የሥልጣን ርክክቡ ለሰላም የሚደረገውን ጥረት ያፋጥናል

ከሰሞኑ የትግራይ የሽግግር መንግሥት መሪ አቶ ጌታቸው ረዳ ሥልጣናቸውን ለምክትላቸው ለሌተናል ጄኔራል ታደሰ ወረደ አስረክበዋል። ይህ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር በሕወሓቶች መካከል በተፈጠረ መከፋፈል ለወራት የቆየውን ውጥረት ያረግበዋል ተብሎ ይገመታል።

መከፋፈሉ እና መከፋፈሉ የፈጠረው ውጥረት የክልሉን ሕዝብ የእለት ተእለት ሕይወት መረጋጋት አሳጥቶት ቆይቷል። በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ተፈፃሚነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል። በተለይ በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች ይስተዋል የነበረው ሕገ ወጥ ድርጊት የስምምነቱን መርሆዎች በቀጥታ የሚጥስ እና አደጋ ላይ የሚጥል እንደነበር ይታወሳል።

የፌዴራል መንግሥቱ በስምምነቱ ዙሪያ ፀብ አጫሪ ድርጊቶቹ በተከሰቱ ቁጥር ትዕግሥት ከማጣት ይልቅ ችግሮችን በትዕግሥት እና በሆደ ሰፊነት በማስተናገድ በክልሉ የሰላም ተስፋ ዳግም እንዲፈጠር ተስፋ ሰጭ ተግባራትን አከናውኗል፤ እያከናወነ ይገኛል።

ለዚህም የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር አካታች በሆነ መንገድ ዳግም እንዲዋቀር፤ ጊዜያዊ መንግሥቱን ሌተናል ጄኔራል ታደሰ ወረደ እንዲመሩት አድርጓል። ይህም ለትግራይ ሕዝብ የሰላም እና የልማት ጥያቄ ትልቅ አቅም እንደሚሆን ይታመናል።

አዲሱን የሽግግር መንግሥት ለመምራት የተሾሙት ሌተናል ጄነራል ታደሰ ወረደ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተከሰቱ ችግሮችን በማረም የክልሉን ሰላምና መረጋጋት ዳግም ለመመለስ፤ ሕግ እና ሥርዓትን ለማስከበር ቃል ገብተዋል።

ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር በተደረሰው የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መሠረታዊ ሕጋዊ ጉዳዮችን ለማስፈፀም ሙሉ ፍቃደኛ መሆናቸውን አሳውቀዋል። የሥልጣን ርክክቡ እና የሽግግር መንግሥቱን ለተጨማሪ አንድ ዓመት የማራዘም ሂደቱ በጠረጴዛ ዙሪያ መከወኑ ለዲሞክራሲ ልምምድ የሚደረገውን ጥረት የሚያፋጥን ሆኖ ተገኝቷል።

ሰላማዊ ሽግግር ለምን?

በሰላማዊ መንገድ የሥልጣን ሽግግሮች ማድረግ ግጭት ከመከሰቱ በፊት የማስቆም ትልቁ መንገድ ነው። መሪዎች ያለ ግጭት ከሥልጣን ሲወርዱ የሕዝብ ሰላም እና ደህንነት የተጠበቀ ይሆናል። ሌሎች ሃሳቦች እና አመራሮች ሥልጣን ተረክበው አዳዲስ አማራጮችን በማምጣት ሕዝብ ሰላም አግኝቶ ወደ ልማት እንዲመለስ የተሻለ እድል ይፈጠራል።

በሕወሓት አመራሮች የተከሰተውን የሃሳብና የአካሄድ ልዩነት ለመፍታትና ለሕዝቡ እፎይታን ለመስጠት ዳግም እድል የሚሰጥ ነው። ዜጎች በመሰላቸው መሪዎች እንዲሁም ድርጅት በምርጫ የመተዳደር መብታቸው እንዲከበር ለማስቻልም የሚኖረው ፋይዳ ትልቅ ነው።

እንደሚታወቀው የፕሪቶሪያ ስምምነትን ተከትሎ የትግራይ ክልል የሽግግር መንግሥት በተቋቋመ ማግሥት በሕወሓቶች መካከል በተከሰተ አለመግባባት የፕሪቶሪያ ስምምነትን የመጣስ ምልክቶች በክልሉ አመራሮች ታይቷል፤ ይህም በክልሉ ዳግም ግጭት እንዳይከሰት ሥጋት ፈትሮ ቆይቷል።

የክልሉ ነዋሪዎች ለአዲስ የፖለቲካ ባሕልና ለውጥ ያሳዩት ጥልቅ ፍላጎት እና ይህንን እንቅስቃሴ ለማዳፈን የተሞከረበት መንገድ ለውዝግቡ መባባስ ምክንያት ነው። በተለይ በእነዚህ መሠረታዊ ልዩነቶች ምክንያት በሕወሓት አመራሮች መካከል በተፈጠረው መከፋፈል ሥጋቱ በአንዳንድ አካባቢዎች ወደ ግጭት ያመራበትም ሁኔታ ተስተውሏል። ግጭቱ የሰው ሕይወት የቀጠፈ ሰብዓዊ መብትን የጣሰም ጭምር ነው።

