
እንዳለፉት ዓመታት ትኩረት ያልተሰጠው የኢትዮጵያ ፕሪሚየርሊግ የ2017 የውድድር ዓመት ወደ መገባደጃው እየተቃረበ ይገኛል። በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስቴድየም በመከናወን ላይ የሚገኘው የፕሪሚየርሊግ ፉክክር ካለፈው ሰኞ እስከ ሐሙስ በ24ኛ ሳምንት መርሃግብሩ በየእለቱ ሁለት ጨዋታዎችን አስተናግዷል። በነዚህ ሳምንታት ጉዞውም ዋንጫውን ለማንሳትና ላለመውረድ የሚደረጉ ፉክክሮች አጓጊ ሆነው ታይተዋል። በቀጣይ ሳምንታትም ቻምፒዮኑን ለመለየት እያንዳንዱ ጨዋታ የዋንጫ ያህል ዋጋ ያለው ሆኗል። ወልዋሎ አዲግራት ከወዲሁ መውረዱን ያረጋገጠ ክለብ ነው። ዘንድሮ አራት ክለቦች ወደ ከፍተኛ ሊግ የሚወርዱ መሆኑን ተከትሎ ግን በደረጃ ሰንጠረዡ ከወገብ በታች የሚገኙ ክለቦች ትንቅንቅ ይበልጥ አጓጊ ሆኖ ቀጥሏል።
በ2015 ዓ/ም ከስምንት ዓመት በኋላ ወደ ፕሪሚየርሊጉ የተመለሰው ኢትዮጵያ መድን በቻምፒዮንነት ፉክክሩ ከፊት ተሰልፏል። ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከጅማ አባ ጅፋርና ከመቀሌ 70 እንደርታ ጋር የሊጉን ዋንጫ ያነሱት አሠልጣኝ ገብረመድን ኃይሌ ዘንድሮም ከመድን ጋር ለማሳካት በጥሩ ግስጋሴ ላይ ይገኛሉ። ያም ሆኖ ዋንጫውን ለማንሳት በቀሪዎቹ ሳምንታት ቀላል ፉክክር አይጠብቃቸውም። መድን ባለፈው ሰኞ በወራጁ ክለብ ወልዋሎ አዲግራት ነጥብ መጣላቸው በደረጃ ሰንጠረዡ ሁለተኛ ሆኖ ከሚከተለው ክለብ ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ይበልጥ ማስፋት ሳይችሉ ቀርተዋል። ያም ሆኖ በ22 ጨዋታ 13ቱን አሸንፈው፣ በ6 ጨዋታ አቻ፣ በ3 ጨዋታ ደግሞ ሽንፈት አስተናግደው በ45 ነጥብና 18 ንፁህ ግብ መሪነቱን ጨብጠው ይገኛሉ። በመጪው ረቡዕም አዳማ ከተማን የሚገጥሙ ይሆናል።
በ36 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የነበረው ኢትዮጵያ ቡና የመድንን ነጥብ መጣል ተከትሎ ልዩነቱን የሚያጠብበት እድል የነበረው ቢሆንም አልተጠቀመበትም። ባለፈው ሐሙስ በባህርዳር ከተማ ሁለት ለምንም ተሸንፎ ደረጃውን 37 ነጥብ መሰብሰብ ለቻለው ወላይታ ድቻ አስረክቧል። በቀጣይ ሰኞም በሦስት ነጥብ ልዩነት ርቋቸው የሚገኘውን ሌላኛውን ጠንካራ ተፎካካሪ ፋሲል ከነማን ይገጥማሉ። የጦና ንቦች ደግሞ ሰኞ በደቡብ ደርቢ የመውረድ ስጋት ውስጥ የሚገኘውን ሐዋሳ ከተማን ያገኛሉ።
ቡናማዎቹን ከጨዋታ ብልጫ ጋር መርታት የቻለው የአሠልጣኝ ደግያረጋል ይግዛው የጣና ሞገዶች ስብስብ ነጥቡን ወደ 34 አሳድጎ የዋንጫ ተፎካካሪነቱን አጠናክሯል። ባህርዳር ከተማ ወጥ አቋም ማሳየት ቢቸገርም የውድድር ዓመቱ ሲጀመር ከዘጠኝ ተጫዋቾች ጋር ተያይዞ አሠልጣኙ ወጣቶችን ልምድ ካላቸው ጋር አጣምሮ ጥሩ ተፎካካሪ ሆኖ የቀረበበት መንገድ ያስመሰገነው ሆኗል። የ25ኛ ሳምንት መርሀግብሮች ከሰኞ ጀምሮ ሲከናወኑ ባህርዳር ከተማን በእኩል 34 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ሀዲያ ሆሳዕና ያገናኘው ፉክክር ተጠባቂ ነው። በተመሳሳይ ሰኞ እለት በእኩል 31 ነጥብ ዘጠነኛና አስረኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት የዓምናው ቻምፒዮን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ከቅዱስ ጊዮርጊስ ያገናኘው ጨዋታ አጓጊ ነው።
ሊጉ ከሚቀሩት መርሀግብሮች አኳያ በደረጃ ሰንጠረዡ ወገብ ላይ የሚገኙ ክለቦችም ከዋንጫው ተፎካካሪነት ውጪ አይደሉም። በተመሳሳይ በደረጃ ሰንጠረዡ መሀል ላይ የሚገኙ ክለቦችም የመውረድ ስጋት ውጪ አይሆኑም።
ዋንጫውን ለማንሳትና ላለመውረድ የሚደረገው ትንቅንቅ አጓጊ እንደሆነው ሁሉ የኮከብ ግብ አግቢነቱ ፉክክርም እጅግ ተቀራራቢ ሆኖ ቀጥሏል። የአርባ ምንጭ ከተማው አህመድ ሁሴን በ 10 ግቦች ቀዳሚው ተጫዋች ቢሆንም ሌሎች በርካታ ተጫዋቾች በአንድ ግብ ልዩነት በቅርብ ርቀት እየተከተሉት ይገኛሉ። የኢትዮጵያ ቡናው አንተነህ ተፈራ፣ የሃዋሳ ከተማው አሊ ሱሌማን በዘጠኝ ግቦች ሲከተሉ ቆይተዋል። በ24ኛው ሳምንት መርሃግብር አፄዎቹ ፈረሰኞቹን 2ለ1 በረቱበት ጨዋታ ጌታነህ ከበደ ሁለት ግቦች ከመረብ አሳርፎ በእኩል ዘጠኝ ግቦች እየተፎካከሩ የሚገኙትን ኮከቦች መቀላቀል ችሏል። የመቐለ 70 እንደርታው ያሬድ ብርሃኑ በስምንት ግቦች፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ ኪቲካ ጅማና የመድኑ መሀመድ አበራ በሰባት ግቦች የኮከብ ግብ አስቆጣሪነቱ ፉክክር ውስጥ የሚገኙ ተጫዋቾች ናቸው።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 4 ቀን 2017 ዓ.ም