140 ካሬ ሜትር ተለዋጭ ቦታ እንዲሰጣቸውም አቅጣጫ ተቀምጦ እንዳልተጠቀሙበት ተጠቆመ
አዲስ አበባ፡- በለገጣፎ ከተማ ከመሬት ወረራና ሕገወጥ ግንባታ ጋር በተያያዘ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ማንነትን መሰረት ያላደረገና ሕገ ወጥነትን የመከላከል ስራ ብቻ መሆኑን የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ገለጸ። የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አድማሱ ባንቴ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፣ በአንዳንድ ማህበራዊ ሚዲያዎች የሚናፈሱ መረጃዎች እውነት ካለመሆናቸው ባሻገር ሆን ተብሎ የክልሉን ገጽታ ለማጠልሸት የሚደረጉ ናቸው። የሚወሰደውን እርምጃ ተከትሎ በአሰራር የተፈጠረ ችግር ካለም ቅሬታ የሚቀርብበትና የማጣራት ስራ የሚሰራ ኮሚቴ የክልሉ መንግስት ያቋቋመው መሆኑን ጠቁመዋል።
በለገጣፎ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞችም ተመሳሳይ እርምጃ እየተወሰደ ነው ያሉት ኃላፊው፣ያለውን ውስን ሀብት በህጋዊነት እኩል ለመጠቀም የተጀመረው በሕጋዊ መንገድ ህግን የማስከበር ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።ከማንነት ጋር የማይያያዝ ህግ የማስከበር ስራ መሆኑንም አመልክተዋል። ኃላፊው እንዳብራሩት ከመሬት ወረራና ሕገ ወጥ ግንባታ ጋር በተያያዘ ሕግን መሰረት ባደረገ መልኩ ህግ የማስከበር ስራ እየተሰራ ያለው ከ2006 ጀምሮ መሆኑን አስታውሰው፣ በለገጣፎ ብቻ ሳይሆን ከዚህ በፊትም በቡራዮ ከ700 በላይ እንዲሁም በመቱ ከ611 በላይ ሕገወጥ ግንባታዎች እርምጃ ተወስዶባቸዋል ።
ይህም እየተደረገ ያለው ./በመጀመሪያ ሕገወጥነትን በመከላከል የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ሲሆን፣ ሁለተኛም ከመሬት ወረራና ሕገ ወጥ ግንባታ ጋር በተያያዘ ሕብረተሰቡ ‹‹ሕገወጥ ግንባታ ተስፋፋ፡ አርሶ አደሩ እየተፈናቀለ ነው›› በማለት በተደጋጋሚ ሲያነሳቸው የነበሩ ቅሬታዎችን መሰረት በማድረግና ጥናት በማካሔድ፣ የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥና የከተሞችን እድገት በፕላን መሰረት በማድረግ ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር ለማስቻል እንደሆነ ገልጸዋል። በለገጣፎ የፈረሱት ቤቶች አንዳንዶቹ ቦታዎች እንደ ጤናና ትምህርት ቤት ለመሳሰሉ ማህበራዊ አገልግሎቶች እንዲውሉ መንግሥት ካሳ የከፈለባቸው ሲሆኑ፣ ቀሪዎቹ ደግሞ ህጋዊ ሰነድ የሌላቸው ናቸው። ይሄም ሆኖ ወደ ማፍረስ ከመገባቱ በፊት የተለያዩ እርምጃዎች ተወስደዋል የሚሉት ኃላፊው።
ጉዳዩ በ2005 በወጣው የሊዝ አዋጅ ከሰባት እስከ አስራ አምስት ዓመት እስራትና መቀጮ የሚያስከትል ቢሆንም ወደዚህ ከመገባቱ በፊት የማወያየት፡ ማስጠንቀቂያ የመስጠትና ህገወጥ ግንባታ አከናውነው ለሚፈረስባቸው መፍትሄ ለመስጠት 140 ካሬ ሜትር ተለዋጭ ቦታ እንዲሰጣቸውም አቅጣጫ የተቀመጠ ቢሆንም፣ በወቅቱ መረጃዎቹን የሚያቀርብና ፈቃደኛ ሆኖ የሚያፈርስ ባለመኖሩ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ህግን መሰረት ያደረገ ሕገወጥነትን የመከላከል እርምጃ ተወስዷል ብለዋል። ‹‹በህጋዊ መንገድ ከአርሶ አደሩ ገዝተን ነው የሰራነው። ሕጋዊ ካልሆነ በወቅቱ ስንሰራ መንግስት ለምን አላስቆመንም›› የሚል ቅሬታ ከተነሺዎች ይቀርባል በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ኃላፊው በሰጡት ምላሽ፣ መሬት የመንግስትና የህዝብ ነው።
ሕገወጥ ስራ ሰርቶ በህጋዊ መንገድ መጠየቅ አይቻልም። መሬት ሊተላለፍ የሚችለው አንደኛ በሊዝ በጨረታ ሲሆን ሁለተኛው ለመኖሪያም ሆነ ለአርሶ አደሩ በምደባ ነው። በመሆኑም ከዚህ ውጪ የሚከናወኑ የመሬት ግዠና ሽያጭ ሕገ ወጥ መሆናቸው አመልክተዋል። በወቅቱ እርምጃ ላለመወሰዱም በተመለከተም፣ የክልሉ መንግሥት እንደዚህ አይነት ህገወጥ ድርጊቶች እንዲፈፀም ያደረጉና መከላከል እያለባቸው ያልተከላከሉ አመራሮችንና አባላቱን ከተሀድሶ ወዲህ ከ7 ሺ በላይ በመለየት ግማሹ እንዲባረሩ ቀሪዎቹም በህግ እንዲጠየቁ ማደረጉን በማስታወስ፣ አሁንም በየከተሞቹ ባለሙያዎች መሀንዲሶች በቁጥጥር ስር እየዋሉ በህግ የሚጠየቁት በህግ እየተጠየቁ አስተዳደራዊ እርምጃ የሚወሰድባቸውም እየተወሰደባቸው እንደሆነ ገልፀዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 16/2011
ራስወርቅ ሙሉጌታ