የኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ከኢትዮጵያ መውጣት

የኢሠፓ ሊቀመንበር እና የደርግ ዘመነ መንግሥት የኢትዮጵያ መሪ የነበሩት ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ስማቸው ተደጋግሞ ይነሳል። ለሺህ ዘመናት የኖረውን ንጉሣዊ ሥርዓት ያስወገደው የደርግ መሪ ናቸውና ወደፊትም በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ስማቸው ተደጋግሞ ይጠራል።

የዚህ ሳምንት ክስተት የሆኑት ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ለምን ከሀገር ወጡ? እንዴት ወጡ? ከወጡ በኋላ ምን ተከሰተ? እርሳቸውና በወቅቱ የነበሩ አመራሮች ምን አሉ? የሚለውን በዛሬው ሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን እናስታውሳለን።

ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ከ34 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ግንቦት 13 ቀን 1983 ዓ.ም ከኢትዮጵያ በመውጣት ወደ ዝምባቡዌ ኮበለሉ። የደርግን ሥርዓት የገረሰሰው ኢሕአዴግ በወቅቱ ‹‹ፈረጠጠ›› በሚል ቃል መግለጹ ይታወሳል። ከዚያ በኋላም በየጊዜው የኢሕአዴግ አመራሮች ‹‹ሀገር ጥሎ ፈረጠጠ›› የሚለውን ቃል ሲጠቀሙ ቆይተዋል።

አንዳንድ ፖለቲከኞች ደግሞ ለሕዝብ ደህንነት ሲባል ኮሎኔል መንግሥቱ ሀገር ጥለው መኮብለላቸውን በበጎ ያዩታል። እንደተናገሩት ‹‹አንድ ጥይት እና አንድ ሰው እስከሚቀር..›› ቢዋጉ ኖሮ አዲስ አበባ ውስጥ ከፍተኛ እልቂት ይፈጠር ነበር።

ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ ኢሕአዴግ አዲስ አበባን ሲቆጣጠር የ44 ዓመት ጎልማሳ እና የታሪክ ምሁርና ተመራማሪ ነበሩ። ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም ኢሕአዴግ አዲስ አበባን ሲቆጣጠር የነበረውን ክስተት ‹‹ሕብር ሕይወቴ መጽሐፋቸው ላይ እንደገለጹት፤ ኢሕአዴግ አዲስ አበባን ሲቆጣጠር ምናልባትም ከቤተ መንግሥቱ ዙሪያ በስተቀር አዲስ አበባ ውስጥ በደርግ እና በኢሕአዴግ ተዋጊዎች መካከል ጥይት አልተተኮሰም። ከዚያ ይልቅ የነዋሪው ሥነ ልቦና ፍርሃትና ጥርጣሬ የተሞላበት ስለነበር መሳሪያ ያላቸው ሰዎች አጋጣሚውን በመጠቀም ተኩሰዋል። ማን እንደሚተኩሰው የማይታወቅ የተኩስ ድምጽ አልፎ አልፎ ይሰማ ነበር፤ ከዚያ ውጭ መንግሥትን ያህል ነገር በትጥቅ ኃይል ሲገለበጥ ሊኖር የሚችለው ጦርነት አልነበረም። ስለዚህ ምናልባትም የኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ሀገር ለቆ መሄድ አዲስ አበባ ውስጥ ሊኖር ይችል የነበረውን እልቂት ቀንሷል ብሎ ለመሞገት ያስችላል። ለመሆኑ እርሳቸው ይህን አስበው ነው ከሀገር የወጡት ወይስ የራሳቸውን ሕይወት ለማዳን ነበር? የሚለው እንደየፖለቲከኞቹ አተረጓጎም ይለያያል።

ፈረጠጡ ወይስ ለፖለቲካዊና ወታደራዊ ዓላማ ነበር የሄዱት? የሚለውን በራሳቸው አንደበት የተባለውን እና በወቅቱ ጓዶቻቸው የተባለውን እንጥቀስ።

