
ባሁኑ አጠራር በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ወገራ ወረዳ ከአምባጊዮርጊስ ከተማ 9 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው በአንድ እግሬ የገበሬ ማኅበር ከአባቱ አቶ መንገሻ ገስጥና ከእናቱ ከወይዘሮ አለምነሽ አዳነ በ1982 ዓ.ም ኤፍሬም መንገሻ ተወለደ።
“ሰባት ሰዓት ሲሆን ከብት ውሃ ሲጠጣ፣
ደሞ አገረሸብኝ ትዝታዬ መጣ።”
እንዲል ተስፋዬ ወርቅነህ፤ ኤፍሬም መንገሻ የከብት ጭራ በሚከተልበት፣ ከእኩዮቹ ጋር በሚቦርቅበት እድሜው ከቀናት በአንዱ ከብቶቹን ውሃ አጠጥቶ ካጠገበ በኋላ በለመለመው መስክ ከወንዙ ዳርቻ ጥቂት አረፍ አለ:: በተኛበት አጋጣሚ ታዲያ ጥላው ሸሽቶ ኖሯል:: ድንገቴ ፀሐይ ደርሶበት በውሃው ነፀብራቅ ገና በአስር ዓመቱ ብርሃኑን ተነጠቀ:: ይህ እውነትም ለወላጆቹ መለያየት ሰበብ ሆነ።
በአንደኛው ቀን ሌሊት፤ የምሽት ጨረቃ በምት ደምቅበት፣ ወግ በሚሞቅበት፣ ፍቅር በሚደራበት ሰዓት እንቅልፍ ያልወሰደው ኤፍሬም የሱን ጉዳይ አንስተው እናትና አባቱ ሲጨቃጨቁ ጆሮው በወጉ ሰማ:: ወዲያው ልቡን ሰርስሮ የዘለቀው መሪር ኃዘን ሰው የመሆን ሕልሙን አቀንጭሮ የልጅነት ሞራሉን መቅኖ ቢስ አደረገው። ካፈሯቸው ዘጠኝ ልጆች ኤፍሬም ስምንተኛው ነው:: አባቱ ባልተማረ እሳቤው በተሳሳተ አመለካከቱ በድንገት ባጋጠመው አካል ጉዳት ሳቢያ ከሕይወት መዝገብ ሰርዞታል:: ከልጅነት ተርታ አስወጥቶታል።
“ሀገር ባወቀኝ ፀሐይ በሞቀኝ ቀዬ አካለ ጎዶሎ ልጅ እንዴት ሊኖረኝ ይችላል? ከእንግዲህ መቼም ሰው አይሆንምና መንደሩ መጠቋቆሚያ ከሚያደርገን ጎዳና እንጣለው አሊያም አፍነን እንግደለው?” ሲል ለሚስቱ ምርጫ አቀረበላት፤ እሷ ግን
“እባብ ገላው መልካም መንታ ነው ምላሱ፣
ምንም እንኳን ቢሆን አይማርም ነፍሱ።”
ብላ ተረተችና “ጭካኔህ ካውሬ ይከፋል ክፋትህ ሰይጣንን ያስንቃል” ስትለው ያባቱ ፈርጣማ እጆች የናቱን ፊት በጥፊ ሲቀቅሉት በትሩ እንደገደል ማሚቶ ኤፍሬም ጆሮ ዘንድ አስተጋባ:: ወዲያው የምንጣፍ መኝታው በዕንባ ራሰ። ወይዘሮ አለምነሽ አዳነ ጎሕ ሲቀድ ጨቅላ ሴት ልጇን አዝላ፣ ኤፍሬምን ይዛ፣ ሐቋን ትታ ዕንባዋን እንደዋጠች አምባጊዮርጊስ ከተማን ማረፊያዋ አደረገች::
