በተኪ ምርት ላይ ያተኮረው የአዋሽ ፊለር ፋብሪካ

ዜና ሀተታ

ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ከተለገሰቻቸው በርካታ ማዕድናት መካከል ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚውሉ ማዕድናት ይገኙበታል። ከእነዚህም መካከል እንደ ድንጋይ ከሰል፣ ካኦሊን፣ ዶሎማይት፣ ኳርትዝ፣ ፊልድስባር፣ ዳያቶማይት፣ ቤንቶናይት እና የመሳሰሉት ለኢንዱስትሪዎች በግብዓትነት የሚያገለግሉ ማዕድናት ክምችቶች ይገኙበታል። ከመረጃዎች በመነሳት የድንጋይ ከሰልን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል። በድንጋይ ከሰል ምርት ሀገሪቱ ራሷን መቻሏንም እንደእዚሁ።

የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የድንጋይ ከሰልን በብዛት ይጠቀማሉ፤ የካኦሊን ማዕድን፣ በውሃ ፋብሪካዎች ይፈለጋል። ኢንዱስትሪዎች እየተስፋፉ ባሉበት በእዚህ ወቅት የማዕድናቱ ተፈላጊነት እለት በእለት እየጨመረ ይገኛል።

ይህን በሀገራችን የሚገኝ እምቅና ያልተነካ የተፈጥሮ ሀብት ክምችት በአግባቡ እየተጠቀሙበት ያሉት ፋብሪካዎቻችን ጥቂት ሲሆኑ፤ አብዛኞቹ ለፋብሪካዎቻችን ግብአት ይሆኑ ዘንድ ምርቶችን ከውጭ ማስገባት ላይ ያተኮሩ ሆነው ነው የምናገኛቸው።

የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አህመድ በርከት ያሉ ምርቶችን እና የፋብሪካ ግብዓቶችን ማምረት በሚችለውና ባለፈው ሀሙስ በተመረቀው ፋብሪካ የምረቃ ሥነሥርዓት ላይ እንደገለጹት፤ አዋሽ ፊለር ፋብሪካ በሀገሪቱ በዓይነቱ የመጀመሪያና በአፋር ክልል ሊገነቡ ከታሰቡት ፋብሪካዎች መካከል አንዱ ሲሆን፤ ፋብሪካው 97 በመቶ የሀገር ውስጥ ግብዓቶችን ይጠቀማል።

እንደ ዋና ሥራ አስፈፃሚው ማብራሪያ ፋብሪካውን ከሌሎች ልዩ የሚያደርገው 97 በመቶ የሀገር ውስጥ ግብአቶችን መጠቀሙ ብቻ ሳይሆን ለበርካታ ኢንዱስትሪዎች ግብአቶች የሚሆኑ ምርቶች ማቅረቡና ፋብሪካዎች ያለ ምንም ውጣ ውረድ ግብአቶችን ከእዚሁ ማግኘት እንዲችሉ ማድረጉና የውጭ ምንዛሪ እጥረትን መቅረፉ ጭምር ነው።

አቶ ጀማል እንደተናገሩት፤ አዋሽ ፊለር ፋብሪካ በካልስየም ካርቦኔት የበለፀገ ኮትድ ምርት እንደሚያመርትና ይህም ምርት በተለይም ለፒፒሲ፣ ለቀለም፣ ለወረቀት፣ ለጫማ ሶል፣ ለፎም እና ስፖንጅ እና ተያያዥ ምርቶች ከ20 እስከ 30 በመቶ ግብአት በመሆን ያገለግላል።

ይህ የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር ሀጂ አወል አርባና ሌሎች በርካታ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ግንባታው ተጠናቅቆ ለመመረቅ የበቃው አዋሽ ፊለር ፋብሪካ የመጀመሪያ ዙር ፕሮጀክት በስቴሪክ አሲድ የተዋሀደ ካልሲየም ካርቦኔት (Coated Filler) የሚያመርት ነው። ይህ ምርት በሀገሪቱ የመጀመሪያው ሆኖ ለፕላስቲክ ኢንዱስትሪዎች ግብአት በመሆን ያገለግላል።

አቶ ጀማል ንብረትነቱ የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የሆነው አዋሽ ፊለር ፋብሪካ ለበርካታ ኢንዱስትሪዎች ግብአቶችን እንደሚያቀርብ ገልጸው፤ለአካባቢው ነዋሪዎች ተጨማሪ የሥራ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን አስገንዝበዋል። በጥሬ ዕቃ አቅርቦት ረገድም ለአካባቢው ነዋሪዎች የሚያበረክተው አገልግሎት በቀላሉ ሊታይ የሚችል አለመሆኑን አስገንዝበዋል።