‹‹…በመሠረቱ ለጉዞዬ ምክንያት የተደረገውና እውነትም የነበረው የብላቴን ጉዞ ነው። ብላቴን ልሄድ ነው፤ ኬንያ የሄድኩበት ምክንያት ሌላ የውጭ መገናኛ በር በማግኘትና በምስራቅ፣ በምዕራብ፣ በደቡብ ተደራጅቶ ለመልሶ ማጥቃት ድርጅት ለእኔ ምሥጢራዊ ተልዕኮ አስረድቼና ሁኔታውን አመቻችቼ እንዲመጣ ነው ተልዕኮዬ። እነርሱ እንግዲህ እንደሚመስለኝ ለእኔ መውጫ ያደረጉት ማለት ነው፤ ምክንያቱም ገና ኬንያ ስሄድ እኔ በሁለት ሰዓት ከሃያ በረራ ስጀምር ሦስት ሰዓት ላይ እነርሱ ስብሰባ እንደጀመሩ፤ እዚያ እንደደረስኩኝ በሰባት ሰዓት የኔ ከሥልጣን መውረድ ዜና ተነገረ፤ ይሄው ነው! እና በዚህ ሁኔታ ነው፤ እኔ አልኮበለልኩም…››

ይህን የኮሎኔል መንግሥቱን ንግግር ግን ደርግን ከሥልጣን ያስወገዱት ብቻ ሳይሆኑ ከራሳቸው ጓዶችም የማይቀበሉት አሉ። በደርግ ዘመነ መንግሥት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና በሌሎች ኃላፊነቶች ያገለገሉት ብርሃኑ ባይህ ‹‹የሀገር መሪ ከመቼ ወዲህ ነው መሳሪያ ሊገዛ የሚወጣው?›› ሲሉ ሞግተዋል። በቅርቡ (ከሁለት ዓመት በፊት) ረጅም ቃለ መጠይቅ የሰጡት እና ‹‹የሻምላው ትውልድ›› የሚለውን ዳጎስ ያለ መጽሐፍ የጻፉት ጓድ ፋሲካ ሲደልል ‹‹ከፍርጠጣው የሽምጠጣው›› በማለት ነገርየው ኮሎኔል መንግሥቱ እንዳሉት ሳይሆን የምርም ፍርጠጣ ነበር የሚል ይዘት ያለው ገለጻ አድርገዋል። ያም ሆነ ይህ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም በኢሕአዴግ ወታደራዊና ፖለቲካዊ ኃይል የሚመሯትን ሀገር ለቀው ዚምባቡዌ ገብተዋል።

የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎችና የፖሊስ ሰራዊት አባላትን ይወክላሉ የተባሉና ከተራ ወታደር እስከ ሻለቃ ድረስ ማዕረግ ያላቸው 120 የጦሩ አባላት ሰኔ 21 ቀን 1966 ዓ.ም በአራተኛ ክፍለ ጦር ግቢ ውስጥ ተሰብስበው ያቋቋሙት ‹‹የጦር ኃይሎች፣ የክብር ዘበኛ፣ የፖሊስ ሰራዊትና የብሔራዊ ጦር አስተባባሪ ኮሚቴ›› መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴን ከዙፋናቸው አውረደው። ስያሜውንም ‹‹ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ›› ብሎ በመለወጥ ስልጣን ይዞ ኅብረተሰባዊነት (Socialism)ን የፖለቲካ ኢኮኖሚ መርሁ አድርጎ አገር መግዛት ጀመረ።

የመሰረተ ልማት አውታሮችን በተለይ ደግሞ ትምህርትን ለማስፋፋት ከተደረገው ጥረት ባሻገር የእርስ በእርስ ጦርነት፣ እስራትና ስርዓት አልበኝነት የአገዛዙ መለያዎች ሆኑ። በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በተለይ ደግሞ ኤርትራ ውስጥ ያለው ጦር ሲሸነፍ ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለማርያም የሚወስዱት እርምጃ፣ የሊቀመንበሩ የአቋም ግትርነት (ድፍረት እንጂ ዲፕሎማሲ አይችሉም እየተባሉ ይታማሉ) እንዲሁም ሌሎች ውስጣዊና ውጫዊ ምክንያቶች ተደምረው የጦሩ መሪዎች በሊቀመንበሩ ላይ ጥርሳቸውን ነከሱባቸው።

