ባለዘርፈ ብዙ ፋይዳው የኪን ኢትዮጵያ ቡድን

ጥበብ ሀገር በመገንባት ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ይታወቃል። በዘመናት ውስጥ ሀገርና ሕዝብን በስልጣኔ፣ በታሪክ፣ በባሕል፣ በማንነት እና በእሴት አቅፎ በመያዝ አይነተኛ ሚና ተጫውቷል።

ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ቀደምት ከሚባሉ በባሕል እና በሥነ ጥበብ ከሚጠቀሱ ቀደምት ሀገራት መካከል አንዷ ናት። ይህን የኢትዮጵያን ከፍታ የሚያሳዩ የጥበብ ሥራ ሁነቶች በሀገር ውስጥም በውጭ ሀገሮችም በተለያየ ጊዜያት ተካሂደዋል። ለአብነትም በውጭ ሀገሮች በ1978 ዓ.ም በቀድሞው ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለማሪያም ዘመን የተካሄደውን ‹ሕዝብ ለሕዝብ› የኪነጥበብ ቡድን መጥቀስ ይቻላል።

በዚህ ቡድን ኢትዮጵያ በ1987 ድርቅ ባጋጠማት ወቅት ዜጎችን ለመታደግ ለደረሱ ሀገሮችና መንግሥታት ምስጋና ቀርቦበታል። ይህ የኪነጥበብ ቡድን በታላቅ መነሳሳት በመላ ዓለም በመዞር ነው ይህን ምስጋና ያቀረበው። በዚህም ኢትዮጵያን በመግለጥ፣ ባሕል እና ሥርዓቷን፣ ወግና እሴቷን ለዓለም ሕዝብ በማስተዋወቅ የድርሻውን ተወጥቷል።

ትውልድ በሽግግር ሂደት ውስጥ አልፎ ከሰላሳ ዘጠኝ ዓመታት በኋላ ኢትዮጵያን የሚያስተዋውቅ ቡድን፤ ‹ኪን ኢትዮጵያ- የኢትዮጵያ ማንሰራራት ብስራት› በሚል መሪ ሀሳብ ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ለማስተዋወቅ ዝግጅቱን ጨርሶ ሰሞኑን ይፋዊ አሸኛኘት ተደርጎለታል።

በሽኝት መርሀ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ፣ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ፣ የኢፌዴሪ ባሕል እና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፣ የኪነ ጥበብ ዘርፉ እንግዶች፣ የሀገራት አምባሳደሮች እንዲሁም ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።

በመርሀ ግብሩ ላይ የኢፌዲሪ ባሕል እና ስፖርት ሚኒስትር ክብርት ሸዊት ሻንካ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር እንዳሉት፤ የባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር በአዋጅ በተሰጠው ስልጣን መሰረት የኢትዮጵያን ቋንቋ፣ ባሕል፣ ወግ፣ እሴት፣ ማንነት፣ ብዙሀነት በማስተዋወቅ ረገድ ሚናው የጎላ ነው።

‹‹የአብሮነትን እና የትብብር መንፈስን በመፍጠር አንድ ሀገር እና አንድ ሕዝብ በመገንባት ረገድ ኪነጥበብ አንድምታው ብዙ ነው›› ሲሉ ሚኒስትሯ ተናግረዋል። ሀገራችን የሰው ልጅ መገኛ ምድር መሆኗን ጠቅሰው፣ ይሄን ዕድል ለማኅበረሰብ ለውጥ፣ ለሀገር ብልጽግና፣ ለትስስርና ለትቅቅፍ ለብዙሀነትም ልንጠቀምበት ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል።

ከዛሬ ሰላሳ ዘጠኝ ዓመት በፊት ሕዝብ ለሕዝብ በተሰኘው የኢትዮጵያ ኪነት ቡድን ‹አደይ አበባ› በሚል መሪ ሃሳብ የተሠራውን ሀገር የማስተዋወቅ ጉዞ ሚኒስትሯ አስታውሰው፣ ከአራት አስርት ዓመታት በኋላ በተመሳሳይ ሀሳብ ስለ ኢትዮጵያ የተቧደኑ እና ያበሩ የኪነጥበብ ባለሙያዎች መፈጠራቸውን ገልጸዋል።