ኑሮን ‹‹እሽሩሩ›› ብትለው ፊት ሲነሳት “ወትሮስ ውሃ ተሸጦ የሰው ቤት እንጀራ ተጋግሮ ሕይወት ሊሆን ኖሯል?” አለችና ጎጆ ወደወጣችበት ቀዬ ተመለሰች:: አባቱን መንገሻ ገስጥን በሸንጎ ጠይቃም አንገት ማስገቢያ ቢሆነኝ ብላ ሁለት ገዝም መሬት ተቀበለችው። “ትምህርት ለልጄ፣ ዛፍ ለደጄ” በሚል ዘመቻ በገጠራማው የሀገሪቱ ክፍል ዘንድ ከተሠሩ ትምህርት ቤቶች መሐል ከኤፍሬም የትውልድ መንደር የተከፈተው ‹‹ፎቶ ቢክ›› አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አንዱ ነውና “ጠላት በምን ይመጣ? ከኋላ እግዜርሳ? በሰው ጥላ” እንዲሉ የትምህርት ቤቱ መምህራን ኤፍሬምን ትምህርት ቤት እንድታስገባው እናቱን ወተወቷት:: እሷም ስለነገ የልጇ ዕጣ ፈንታ ስትል በመሸነፍ መልሳ አምባጊዮርጊስ አደረሰችው፤ ከመኪና ጎማ የሚሠራ ጫማ በአንድ ብር ከሃምሳ ሳንቲም ገዛችለትና ከአንድ እግሬ አምባጊዮርጊስ ዘጠኝ ኪሎ ሜትር ውሎ ገባ እያመላለሰች ለማስተማር ሞከረች:: ትርፉ ድካም ብቻ ሆነባት::
ትምህርት ቤቱ ካለበት አንድ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ‹‹ተልባ ምንጭ›› መኳንንት ተስፋዬ ከሚባል የአካቶ ተማሪ ጋር ከሚሰጣቸው ሠላሳ ብር የድጎማ ገንዘብ ቀንሰው በማቀናጀት ቤት እንዲከራዩ ተደረገ። ኤፍሬም እናቱ ለሳምንት የሚሆን በርበሬ ድልህ ቀብታ የምታመጣለት አራት እንጀራ ቀኑን አደርስ አደርስ ሲል እየሸበተ፣ እየሻገተ አልበላ ብሎት ረሃቡ ከትምህርቱ ይጎትተው ያዘ:: ደግነቱ የመኳንንት ወላጆች እጃቸውን ዘረጉለትና ከጭንቀት ገላገሉት።
እነሱ ለልጃቸው ስንቅ ሲቋጥሩ ኤፍሬምንም እያሰቡ ነው:: አጋጣሚው የሚያዛጋ ሞሰባቸውን ርሽርሽ አደረገው። ከዚህ ባለፈ ኤፍሬም በአቅራቢያው ከሚገኝ ደብር አስፈቅዶ የአብነት ትምህርቱን በመከታተል ለሙታን መታሰቢያ የሚዘጋጀውን መሃራ [ተስካር] በመካፈል የምግብ ጥያቄውን መቅረፍ ቻለ:: ይሁን እንጂ እንደእኩዮቹ ያሻውን መልበስ ባለመቻሉ ቅሬታ ይሰማው ጀመር:: በትካዜ ብቻ አልቆየም::
እስከ ጎንደር ለሚጭኑ የሕዝብ ማመላለሻ መኪኖች ረዳትነት ገብቶ የገንዘብ ማግኛ መንገዱን ፈጠረ:: ሕይወት ‹‹ዓለምዬ ሶራ›› ሆነችለት፤ በቀለም አቀባበሉ ጎበዝ ስለነበር ዓይነስውራንን ብሬል በማስጠናት ለሻይ መጠጫ ኪሱን ማርጠብ ቻለ። ትምህርት አልቆ ክረምቱ ሲገባ ለእረፍት አምባጊዮርጊስ የመጡት አቤል አጽበሃና ሲራክ ድረስ የሚባሉ ዓይነስውር ጓደኞቹ ለኤፍሬም ስለአዲስ አበባ ከማር አጣፍጠው፣ ከጨረቃ አስውበው ተረኩለትና ልቡን አሸፈቱት:: ሀገር ጥሎ ለመኮብለል ውስጡ ተነሳሳ::