አለመግባባቱ ከዚህም በላይ የከፋ ጉዳት ሳያስከትል መፍትሔ አመላካች እልባቶችን ያገኘ ይመስላል። በተለይ የሰሞኑ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር፤ ሥጋቶችን በማርገብ ሂደት የተሻለ እድል እንደሚፈጥር ይታመናል፤ ሰላምም ዳግም ያሸንፋል የሚል ተስፋ ሰንቋል።

በርግጥ ሰላማዊ የሥልጣን ርክክብ መተማመንን ይፈጥራል። መሪዎች ከግል ጥቅም ይልቅ አንድነትን ሲያስቀድሙ የሕዝብ አጀንዳ የሆኑት ሰላምና ልማት እውን ይሆናሉ። ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ተቋማትን ያጠናክራል።

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግሥት በክልሉ ያለው ግጭት እንዳይባባስ ሰላማዊ መንገድን መርጦ የማደራደርና ችግሩ የማብረድ ሚናን ተጫውቷል። የኢትዮጵያ መንግሥት የክልሉን ሰላም ለመመለስ፣ ሕዝቡ ከገባበት ችግር ወጥቶ እፎይታን እንዲያገኝ ለማድረግ የሚያስችሉ የፖለቲካ ውሳኔዎችን አስፈፅሟል።

የፌዴራል መንግሥት ውሳኔዎች በክልሉ የተከሰተው አለመግባባት በውይይት እንዲፈታ መንገድ የጠረገ ነው። ተቋማት በፍትሃዊነት ለዲሞክራሲ ሲሠሩ ሰዎች በፍትህ ያምናሉ። ችግሮችም በውይይትና በሕግ አልባት ያገኛሉ። ከሰሞኑ የተጀመረው ርምጃም ይህንኑ የሚያጠናክር ነው።

መንግሥት ሕገወጥ ድርጊቶችን ሲመለከት ከስክነት ይልቅ ሕግ የማስከበር ርምጃዎችን ቢወስድ ኖሮ አሁን እያየን ያለነውን አንፃራዊ መረጋጋት መመልከት አንችልም ነበር።

የትግራይ የፖለቲካ ኃይሎች አሁን የጀመሩትን የጠረጴዛ ውይይት እስከ መጨረሻው ከገፉበትና የሕዝቡን ጥያቄዎች መመለስ ከቻሉ የክልሉ ልማት ዳግም የሚያንሰራራበት አሰቻይ ሁኔታ ይፈጠራል። ንግድና ኢንቨስትመንት ዳግም ይጀመራል። ትምህርት ቤቶች እንደገና በአግባቡ ሥራቸውን ይሠራሉ።

ሆስፒታሎች ሕሙማንን ያስተናግዳሉ። የትግራይ ሕዝብ ነዋሪዎቿ ይህን የሰላም መንገድ በአስቸኳይ ይፈልጋሉ። በሃሳብ ልዩነት እንዲሁም ለሥልጣን በሚደረግ ትግል በክልሉ የሚያስፈልገውን ርዳታ እና መልሶ ግንባታን ያዘገየ ነበር። ከዚህ በኋላ ግን ክልሉ በመልሶ ግንባታ ላይ እንዲያተኩር ያደርጋል።

ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ዲሞክራሲን ያጠናክራል። ዲሞክራሲ ማለት ከምርጫ በላይ ነው። አለመግባባቶች በሚፈጠሩበት ጊዜ እንኳን ደንቦችን ማክበር ማለት ነው። ከሰሞኑ ውጥረቱ ተባብሶ በነበረው የትግራይ መሪዎች መካከል የተደረገው ሥልጣን የማስተላለፍ ርምጃ በኃይል ሳይሆን በዲሞክራሲ ሂደት አድርገዋል። ይህ ለሌሎች አካባቢዎችም ምሳሌ ይሆናል።

ሥልጣን በሰላማዊ መንገድ ሲቀየር ማንም ከሕግ በላይ እንዳልሆነ ያረጋግጣል። ሥልጣን አስረካቢውም ሆነ ሥልጣን ወሳጁ አካል በጉልበት ሃሳባቸውን ተፈፃሚ ማድረግ አይችሉም። ከሁሉም በላይ ግን ሥልጣን በዲሞክራሲያዊ መንገድ ሲተላለፍ አለመግባባቶችን በውይይት መፍታት እንደሚቻል ዜጎች ይማራሉ።

ለምሳሌ በ2022 የኬንያ ምርጫ ተፎካካሪዎች የፍርድ ቤት ውሳኔዎችን ሲቀበሉ በቀላሉ ሊከሰት የሚችልን ሁከት ማስወገድ ተችሏል። እንዲህ ያሉ ድርጊቶች ዴሞክራሲን በአንድ ሀገር ውስጥ መሠረት እንዲኖረው ያስችላሉ።