በምረቃ ሥነሥርዓቱ ላይ በመገኘት መልዕክታቸውን ያስተላለፉት የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሀጂ አወል አርባ የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ፋብሪካውን አጠናቆ ወደ ሥራ ማስገባቱን አድንቀው፤ ኩባንያው ቃል በገባው መሠረት ወደ ፊትም በርካታ ሥራዎችን እንደሚሠራ፤ ለሚሠራቸውም ሥራዎች ሁሉ ክልሉ አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር እንደሚያደርግለት ገልጸዋል።

“ከእንግዲህ ሜድሮክ አፋር ነው። አፋርም ሜድሮክ ነው” ሲሉም የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በክልሉ እያከናወነ ያለውን እንቅስቃሴ ገልጸዋል።

አዋሽ ከተማ ከሁሉም የሀገሪቱ አቅጣጫ ለሚመጣ ሁሉ ማእከል፣ ለኢንቨስትመንት ወሳኝ፣ በወደቦች አካባቢ የምትገኝ ከተማ በመሆኗ የኢኮኖሚ እና ኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድር ሀጂ አወል አርባ አስታውቀዋል።

ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በአምራች ዘርፎች እያከናወናቸው ከሚገኙት ሰፋፊ ፕሮጀክቶችና እያስገነባቸው ካሉት ፋብሪካዎች መካከል አንዱ የሆነው አዋሽ ኮትድ ካልሺየም ካርቦኔት (ኮትድ ፊለር ፋብሪካ) ሲመረቅ በስፍራው ተገኝተን ያነጋገርናቸው የፋብሪካው ሠራተኞች እንደ ነገሩን ከሆነ፤ የፋብሪካው መገንባት ለሀገር ኢኮኖሚ ከሚያበረክተው አስተዋፅኦ ባልተናነሰ ለአካባቢው ነዋሪዎች የገቢ ምንጭ በመሆን እያበረከተ ያለው ድርሻ በቀላሉ የሚታይ አይደለም ይላሉ።

በአዋሽ ሰባት የማስፋፊያ ግንባታው ተጠናቆ የተመረቀው ይህ ፋብሪካ ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል የፈጠረ፤ ወደ ፊትም በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎችን በማሳተፍ ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፤ ከአዲስ ዘመን ጋር ቆይታ ያደረጉት የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ባሩ ሀምዶ እንደገለጹት፤ በአሁኑ ጊዜ ብቻ ለ75 ቋሚ እና ለአንድ ኮንትራት ሠራተኞች የሥራ እድል ፈጥሮ ሰዎቹ በሥራ ላይ ይገኛሉ።

በተለያዩ መጠኖች ኮትድ ካልሺየም ካርቦኔት በሚያመርተው ፋብሪካ ቆይታችን ወቅት ያነጋገርናቸው ሠራተኞች እንደ ነገሩን ከሆነ፤ የፋብሪካው አዋሽ ሰባት መከፈት ሠርቶ ለመኖርና የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለመሆን ከፍተኛ እድል ፈጥሮላቸዋል።

እየተስፋፋና እያደገ በመጣው በእዚህ ፋብሪካ ውስጥ ለ21 ዓመታት ያገለገሉትና እያገለገሉም የሚገኙት፣ ባለ ትዳር እና የአንድ ልጅ አባት የሆኑት አቶ በሀይሉ ፀጋዬ እንደነገሩን ከሆነ፤ ፋብሪካው የሥራ ቦታቸው ብቻ ሳይሆን ልክ እንደ ቤታቸው ሆኖ ነው የሚሰማቸው። ፋብሪካውን እዚህ የገነቡትን ባለሀብቶችንም ከልባቸው ነው የሚያመሰግኑት።

ሌላዋ ያነጋገርናቸው የፋብሪካው ሠራተኛ ወይዘሮ እየሩስ ፍሮንሳ ሲሆኑ፣ በፋብሪካው ሠራተኛነታቸውን ተጠቃሚነታቸውን ከገለጹ በኋላ ይህ “ፋብሪካ የተዳርኩበትና የተኳልኩበት ብቻ ሳይሆን ልጅ ያፈራሁበት ጭምር ስለሆነ ከቤቴ ለይቼ አላየውም፤ በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተውናል።

ላለፉት 11 ዓመታት እዚሁ ተቋም ያገለገሉትና እያገለገሉ የሚገኙት አቶ እዮብ አወልም በሠራተኞች በኩል ያለውን የእርስ በርስ መግባባትና ፍቅር ገልጸውልናል። በአመራሩ በኩል ያለውን የአመራር ብቃትና ሠራተኛ ተኮር እቅስቃሴም አድንቀዋል። ሌሎች ባለ ሀብቶችም እንደ ሜድሮክ ሁሉ ከአዲስ አበባ ወጣ እያሉና በክልሎች እየገነቡ ራሳቸውን፣ ሀገራቸውንና ወገናቸውን እንዲያገለግሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን እሁድ ግንቦት 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You