የሀዋሳው የኢ.ህ.አ.ዴ.ግ. 11ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ ያስተላለፋቸውን ውሳኔዎችና ያካሄደውን ምርጫ የኢትዮጵያ ህዝብ በሙሉ በከፍተኛ ደስታና እልልታ ተቀብሎታል። እጅግ በጣም ታላቅና ታሪካዊ ውሳኔና ምርጫ ነው። ጉባኤው እንደሚካሄድ ከተነገረ ጊዜ ጀምሮ አብዛኞቻችን ሥጋት ነበረን። ሁላችንም የዶ/ር አብይ አህመድን መጨረሻ በጉጉት ጠብቀናል። እርሳቸው እንዳይመረጡ የሚያደርጉ ሥራዎች በፀረ ለውጥ ኃይሎች ሊፈጸሙ እንዳይችሉ ፀልየናል፡፡ ጉባኤው በሰላም በመጠናቀቁና ህዝቡ የሚያምንባቸው መሪዎች በመመረጣቸው ደስታውና እፎይታው ወደር የለውም። እርሳቸው ባይመረጡ ኖሮ ሊደርስ የሚችለውን ችግር ከወዲሁ ማሰብ ይከብዳል። በጉባኤተኛው ንቁ ተሳትፎ፣ በህዝቡ ድጋፍና በፈጣሪ ድጋፍ መመረጣቸው ጉባኤውን ታሪካዊ አድርጎታል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ የተገኘውን አገራዊ ለውጥ ለማስቀጠል ለሚወጡ አቅጣጫዎች ተግባራዊነት በጋራ መረባረብ እንደሚገባ አስታውቋል። ባለፉት 6 ወራት ብቻ እጅግ ግዙፍ የሆኑ ለውጦች ተመዝግበዋል። በዲፕሎማሲ፣ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና በማህበራዊ ዘርፎች ከፍተኛ ለውጥ እየተደረገ ባለበት ወቅት ጉባኤውና ምርጫው መካሄዱ የሀዋሳውን ጉባኤ ታሪካዊ ያደርገዋል። ጉባኤው የአገራችን የውስጥ ፖለቲካዊ መረጋጋት አደጋ ላይ ወድቆ የነበረውን የአገራችንን ህልውና የታደገ መሆኑ ተረጋግጧል። የፖለቲካ ምህዳሩም እየሰፋ ይገኛል። ምህዳሩ ጠባብ በነበረ ጊዜ ተዘግተው የነበሩና በስደት ሆነው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የዜና አውታሮችና ድረ-ገፆች በሙሉ ተከፍተዋል። ወደ አገር ውስጥ መግባት ብቻ ሳይሆን እስከ ቤተመንግሥትና የጉባኤ አዳራሾች ተገኝተው ሂደቶችን እንደወረደ ለማሰራጨት ችለዋል። አፋኝ የተባሉ ህጐች እንዲሻሻሉ ጥረት እየተደረገ ነው።
በሰብዓዊ መብት አያያዝ ረገድ ችግር የነበረባቸውን የፀጥታና የህግ አስከባሪው ተቋማትን የህዝብ አገልጋይ ለማድረግ እየተሠራ ነው። የመንግሥት አስተዳደር ሲቪል ሰርቪሱ ለህዝብ አርኪ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ለማድረግ የሪፎርም ማስተካከያና ለውጥ እንደሚደረግ አቅጣጫ ተቀምጧል። እነኝህ ሁሉ ሥራዎች የተሠሩት በኢ.ህ.አ.ዴ.ግ. በኩል ቢሆንም የዶ/ር አብይ የተለየ ሚና ወሳኝ የነበረበት ነው። እንደ ድርጅት በቡድን ቢሠሩም እንደ ግለሰብ ደግሞ መሪዎች የሚጫወቱት የራሳቸው ድርሻ አለ። የግላቸው ስብዕና አለ። ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት አለመግባባቶችን አለሳልሶ በመግባባት የቅርቡንም የሩቁንም በፍቅር ወደ መደመር የመጥራት ከመገፋፋት ይልቅ ወደ መደጋገፍና መተቃቀፍ የማምጣት ብልሃት ትዕግስትም አርቆ አስተዋይነት ዋናው የመንግሥትነት ግብዓት ነው። ይህም በዶ/ር አብይ አመራር ስብዕና ውስጥ የተረጋገጠ ነው። ህዝቡም ይህ ከፈጣሪ የተሰጠ ፀጋ ነው ብሎ ያመነው ከሥራቸውና ካስገኙት ውጤት በመነሳት ነው።
