በምሥራቅ ሀረርጌ በአጭር ጊዜ የሚደርስ 2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሙዝ ተተከለ

ባቢሌ፡– በዞኑ በበጀት ዓመቱ በ922 ሄክታር መሬት ላይ ሁለት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ቲሹ ካልቸር የተሰኘ ሙዝ መተከሉን የምሥራቅ ሀረርጌ ዞን ገለጸ::

የምሥራቅ ሀረርጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ወይዘሮ ሚስኪ መሃመድ በዞኑ የመስክ ጉብኝት ላደረጉ ጋዜጠኞች እንደገለጹት፤ ከደቡብ በተለይም ከአርባምንጭ አካባቢ እየተመረተ ወደ መሀል ሀገር እንደሚሸጠው አይነት ሙዝ ሁለት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ካልቸራል ቲሹ ሙዝ በ922 ሄክታር መሬት ላይ መትከል ተችሏል:: በዚህም 25 ሺህ አባ ወራዎችና ወጣቶች በሥራው ላይ እንዲሠማሩ ተደርጓል ብለዋል::

በአጭር ጊዜ ውስጥ በተሠራው ሥራ ቲሹ ካልቸር የሙዝ ምርትን ለአካባቢው ገበያ አቅርቦ ወደ ሌሎች ከተሞችም ማሰራጨት እንደተቻለ ጠቁመው፤ እንደ ሶማሌላንድን ወደ መሳሰሉ ጎረቤት ሀገራትም ኤክስፖርት ማድረግ መቻሉን ወይዘሮ ሚስኪ ጠቁመዋል::

የክልሉ መንግሥት ለአርሶ አደሩ ግንዛቤ በመፍጠሩ፣ ሥልጠና በመስጠቱና ግብዓቶችን በማቅረቡ ውጤታማ ሥራ ሊሠራ ችሏል ያሉት ዋና አስተዳዳሪዋ፤ በቀጣይም የተፋሰስ ልማትን አጠናክሮ በመሥራት በሁሉም የዞኑ አካባቢዎች ምርቱን ማምረት እንደተፈለገና ወደ ውጭ ኤክስፖርት በማድረግ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት እንደታሰበ ጠቅሰዋል::

አርሶ አደር ከዲር አብዱላሂ በጉርስም ወረዳ የሀሮ ባቲ ቀበሌ ነዋሪ ቲሹ ካልቸር ሙዝን ለመጀመሪያ ጊዜ በ2016 ዓ.ም ህዳር ወር በአምስት ሄክታር ከግማሽ በሚሆን መሬት ላይ 5ሺህ 300 እግር መትከሉን ገልጿል::

ቀደም ሲል ቦታው ላይ ይዘራ የነበረው በቆሎ እንደነበር ያስታወሰው ከዲር፤ መሬቱ ለሙዝ መሆን እንደሚችል ከተጠና በኋላ በባለሙያዎች እገዛ እና ድጋፍ ሙዙን መትከል እንደቻለ ተናግሯል::

ቲሹ ካልቸር ሙዝ አንዱ እግር ከ400 እስከ 500 ፍሬ ወይም ከ35 እስከ 40 ኪሎ እንደሚይዝ ገልጾ፤ ይህም ውጤታማ የሚያደርግ ነው ብሏል::

ይህን የሙዝ ዝርያ ካዩ በኋላ ሌሎች አርሶ አደሮችም ለመትከል እየተነሳሱ እንደሆኑ ጠቅሶ፤ ሙዙ ከስር የሚወልዳቸውን ችግኞች መትከል ለሚፈልጉ አርሶ አደሮች እየሠጠ ስለመሆኑ ተናግሯል::

የወረዳው ግብርና ቢሮ አዲሱ የሙዝ ዝርያ ውጤታማ እንዲሆንና በአካባቢው አርሶ አደሮች ዘንድ እንዲስፋፋ የግብዓት አቅርቦት፤ የክትትልና ድጋፍ አገልግሎት እየሠጣቸው እንደሚገኝም ጠቅሷል::

ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ መኪና ሙዝ ወደ ገበያ ማውጣቱን የተናገረው ከዲር፤ ምርቱ በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ በጣም ተፈላጊ እንደሆነ ማረጋገጡን ገልጿል::

ከአርባ ምንጭ የሚመጣው ሙዝ በኪሎ 80 ብር እንደሚሸጥ ጠቅሶ፤ እርሱ የሚያመርተውን ሙዝ 50 ብር በመሸጥ ገበያውን የማረጋጋት ሥራም እየሠራ መሆኑን አስረድቷል::

ቲሹ ካልቸር ከምርት ብዛቱ ፣ ቶሎ በመድረሱ፤ በአንድ ጊዜ ብዙ ችግኞችን መውለድ በመቻሉ ተመራጭ እንደሆነ ገልጾ፤ በአጠቃላይ የተተከለው ቲሹ ካልቸር ሙዝ ተሽጦ ሲያልቅ አምስት ሚሊዮን ብር ገቢ የሚያገኝ ስለመሆኑም ግምቱን አስቀምጧል::

አቶ ነስረዲን አብዱራማን የጉርሱም ወረዳ አስተዳዳሪ በበኩላቸው እንዳስረዱት፤ የግብርናውን ምርታማነት ለማሳደግ እየተወሰዱ ባሉ ርምጃዎች በወረዳው በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል:: ከዚህ በፊት የማይታወቁት የበጋ ስንዴ፣ የሩዝ ምርት፣ የቅባት እህሎች የቲሹ ካልቸር ሙዝ ከአዳዲስ ትግበራዎች መካከል የሚጠቀሱ እንደሆኑ አመላክተዋል::

ቀደም ሲል በአካባቢው ይተከል የነበረው ሙዝ ፍሬ ለማፍራት ከአራት እስከ አምስት ዓመት እንደሚያስፈልገው ገልጸው፤ ቲሹ ካልቸር ሙዝ ግን በአንድ ዓመት ከስድስት ወር ለፍሬ የሚበቃ መሆኑን ገልጸዋል:: ቲሹ ካልቸር በአካባቢው ከሚመረተው ሙዝ በመጠንም በጥራትም የተሻለ እንደሆነና በምርት ብዛትም ሁለት እጥፍ ውጤት የሚገኝበት ስለመሆኑ ገልጸዋል:: በአሁኑ ጊዜ በወረዳው ከ50 ሄክታር በላይ እየተመረተ እንዳለ ጠቅሰው፤ በቀጣይም ወደ 150 ሄክታር ለመሸፈን ታቅዷል ብለዋል::

ምርታማነትን ከማሳደግ፣ የሥራ እድልን ከመፍጠር፣ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥም በላይ ቲሹ ካልቸር ሙዝ ገበያን ለማረጋጋት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል:: ጉርሱም ወደፊት ልክ እንደ አርባ ምንጭ ሁሉ ሙዝን በማልማት እንድትታወቅ በር የከፈተ አዲስ የሥራ ባህል እንደሆነ አቶ ነስረዲን አስረድተዋል::

ኢያሱ መሰለ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 4 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You