ኢንስቲትዩቱ በመጪው ክረምት ከመደበኛ በላይ ዝናብ ስለሚኖር ጥንቃቄ እንዲደረግ አሳሰበ

አዲስ አበባ፡- በመጪው የክረምት ወቅት ከመደበኛ በላይ የዝናብ መጠን ስለሚኖር ከወዲሁ አስፈላጊው ጥንቃቄ እንዲደረግ የኢትዮጵያ ሜቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አሳሰበ።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ የበልግ ወቅት የአየር ትንበያ ግምገማ እና የክረምት ወራት የአየር ፀባይ አዝማሚያን ይፋ ሲደረግ እንደተናገሩት፤ በቀጣይ የክረምት ወቅት ከመደበኛ በላይ የዝናብ መጠን ይኖራል። ከመደበኛ በላይ የዝናብ መጠን በሚኖርበት ጊዜ ለጎርፍ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ላይ ቅፅበታዊ ጎርፍ እና የወንዞች ሙላት ሊከሰት እንደሚችል ይጠበቃል። በጎርፍና በማሣ ውስጥ የውሃ መተኛት አደጋዎችን ለመከላከል ከወዲሁ አስፈላጊውን የጥንቃቄ ርምጃዎች መውሰድ ያስፈልጋል ብለዋል።

የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎችን አስቀድሞ በመሥራት ቅድመ ጥንቃቄዎችን ማድረግና በእነዚህ አካባቢዎች ለሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች አስፈላጊውን ግንዛቤ መስጠት እንደሚገባ አመልክተዋል።

በሰሜን ምሥራቅና በደቡብ ምዕራብ የሚኖረው ከፍተኛ ዝናብ በማሳ ላይ ውሃ መተኛት የሚያስከትል መሆኑን ገልጸው፤ይህም ለወባ ትንኝ መራባት ምቹ ሁኔታ ስለሚፈጥር የውሃ ማፋሰሻ ቦዮችን በማፅዳት ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል።

በመጪው የክረምት ወራት ላይ በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍሎች በሰሜን ፣ሰሜን ምሥራቅ፣ ሰሜን ምዕራብ፣ ምዕራብና ምሥራቅ የሀገሪቱ ክፍሎች ዋነኛ የዝናብ ወቅት በመሆኑ 85 በመቶ ዝናብ እንደሚያገኙ አመልክተው፤ ይህም በክረምት ወቅት ለሚከናወኑ የግብርና ሥራዎች ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ጠቁመዋል።

የአየር ትንበያዎች ላይ ባደረገው ግምገማ 75 በመቶ የትንበያ ትክክለኛነት መኖሩን ጠቁመው፤ ኢንስቲትዩቱ የሚያስቀምጣቸው ትንበያዎችም መሬት ላይ ካለው የአየር ፀባይ ጋር ያለው መጣጣም መሻሻል አሳይቷል ብለዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ ኢንስቲትዩቱ የአየር ፀባይ ትንበያዎችን ፣ ቅድመ ማስጠንቀቂያዎችን በተከታታይ የሚያጋራ በመሆኑ የክረምት ወቅት የአየር ፀባይ ትንበያዎችን አስቀድሞ መከታተል ያስፈልጋል። በትንበያዎቹ መሠረት የሚሰጡ የቅድመ ጥንቃቄ መረጃዎችን ተግባራዊ ማድረግ ይገባል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሚኒስትሩ አማካሪ አቶ ሞቱማ መቃሳ፤ ኢንስቲትዩቱ በቴክኖሎጂ እና በሰለጠነ የሰው ኃይል በማሳደግ ጊዜውን የጠበቀ የአየር ትንበያ እያደረሰ መሆኑን ገልጸው፤ ለእዚህም የበልግ ወቅት የአየር ትንበያ መሬት ላይ ካለው ተቀራራቢ መሆኑ ማሳያ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ኢንስቲትዩቱ በሚያቀርባቸው የአጭር ጊዜና የረጅም ጊዜ የአየር ትንበያዎችም ለጤናና ግብርና ሴክተሮች በማቅረብ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢንስቲትዩቱ ባዘጋጀው የምክክር መድረክ ከተለያዩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ባለድርሻ አካላት ጋር በክረምት ወቅት ስለሚከሰተው የዝናብ መጠን እና ሊደረጉ የሚገባቸው ጥንቃቄዎች ላይ ውይይት መደረጉ ታውቋል።

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን እሁድ ግንቦት 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You