ኤፍሬም ‹‹ቶኪንግ ዋች››፣ ነጭ በትርና የብሬል መጽሐፍት እንደልብ መሆኑን ነግሮ ወዳጁ መኳንንት አብሮት አዲስ አበባ እንዲሄድ ሲያግባባው እሽታውን አገኘ:: ለደከሙበት የአብነት ትምህርት ድቁናን ለመቀበል አስበው ጉዞን ወደሸገር አደረጉ:: 1997 ዓ.ም ሰኔ አንድ ቀን መንገዱ በእግር ተጀመረ። ፀሐይ አኩርፋ በሯን ስትዘጋ ጀንበር ከጨረቃ ጋር ስታወጋ በየደብሩ በእግዜር እንግድነት እያደሩ ጎዳናውን ተያያዙት፤ ኑሯቸው በቆሎ ትምህርት የተሟሸ ነውና የኩበት ጪስ እያሸተቱ የውሻና የዶሮ ድምፅ ሲሰሙ በአቅራቢያ መንደር መኖሩን ይገምታሉ:: ወደዚያው በማቅናትም አኮፋዳቸውን አስቀድመው “በንተስማለማርያም” በማለት ረሃባቸውን ያስታግሳሉ።
ሁኔታቸውን አይቶ ያዘነ ሹፌር በነፃ እየያዛቸው፣ አልፎ አልፎም መንገደኛው የትራንስፖርት እየከፈለላቸው ያለችግር ተጓዙ:: መንገድ በጀመሩ በአንድ ዕለት ፀሐይዋን ቀድመው መራዊ ከተማ ደረሱ:: ማደር አልፈለጉም:: መንገድ ለማቅለል ሲሉ ወደ ዱር ቤቴ አቀኑ:: እንዲያም ሆኖ መንደር ካለበት ስፍራ አልደረሱም:: መሐል ጫካ ላይ መሸባቸውና ከቦታው ማደር ግድ ሆነባቸው። ውዳሴ ማርያም ደገሙና ከመንገዱ ጥግ ጎናቸውን ከማስነካታቸው በጅብ መንጋ ተከበቡ:: ዙሪያቸውን እያሽካኩ የሚዞሯቸው ጅቦች እንዳሉ ባወቁ ግዜ መላከ ሞትን ቆሞ ያዩት ያህል ተሰማቸው::
“ተምረን ሰው ሳንሆን ቀደምከን?” ከማለት በቀር ቃል አልተነፈሱም፤ ያልታዘዘው አይሆንምና ምድር የጨለማ ክንብንቧን ገልጣ የብርሃን ጸዳል ስትጎናጸፍ የተረፉበትን ታምር በማመስገን የእግር ጉዟቸውን ቀጠሉ። አማኑኤልን አልፈው በውቀቱ ሥዩም በመጽሐፎቹ የሚያቀማጥላትና የማርቆስ በር ከሆነችው ‹‹ወንቃ ሲደርሱ›› የደጃፏ ድልድይ ግማሽ ጎኑ ተገምሶ ኖሮ የሚጠቁሙበት በትራቸው መስመሩን ሳተ::
