ተቋሙ በቴክኒክና ሙያ የሠለጠኑ ወጣቶችን ወደ ሥራ ማሠማራቱን ገለፀ

አዲስ አበባ፡- የካቶሊክ የገዳማት ጥምረት ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት እንዲሁም ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር በክህሎት ሥልጠና የተመረቁ ወጣቶችን ከ70 በላይ ቀጣሪ ድርጅቶች ጋር ለሥራ ቅጥር ማገናኘቱን ገለፀ::

የተቋሙ ከፍተኛ ባለሙያ ዲና መኮንን በተለያዩ መስኮች የተሰጣቸውን ትምህርትና የክህሎት ሥልጠናዎችን አጠናቅቀው የተመረቁ አንድ ሺህ ተማሪዎችን ከ70 በላይ አሠሪ ድርጅቶች ጋር በማገናኘት ሥራ እንዲቀጠሩ በማድረግ ሀገራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ ተናግረዋል::

ባለሙያዋ እንደገለፁት፤ የካቶሊክ የገዳማት ጥምረት ተቋም ላለፉት ሰባት ዓመታት ከትምህርት ሚኒስቴር፣ ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ ከዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም ከመንግሥት ተቋማትና እና ከግል ድርጅቶች ጋር በመሥራት ላይ ይገኛል::

የገዳማቱ ጥምረት ከህዳር 2020 ጀምሮ ከ ‹ግሎባል ሶሊዳሪቲ› በተገኘው የገንዘብ ድጋፍ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ጠቁመው፣ የሥራ ገበያን በማጥናት ገዳማቱ ባላቸው የቴክኒክና ሙያ ማሠልጠኛ ኮሌጆች ተማሪዎችን በተለያዩ የሙያ ዘርፎች አሠልጥኖ ከቀጣሪ ድርጅቶች ጋር የማገናኘት ሥራ እንደሚሠራ ገልፀዋል::

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የጳጳሳት ጉባዔ ፕሬዚዳንት ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ፤ በልዩ ልዩ ሥልጠናዎች የተመረቁ ወጣቶችን ከቀጣሪ ድርጅቶች ጋር በማገናኘት የተሠራው ሥራ ትልቅ ኃላፊነት ስለሆነ ወደፊትም መበረታት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል::

‹‹ሀገራችን ኢትዮጵያ ከናይጀሪያ ቀጥሎ ትልቅ ሕዝብ ያላት እና በኢኮኖሚም ቢሆን ያጋጠማትን ችግር እያለፈች ወደ ፊት እየተራመደች ያለች ሀገር ናት፤ በፀሎት በኅብረት እና በመከባበር ሰላምን ካሰፈንን ለአፍሪካ ቀንድ ምሳሌ የምትሆን ሀገር ነች›› ብለዋል::

በተጨማሪም ‹‹ማንኛውንም ሥራ ዝቅ ብለን በሀገራችን ከሠራን ከፍ ያለ ቦታ ላይ እንደርሳለን:: በርካታ ሰዎች ከቀን ሥራ እና ጫማ ከመጥረግ በመነሳት ተቋም መሥርተው ሌሎችን እየቀጠሩ በማሠራት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሰዋል›› በማለት ይህም ለሌሎች አርዓያ እንደሚሆንና በዚሁ መንፈስ መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል::

ሔርሞን ፍቃዱ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 4 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You