መሪ ለመሆን እንደ ዶ/ር አብይ ጠንካራ ሠራተኛ መሆንን ይጠይቃል። የሰሞኑን ሥራቸውን በምሳሌነት እንጥቀስ። ከመስከረም 23 /ረቡዕ ጀምሮ እስከ 25 ድረስ በጉባኤ ስብሰባቸው ላይ መቆየት፣ መስከረም 26 ዋናው የጉባኤ ማጠናቀቂያ ላይ በሀዋሳ ዓለምአቀፍ ስታዲየም መገኘት፣ መስከረም 27 የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ምረቃ ላይ መገኘት መስከረም 28 በሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ መክፈቻ ላይ መገኘት፣ ሳምንቱን ሙሉ ያለ እረፍት መሥራት ልዩ ብርታት ካላቸው መሪዎች ብቻ የሚገኝ ነው። የእርሳቸው መመረጥ ለኢትዮጵያ ብስራት፣ ኩራትና ተስፋ ነው። ሁለቱ የኦርቶዶክስ ሲኖዶሶች መታረቅ የኢትዮ- ኤርትራ ሰላም መረጋገጥ በዶ/ር አብይ የላቀ ብስለትና አርቆ አስተዋይነት የተገኙ ድሎች ናቸው፡፡ ለዚህም ልባዊ ክብር እንሰጣለን ወደፊትም በዚሁ ትጋታቸው እንደሚቀጥሉ እምነታችን ጽኑ ነው።
ጉባኤው ለአገር ሰላም መከበርና ለህግ የበላይነት መረጋገጥ ትልቅ ትኩረት ሰጥቷል። ሰላም ከሌለ ህዝቡ ወጥቶ መግባት አይችልም። ልጆቹን ማስተማር ይቸግረዋል። በገዛ አገሩ እንደልቡ ተዘዋውሮ ሠርቶ ለመብላትና ሀብት አፍርቶ ትዳር መስርቶ ጐጆ ቀልሶ ለመኖር ያቅተዋል። ይህን ችግር ለመፍታት መንግሥት አቋም ወስዷል። ሠርቶ በማትረፍ እንጂ በመዝረፍ አይሆንም ብሏል። ማንም ከህግ አግባብ ውጪ እንደልቡ የሚፈነጭባት አገር እንደማትሆን አቅጣጫ አስቀምጧል። የሰላም መጥፋት የአገሪቱን የቱሪዝም ልማት ዘርፍ ያስተጓጉላል፤ ኢትዮጵያ የቱባ ባህል፣ የበርካታ ቋንቋዎች፣ እምነቶች፣ ጥንታዊ ቅርሶች ባለቤት ናት ቱሪስቶች ከመላው ዓለም መጥተው የሚጐበኟት አገር ናት ከዚህ ዘርፍ የሚገኘው ገቢም ለአገሪቱ እድገት ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ነው። ለዚህ ሁሉ ዋና መሠረቱ ሰላም ነው። ለሰላም መከበር ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ. በጉባኤው ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ሁላችንም እንደ ህዝብ አንድ ሆነን በጋራ ከመንግሥት ጐን ቆመን ለውጡን ለማስቀጠል መረባረብ አለብን።
እንደ እውነቱ ከሆነ ባለፉት 6 ወራት ለተገኙት አስደናቂ ውጤቶች እንደ መሪ የዶ/ር አብይ አስተዋጽኦ ታላቅ መሆኑን ምስክሮች ተሰጥተዋል። የህወሓቱ ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በጉባኤው ላይ የተናገሩትን መጥቀስ ይቻላል። «… በለውጡ ለተመዘገቡ አስደናቂ ውጤቶች ዶ/ር አብይ እንደ መንግሥት መሪ የራሱን ፈጠራ፣ ድፍረት፣ ጥበብና ሁለንተናዊ የአመራር