ወደጥልቁ ገደል ሊወረወሩ ሲሉ ከስሩ የሚያርስ አንድ አርሷአደር እየጮኸ “ወደኋላ ተመለሱ” ሲላቸው ዓይነስውራኑ እርስ በርስ ተሳስበው ለሁለተኛ ጊዜ ከሞት አፋፍ አመለጡ፤ ይህ ደግ ሰው ከቋጠረው ማርሳና ከያዘው ጠላ በኮልባ ዋንጫ ሲዘይራቸው ድንጋጤና ረሃብ የደቆሰው አካላቸው ተጠግኖ መንቆረር /ደብረማርቆስ/ ዘለቁ፤ ዳሩ ግን የከተማ ደብር ዘንድ ከመሸ አይኬድምና በአስር ሳንቲም ለወለል ከፍለው አደሩ። ንጋቱ ያህያ ሆድ ሲመስል ጮራዋን ቀድመው ማልደው ተነሱና የነፋሲትን ጫካ ነፋሻማ አየር እየሰነጠቁ ጎጃም ወለላውን እያደነቁ ስንዝር ርምጃቸውን እየቆነጠሩ ሲያዘግሙ አንድ የጭነት መኪና አሳረፋቸውና በጊዜ ለደጀን ከተማ አበቃቸው:: የቀትሯ ፀሐይ አሳሳቻቸውና አሁንም እንደለመዱት መንገድ ለመቀነስ ብለው በድፍረት የዓባይ ቁልቁለትን ተጋተሩት:: ጭው ያለው በረሃ ጽልመት ለብሶ ጠበቃቸው። ሰው ቀርቶ አራዊት እንኳን የጠሉት ቦታ የተፈጥሮ ለዛው ርቆት ሰማይ ጠቀስ ዛፎቹ ሲያፏጩ መስማት ለጆሮ ይሰቀጥጣል።
“አዲስ አበባ ላይ ወድቄ ብነሳ፣
የሠራ አካላቴ ወርቅ ይዞ ተነሳ።”
ሲባል እየሰሙ ያደጉት እነኚህ ዓይነስውራን መንገደኞች የመጻኢ ዕድላቸውን ከሕይወት ምዕራፍ ሊገልጡ የሕልማቸውን መፍቻ ቁልፍ ሊያስሡ ዓባይ ማዶ ያለውን ምድር ባሻጋሪ እያለሙና የከለላቸውን አቀበት በተስፋ መዶሻ እየናዱ ጉዟቸውን በጽናት ተያያዙት።
ፍልቅልቅ ከተማ ከመግቢያው ሲደርሱ ረሃብ አሸንፏቸው ለዳገቱ እጅ ሰጥተው ነበር:: የላይኛውን አሸዋ ሰርስረው ቆፈሩና ከለም አፈሩ ጥቂት ጎረሱለት:: የዕምነታቸው አስተምሮት “በሰንበት ቀን ከቅዳሴ በኋላ እህል ቢጠፋ አፈር ቅመሱ” ይላልና። ዛሬ ላይ ኤፍሬም “እንደዚያ አፈር የየትኛውም ቅንጡ ሆቴል ምግብ አይጥመኝም” ይላል በኩራት።
የዛን ቀን ማለዳ የኩበት ጭስ ጠርቷቸው ሽታውን ተከትለው ከመንደሩ ዘለቁ:: ያገኟቸው ሰዎች ልሳናቸው ኦሮምኛ ሆኖ መግባባት አልቻሉም:: ሆዳቸውን እየተመተሙ ረሃባቸውን ሲገልፁላቸው ግን ገራገሮቹ ነዋሪዎች እንጀራ በእርጎ አቀረበላቸው:: ስለተደረገላቸው መልካምነት ሁሉ ከልብ አመሰገኑ:: ጥቂት ቆይተው ለጉዞ ሲነሱ የመቆያ ስንቅ እንዲሆናቸው ብስል ከጥሬ ተቋጠረላቸው “መሬታችንን ጾም ከማደር፣ ሕዝባችንን ከመለያየት ጠብቅልን” እያሉ ለፈጣሪያቸው ጸሎት አደረሱ። ባልንጀሮቹ መንገደኞች የፍቼን አፈር ጫማቸው ሲልስ አንዳንድ የከተማው ሰው የት እንደሚሄዱ ጠየቃቸው “ቅኔ ለመማር ነው እያሉ የሰጡትን ምክንያት መድገም አልፈለጉም:: ይልቁንም ‹‹አዲስ አበባ የዓይን ሕክምና አለ ሲባል ሰምተን ዕድላችንን ለመሞከር በእግራችን ጉዞ ጀመርን” ማለትን ደጋገሙ::