መፈንቅለ መንግሥት ለማድረግም ሞክረው ሳይሳካ ቀረ። የሀገሪቱ ችግርም ከድጡ ወደ ማጡ ሆነ።

ከዚህ ሁሉ ችግር ለማምለጥ ከሀገር መውጣትን ምርጫቸው ያደረጉት የሀገሪቱ ፕሬዚደንት ግንቦት 13 ቀን 1983 ዓ.ም ሌተናል ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም በኬንያ በኩል አድርገው ዚምባብዌ ገቡ። ኮሎኔል መንግሥቱ ከሚመሩት መንግሥት ጋር ሲዋጉ ከነበሩት አማፂያን መካከል ‹‹ሻዕቢያ›› ኤርትራን ገነጠለ፤ ሕወሓትና አጋሮቹ ደግሞ ግንባር ፈጥረው ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም አዲስአበባ ገቡ።

ከቀኑ ስድስት ሰዓት ላይ የኢትዮጵያ ሬዲዮ ከመንግሥት ምክር ቤት የሚሰጥ መግለጫ እንዳለ እየደጋገመ ሲገልጽ ከቆየ በኋላ በመጨረሻ «ጦርነቱ ያስከተለው ሁኔታ እንዲለወጥ በልዩ ልዩ ወገኖች በልዩ ልዩ መልክ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል። ሆኖም ችግሩ አልተቃለለም። ይልቁንም ወደ ባሰ ደረጃ እየተሸጋገረ ይገኛል። ስለዚህ ደም መፋሰስ እንዲቀርና ሰላምም እንዲሰፍን በልዩ ልዩ ወገኖች የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ከስልጣን መውረዳቸው እንደሚበጅ የታመነበት ስለሆነ ይህንኑ በማመዛዘን ፕሬዚደንት መንግሥቱ ኃይለማርያም በዛሬው ዕለት ከስልጣን ወርደው ከኢትዮጵያ ውጪ ሄደዋል። ፕሬዚዳንቱ ከስልጣን በመውረድ ሀገር ለቀው በመሄዳቸው የሪፐብሊኩ ምክትል ፕሬዚዳንት ሌተናል ጀኔራል ተስፋዬ ገብረኪዳን ተክተው ይሰራሉ» የሚል አጭር መግለጫ ተላለፈ። በዚያው ኢሕአዴግ ሀገሪቱን ተቆጣጠረ። የዚህን ዝርዝር በግንቦት 20 ታሪኮች እናየዋለን።

ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ግንቦት 13 ቀን ከሀገር ከመውጣታቸው ቀደም ብሎ ባሉት ቀናት የነበሩትን ሁነቶች ኮሎኔል ፍስሐ ደስታ ‹‹አብዮቱና ትዝታዬ›› በሚለው መጽሐፋቸው ያስታውሱናል።

ግንቦት 10 ቀን 1983 ዓ.ም ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማሪያም በመኖሪያ ቤታቸው ለከፍተኛ ባለስልጣኖቻቸው የእራት ግብዣ አደረጉ። ግብዣው ሲጠናቀቅ ፕሬዚዳንቱ ከዚህ በፊት ባልተለመደ መልኩ ሁሉንም ተጋባዥ እንግዶች እበራፋቸው ላይ በመሆን አንድ በአንድ እየጨበጡ ሸኟቸው።

ግንቦት 12 ቀን 1983 ዓ.ም፤ ፕሬዚዳንት መንግስቱ መሉውን ቀን የተለያዩ ወረቀቶችን ቢሯቸው ውስጥ ሲቀዳድዱ ዋሉ፤ አመሻሽ ላይ ግን ወደ ዘመቻ መምሪያ በማምራት ለከፍተኛ የጦር አዛዦቻቸው ንግግር አደረጉ።

ማክሰኛ ግንቦት 13 የፕሬዚዳንቱ ልዮ ረዳት ሻምበል መንግስቱ፤ ብላቴ ማሰልጠኛ ጣቢያ ደርሶ ከዚያም ወደ አስመራ ደርሶ መልስ የሚበቃ ነዳጅ የሞላ አንድ ዳሽ 5 አውሮፕላን እንዲዘጋጅ ትእዛዝ አስተላለፈ።

በዚያው ዕለት ከጠዋቱ ወደ 2 ሰዓት ገደማ ፕሬዚዳንቱ ከተመረጡ አጃቢዎቻቸው እንዲሁም ከሶስተኛ ክፍለ ጦር የመጣና የቅርብ አጃቢያቸው ከነበረው ከሻንበል ደመቀ ባንጃው ጋር በመሆን በኮሎኔል ተስፋዬ መሪነት ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ በመድረስ ተዘጋጅታ ትጠብቅ ከነበረችው አውሮፕላን ተሳፈሩ።

