
በትዝታ ሽርፍራፊ የኋላኛውን ዘመን የሙዚቃ ጠረን የናፈቁ እንደሆን፣ በዓይነ ሕሊና ምስል የከሰቱለት እንደሆነም፣ ከሩቅ ደምቀው የሚነበቡ ጥቂት ስሞችን ቢጠሩ፤ በእዚህና በሌሎችም ሁሉ ከፊት ንጋቷ ከልካይ ትኖራለች።
ደርባባ ደርባቢት ናት። በእነዚያ የዘመን ጥበባት ውስጥ የመልኳ ጸአዳነት ይለያል፤ የውስጧ ንጋት ጮራ ፊቷ ላይ የፈነጠቀ ዓይነት። ንጋቷ ሀገር ፍቅር ብቅ ስትልም ሆነ ከዚያ በፊት፣ ሴት ተዋንያን ያነበሩበትና የማይታወቅበት ጊዜ ነበር፤ ወንዶች ሴት ሆነው ይተውናሉ። ይህን ስታይ ነጠላዋን ከትከሻዋ አውርዳ፣ ወገቧን አስራ፣ እጇን አፍተልትላ፣ ወንዶቹ እየተመለከቷት ተወነች። ብትተውንም ልቧ ግን ሙዚቃው ነው። ክራሯን አንስታ አንጎራጎረች። ሙዚቃዋን አንጎራጉራም ‹የመጀመሪያዋ ሴት ድምጻዊት› ለመባል በቃች።
የማትጠልቅ የንጋት ጀንበር፣ ጥበብ ከፀዳሏ የቀሚስ ዘርፏን ሰሜን ሸዋ ቡልጋ ላይ ያለከልካይ ዠርገግ አድርጋ፣ ከገጠራማው መንደር ውስጥ ንጋቷን ከነምልክቷ ለራሷ ጻፈቻት። እርሷም ጥበብን ልታጅባት ጥቅምት 12 ቀን 1890 ዓ.ም ንጋቷ ከልካይ ተወለደች። ከመወለዷ ማንጎራጎር የሚቀናት ነበረች። ቅሉ ከልጅነት ጋር ስታንጎራጉር ገና በ13 ዓመቷ ለባል ሰጧት። ፈጽሞ አልተመቻትም ነበር።
እንደምን አፈትልካ በሽሽት የትውልድ ቀዬዋን ለቃ አዲስ አበባ ገባች። አራዳ ላይ እህቷ ነበረችና ወደርሷው አመራች። የሕይወት እንጀራዋን አራዳን አየች። እያየችም አንጎራጎረች። አንድ ቀን ወደቤታቸው የመጣችው አይቷ (የእህት ባል እህት) የንጋቷን ሁኔታ ስትመለከት አዝና ወደራሷ ቤት ወስዳ ትምህርቷን አስጀመረቻት። ሴትየዋ አዝማሪ ነበረችና እንጉርጉሮ ለምትወደው ንጋቷ የተመቸች ነበረች። ሙዚቃን እያላመደቻት፣ ንጋቷም ስለድምጽዋ ውበት አራዳ አካባቢ ይወራላት ጀመረ። ምን አራዳ ብቻ…ሰተት ብላ ከቤተ መንግሥቱም ገባች።
ንግሥተ ንግሥት ዘውዲቱ ከቤተ መንግሥታቸው ውስጥ ሆነው ሲከወን ለማየትና ለመስማት የሚፈልጉት አንድ ነገር ቢኖር ሙዚቃ ነው፤ በተለይ ከአጼ ምኒልክ ሞት በኋላ። ፊታቸው ሆኖ የሚያንጎራጉር አዝማሪ ይወዳሉ፤ በተለይ ንጋቷ ከልካይን። እንጉርጉሮ መስማት ናፍቀውም ሆነ ለእንግዶች ድግስ አዘጋጅተው፣ ንጋቷ ከልካይ ከነ ክራሯ አትቀርም። ትመጣና የናፈቁትን ቀጭን ስጥንጥን ድምጽዋን ታንቆረቁረዋለች። ከመጠን በላይ በሚወዷቸው አባታቸው ሞት ብቸኝነቱ ይጠናባቸው ነበርና በንጋቷ እንጉርጉሮ ውስጥ በትዝታ መሸንቆሩን አብዝተው ተላመዱት። አንዳንዴማ እንባቸውን ያዘሩም ነበር።