በአንጻሩ ሥልጣን ከዚህ ቀደም በትግራይ ክልል እንደተሞከረው በግዳጅ መውሰዱ አለመተማመንን ይፈጥራል። የሱዳን 2021 መፈንቅለ መንግሥት ተቃውሞ እና የኢኮኖሚ ውድቀት ለዚህ ሁነኛ ምሳሌ ነው። የትግራይ ሽግግር ደካማ ቢሆንም የተሻለ የሰላም መንገድ ያሳየ ነው። ይህንን አንፃራዊ ሰላም የሚያደፈርስ የሥልጣን ንጥቂያና ሽኩቻ ግን ችግሩን ከድጡ ወደ ማጡ የሚወስድ ነው።

የፕሪቶሪያ ስምምነት

በፕሪቶሪያ ስምምነት (እ.ኤ.አ. ኅዳር 2022 የተደረገው) የኢትዮጵያን የሁለት ዓመት አስከፊ ጦርነት አብቅቷል። የሰላም አየር እንዲሰፍን፣ የርዳታ እና የመልሶ ግንባታ በተጎጂ አካባቢዎች እንዲደርስ መንገድ የከፈተ ነበር። ነገር ግን በቅርቡ በሕወሓት አመራሮች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ይህንን ስምምነት ሊያፈርስ ተቃርቦ ነበር። የክልሉ መሪዎች ለሕዝቡ የገቡትን ቃል ወደጎን ብለውና ግዴታቸውን ዘንግተው በሥልጣን በውስብስብ የሴራ ትንተና ውስጥ ቆይተዋል። ይህ አደገኛ ርምጃ ነበር።

የፕሪቶሪያ ስምምነትን ማክበር ወሳኝ ነው። ስምምነቱን ማክበር የሚከተሉት ቁልፍ ጉዳዮች እንዲሳኩ ይረዳል። የመጀመሪያው አላግባብ በጦርነትና ግጭት የሚጠፋውን ሕይወት ያድናል። ጦርነቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚገድል አስከፊ ድርጊት ነው። ስምምነቱን አፍርሶ ዳግም ወደ ግጭት መመለስ ጭል ጭል የሚለውን ሰላም ጭርሱኑ ያጠፋል። በዚህ ምክንያት ስምምነቱን ማክበር ይገባል። ሌላው የስምምነቱ ወሳኝ ግብ ኢትዮጵያን አንድ ማድረግ ነው። ስምምነቱ መለያየትን የሚነቅፍና ይልቁኑ ችግሮችን በውይይት ፈትቶ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚያስከብር ነው።

የፕሪቶሪያ ስምምነት መከበር ለሕዝቡ እፎይታን እና ድጋፍ የሚያመጣ ነው። በሚሊዮን የሚቆጠሩ የትግራይ ሰዎች ምግብና መድኃኒት ያስፈልጋቸዋል። በመሆኑም እያንዳንዱን የስምምነቱን መርሆ ማክበር በተረጋጋ ሁኔታ ለሕዝቡ ርዳታ መድረሱን ማረጋገጥ እንዲቻል እድል ይፈጥራል። ከሰሞኑ የሽግግር መንግሥቱን የሚመሩት የትግራይ ክልል መሪዎች በሰላማዊ መንገድ ክልሉን ለመምራት የሚያስችል የሥልጣን ርክክብ ማድረጋቸው የፕሪቶሪያን ቃል ኪዳኖች የሚያስጠብቅ ነው።

አቶ ጌታቸው ረዳ ለሌተናል ጄኔራል ታደሰ ወረደ የትግራይ ክልላዊ ሽግግር መንግሥት ፕሬዚዳንትነት ሥልጣኑን መስጠቱ ትልቅ ትርጉም ያለው ትንሽ ርምጃ ነው። በዋነኝነት ከአለመግባባትና ከግጭት በኋላ እንኳን ሰላም ሊኖር እንደሚችል የሚያሳይ ምሳሌ ነው። ሰላማዊ ሽግግር ሰላምን አስፍኖ የሰዎችን ውድ ሕይወት ይጠብቃል።

ለዚህ ነው መሪዎቹ በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው በክልሉ ያሉ ችግሮችን በጋራና በመደጋገፍ ለመፍታት ቁርጠኛ መሆናቸውን ሲያሳዩ ከምንም በላይ ሕዝቡ ደስተኛ የሚሆነው። በርምጃቸው ማኅበረሰቡ እፎይታን እንዲያገኝ አስችለዋል፤ በሌላ በኩል ዴሞክራሲ የበለጠ የሚያጠናክር ሥልጡን ርምጃን ወስደዋል።

የፕሪቶሪያ ስምምነት ፍኖተ ካርታ ነው፤ በሁሉም መሪዎች መመራት አለበት። የትግራይ ሕዝብ መረጋጋት ይገባዋል። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም የኢትዮጵያን ጥረት መደገፍ አለበት። መሪዎች ከአመጽ ይልቅ ውይይትን በመምረጥ ለተሻለች ኢትዮጵያ ሊተጉ ይገባል። ለሰላም ምን ጊዜም ቢሆን ጥረት ማድረግ ባሕላችን ይሁን። ሰላም!!

ሰው መሆን

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 4 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You