‹
«ጀግናው መከላከያ ሠራዊታችን በዘመናት ሁሉ ያጋጠሙትን የውጭም ሆነ የውስጥ ሉዓላዊነት ፈተናዎች በከፍተኛ ወኔና ቁርጠኝነት የተወጣ የአገር መከታና አለኝታ የሆነ ተቋም ውስጥ በማገልገላችሁ ኩራት ሊሰማን፤ ሊሰማችሁ ይገባል»።ይህን ያሉት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትርና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዶክተር አብይ አህመድ ሰባተኛው የመከላከያ ሠራዊት ቀን በአዳማ ሲከበር ነው፡፡ ይህን ያሉበት ዋናው መነሻ የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር ሙያዊ ብቃት የተላበሰ (ፕሮፌሽናል) ሠራዊት ለመገንባት በለውጥ ላይ በመሆኑና የተሳካ ሥራ እየሠራ እንደሆነ ለማመላከት ነው፡፡
እውነት ነው ጀግና ሠራዊት ባለበት ተቋም ማገልገል ኩራት ነው!
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ከፖለቲካ ወገንተኝነት በጸዳ መልኩ ግዳጁን የሚወጣ፣ ሙያዊ ብቃት ያለው ሠራዊት ለመገንባት ከፍተኛ የሪፎርም ሥራ ላይ ያለ ተቋም ነው፡፡ መከላከያ ሠራዊቱን ለማዘመንና በሙያ ከማብቃት ጎን ለጎን የሀገራችን ወጣቶች የሠራዊቱን ዘመናዊ ተቋማት ግንባታና የቴክኖሎጂ ልህቀት ማእከል የመሆን እርምጃ ማገዝ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለዚህ ይሆን ዘንድ በቅርቡ ወጣት መኮንኖችን ማፍራት እንዲቻል የመከላከያ ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ ማሻሻያ ተደርጓል፡፡ ይኸውም ከዩኒቨርሲቲ የሚመረቁ ወጣቶችን ተቀብሎ በመኮንንነት አሰልጥኖ ለመቅጠር የሚያስችል ነው፡፡ ይህ ሂደት ፕሮፌሽናል ሠራዊት ለመገንባት መንግሥት ለያዘው ቁርጠኛ አቋም እጅግ አስፈለጊ ነው፡፡ ወታደርነት ተመርጦ የሚገባበት ሙያ እንዲሆን፣ ሥርዓት በተለወጠ ቁጥር የማይለወጥና በህዝብ ምርጫ አሸናፊ ሆኖ ከመጣ ፖለቲካ አመራር ጋር ለህዝብና ሀገር ጥቅም የሚሠራ ሊሆን ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ ሙያውን የሚያከብር፤ ለሀገር ተቆርቋሪና ለህገ መንግሥቱ ታማኝ መሆን ይጠበቅበታል፡፡
በዓለም አቀፍ አሰራር አንድ ሠራዊት ፕሮፌሽናል ሠራዊት ነው የሚባለው ለህገ መንግሥትና ለህዝብ ታማኝ ሲሆን፣ ግዳጅን በከፍተኛ ኃላፊነትና ብቃት መወጣት ሲችል፣ ለህዝብና ለሀገር አክብሮት ሲኖረው፣ ከግሉ ይልቅ የሀገርና የህዝብ ጥቅምን ሲያስቀድም፣ ለመለዮው ክብር ሲሰጥ፣ በሃቀኝነት መሥራት ሲችልና በወሳኝ ወቅት አደጋን ለመቀነስ ያለፍርሃት ግዳጁን ለመወጣት በአካልና በሞራል ጠንካራ ሲሆን ነው፡፡ ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሙሉእ ነው ሊባል አይችልም፡፡ ነገር ግን አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በርካታ መሻሻሎች እያሳየ ፕሮፌሽናል ሠራዊት ለመሆን በሂደት ላይ ያለ ሠራዊት ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡
ሠራዊቱ በእስካሁኑ ሂደት የተጣለበትን ኃላፊነት በቁርጠኝነት እየተወጣ ነው፡፡ የሀገርና የህዝብ ሰላም ለመጠበቅ የሚሠራቸው ሥራዎች፣ በተለያዩ ቦታዎች ተከስተው በነበሩ
