢ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ ያለ ዓለም አቀፍ ችግር ነው:: በሀገራችንም ከፍተኛ ችግር እየፈጠረ የሚገኝ አደጋ ነው:: ስለሆነም ማኅበረሰቡ ስለ ምንነቱ፤ መከላከያ መንገዱ በሚገባ ማወቅና መጠንቀቅ ይኖርበታል:: ለዚህ ደግሞ ከቢሮው ባሻገር መገናኛ ብዙኃኑ ትልቁን ኃላፊነት ወስደው ሊሠሩ ይገባል:: እናም የተሰጠንን ኃላፊነት ከመወጣት አንጻር ባለሙያዎቹ ያሉንን እንደሚከተለው አቅርበነዋል::
በአዲስ አበባ ዩነቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ፋርማኮሎጂ ረዳት ፕሮፌሰር ሰለሞን አሰፋ ሥልጠናውን ከሰጡት መካከል አንዱ ሲሆኑ፤ ስለ ፀረ ተህዋስያን መድኃኒቶች በጀርሞች መለመድ ምንነት፤ ችግሩ እንዴት እንደሚከሰትና መከላከያ መንገዳቸውን አንስተዋል::
እርሳቸው እንዳሉትም፤ የፀረ-ተህዋስያን መድኃኒቶች በጀርሞች መለመድ ማለት በተህዋስያን አማካኝነት ለሚመጡ ሕመሞች የሚወሰዱ መድኃኒቶች ተህዋስያንን መግደል፣ መቆጣጠር ወይም መራባታቸው መግታት ማለት ነው:: ስለዚህም መድኃኒቶቹ በደም ውስጥ ቢኖሩም ተህዋስያኑ መራባት ይችላሉና የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት አይችሉም። ከዚህ አንጻርም በፀረ-ተህዋስያን መድኃኒቶች በጀርሞች መለመድ ዓለማችን ከሚያሰጓት ትልልቅ ችግሮች መካከል የሚጠቀስ ሆኖ እናገኘዋለንም::
እ.ኤ.አ. በ2017 ወደ 271 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች የተለመዱና አላግባብ የሚውሉ መድኃኒቶችን እንዲጠቀሙ የተደረጉ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ 35ነጥብ6 ሚሊዮን የሚሆኑት ከመድኃኒት ጋር የተዛመዱ ችግሮች ያጋጠማቸው መሆናቸውን የሚያነሱት ረዳት ፕሮፌሰሩ፤ ከዚህ አንጻር ደግሞ የትራማዶል ዝውውር እና ከሕክምና ውጭ መጠቀም ጋር ተያይዞም በብዙ የአፍሪካ ሀገራት ቀዳሚዎቹ የስጋት ምንጭ እንደሆኑ ያመላክታሉ::
በሰው በእንስሳትና በአካባቢ ጤና እንዲሁም በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ችግር እያስከተለ ያለው ይህ የመድኃኒት መላመድ በሁሉም የዓለም ሀገራት ውስጥ ይከሰታል:: ሆኖም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ ሀገራት ውስጥ የችግሩ አሳሳቢነት ጎልቶ የሚታይ ነው:: ስለዚህም የችግሩን አሳሳቢነት በጥቂቱ ለመጠቆም ያህል የቲቢ፣ ኤች.አይ.ቪ እና የወባ መድኃኒቶች እንደዚሁም በስፋት በምንጠቀምባቸው በሌሎች የፀረ-ተህዋስያን መድኃኒቶች ላይ እየተከሰተ ያለው የመድኃኒቶች በጀርሞች መለመድ ችግር ለመፍታት በመንግሥት በኩል ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ እንደሚገኝም ይናገራሉ::