ቆይታቸው ፈጽመው ንጋቷን ሲሸኟት ሁልጊዜም ሽልማት አላት። ታዲያ ሁል ጊዜ ከቤተ መንግሥት እየመጣች ንግሥቲቱን ማስለቀሷን ያልወደዱት ሹማምንቱ፣ ይህን ተግባሯን እንድታቆም ንጋቷን ገሰጽዋት። “እንዲያውም አልመጣም። አዝማሪ የመጣለትን ነው እንጂ ታዞ ሲዘፍን ልክ አይመጣም” ብላ በቀጣዩ ጊዜ ሳትመጣ ቀረች። ብዙ ጠብቀው አለመምጣቷ ግራ ያጋባቸው ንግሥት ዘውዲቱ ነገሩን የሰሙ ዕለት፣ ሄደው ንጋቷን መድኃኒታቸውን እንዲያመጡላቸው አዘዙ። ንጋቷም ዳግም ተመልሳ እንጉርጉሮውን በቅኔ እያፈሰሰች አንጀታቸውን ታርሰው ቀጠለች።
“ደርባባ ደርባባ ይወልዳሉ እናቱ
እሱም ደርባባ ነው…
የኔ ቤት ደጋ ነው ከነፋሻው ላይ
ያንተ ቤት ቆላ ነው ከሙቀቱ ላይ
የበረደው ይምጣ ማለትህ ነው ወይ”
ንጋቷና ሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት፣ ተጋምዷቸው የነብስ ያህል ነው። ‹ሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት› ከሚል ስም ውስጥ ስሟ ነብስ ይዘራል። ስሟን ከስያሜው ጋር የጣፉ ስውር ፊደላቶች ይነበባሉ።
ጊዜው ከ1927 ዓ.ም ቀደም ብሎ ነበር…ሀገር በፋሽስት ልትታመስ ሆኗል። እንደ ገብረ ጉንዳን የተደረተው የሰላቶው ወታደር ዓይኖቹን በወራ ያጉረጠርጣል። ዘመናዊ የጦር ታንክና መድፎች ወዲያ ወዲህ እየተንጎራደዱ እሳት ለመትፋት አፋቸውን ያሞጠሙጣሉ፤ እሳት የሀገር ፍቅርን ያነድ መስሏቸው። ከዚህ መሃል ግን አርበኛው ውስጥ ውስጡን ውልብ እያለ፣ ለጣይቱ ጭንቅ ሆኖበታል። በተለይ ኪነት መንደር ውስጥ የሚነፍሰው “የሀገር ፍቅር” የሚል ህቡ እንቅስቃሴ፣ ሐምሌ 11 ቀን 1927 ዓ.ም ተወለደ። ልባቸው በሀገር ፍቅር የተቃጠለና በሀገር መደፈር የእሳት ነበልባል የጎረሱ የጥበብ ልጆች ተሰባስበው ይህን ማኅበር አቋቋሙ።
በጥበብ ለመታገል የተነሱ እነዚህ ታጋዮችም፤ የቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ንጉሤ፣ ንጋቷ ከልካይ፣ ተሰማ እሸቴ፣ አገኘሁ እንግዳ፣ መላኩ በጎሰው፣ አበበ ወልዴ፣ ብላታ ሳሕሌ ፀዳሉ እና ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስ ግንባር ቀደሞቹ ነበሩ። ከእነዚህ መካከል ንጋቷ የማኅበሩ ድምጻዊት ሆና በድምጽዋ የውስጥ አርበኛውን ትቀሰቅስ ነበር።
የሀገር ፍቅር ማኅበር ግን ውስጥ ውስጡን ሥራውን ይሠራል። የሕዝቡ ልብ እንዳይወላውል፣ ለሀገሩ ዘብ ቆሞ ሰላቶውን እንዲመክት በማነሳሳት ሀገር ምድሩ፣ ሳር ቅጠሉና አየሩ ሁሉ መዓዛው የሀገር ፍቅርን እንዲሸት ሲያደርጉት ነበር። ድንኳን እየዶከኑ በጥበብ ያሰናዱትን የአርበኝነት ጸበል ጻድቅ ያቀምሳሉ። ኋላ ፋሽስቱ ከማይጨው አዲስ አበባ ሲገባ ግን በማኅበሩ የነበሩት እነ ንጋቷ ከልካይ ተበታትነው በዱር በገደሉ ከሚዋደቀው አርበኛ ጋር ተቀላቀሉ። የሆነው ሁሉ ከሆነና ካለፈ በኋላ፤ በ1933 ዓ.ም ኢትዮጵያ ነጻ ወጣች። በሚያዚያ 5 ቀን 1933 ዓ.ም “የወጣቶች ምንጭ የሀገር ፍቅር ማኅበር” የተሰኘው የቀድሞው ማኅበር ዳግም ብቅ አለ።