ግንቦት 13 ቀን 1983 ዓ.ም ፕሬዚዳንት መንግስቱ የ 17 ዓመት ስልጣናቸውን ለቀው ከኢትዮጵያ ወጡ፤ እነሆ እስከ አሁን ድረስም በዚምባቡዌ ሐራሬ ይኖራሉ።

የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመሥረት

ሌላኛው የዚህ ሳምንት ክስተት የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (በኋላ የአፍሪካ ሕብረት) የተመሰረተበትን ነው። የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የተመሰረተው ከ62 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት በዛሬዋ ቀን ግንቦት 17 ቀን 1955 ዓ.ም ነው።

ኢትዮጵያ በቅኝ ያልተገዛች ነፃ ሀገር በመሆኗ፤ የተባበረች አፍሪካን ለመመስረት እንቅስቃሴ ማድረግ የጀመረችው ከ1950ዎቹ መጀመሪያ አንስቶ ነበር። በወቅቱ የነበሩትን 30 አካባቢ የሚሆኑ ነፃ የአፍሪካ ሀገራትን በማነሳሳትና የመሪነት ሚና በመጫወት ግንቦት 17 ቀን በ1955 ዓ.ም በአዲስ አበባ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ተመሰረተ።

ይህ ድርጅት ሲመሰረት፤ ከሃያ በላይ በአውሮፓውያን ቅኝ ግዛት ስር የነበሩ የአፍሪካ ሀገራትን ነፃ ማውጣትና የጥቂት ነጮች የበላይነት ስርዓት ያለባቸውን ሀገራትም ከዚህ የዘር መድልዎ ስርዓት ማላቀቅ ዋነኛ ዓላማው ነበር። የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ይህን ዓላማውን አሳክቷል።

በመጨረሻ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን የተቀላቀለችው ሀገር ደግሞ ደቡብ አፍሪካ ነበረች። ደቡብ አፍሪካ የጥቂት ነጮች የዘረኝነት ስርዓትን አስወግዳ በ1986 ዓ.ም የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ተቀላቀለች።

የአፍሪካ ሀገራትን ነፃነት ማረጋገጥ ቀዳሚ ዓላማው አድርጎ የተመሰረተውና ዓላማውን ያሳካው አፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲመሰረትና ተልዕኮውን እንዲወጣ በማድረግ ረገድ የወቅቱ የኢትዮጵያ መሪ የነበሩት ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ትልቅ ድርሻ ነበራቸው። ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ የመሪነት ሚና እንዲጫወቱ ያደረጋቸው ደግሞ የነፃይቱ ሀገር ኢትዮጵያ መሪ መሆናቸው ነው።

የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በዚህ ስሙ የቆየው ለግማሽ ክፍለ ዘመን ያህል ነው። ድርጅቱ በ1994 ዓ.ም ወደ ሕብረትነት በመለወጥ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የነበረው የአፍሪካ ሕብረት ተብሏል። የአፍሪካ ሕብረት የተባለው በ1993 ዓ.ም በዋና መቀመጫው አዲስ አበባ ኢትዮጵያ ቢሆንም ይፋ የተደረገው ግን በ1994 ዓ.ም ደቡብ አፍሪካ ነው።

የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ለመመስረት ኢትዮጵያ በመሪዋ ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴና በወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከተማ ይፍሩ ከፍተኛ ጥረት እንዳደረገችው ሁሉ የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ አዲስ አበባ እንዲሆንም የወቅቱ የኢትዮጵያ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል።

በ1994 ዓ.ም የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ የሴኔጋል መንግሥት ተወካይ የሕብረቱ ማቋቋሚያ ሰነድ ላይ የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ አዲስ አበባ ይሁን የሚለውን አንቀጽ (አንቀጽ 24) ተቃወሙ። ወደ ሌላ ሀገር መሄድ እንዳለበትም ምክረ ሀሳብ አቀረቡ። የወቅቱ የኢትዮጵያ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ የሴኔጋላዊውን ሐሳብ በመቃወም የሚከተለውን ንግግር አደረጉ።

