ጃፓን ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ እድገት የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ ትቀጥላለች

አዲስ አበባ፦ ጃፓን ለኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ኢኮኖሚያዊ እድገትና ሰላም የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ ትቀጥላለች ሲሉ በኢትዮጵያ የጃፓን ኤምባሲ አምባሳደር ሺባታ ሂሮኖሪ ገለጹ።

በኢትዮጵያ የጃፓን ኤምባሲ በሲዳማና በትግራይ ክልል ለሚከናወኑ ሁለት ፕሮጀክቶች 144 ሺህ 851 ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉንም ገልጸዋል።

በወቅቱ በኢትዮጵያ የጃፓን ኤምባሲ አምባሳደር ሺባታ ሂሮኖሪ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ እና ጃፓን የ 100 ዓመታት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት ናቸው። በእነዚህ ዓመታት ጃፓን ከኢትዮጵያ ጋር በትምህርት፣ በጤና፣ በውሃ አቅርቦት፣ በግብርና፣ በአምራች ኢንዱስትሪ እና በሌሎችም ዘርፎች በትብብር ስትሠራ ቆይታለች።

እነዚህም በኢትዮጵያ ሰላምና ኢኮኖሚ ላይ የነበራቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው፤ ጃፓን ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ እድገትና ሰላም የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።

ይህንንም በይበልጥ ለማጠናከር ኤምባሲው በሠብዓዊ ርዳታ ፕሮግራሙ በኩል በሲዳማ ክልል በይርጋለም ከተማ አንድ ትምህርት የማስፋፊያ ግንባታ ሊያካሂድ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህም በ “የካቲት 25” አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ማሻሻያ ፕሮጀክት ስር የሚከናወን ነው። በዚህም አራት ክፍሎች የተሟላ የትምህርት ቁሳቁስ እንዲኖራቸው ይደረጋልም ብለዋል።

ፕሮጀክቱ ለአንድ ሺህ 800 ተማሪዎች የተሻለ እና ደህንነቱ የተጠበቀ የትምህርት እንዲያገኙ ለማስቻል እንደሆነ ገልጸው፤ ከዚህ በተጨማሪ በትግራይ ክልል በመቀሌ ከተማ ፆታዊ ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች መጠለያ ሊገነባ መሆኑንም ገልጸዋል። ይህም 150 ሴቶች ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

በአጠቃላይ ለሁለቱ ፕሮጀክቶች ጃፓን 144 ሺህ 851 የአሜሪካን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ማድረጓን ተናግረው፤ እ.እ.አ ከ1989 ጀምሮ ጃፓን በመላው ኢትዮጵያ ከ450 በላይ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ አድርጋለች ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ የጥሩ ጎሮቤት በጎ አድራጎት ድርጅት ዳይሬክተር ዮዩንሱ ኪም በበኩላቸው፤ ድርጅቱ በኢትዮጵያ እ.እ.አ ከ1997 ጀምሮ የበጎ አድራጎት ሥራውን መጀመሩን ገልጸው ፤አሁን ላይ በአሶሳ፣ በትግራይ፣ በምዕራብ ጉጂ፣ በጅግጅጋ እና ሲዳማ የበጎ አድራጎት ሥራውን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

የጃፓን ኤምባሲ የገንዘብ ድጋፍ ያደረገበት እና በሲዳማ ክልል በይርጋለም ከተማ የሚገነባውን ማስፋፊያ ትምህርት ቤት በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ገንብቶ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

የትግራይ ክልል ሴቶች ማህበር ዳይሬክተር አበባ ኃይለሥላሴ በበኩላቸው፤ በትግራይ ክልል በጦርነቱ ወቅት ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ቁጥር በርካታ መሆኑን ገልጸው፤ ጥቃት ለደረሰባቸውን ሴቶች መጠለያ ለመገንባት የሚያስፈልገውን በጀት የጃፓን ኤምባሲ በኢትዮጵያ ድጋፍ በማድረጉ አመስግነዋል።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 4 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You