በ1934 ዓ.ም ወደ ባሕል ሙዚቃ ስብስብ ከፍ ያለው ይሄው ማኅበር፣ የዛሬይቱ ሀገር ፍቅር ቲያትር ቤትን አምጦ ወለደ። እናም ከዚህ ግዙፍ ዋርካ ስር ንጋቷ ከልካይ አለችበት። ሀገር፣ ፍቅር፣ ጀግንነት፣ ጥበብ…የመሳሰሉትን ከውስጣዊ ስሜታቸው ጋር አስተሳስረው የሀገር ፍቅርን ከመሠረቱ ጥቂት ሰዎች መካከል ንጋቷ አንዷ ናት።
የእርሷ ሕይወት በሽቅብ ቁልቁለት ፍሰቱ ከሀገር ፍቅር ቦይ የራቀ አይደለም። በዚያው 1927 ዓ.ም ገደማ፣ የሀገር ፍቅር እሳት ሲያቀጣጥሉ የነበሩት ሀገር ፍቅሮች አንድ ሕዝባዊ ዝግጅት ማሰናዳት ጀመሩ። ጠላት ኃይሉን እያጠናከረ ጌኛ ኮቴውን ሲያንቋቋ የነበረበት ጊዜ ነበርና ዝግጅቱ ‹እንዴት እንመክት› የሚለው የውስጥ እንቅስቃሴ አንደኛው አካል ነበር። እናም ይህን ዝግጅት የሚያሰናዱበትን ቦታ ሲፈልጉ፣ አራዳ ላይ የነበረች አንዲት ኳስ ሜዳ ዓይናቸው ውስጥ ገባች። ከሜዳዋ ፈቀቅ ብሎ ደግሞ የዓይን ማረፊያ የነበረች አንዲት ፎቅ ትገኛለች። ድንኳኑንም ከዚያቹ ፎቅ ጋር አስታከው ደኮኑት። በዕለቱ የአዲስ አበባ ሕዝብ ከየአቅጣጫው እየጎረፈ ከሜዳው ላይ ተኮለኮለ። የዳር ሀገሩ መሳፍንትና መኳንንቱ ሁሉ አልቀሩም። ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ አሉ። የቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ንጉሤ ሁሌም የቀኙን መስመር እንደያዙ ነው። የሙዚቃዊ ዝግጅቱ መሪ ናቸው። ግጥምና ዜማ ደርሰው ንጋቷ እንድትጫወተው መርጠዋታል። ንጋቷ ለመዝፈን ወደ መድረኩ ወጣች።
ከድንኳን ውስጥ ከተሠራው ትንሽ መድረክ ላይ በግራና ቀኝ፣ ከፊት ከኋላ የባሕላዊ ሙዚቃ መሣሪያዎቻቸውን ደግነው የሚጠባበቁ ተጫዋቾች ይገኛሉ። አንድ ባለ ዋሽንት፣ አንድ ባለ መለከት እና ሌላ አንድ ባለ እንቢልታ ንጋቷን ለማጀብ ተዘጋጅተዋል። ንጋቷ ወጣች። የሕዝቡ ዓይኖች ወደ መድረኩ ፈጠው በጉጉት ይቁለጨለጫሉ። ወኔ… ቁጭት…ፍቅር…ኢትዮጵያዊነት…ከመለከቱ አፎች ተግተለተሉ። እንቢልታው ‹ሀገሬን ሀገሬን› እያለ በውብ ዜማ አጓራ። የዋሽንቱ ድምጽ ለስለስ ብሎ፣ ኩልል እያለ ወረደ። ውብ ደርባባዋ ንጋቷ ከልካይ ከመድረኩ ልትዘፍን ቆመች። የሚመለከቷትን ምስኪን የሕዝብ ዓይኖች እየተመለከተች፣ ድምጽዋን በዜማ ቃኝታ እንዲህ ስትል አንጎራጎረች…
“አይባባ ልብሽ አይባባ