‹‹የሴኔጋሉ ተወካይ አንቀጽ 24ን በተመለከተ አሁን መወሰን በጣም እንደሚያስቸግር፤ በተቀሩት አንቀጾች ላይ ግን ምንም ችግር እንደሌለባቸው ተናግረዋል። ተወካዩ የአፍሪካ ሕብረት ጽሕፈት ቤት መቀመጫ የት መሆን እንዳለበት ለመወሰን እንደሚቸገሩ ገልጸዋል።

በእኔ እምነት በጣም ቀላሉ አንቀጽ ይሄኛው አንቀጽ ይመስለኛል።

ይህን ጉዳይ አሁን ለመወሰን እንደ እኔ ከሁሉም በጣም የቀለለ ጉዳይ ይመስለኛል፤ ልክ ጁሊየስ ኔሬሬና ክዋሜ ንኩርማህ አዲስ አበባ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መቀመጫ እንድትሆን እንደወሰኑት ማለት ነው።

የያኔዋ ኢትዮጵያ በዘውድ ሥርዓት፣ በአፄ ኃይለሥላሴ ነበር የምትተዳደረው። ኢትዮጵያን የትኛውም ዓይነት መንግሥት ያስተዳድራት ሁሌም ለአፍሪካ ነፃነት በፅናት መቆሟን ማንም ሰው ሊክደው የማይችለው ሐቅ ነው።

የደቡብ አፍሪካውን የነፃነት ታጋይና አርበኛ ማንዴላን ማን አሰለጠናቸው?! … አፄ ኃይለ ሥላሴ አብዮተኛውን ማንዴላ ኢትዮጵያ ውስጥ አሰልጥነዋቸዋል። የዚምባቡዌው ሙጋቤ ያደረገውን ፀረ ሮዴሽያ ትግል ማን ነው የደገፈው?! መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ነው። መንግሥቱ በሀገር ውስጥ አምባገነንና ጨፍጫፊ ነበር። በአፍሪካ ጉዳይ ግን መንግሥቱም እንደ አፄ ኃይለ ሥላሴ ጠንካራ አቋም ነበረው። ኢትዮጵያ በአፍሪካ ጉዳይ ላይ ያላት አቋም መንግሥታት በተቀያየሩ ቁጥር የማይቀያየር የፀና አቋም ነው …። ››

የአፍሪካ ሕብረት የኢትዮጵያ መሪዎች የሚሞገሱበት ነው ማለት ይቻላል። ሥርዓትና መሪዎች ቢቀያየሩም የአፍሪካ ሕብረት ግን የኢትዮጵያን የነፃነት ተምሳሌትነት ሲመሰክር ይኖራል።

በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ሌላው ከፍተኛ ሚና የተጫወቱት ሰው ደግሞ የንጉሡ ዘመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ከተማ ይፍሩ ናቸው። እኝህ ሰው የንጉሡ ዘመን የውጭ ጉዳይ ግንኙነት አድራጊ ፈጣሪ ነበሩ፤ የንጉሡም ዋና ልዩ አማካሪ ነበሩ።

የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሲመሰረት በነበረባቸው ጊዚያት ካዛብላንካ እና ሞኖሮቪያ የሚባሉ እንቅስቃሴዎች ነበሩ። በእነዚህ እንቅስቃሴዎች ጊዜ የአፍሪካ ሀገራት ተዋህደው አንድ መሆን አለባቸው የሚለው የካዛብላንካ እንቅስቃሴ እና መጀመሪያ መተባበር ይቀድማል የሚለው የሞኖሮቪያ ቡድን እሳቤዎች ነበሩ። በከተማ ይፍሩ የሚመራው የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ግንኙነት እነዚህን ሀሳቦች የማስታረቅ ሥራ ነበር የሚሠራው።

ብልህና በሳል የነበሩት ከተማ ይፍሩ ነገሩን በዲፕሎማሲያዊ ዘዴ ሲያግባቡ ቆይተው የካዛብላንካንም ሆነ የሞኖሮቪያ ሰዎችን ከንጉሡ ጋር በማወያየት የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲመሰረት አድርገዋል።

በአጠቃላይ ኢትዮጵያ፤ በቆራጥና ጀግና አርበኞቿ ነፃነቷን አስጠበቀች፣ በብልህ ዲፕሎማቶቿና መሪዎቿ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን መሰረተች፣ መቀመጫውንም አዲስ አበባ አስደረገች።

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን እሁድ ግንቦት 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You