ሰዎቹ ወደሸገር የሚሄድ የመንግሥት መኪና ተባበሯቸውና መኪናው አዲስ አበባ ፒያሳ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ደጃፍ ጣላቸው። ከሠላሳ ሦስት የመከራ ቀናት በኋላ ሐምሌ አራት ሸገር የገቡት ዓይነስውራን ሁሉም ነገር ግር ብሏቸው ቆዩ:: ወዲያው ግን በተቀመጡበት በብር ጎርፍ እንደተዋጡ አወቁ:: በሕዝቡ ደግነት ከልብ ተደነቁ:: በኋላ የአቦ ደብርን እንዲያሳይዋቸው በጠየቁ ጊዜ አንዲት ባልቴት በሰላሳ አምስት ሳንቲም 12 ቁጥር አውቶቡስን አሲይዘው ፈረንሳይ ለጋሲዮን ሸኟቸውና ሌሊቱን አቦ ቤተክርስቲያን ሲያገለግሉ አደሩ:: ጠዋት ላይ ምዕመኑ በየፊናው ተበተነ:: እነሱ መሄጃ አጥተው እንደቆሙ የዲያቆን አየነው ተስፋዬን ትንፋሽ ቢያገኙ እግዜር ከሰማይ የወረደ ያህል ተሰማቸው::
ለአብሮ አደግ ወዳጃቸው ያሳለፉትን ፈተናና የመጡበትን ዓላማ አወጉት “አይዟችሁ ወንድሞቼ እኔ እያለሁማ አትለምኑም” ብሎ 1500 ብር አወጣና መርካቶ አውቶቡስ ተራ አዳራሹ ፊት የውስጥ አልባሳትና ካልሲዎችን አሲይዞ ሁለቱንም የንግድ ሥራ አስጀመራቸው። እጃቸው ተፈቶ ሃሳባቸው ቀንቶ ሲደላደሉ ጎጃም በረንዳ በየቀኑ ሃምሳ ሳንቲም እየከፈሉ መደብ ከማደር ወደቤት ኪራይ ተሸጋገሩ:: ይህን ጊዜ ኤፍሬም የትምህርት ጉዳይ ውል አለው:: ሀሳቡንም ለጓደኛው አጋራው:: መኳንንት ግን ፍላጎት እንደሌለው አሳወቀው:: ኤፍሬም ለትምህርት ያለው ቦታ ከፍ ያለ ነበርና ክሬሽን ልብስና የአንበሳ ቆዳ ጫማ ገዝቶ በጊዜው ፋሽን ደመቀና መሸኛ ሊያመጣ አምባጊዮርጊስ ተመለሰ:: መሄዱን ሳይነግራት በመራቁ ያኮረፈች እናቱ ለውጡን ስታይ ተደሰተች::
አዲስ አበባ ሲመለስ ዳግማዊ ምኒሊክ ትምህርት ቤት ገባ፤ ሚኒስትሪ ተፈትኖ በጥሩ ውጤት ቢያልፍም ግማሽ ቀኑን ትምህርት እኩሉን ሥራ እያለ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አደበዘዘበት:: ይሁን እንጂ ከቶጎ ውጫሌና ከጋንቦ ሞያሌ ሮጦ ኑሮውን በመደጎም ለሃዋሳ ዩኒቨርስቲ በቅቶ ‹‹ገቨርናንስ ኤንድ ዴቬሎፕመንንት ስተዲስ››ን ለመቀላቀል ቻለ። የማዕረግ ተመራቂው ወጣት ሥራ ፍለጋ ቢኳትንም አልሆነለትም::