አዲስ አበባ ልብሽ አይባባ
ማሽላና ስንዴ ባንድ አብረን ስንቆላ
እያረረ ሳቀ የባሕር ማሽላ
አይባባ ልብሽ አይባባ”
ንጋቷ እያንጎራጎረች የአብዛኛው ሕዝብ ፊት በእንባ ረጥቧል። የውስጥ መከፋቱ፣ የእናት ሀገር ፍቅሩ፣ የወኔ የነጻነት ሀልዎቱ፣ የትዝታ፣ የደም አጥንት ህማማቱ፣ የመብሰልሰል የመብከንከን እንፋሎቱ…ጥርቅም ስሜቶቹ በእንጉርጉሮው ገንፍሎ የውስጡን በእንባ ተራጨው።
ከብዙ ዓመታት በኋላ… ንጋቷ ከልካይ እርጅናው ሊጫጫናት ሲያኮበኩብ በነበረበት ጊዜ ላይ የሆነውን ሁሉ እያስታወሰች፣ ሕዝቡን በእንባ ስላራጨችበት አጋጣሚ ስታወራ “…ስዘፍን ሕዝቡ ተሰብስቦ ይላቀስ ነበር። ያኔ መልከ መልካም ነበርኩና በኔ ድምጽ በኔ መልክ መስሎኝ ተደስቼ ነበር። ለካ በሀገር ጉድ መጥቶ ኖሯል” ስትል ያለፈ ትዝታዋን በቀልድ ትጫወተዋለች። ንጋቷ ከልካይ ሁሌም ቀልድ የማያጣትና በጨዋታዋ የማትጠገብም ጭምር ነበረች። ከወጣትነቷ አንስቶ ቁንጅናዋን ትወደውና ትኮራበት ነበር። በእርጅናዋ ጊዜ ላይ ደግሞ ትቀልድበት ነበር። ሽንቅጥቅጥ ያለች ለግላጋ ወጣት ሳለችም ይሁን በእርጅናዋ “ልቅም ያልኩ ቆንጆ ነኝ” ስትል ምንም ፈራ ተባ፣ ምንም ዓይነት ትምኪተኝነት የለባትም። በንጹህ ልብ ቁንጅናዋንም ቀልዱንም፣ ሁለቱንም ትወዳቸዋለች።
ንጋቷ ከልካይ ውቤ በረሃ ላይ ሊያዩዋትና ሊያደምጧት የሚፈልጓት ወፍ ነበረች። ንጋት ሲማልድ ዝማሬዋ የሚናፈቅ ወፍ። ዛሬ አይተዋት ነገን ዓመት የምታሳክል ተናፋቂ የሶሪት ወፍ። በተለይ በ1940ዎቹ እና 50ዎቹ የአራዳው የንጋት ኮከብ እርሷ ነበረች። ጥበብ አራዳ ላይ በአካለ ስጋ የተገለጠች ያህል፣ ከየአቅጣጫው አራዳ ይተማል፤ በመልክ የተገለጠችውን ጥበብን ሊያይ። አጀብና አጃኢብ የማያጣትን አራዳን አይቶ ሊደመም። ኪነት የሸተተው ሁሉ ከአራዳም ውቤ በረሃ ላይ ተቃጥሮ ይገናኛል። በውቤ በረሃም መደዳውን እጅ ለእጅ ተያይዘው የቆሙ የሚመስሉ ተአምረኛ ጠጅ ቤቶች አሉ። የሚያሰክረው ግን ጠጁ ሳይሆን ከጠጅ ቤቶች ውስጥ የሚፈልቀው የሙዚቃ ትርዒት ነው። እኚያ ቤቶች እንደ ዋዛ ‹ጠጅ ቤቶች› ተብለው የሚታለፉ አይደሉም። በተለይ ከዚያች መንደር ውስጥ ብቅ ስላሉ ድምጻውያን የሕይወት ታሪክ መተረክ የጀመሩ እንደሆን ወገብ ይዘው ‹ስለ እኛስ?› የሚሉ ናቸው። ከዝነኞቹ እኩል ዝና አላቸው።
