“ለብልህ አይነግሩ ለአንበሳ አይመትሩ!”- የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)

“ለብልህ አይነግሩ ለአንበሳ አይመትሩ!” እንዲሉ አበው፣ ጃውሳው በቃህ ተብሏል፡፡

መንግሥት በአማራ ክልል የትምህርት አገልግሎትን በተሟላ መልኩ ወደነበረበት ለመመለስ እያደረገ ያለውን ጥረት ማገዝን ጨምሮ የትምህርት ቤት የምገባ መርሃ ግብሮችን ተግባራዊ ለማድረግ እንደ ዩኒሴፍ የመሳሰሉት ግብረሰናይ ድርጅቶች የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል። የገንዘብ ድጋፉ ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለማቋቋም፣ ትምህርት የማቋረጥ ምጣኔን ለመቀነስ እና ለ50,000 ህጻናት የተመጣጠነ ምግብ ለማቅረብ ያለመ ነው፡፡

ይህ ሠብዓዊነት የተላበሰ መልካም እይታና እንቅስቃሴ ይበል የሚሰኝና አርአያነት ያለው ሆኖ ሳለ፣ የእውቀትና ትውልድ ቀጣይነት ጉዳይ ፈፅሞ የማይገባቸው የድንቁርና ጌቶቹ የጃውሳው ሰዎች፣ ይህ የተቀደሰ ተግባር እንደ አበደ ውሻ እንዲቅበዘበዙ አድርጓቸዋል፡፡

የአማራ ሕዝብ በሰላም እጦት እንዲታመስ ከውስጥና ከውጭ የጥፋት ሃይሎች ጋር ተመሳጥረው ያደረሱት ታሪክ የማይዘነጋው ጥፋትና ውድመት ሳያንስ፣ ህፃናት ላይ ትኩረት አድርጎ በሚሠራው ዓለም አቀፍ ተቋም (ዩኒሴፍ) ሠራተኞች ላይ የጥፋት በትራቸውን አንስተዋል።

የጃውሳው ሰዎች፣ ህፃናትና ታዳጊዎች ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመለሱ ለምን አደረጋችሁ? የገንዘብ ድጋፍ በመለገስ ለህፃናት የተመጣጠነ ምግብ ለማድረስ ለምን ሠራችሁ? በማለት የዩኒሴፍ ሠራተኞችን የማገትና ባህር ዳር በሚገኘው ተቋማቸው አቅራቢያ የእጅ ቦንብ የመወርወር ሰይጣናዊ ተግባር ፈፅመዋል። ይህ አረመኔያዊነትና ዓላማ የሌለው የጥፋት እሳቤና ፈሊጥ የጥፋት ቡድኑን አጀንዳ ይበልጥ ከማጋለጥ ባለፈ ብዙዎችን አሳዝኗል፡፡

የጃውሳው ፍላጎትና ተግባር፣ የአማራ ሕዝብ እንቅስቃሴ እንዲታወክ በማድረግ ሕዝቡ ራሱንና ሀገሩን ለማሳደግ የሚያደርገውን ጥረት በሁሉም መስክ የማዳከም፣ ክልሉን የቀነጨሩ እና ከትምህርት ገበታ የራቁ ህጻናት ማዕከል የማድረግ እንደሆነ በግልፅ ያሳያል። ጃውሳውን ከውጭ ሆነው የሚነዱ የድንቁርና ሃይሎች እነሱ የማይቀምሱትን እሳት ከሩቅ ሆነው እያቀጣጠሉና በጃውሳው ዓላማ የለሽ ዘራፊዎችና ጥቃት ሕዝቡን እያሳቀቁ በሕዝቡ ስም የሚነግዱ ተኩላነታቸውንም እያረጋገጡ ነው።

የግብረሰናይ ድርጅቶች ሠራተኞችን እንቅስቃሴ በማወክ በአማራ ህፃናት ላይ እየፈፀሙት ያለው ኢሠብዓዊነት የዚህ ስብስብ የውስጥና የውጭ ሴራ ጥምረት ውህድ ውጤት ነው።

የተለያዩ ረድኤት ድርጅቶችና ለጋሽ አካላት ድንበር ሳይገድባቸው በሠብዓዊነት ስሜት በሚያሰባስቡት ገንዘብ ህፃናትን ይደግፋሉ፤ የጃውሳው ሰዎች ደግሞ ለሽብርና ጥፋት በስሙ በሚነግዱበት የአማራ ሕዝብና የአብራኩ ክፋይ የሆኑ ታዳጊዎችና ህፃናት የነገ ተስፋ እንዲጨልም ሳይታክቱ ለሽብር ይሠራሉ።