ብቃት ተጠቅሞ ያመጣው ለውጥ ነው። ለዚህም ተገቢውን እውቅናና ክብር መስጠት ያስፈልጋል» ብለዋል። ትልቅ ምስክርነት ነው። በዚህ የዶ/ር አብይ አመራር በአገራችን የፖለቲካ መረጋጋት ተፈጥሯል። ይህም ለህዝቡ ትልቅ እፎይታ ነው። ስብሰባው /ጉባኤው/ እስኪጠናቀቅ ድረስ እያንዳንዱን ቀን ምን ተፈጥሮ ይሆን?» እያልን የተጨነቅንበት ሁኔታ ነው የነበረው፡፡ ነገር ግን በሚያስገርም ሁኔታ ያለምንም ኮሽታና ፍንዳታ፣ ያለአንዳች የፀጥታ ችግር መጠናቀቁ ከፍተኛ አግራሞት የፈጠረ ነው። ጨዋ ህዝብ ማለት ይህ ነው።
ጨዋ ህዝብ አለን ጨዋ መሪም አግኝተናል የሀዋሳው ጉባኤ ማጠናቀቂያ ማግስት በአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ምረቃ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ስለ ዶ/ር አርከበ እቁባይ የሰጡትን ምስክርነት ሰምተናል። «አርከበ የፖለቲካ አሻጥር የማይነካካው በሳምንት ሰባት ቀን የሚሠራ በሥራ ብቻ የሚያምን ብርቅዬ ኢትዮጵያዊ ነው» ከዚህ በላይ ምስክርነት ከየት ይመጣል? ይህ የሠራ ይከበር የሚል አቋም ካለው ጨዋ መሪ አእምሮ የሚመነጭ ነው። ይህን እንኳ እኛ ሩቅ ሆነን በሚዲያ የሰማነው ሰዎች ዶ/ር አርከበ እራሳቸው የጠበቁት ነገር አይመስልም፡፡ 148 ሚሊዮን ዶላር በፈጀውና ሥራውን ሲጀምር በዓመት 38 ሚሊዮን ዶላር ለአገራችን ያስገኛል ተብሎ በሚጠበቀው ግዙፍ ፕሮጀክት የምረቃ ሥነሥርዓት ላይ በዚህ ሁሉ ታዳሚ መሃል በዓለም ሚዲያዎች በሙሉ በሚዳረስ ስርጭት ይህን ያህል ምስክርነትና ምስጋና ሲሰጥ የዶ/ር አብይን ምንነትና የዶ/ር አርከበ አርአያነት በግልጽ ያሳየ የታላቅ መሪ መገለጫ ነው። የሠራ ይከበር ማለት እንዲህ ነው። ህዝቡ ሁሉ አገር ምድሩ ተደስቷል። ለዶ/ር አርከበ ይገባዋል ያላለ ሰው አላጋጠመኝም፡፡ አርከበ በህዝብ ዘንድ የሚወደዱ ሥርዓት ያላቸው ሰው መሆናቸውን መላው የኢትዮጵያ ህዝብ መስክሮላቸዋል። ዶ/ር አብይ የሠራን እንዳከበሩ ፈጣሪ ያክብራቸው ክብርን የሰጠ የበለጠ ክብር ያገኛል። ጥላቻን የዘራም የስብዕና አረሙን ያጭዳል፡ ሁሉም የሥራውን ያገኛል።
የሠራ ይከበር አርአያነት የእኛም ኃላፊነት ሆኖ የሚቀጥል ነው፡፡ በሳምንት ሰባቱንም ቀን የሚሠራ፣ የሚከፈለውን ያህል ብቻ ሳይሆን ከሚከፈለው በላይ የሚሠራ፣ ሌብነትን የሚፀየፍ፣ ብልሹና መጥፎ አሠራርን የማይሸከም ትውልድ እንደሚያስፈልጋት የተገለጸበት ጭምር ነው። አሁን መሬት ላይ ያለው ችግራችን ከሚከፈለው በላይ የሚሠራልን ሳይሆን ወይም የሚከፈለውን ያህል ብቻ የሚሠራ ሳይሆን ችግራችን ከሚከፈለው በታች የሚሠራው ዜጋ መብዛቱ ነው። በሥራ ሰዓት አይገቡም። ሥራ ላይ አይገኙም፣ በወሬ የሚያባክኑት ጊዜ ይበልጣል። በተለይ ከሰዓት በኋላ የቢሮ ጠረጴዛዎች በሙሉ ባዶ ናቸው። «ሠራተኛ» ተብለው የተመደቡት ልጆችም ስለሥራውም ሆነ ስለህዝብ መስተንግዶ የሚያውቁት ነገር የለም። «እርስዎ» እና «አንተ» የሚባለውን የአክብሮት ቃላት አይለዩም። ከተቀላቀሉት ማህበረሰብ ባህልና ልማድ ጋር ራሳቸውን ለማግባባት አይተጉም። ተቀዳሚው ተጠቃሚ ደግሞ እነሱ ናቸው። ጉቦው ይቅርና አንድን ጉዳይ ለማስፈጸም እነሱን «እባክሽ ልጄ-ልጄ» ሲሉ መዋል ያስመርራል። በተለይ በወረዳ ደረጃ ላሉ አደረጃጀቶችም ሆነ ሠራተኞች ሪፎርም የግድ አስፈላጊ ነው። ለዚህም መንግሥት አቅጣጫ አስቀምጧል።
በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት የተጀመረውን ተስፋ ሰጭ ለውጥ ለማስቀጠል በጋራ መረባረብ አለብን። ኃላፊነቱን በመሪዎቻችን ትከሻ ላይ ብቻ ጥለን የምንሄድ ከሆነ ወደ ግባችን አንደርስም መሐል መንገድ ሳንደርስ እንቀራለን። መሪዎች ባስቀመጡት አቅጣጫ የየበኩላችንን የሥራ ድርሻ መወጣት አለብን። ሰላምን መስበክ አለብን። ችግሮች ቢኖር ሥርዓት ባለው ጨዋ አቀራረብ መጠቆምና መፍትሔዎችን ማመላከት አለብን። ምንጫቸው የማይታወቁ አሉባልታዎችን፣ ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩ አሉባልታዎችን በየፌስቡኩ ላይክ /ሼር/ ከማድረግ እንቆጠብ ። ለምናደርገውና ለምንናገረው ነገር ሁሉ ምክንያታዊ እንሁን።
በመጨረሻም ስለፌዴሬሽንና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዓመታዊ የጋራ ስብሰባ ጥቂት እንበል ስብሰባው በሕገ መንግሥቱ መሠረት የተካሄደ ነው። የተወካዮች ምክር ቤት የሥራ ጊዜ ከመስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት ሰኞ ይጀምራል፡፡ /አንቀጽ 58/ ፕሬዚዳንቱ ይህን የጋራ ስብሰባ በንግግር ይከፍታሉ። /አንቀጽ 71/። በዚህ መሠረት መስከረም 28 ቀን 2011 ዓ.ም ሰኞ ዕለት ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ስብሰባውን በንግግር ከፍተዋል። ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው የዓመቱን የመንግሥት እቅድ አቅጣጫዎች አስቀምጠዋል። በዋነኛ ከተጠቀሱት መካከል የእያንዳንዱ ዜጋ ደህንነት ነፃነት ማስከበር የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት የፀረ ሽብር አዋጅ የሲቪክ ማህበራትና የበጐ አድራጐት አዋጅ የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ እና ሌሎችም የማሻሻል ሥራ ማጠናቀቅ ለወጣቱ ክፍል ከተቀረጸው የሥራ ፈጠራ መርሐ ግብር ጐን ለጐን የኢኮኖሚ ምህዳሩን ማስፋትና ተጨማሪ ኢንቨስትመንትን መሳብ መንግሥታዊ አካላት ግልጽ ዓላማ ያላቸው በቅንጅት የሚሠሩ ውጤታማና ወጪ ቆጣቢ ለማድረግ ተገቢውን ማሻሻያ ማድረግ ወዘተ… ናቸው።
በእኛም በኩል መንግሥት ያስቀመጠውን አቅጣጫ ተከትለን ለውጡን ለማስቀጠል መረባረብ አለብን። ዕቅዱ የኛ ነው! ፈጻሚዎቹም እኛ ነን! ተጠቃሚዎቹም እኛ ነን። ፈጣሪ አገራችንን ይባርክ! መልካም የሥራ ጊዜ ለሁለቱ ምክር ቤቶች ይሁን!!
ግርማ ለማ