በአንዳንድ የጥናት ውጤቶች እንደሚታዩት በዚህ ችግር ምክንያት በዓለም ላይ ከ700ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎች በየዓመቱ ይሞታሉ:: ችግሩን ለመቀነስ ርምጃ ካልተወሰደ እ.ኤ.አ በ2050 ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በአጠቃላይ የዓለም ኢኮኖሚ ላይ ከ2 እስከ 3 በመቶ ማለትም ወደ10 ትሪሊየን ዶላር ኪሳራ ያስከትላሉ:: በታዳጊ ሀገሮች ሲሆን ደግሞ ከአምስት በመቶ በላይ የኢኮኖሚ ኪሳራ ውስጥ የሚከት እንደመሆን ይታመናል:: ስለዚህም ይህንን ዓለም አቀፍ ችግር ለመግታትና ለመቆጣጠር የዓለም ጤና ድርጅት፤ የዓለም የምግብና ግብርና ድርጅት እና የዓለም የእንስሳት ጤና ድርጅት በመተባበር ዓለም አቀፍ የፀረ ተህዋሲያን መድኃኒት መለመድ የመከላከልና የመቆጣጠር ስትራቴጂና ዕቅድ አውጥተው አባል ሀገሮች ተግባራዊ እንዲያደርጉ ጥረት በማድረግ ላይ ስለመሆናቸውም ይናገራሉ::
«ኢትዮጵያም የፀረ ተህዋስያን መድኃኒቶች መለመድ በሰው፤ በእንስሳትና አካባቢ ጤና እንዲሁም በኢኮኖሚ ላይ እያደረሰ ያለውን ችግር በመገንዘብ ስትራቴጂክ እቅድ በማውጣትና ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በመሥራት ላይ ትገኛለች» ያሉት ደግሞ በጤና ሚኒስቴር የፀረ ተህዋስያን መድኃኒቶች መለመድ መከላከልና መቆጣጠር ተጠሪ ባለሙያ አቶ ወንድወሰን ሸዋረጋ ናቸው::
እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ በኢትዮጵያ በፀረ ተህዋስያን መድኃኒቶች መለመድ በሰው፤ በእንስሳትና አካባቢ ጤና እንዲሁም በኢኮኖሚ ላይ እያደረሰ ያለውን ችግር በመገንዘብ ሀገራዊ አማካሪ ኮሚቴ በማዋቀር ላለፉት ዓመታት የፀረ ተህዋስያን መድኃኒቶች መላመድን የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል:: በዚህም ለውጦች ታይተዋል:: ይሁን እንጂ አሁንም በርካታ ጉዳዮች ጥንቃቄ ያሻቸዋል::
ግንዛቤ መፍጠሩ ደግሞ ለጥንቃቄው ወሳኝ ሚናን እንደሚጫወት የጠቆሙት ባለሙያው፤ የፀረ-ተህዋስያን መድኃኒቶች በጀርሞች መለመድ በተለያዩ ምክንያቶች ሊከሰት እንደሚችል ይናገራሉ:: አንዱ መከሰቻ አጋጣሚው ደግሞ የፀረ-ተህዋስያን መድኃኒቶችን ያለ ጤና ባለሙያ መውሰድ እንደሆነ ያነሳሉ:: ከዚያ ሻገር ስንል ደግሞ የታዘዘን የፀረ-ተህዋስያን መድኃኒቶች ማቋረጥ፤ የታዘዘን መድኃኒት መጠን በመቀነስና በመጨመር መጠቀምም እንደ ምክንያት እንደሚጠቀስም ያብራራሉ::
