
አዳሚ ቱሉ፡- በኦሮሚያ ግብርና ኅብረት ሥራ ማህበራት ፌዴሬሽን እና በቡልቡላ ደንበል መስኖ ልማት ኅብረት ሥራ ዩኒየን መካከል ቀደም ብሎ በተደረገው የኮንትራት ፋርም ስምምነት መሠረት፤ የዘር መዝራትና የጸረ አረም መድኃኒት መርጨትን ያካተተ የማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ተከናውኗል።
በማስጀመሪያ መርሃ-ግብሩ በ300 ሄክታር መሬት ላይ የበቆሎና ቦለቄ ምርጥ ዘር የተዘራ ሲሆን፤ ጎን ለጎንም የጸረ አረምና ጸረ ተባይ መድኃኒት ርጭት ተካሂዷል።
የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ በሪሶ ፈይሳ ከትናንት በስቲያ በምሥራቅ ሸዋ ዞን አዳሚ ቱሉ ወረዳ ጊዶ ኮምቦልቻ ቀበሌ የማስጀመሪያ መርሃ-ግብሩ ሲከናወን እንደተናገሩት፤ በአካባቢው በግብርና ዘርፍ የተሠማሩ የኅብረት ሥራ ማህበራት ተደራጅተው ወደ ዩኒየን አድገዋል። ዩኒየኑ ከኦሮሚያ ግብርና ኅብረት ሥራ ማህበራት ፌዴሬሽን ጋር የኮንትራት ፋርም ስምምነት በማድረግ ወደ ሥራ ገብቷል ብለዋል።
አርሶ አደሮች በማህበርና ዩኒየኖች ተደራጅተው መሥራታቸው ከምርት ማምረት እስከ ገበያ ትስስር ባሉ ሂደቶች ተጠቃሚ የሚያደርጋቸው መሆኑን አስረድተዋል።
በተለይም ከገበያ አኳያ ስምምነት መደረጉ አምራች ዩኒየኖች የት እንሸጣለን? በምን ያህል ዋጋ እንሸጣለን? ብለው ስጋት እንዳይፈጠርባቸው እና ፌዴሬሽኑም የምርት እጥረት ይገጥመኛል ብሎ እንዳያስብ ያደርገዋል ሲሉ ገልጸዋል።
ዩኒየኖች የመሬት አቅርቦት ተደርጎላቸው እና የግብርና ፓኬጆችን ተጠቅመው ምርትና ምርታማነትን እንዲያሳድጉ የክልሉ ግብርና ቢሮ የራሱን እገዛ እያደረገ መሆኑን ተናግረው፤ በእለቱ የተዘራው መሬትም በየደረጃው ባሉ የክልሉ ግብርና ቢሮዎች ድጋፍ እና ትብብር ዩኒየኑ በጊዜያዊነት እንዲጠቀምበት የተሰጠው መሆኑን ተናግረዋል።
የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ እቅዶችን እያወጣ እና እየተገበረ፤ አርሶ አደሮች በግል፣ በማህበርና በዩኒየን ደረጃ የሚሠሯቸውን የግብርና ሥራዎች ተነቃቅተው በመሥራት ምርታማነትን እንዲያሳደጉ እያገዘ እንደሚገኝ አቶ በሪሶ አስረድተዋል።
በኦሮሚያ ግብርና ኅብረት ሥራ ማህበራት ፌዴሬሽን ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ አለማየሁ ተሾመ በበኩላቸው፤ ፌዴሬሽኑ በሥሩ እስከ 68 የሚደርሱ ዩኒየኖች እንዳሉት ገልጸው፤ እነዚህንም በተለያየ መንገድ ይደግፋል ብለዋል። በእዚሁ መሠረት ኬሚካልን ጨምሮ የግብዓት አቅርቦት፣ የብድር፣ የማማከር፣ የስልጠና ፣ የክትትልና ድጋፍ ሥራዎችን ይሠራል ሲሉ አስረድተዋል።
የእለቱ መርሃ-ግብር የኮንትራት ፋርም ማስጀመሪያ እንደሆነ ጠቅሰው፤ መሬቱ ሲታረስ ጀምሮ ፌዴሬሽኑ ሙያተኛ መድቦ ክትትልና ድጋፍ እያደረገ እንደነበር አስታውሰዋል። የአፈር ማዳበሪያና የኬሚካል አቀርቦት በራሱ ወጪ ገዝቶ እንዳቀረበም ተናግረዋል። ዩኒየኑ የሚያመርተውን የበቆሎ ምርት በወቅቱ በሚኖረው ገበያ ላይ አስር በመቶ ጭማሪ በማድረግ ፌዴሬሽኑ ላሉት ፋብሪካዎች ግብዓት የሚረከብ ስለመሆኑም ገልጸዋል።
የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ ምክትል ኃላፊ እና የግብይት ዘርፍ አስተባባሪ አቶ አበራ አቦሴ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ የዩኒየኖችና መሠረታዊ ማህበራት አንዱ ችግር የገበያ እጦት ነው፤ የገበያ ትስስር እንዲፈጠርና ማህበራትና ዩኒየኖች በገበያ ተወዳዳሪ ሆነው የድርሻቸውን እንዲያገኙ ለማድረግ ኤጀንሲውና አጋር አካላት ርብርብ እያደረጉ ናቸው። በኮንትራት ፋርም የሚገኘው ምርት ከማሳ እስከ ፋብሪካ ጥራቱ ተጠብቆ የፋብሪካውም ምርት ገበያ ውስጥ ሲገባ የተወዳዳሪነት አቅሙ እንዲጨምር እና ተፈላጊ እንዲሆን ኤጀንሲው ድጋፍና ክትትል የሚያደርግ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።
አምራቾች በሀገር ውስጥ እና በውጭ ገበያው የተወዳዳሪነት አቅም እንዲኖራቸው ኤጀንሲው የግንዛቤ ማስጨበጥ፣ የድጋፍና ክትትል ሥራ የሚሠራ እንደሆነም ገልጸዋል።
የቡልቡላ ደንበል መስኖ ልማት ኅብረት ሥራ ዩኒየን ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ኡካ ገመቹ፤ ዩኒየኑ አራት ማህበራት ተዋህደው በ663ሺህ ብር መናሻ ካፒታል የተቋቋመ እንደሆነ ገልጸዋል። ዘር የማብዛት ፣ ቋሚና ጊዜያዊ አትክልትና ፍራፍሬዎችን የማምረት ተግባራትን እያከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።
ዩኒየኑ ከተመሠረተ ገና አጭር እድሜ እንዳስቆጠረ ተናግረው፤ በቀጣይ በበጋ መስኖ ሥራዎችና በእንስሳት እርባታ ላይ ጭምር በስፋት የሚሠራ መሆኑን ገልጸዋል። ከኦሮሚያ ግብርና ኅብረት ሥራ ማህበራት ፌዴሬሽን ጋር ያደረጉት የኮንትራት ፋርም ጥራት ያለው ምርት ለማምረትና የገበያ እድል ለማግኘት እንደሚረዳቸው የዩኒየኑ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ኡካ ተናግረዋል።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን እሁድ ግንቦት 17 ቀን 2017 ዓ.ም