በኪነ ጥበብ የተደገፈ ሀገርና ሕዝብን መሰረት ያደረገ የሕብረብሄራዊነት አቋም ራስን ከማስተዋወቅ፣ ቱሪዝምን ከመግለጥ፣ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን ከማጠንከር፣ ገንቢ ትርክት ከመፍጠር አኳያ ፋይዳው ብዙ መሆኑን አመልክተው፣ ይህ ሥራ ቀጣይነት እንደሚኖረውም ገልጸዋል።

ከሀምሳ በላይ ብሔር ብሔረሰቦችን ያቀፈው የኪን ኢትዮጵያ ቡድን በአጭር ቃል ቢገለጽ ‹የኢትዮጵያዊነት ቀለም› የሚል መልክ እንደሚሰጠው ሚኒስትሯ አስታውቀዋል። ‹‹የጋራ ሀገር በመገንባት፣ አንድነታችንና አብሮነታችንን በማጽናት፣ በማስቀጠል፣ በመጠበቅ፣ በማጠንከር ከብዙሀነት ውስጥ የተወለዱ እንዲህ ያሉ የሕዝብ መልኮች እጅግ ብዙ ዋጋ አላቸው›› ሲሉ አመላክተዋል።

‹‹ሀገር የተደራችበት የእርስበርስ መስተጋብር እኛጋ ብቻ እንዳይቀር ማንነታችንን ሌሎች እንዲያውቁ ረጅም ርምጃዎችን ሄደናል። ኢትዮጵያን ያቀፈ፣ ያጎላ ተሳትፎ በቱሪዝሙም ሆነ በሌሎች ዘርፎች ላይ እንደ አንድ የኢኮኖሚ ምሰሶ ተደርጎ የሚወሰድ በመሆኑ ተሳትፎው ቀጣይነት እንዲኖረው እንሠራለን›› ሲሉም ተደምጠዋል።

ሰፊና ግዙፍ የተፈጥሮ ምኅዳር ያለን ሕዝቦች ነን። አስቻይ ሁኔታዎችን በመፍጠር የእድሉ ተጠቃሚ ለመሆን የሁላችንንም ኃላፊነት ይጠይቃል። ስለሀገርና ሕዝብ የምናምጠው በጎ ምጥ ነገ ላይ የተባረከ ትውልድ በመስጠት የታመነ ነው። ሀገራችን የጋራ ኃላፊነት፣ የጋራ ትብብር፣ የጋራ ሀሳብ ትፈልጋለች በኪነ ጥበቡ ላይ የታየው በጎ የቡድን ስሜት የጋራ ለውጥን የሚሰጥ፣ እምቅ የተፈጥሮ ሀብታችንን እንድንጠቀም፣ ወደገንዘብ እንድንቀይር የሚያበረታታ በመሆኑ ይበል የሚያሰኝ ነው ብለዋል።

ከየትም እንምጣ መጠሪያ ስማችን ኢትዮጵያዊ ነው ያሉት ክብርት ሚኒስትሯ፣ የምንኖረው ኢትዮጵያን ተሸክመን፣ ስለሌላው ግድ እያለን በመሆኑ በሀገራችን ውስጥ የሚሆነው ሁሉ የጋራችን ነው። የተደበቁ እምቅ ውበቶቻችን አደባባይ ወጥተው ሌሎች እንዲያዩዋቸው፣ እንዲደነቁባቸው መደረጉ ይበል የሚያሰኝ ነው ሲሉ አስገንዝበዋል።