የፀረ-ተህዋስያን መድኃኒቶችን ከሌላ ሰው ተውሶ በመውሰድ፤ የታዘዘን መድኃኒት የመውሰጃ ሰዓት ማዛባትም ችግሩን ከመፈጥሩ መካከል መሆናቸውን ይገልጻሉ:: አክለውም በሀገራችን በአብዛኛው እንስሳት ሲታመሙ የፀረ-ተህዋስያን መድኃኒቶችን የሕክምና ባለሙያዎችን ሳናማክር እንሰጣቸዋለን:: ይህ ደግሞ እንስሳቱን ብቻ ሳይሆን የሰውን ጤና ጭምር ሊጎዳ የሚችል ችግር ይፈጠራልም ይላሉ::
ከዚህ በፊት ተወስዶ ስላዳነ ብቻ ተመሳሳይ መድኃኒቶችን ገዝቶ መጠቀምም የችግሩ ሰለባ እንደሚያደርግ፤ አሁን ላይ በስፋት እየተለመደ የመጣው መድኃኒት ለማያስፈልጋቸው ወይም ሰውነታችን በተፈጥሮ ባለው ኃይል ሊቋቋማቸው ለሚችሉ ሕመሞች መድኃኒት መውሰድ፤ የግልና የአካባቢ ንጽህናን አለመጠበቅ፤ ትክክለኛ መድኃኒት ለትክክለኛው ሕመም አለመውሰድ፤ ትክክለኛ የመፈወስ አቅም የሌላቸውን መድኃኒቶች ሕጋዊ ካልሆኑ መድኃኒት ቤቶች ወይም ግለሰቦች ገዝቶ መጠቀም የሚሉትም በዋና ዋና ምክንያትነት የሚጠቀሱ ስለመሆናቸውም ይናገራሉ::
አቶ ወንድወሰን የጤና ባለሙያዎች የፀረ-ተህዋስያን መድኃኒቶችን አላግባብ እንዲያዙ መገፋፋት፤ የፀረ ተህዋስያን ቅሪት ያለበትን የእንስሳት ተዋፅኦ መመገብና ጥቅም ላይ ማዋል፤ የፀረ-ተህዋስያን መድኃኒቶች ያለ አግባብ በቆሻሻ መልክ መጣል የሚሉትም ለችግሩ ሰለባ ከሚያደርጉትን ምክንያቶች ውስጥ እንደሆኑም ያስገነዝባሉ::
የፀረ-ተህዋስያን መድኃኒቶች በጀርሞች መላመድ የሚያስከትለው ችግሮችም ሰፋ ያሉ ማብራሪያዎችን የሰጡት አቶ ወንድወሰን፤ አንዱ በሽታ አምጪ ተህዋስያን በቀላሉ በመድኃኒት መወገድ ባለመቻላቸው ምክንያት ሕሙማንን ለተጨማሪ ሕመምና ወጪ እንዲሁም እንግልት መዳረጋቸው ነው:: ይህ ሲሆን ደግሞ በቁጥር ውስን የሆኑት እነዚህ የፀረ ተህዋስያን መድኃኒቶች ከአገልግሎት ውጭ እንዲሆኑ ያስገድዳቸዋል:: ማለትም ፈዋሽነት ላላቸው ሕመሞች መወሰድ ባለመቻላቸው የተነሳ በጀርሞች ይለመዱና ጥቅማቸው ዋጋ ያጣል:: በዚህም በርከት ያሉ መድኃኒቶች አግባብ ላለው ሕመም ፈውስነት እንዳይውሉ ገደብ ይጥልባቸዋል:: ይህ ሁኔታም ከፍተኛ ወጪ የሚያሶጣ ጥቂት መድኃኒቶች ብቻ እንዲኖሩ ያደርጋቸዋል::
ሌላው የመድኃኒቶች ፈዋሽነት ማነስ የጎንዮሽ ጉዳታቸው ከፍ ያለ መድኃኒቶችን ለመውሰድ እንድንገደድ ጭምር ያደርገናል:: በተመላላሽ ሕክምና መታከም የሚችሉ ሕሙማንንም ሆስፒታል ተኝቶ እስከ መታከም ሊያደርሳቸው ይችላል:: ከዚህ በተጨማረም ከፀረ-ተህዋስያን መድኃኒቶች ጋር በተያያዘ የተላመዱ በሽታ አምጪ ጀርሞች ከአንድ ሰው ወደ ሌላ ሰው ስለሚተላለፍ የኅብረተሰብ ጤና ችግር እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል::
የጤና ችግሩ የኅብረተሰብ ችግር ሆነ ማለት ደግሞ ምርታማነትን ይቀንሳል፣ በግለሰብና በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ አደጋን ይደቅናል:: በመጨረሻም በገበያ ላይ ያሉ መድኃኒቶች በሽታ አምጪ ጀርሞችን ማከም ባለመቻላቸው ለሞት የሚዳረገውን ሰውና እንስሳትን ቁጥር ከፍ ያደርገዋል ሲሉም ይገልጻሉ::