ታዲያ ከእነዚህ የአራዳ ጠጅ ቤቶች ውስጥ ሙዚቃን የምታንቆረቁር ንጋቷ ከልካይ አለች። ዝነኛም ተወዳጅም ናት። እርሷ ስትዘፍን ለመስማት ብሎ ብርሌውን የሚጨብጥ ብዙ ነው። ከክራርና ከመሰንቆ ጋር ስትውረገረግ ለመመልከት ተቃጥሮና ናፍቆ የሚመጣም አለ። ያቺ ባለክራሯ ሜሪ አርምዴ እንኳን ከቤት የተላከችበትን ዘንግታ፣ በመጋረጃው ተደብቃ የምትመለከተው ንጋቷ ከልካይን ነው። እርሷን እየተመለከተች ልክ እንደርሷ ለመሆን ትመኝ ነበር። እዚያ አራዳ መንደር ውስጥ ብቻውን ተጽፎ ብቻውን የሚነበብ ታሪክ የለም። ከአንዲት ጥበብ ስር ሺዎች አክብበው ሲዞሯት እንመለከታለን። ንጋቷ አራዳ ውስጥ ሙዚቃን ለክታ የምትጫወት ዝነኛ ነበረች። በዚሁ ጊዜ በማሲንቆ አጨዋወቱ ከሚደነቀው ፈረደ ሞላ ጋር ተገናኙ። ከማሲንቆና እንጉርጉሮ ውህደት አልፈው በትዳር ተጣመሩ። የንጋቷ ከልካይን አንድ ብቸኛ ልጅም ወለዱ።
በ1950ዎቹ መጨረሻ፤ ሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት ደጃፍ የሚነፍሰው ነፋስ ከስጋ አልፎ ውስጥን የሚጋረፍ ነበር። ከውጭ የነበረው የፖለቲካ ትኩሳት እንዳለ ሆኖ፣ ከቲያትር ቤቱ ውስጥ የነበረው የአስተዳደር ሥርዓት በሠራተኞቹ ዘንድ በጥያቄ ምልክት የተጥለቀለቀ ነበር። ከኪስ ረሃብ ጀምሮ በርከት ያሉ ጥያቄዎች ቢኖሩም፤ ለንጋቷ ከልካይ ግን የሃሳብ ነጻነቱ ከጥበብ ጋር ከመጨፍለቁ በላይ የሚቆጠቁጥ ነገር አልነበራትም። ይሁንና ምሬቱ ገንፍሎ፣ አመጹ ያየለው አብዛኛው ባለሙያ ‹ለምን የራሳችንን ሀገር ፍቅር አንገነባም› የሚል ዓይነት ነፋስም ውስጥ ውስጡን ይነፍስ የነበረበት ጊዜ ነበር። ገና ያኔ መሠረቱ ሲጣል ከጥቂቶች ጋር ሆና የደከመችበትንና ስንት ያየችበትን ሀገር ፍቅርን ትቶ አዲስ ሀገር ፍቅር ማቆሙ ለንጋቷ የሚመስልና የሚመጥን ሀሳብ አይደለም። ፍላጎቷ የሚደማበትን ቦታ አክማ የማዳን ቢሆንም፤ ነገሮች የተገላቢጦሽ ፈረጠጡና እርሷንም አሽቀነጠራት።
ንጋቷ ከልካይ ‹አመጸኛ› ተብላ ከምትወደው ሥራና ሀገር ፍቅር ተባረረች። የእርሷ ሀሳብና ሕልሟ ምንም ይሁን ምን፤ ቲያትር ቤቱ ውስጥ የነበራት አቅም ቀላል የሚባል ስላልነበረ፣ ምናልባትም በትሩ አነጣጥሮ እርሷ ላይ ማረፉ ይህንኑ ፍራቻ ይሆናል። የፈሪ ዱላ አንድ ሁለት የለውምና እንቅስቃሴዋ ምቾትን የነፈጋቸው አሳቻ የደመነብስ ወርውረው አገኟት። የምትወደውን ቤት ለቃ ስትሄድ፣ ባልደረቦቿ ግን የውስጥ ትግላቸውን ቀጠሉ። ሁኔታው ቅስሟን ቢሰብረውም፣ ንጋቷ ከሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት ወጥታ በቀጥታ የሄደችው ወደ እርሻ ሥራ ነበር። የጥበብ ሰው ሁሌም ልክ እንደ ገበሬ ነው። በሙዚቃና ቲያትር ማሳ ላይ ቆፍራ፣ አለስልሳ፣ የጥበብ ዘሯን ስትዘራ ነበር። አረሙን ለመንቀል ስትታገል፣ አዝመራውን ለመሰብሰብ፣ ክምሩን ወቅታ ምርቱን ከገለባው ለመለየት ከነፋሱ ስትታገል ነበር፤ ዳሩ ግን ነፋሱ ራስዋኑ ገፍቶ አራቃት እንጂ። ከወዲያ ከተገፋችበት ሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት ውስጥ የነበረው ነገር ከሮ በአንድ ጀንበር 50 ያህል ሠራተኞች ተባረሩና የንጋቷን እጣፈንታ ተጋቱ። እሳቱን በቤንዚን እንደማጥፋት ሆነና አመጹ ከዓመታት በኋላ የ1966ቱ አብዮት አንድ አካል ሆነ።