ለአንድ ዓመት ያህል ሎተሪ እያዞረ ኑሮን መግፋት ያዘ:: በኋላ በለስ ቀናውና የሙያና የሲቪል ማኅበረሰብ ማደራጃ ጽሕፈት ቤት ውስጥ የዜጎች አቅም ግንባታ ጀማሪ ኦፊሰር ሆኖ ተቀጠረ፤ ቢሆንም ግን ምቹ ሁኔታዎች ስላልተፈጠሩለት ሥራውን ትቶት ሶማሌ ላንድ ተሰደደ:: ሀገሪቱ ከልመና በቀር አላቆየችውም፤ በዚህም ተስፋ ሳይቆርጥ ወደየመን በባሕር ለመሻገር ያደረገው ጥረት ሳይሳካለት ቀረና ተመልሶ በድሬዳዋ በኩል ጅቡቲን ጎበኛት:: እሷም ብትሆን ያው ነበረች:: በወቅቱ ስለውጭ ጉዞ ያናገራቸው ሰዎች በመርከብ ወደፈረንሳይ ለማሻገር የጠየቁት አምስት ሺህ ዶላር ነበር:: ይህ እውነት ሕልሙን አጨናግፎ ‹‹ሀገሬን›› አስባለው።
የኢትዮጵያን አድባር ተማፅኖ ጥርሱን ነከሰና ባጠራቀመው ጥሪት በፖለቲካል ሳይንስ ሁለተኛ ዲግሪውን ለመማር ባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ ከተመ:: ይሁን እንጂ ለትምህርት ክፍያው እጅ አጥሮት መተጓጓል ያዘ:: ጊዜው በሀገራችን ኮሮና የገባበት ነበር:: ይህ አጋጣሚ ግን ለእሱ መልካም ሆነለት:: ማስክና ሳኒታይዘርን ለሦስት ወራት ያህል ሸጦ አንድ መቶ አስር ሺህ ብር በማጠራቀም የተዳፈነ ትምህርቱን አበራው:: 3 ነጥብ 97 በማምጣትም በኩራት ደመቀበት። ከዚህ በኋላም ፈተና አላጣውም:: ለዘመናት የተጠማውን የዩኒቨርስቲን መምህርነት ለመወጣት ደጅ ቢጠናም ሕልሙን እንዳያሳካ ገፊ ምክንያቶች በዙበትና የጠላውን ስደት ዳግም ተመለሰበት:: ዳሩ ምን ይሆናል? ጅቡቲም ከምፅዋት በቀር የዘረጋችለት ነገር አልነበረም:: ዙሪያ ገደል ሲሆንበት “ለመቸገርማ ሀገሬስ መቼ ታንሳለች?” ብሎ ተመለሰና መገናኛ በሚገኘው ከቦሌ ክፍለከተማ ጀርባ ትናንሽ የቤት እቃዎችን በመሸጥ ኑሮን መግፋት ጀመረ::
ቃለመጠይቅ ባደረኩለት ጊዜ ሞራልን የሚያድስ ጽናትን የሚያላብስ ሃሳብ ሰጠኝ። “መማር ማለት መሸነፍ አይደለምና አኗኗሬ የሰንበሌጥ ስትራቴጂ ነው፤ ሰንበሌጥ ከባድ የውሃ ማዕበል ሲመጣ አጎንብሳ ታሳልፈዋለች፣ እንጂ ስሯ እስኪነቀል አትታገለውም፤ እኔም ልክ እንደሷ ነኝ” አለኝ:: ብሩህ የተስፋ ገጹን እንደ ፀደይ የለምለም መስክ አፍክቶት።
ቀናት ተመሳቅለው ጊዜ እየሾረ፣
ትናንት እስከዛሬ እንዲህም ተኖረ።
ነገስ?
ብታሙ ባንታየሁ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 4 ቀን 2017 ዓ.ም