በርግጥ ጃውሳው ዓላማ የለሽ የዘራፊዎች ስብስብ ስለሆነ ይህን እኩይ ድርጊት ማሰቡም ሆነ መፈፀሙ አይገርምም። የጤና ባለሙያዎችን፣ መምህራንን፣ የኮንስትራክሽን ሠራተኞችን፣ ተማሪዎችን እና እግር ኳስ ተጫዋቾችን እየመረጡ ማገት፣ መግደል፣ መዝረፍ ከባህሪያው የሚመነጭ የሽብር ድርጊት ነው፡፡

የክልሉን አርሶ አደር እንስሳት እየዘረፉ አርደው መብላት፣ እህሉን እየቀሙ ቀለብ ማድረግ፣ ማዳበሪያ፣ መድሃኒት እና ለተጎጂዎች የርዳታ እህል እንዳይቀርብ ማስተጓጎል የጃውሳው የዘወትር መገለጫ ነው። ይህም ብቻ ሳይሆን በክልሉ ወጣቶች ሠርተው እንዳይለወጡ ሰላም በማሳጣት ህልማቸውን እያጨናገፈ ነው።

ጉዳዩ እዚህ ድረስ አዋራጅና አሳፋሪ ሆኖ እያለ ነው እንግዲህ እጅግ የዘቀጠና ቅጥ ያጣ የጃውሳው ነውረኛ ተግባር በባንዳዎቹ ሚዲያዎች እና አንዳንድ “አንቂ ነን” ባዮች ጃውሳዎቹን “ጀግኖቻችን” ያስባላቸው፡፡

የጃውሳውን ጥፋትና ክህደት ሕዝቡ ከበቂ በላይ ተረድቶታል፤ የሚያደርሰውንም እኩይ ተግባር በበቂ መጠን ተገንዝቧል። ለዚህም ነው ከሕዝቡ የተውጣጣው ሚሊሻና የፀጥታ ሃይል በሽብር ቡድኑ ላይ ርምጃ በመውሰድ ወደ መበታተንና ተራ ሽፍትነት እንዲወርድ እያደረጉት ያለው።

እናም የጃውሳው ጉዳይ “ንጉሥ ሆይ እርቃንዎትን ነዎት” እንደተባለው የድሮ ዘመን የንጉሥ ታሪክ፣ ጃውሳው ዛሬ እርቃኑን ቀርቷል፡፡ የባንዳዎቹ ፕሮፖጋንዳ ሌላ፣ መሬት ላይ ያለው ሀቅና እውነታ ለየቅል ሆኗል፡፡

የክልሉን መንግሥት በሃይል ለመገልበጥ የተደረጉ ሙከራዎችም ሆኑ የ “ኪሎ ፖለቲካ” ህልሞች ከሽፈዋል ብቻ ሳይሆን ቅዠት ሆነዋል።፡ በሁከት እና በሴራ ፖለቲካ ሕዝብ እያሸበሩ በሚፈፀሙ ጥፋቶች የትኛውንም ግብ ማሳካት እንደማይቻልም የጃውሳው ተሞክሮ ትምህርት ሰጥቶ አልፏል፡፡

አበው ያወረሱት ሽምግልና ምክክርና እርቅ የቆየ ባህሉ የሆነው የአማራ ሕዝብ፣ እኔ አውቅልሃለሁ ባዮቹ ጃውሳዎች እንደሚሉት ሳይሆን መሠረታዊ ጥያቄዎቹ እንደሌሎቹ ወገኖቹ ሁሉ በውይይትና በትብብር ብቻ መፈታት እንዳለበት ከተገነዘበ ውሎ አድሯል፡፡ ሕዝቡ በተለያዩ መንገዶችም በተደጋጋሚ ይህንኑ ፍላጎቱን በአደባባይ ገልጧል፡፡

የራሱን አካባቢ ሰላም በራስ አቅም ለመጠበቅ የሚደረገውን እንቅስቃሴ ደግፎም በጽናት ቆሟል፡፡ እውነት በሰላማዊ ምክክር ብቻ እንደሚገኝ በመገንዘብ ሰላምን የሚያረጋግጥ አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት ግንባታ ምዕራፍን በንቃት ጀምሯል፡፡

በምክክር ኮሚሽኑ አማካይነት ሰሞኑን የተካሄደው እና ሁሉንም የክልሉ አካባቢዎችና የማህበረሰብ ክፍሎችን በነቂስ ያሳተፈው የአማራ ክልል የመጀመሪያ ምዕራፍ የምክክር አጀንዳ ማሰባሰብ ሥራ በስኬት መጠናቀቅ ለዚህ ጉልህ ማሳያ ነው፡፡

የአማራው ሕዝብ፣ ይህ የመጀመሪያ ምዕራፍ የምክክር ሂደት የቱ እንደሚበጅ አረጋግጦ በግልፅ ለጃውሳው “በቃህ!” የሚል መልዕክት ያስተላለፈበትም ጭምር ነው። “ለብልህ አይነግሩ ለአንበሳ አይመትሩ!” እንዲሉ አበው።

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 4 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You