አለመረጋጋቶች ሳቢያ ሀገር እንዳትፈርስ መከላከል የቻለ ሠራዊት ነው፡፡ ይህ ሆኖ በግዳጅ አፈጻፀሙ የሚነሱበት ቅሬታዎች የነበሩ ቢሆንም ከለውጡ በኋላ በአካሄደው ሪፎርም ሥራ ግን ከፍተኛ ለውጥ አምጥቷል፡፡ ይህ ሠራዊቱ ፕሮፌሽናል ሠራዊት ለመሆን የጀመረው ጉዞ በትክክለኛ ጎዳና መሆኑን አመላከች ነው፡፡ ለጠላቶቹ የፍርሃት ለወዳጆቹ ደግሞ የኩራት ምንጭ እየሆነ መምጣቱንም ማሳያ ነው፡፡
ሠራዊቱና ተቋሙ ህገ-መንግሥታዊ ተልኮውን በመወጣት የአገሪቱን ሰላምና የህዝቡን ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነቱን በብቃት ይወጣ ዘንድ በሰው ኃይል፣ በቴክኖሎጂ እና በትምህርት ለማብቃት የሚደረገው ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ አደራጃጀቱም የተጣለበትን ተልዕኮ በብቃት ለመወጣትና አዳዲስ የሰው ኃይል ለማካተት በሚያስችል መንገድ ለመገንባት የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡ ይህ ሲሆን ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ እንዳሉት ‹‹የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ለጠላቶቹ የፍርሃት ምንጭ፤ ለኢትዮጵያዊያንና ወዳጆቿ ኩራት›› መሆኑን የሚችለው፡፡
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ኢትዮጵያ በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ባለፈችባቸው ጊዜያት ሁሉ በታላቅ ቁርጠኝነት ያለፈ ትልቅ ተቋም ነው፡፡ በአገር ውስጥም ሆነ ሠላም ለማስከበር በሄድንባቸው አገራት ህዝባዊነቱን ያስመሰከረ ምስጉን ሠራዊት መሆኑንም ዓለም የመሰከረለት ነው፡፡ በተቋሙ እየተሠራ ያለው ሪፎርምም የሲቪል ቁጥጥርን በተቋሙ ውስጥ በማረጋገጥ ለፕሮፌሽናል መከላከያ ግንባታ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው፡፡
የአገር መከላከያ ሠራዊት አገርና ህዝብ ጠባቂ በመሆኑ በህዝብ ምርጫ ለተወሰነ ጊዜ ከሚመረጡ የህዝብ ወኪሎች ጋር መለዋወጥ የለበትም፡፡ ሠራዊታችን ከፖለቲካ ወገንተኝነት የፀዳ ሆኖ ህዝባዊነቱን አጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ ይህም ሠራዊቱን የሀገርና የህዝብ መከታ፣ ለጠላቶቹ ደግሞ ፍርሃትና ጭንቀት እንዲሆን በማድረግ ሉዓላዊነቷ የተከበረ ሀገር እንድትኖረን ያደርጋል፡፡
ሠራዊቱ የመከላከያን የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ለማሳደግም በትኩረት እየተሠራ ነው፡፡ በሳይበር እና በህዋ ምርምር መስክ ብቃትና ፍላጎት ያላቸው ወጣቶች መሳተፍ እንደሚችሉም ምቹ ሁኔታዎች አሉ። ‘መከላከያን ለማዘመን ጊዜ የሚጠይቅ ቢሆንም ከዘመን ጋር አብሮ መዘመንና ሠራዊቱም በየወቅቱ ራሱን ማብቃት አለበት። ሠራዊታችን ፕሮፌሽናል ሲሆንና በቴክኖሎጂ የታገዘ ግዳጅ መፈጸም የሚያስችለውን አቅም መፍጠር ሲችል በኢትዮጵያ ጠላቶች የማይደፈር፣ በወገኖቹና በወዳጆቿ ደግሞ የሚከበር የአለኝታና ጀግና ሠራዊት ባለቤት እንሆናለን!
አዲስ ዘመን የካቲት 9 ቀን 2011