አቶ ወንድወሰን የችግሩን ሁኔታና አሳሳቢነት ከእነሱም በኋላ ስለ መከላከያውም አብራርተዋል:: እርሳቸው እንዳሉትም፤ የመጀመሪያው ማንኛውንም መድኃኒት በጤና ባለሙያዎች ትዕዛዝ ብቻ መውሰድ፤ ለሌላ ሰው የታዘዘን መድኃኒት አለመጠቀም፤ በቂ የሆነ ምርምራ በማድረግ፤ የህመሙን ዓይነትና ደረጃ በማወቅ መድኃኒቶችን መውሰድ የግልና የአካባቢን ንጽህና መጠበቅ፤ ምግቦችን በሚገባ አጥቦና አብስሎ መመገብ የሚሉት ናቸው::
ሌላው መደረግ ያለበት ጥንቃቄ ለአንዳንድ የፀረ-ተህዋስያን መድኃኒቶች አለርጂ ከሆንን መድኃኒት በሚታዘዝልን ወቅት በቅድሚያ ለባለሙያው መናገር ሲሆን፤ ለተወሰነ ቀን የፀረ-ተህዋስያን መድኃኒቶችን ወስደን ቢሻለን እንኳን መድኃኒቱን እስከ መጨረሻው ቀን ድረስ መውሰድ አንዱ መከላከያ መንገዱ ነው::
የፀረ-ተህዋስያን መድኃኒቶችን ከታዘዘው መጠን አሳንሶ ወይም አብልጦ አለመጠቀም፤ የፀረ-ተህዋስያን መድኃኒቶች ታዝዘው መውሰድ ከተጀመረ በኋላ የጤና ባለሙያ ሳያማክሩ አለማቋረጥ፤ አግባብ ያልሆነ የፀረ-ተህዋስያን መድኃኒቶች አጠቃቀም ለእርስዎ፣ ለልጅዎ፣ ለቤተሰቦችዎ እና ለኅብረተሰቡ ጎጂ መሆኑን መገንዘብም ችግሩን ከምንከላከልባቸው መንገዶች ውስጥ ይጠቀሳል::
ከፀረ-ተህዋስያን መድኃኒቶች ጋር የተላመዱ በሽታ አምጭ ጀርሞች ሲያጋጥም በቶሎ ምርመራ ማድረግ፤ የፀረ-ተህዋስያን መድኃኒቶችን ለሰውና ለእንስሳት በአግባቡ መጠቀምና መድኃኒቶች ሕጋዊ ከሆኑ መድኃኒት ቤቶች መግዛት፤ ባሕላዊ መድኃኒቶች አካባቢ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ የሚሉት በዋናነት ችግሩን የምንከላከልባቸው መንገዶች ስለመሆናቸውም አቶ ወንድወሰን ያስገነዝባሉ::
እንስሳትንም ሆነ የሰውን ልጅ ጤና እንዲሁም የአካባቢያችንን ደህንነት የምንፈልገው ከሆነ ፀረ ተህዋስያን መድኃኒቶችን ለታለመላቸው ዓላማ ብቻ መጠቀም ያስፈልጋል:: ሳይታዘዝና ምርመራ ሳያደርጉም መጠቀም ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ከባድ ይሆናል:: ስለዚህም ማኅበረሰቡ ይህንን ተገንዝቦ የተሰጠውን ምክር በተግባር ሊያውለው እንደሚገባ ይመክራሉ:: ዓለም ብሎም ሀገራችን እየተፈተነችበት ያለ ችግር በመሆኑ የፀረ ተህዋስያን መድኃኒቶችን በጀርሞች መላመድን ሁኔታ እንደ ቀላል ልንመለከተው አይገባም:: ከዚያ ይልቅ ሙያዊ ምክሩን አድምጠን በመተግበር የራሳችንንም ሆነ የአካባቢያችንን ጤንነት እናረጋግጥ በማለት ለዛሬው አበቃን::
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 4 ቀን 2017 ዓ.ም