ከነገሮቿ ሁሉ ንጋቷ ወኔዋ የተለየ ነው። ለሀገሯ ያላት ስሜት ፍቅር ብቻ አይደለም፤ መግነጢሳዊ እሳት አለበት። ታንክና መትረየስ አሰልፈው የቆሙትን፣ ያለ አንዳች መወላወል በክራሯ ልትገጥማቸው ትቆማለች። ፋሽስቱ ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት አፈሹማቸውን ፊት አስቀምጠው “ኢትዮጵያውያንን እኛ እናሠለጥናቸዋለን። እነርሱ ዘፈናቸውም ሆነ ለቅሷቸው አንድ ነው” አለ። ይህ ንግግር ለንጋቷ ከልካይ እሳት ከሚተፋው ታንካቸው በበለጠ የሀገሯን ክብር የሚነካ ነውና ተቀላቅሎ ከተሰበሰበው መአት ሕዝብ መሃል እሳት ለብሳ እሳት ጎርሳ ከተቀመጠችበት አፈፍ! ብላ ተነሳች። ውስጧ በስሜት ነዶ “ይኸውና ዘፈናችን ስሙት!” ብላ ግጥም ዜማውን በድምጽዋ አዘነበችው። በዚህም ሳታቆም “እንካችሁ ለቅሷችንን!” ብላ ደረቷን እየደቃች፣ በዋይታና እሪታ ሙሾውን አወረደችላቸው። በዚህ ድርጊቷ ልባቸው የተነካ ወደ እርሷ ጠጋ እያለ በገንዘብና በያዘው ሁሉ ሽልማቱን አርከፈከፈላት። አፋቸውን ከፍተው ይህን ጉድ ሲመለከቱ የነበሩት ሰላቶ የፋሽስት ወታደሮች የሚሉት ነገር አጡ። የሚያደርጉት ግራ ገብቷቸው ዝም! ብቻ።
ንጋቱ ከልካይ በድምጽዋ ያንቆረቆረቻቸው ዜማዎች ሁሉ ባደመጣት አድማጭ ልብ ውስጥ የቀሩ ጣፋጭ ትዝታዎች ሆነዋል። “ደርባባ ደርባባ” እንዳለችውም እርሷም ደርባቢት ነበረች። ሙዚቃዎቿ በጆሮ ሲገቡ ፍቅር ፍቅር የሚጫወቱ፣ ፍቅርን የሚሸቱ ናቸው፤ እርሷ ግን “እኔ ስለ ሀገር እንጂ ስለፍቅር አልዘፈንኩም” ትል ነበር። ምክንያቱም ሰሙን ፍቅር፣ ወርቁን ሀገር አድርጋ ነበርና የምትዘፍነው።
“…ሰውነቷ እንዲያው ሰውነቷ
…
አመመኝ ደከመኝ ተሳነኝ ቀረሁኝ
ዋ መጨረሻዬን ጠብቃለሁኝ”
የእርሷ መጨረሻ ትልቅ ነበር። ላበረከተችው ታላቅነት ሁሉም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬትን አጎናጽፏታል። ሁሉን ሠርታ፣ ሁሉንም አልፋ ሰውነቷን ለድካም፣ ሰውነቷን ለአፈር መስጠቷ አልቀረም። ስትሸሸው ከኖረችው ሞት ጋር ተፋጠጠች። በስጋዋ ዕድሜን ጠግባ ብቻ ሳይሆን፣ ነብስያዋም እንዳይቆጫት ሆና ሩጫዋን ፈጸመችው።
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን እሁድ ግንቦት 17 ቀን 2017 ዓ.ም