እንደ ሀገር ዓለም ሊያይልን የሚገባ ብዙ ሀብቶች አሉን። ማንነታችን እና ብዙሀኑ ባህላችን ከትውውቅ ባለፈ ለቱሪዝም ዘርፉ ወሳኝ ሚናን ይጫወታል። በመሆኑም ማስተዋወቁ ሌሎች እንዲያውቁን አውቀውንም እንዲጎበኙን እድል ይሰጣል ብለዋል።

እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ነጣጣይ ወጎችን ሽሮ ለትቅቅፍ እና ለትስስር ጥበብ ያለው ሚና አይነኬ ነው። እንዲህ ያሉ ብዙሀኑ እሳቤዎች ለሀገራዊ አውድ ያስፈልጋሉ። የልኡክ ቡድኑ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በመዞር ኢትዮጵያን በማስተዋወቅ እንደ ሀገር የተሰጠውን አደራ እንዲወጣም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የልኡክ ቡድኑን በአንድ ፕሮዳክሽን በማሰባሰብ፣ በማሰልጠን፣ አንድ ዓላማ ይዞ እንዲነሳ በማድረግ ረገድ ከፍተኛውን ሚና የተጫወተው የሻኩራ ፕሮዳክሽን ባለቤት እና ሥራ አስኪያጅ የሙዚቃ ባለሙያ እና አቀናባሪ ካሙዙ ካሳ ስለቡድኑ ማብራሪያ ሰጥቷል።

የባሕል እና ስፖርት ሚኒስቴር ያወጣውን ጨረታ በማሸነፍ ሀገሪቱን ለማስተዋወቅ ዕድል በማግኘቱ የተሰማውን ደስታውን ገልጾ፣ ሀገሪቱ ካላት የታሪክ፣ የማንነት፣ የዘመናዊነት እና የቀደምትነት ቱባ ቀለም አኳያ የተቀበልነው ኃላፊነት ትልቅ ነው ሲልም አስታውቋል፤ ለእዚህም የልኡክ ቡድኑ አባላት በከፍተኛ ወኔ እና ቁርጠኝነት አደራቸውን እንደሚወጡ አረጋግጧል።

መንግሥት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሚከተለው የለውጥ ጎዳና ኢትዮጵያዊነት ላይ ያተኮሩ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙ ጠቅሶ የተቀበልነው ኃላፊነትም የዛ ተልዕኮ አንዱ ውጤት ነው ሲልም ተናግሯል።

የሙዚቃ ባለሙያው አያይዞ ሀገር ውስጥ ብቻ ተወስኖ የቆየውን የታሪክ እና የባሕል ምንነትን የመግለፅ ሥራ ዓለም አቀፍ መልክ በመስጠት ተጠቃሚ ለመሆን እየሠሩ እንደሚገኙ አመላክቷል።

እሱ እንዳለው፤ በትብብር የተገኘ ጠንካራ የማንነት ግንባታ በሀገር ላይ ወሳኝ ሚና መጫወት ይችላል፣ ለልማት፣ ለዕድገት፣ ለኢኮኖሚ እና ለማኅበራዊ መስተጋብር ወሳኝነቱ አጠያያቂ አይሆንም። በመሆኑም ከሕዝብ የተቀበልነውን አደራ በቁርጠኝነት ከዳር ለማድረስ እንሠራለን ሲል ገልጧል።

በመድረኩ ላይ ለዓለም አቀፉ ጉዞ ከተሰናዱ ዝግጅቶች መካከል የተወሰኑት ለተመልካች ቀርበዋል። ‹የሰው ልጅ ክቡር› በሚለው የእጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) ሙዚቃ መክፈቻውን ያደረገው መድረኩ፣ የተለያዩ ብሔረሰቦችን ሙዚቃ፣ ጭፈራ፣ አለባበስ እንዲሁም ባሕል እና ማንነት በማሳየት ታዳሚውን አዝናንቷል። የብሔረሰቦችን ባሕላዊ አለባበስ ጨምሮ በልዩ ተሰጥኦ በተካኑ የሰርከስ ቡድኖችም የተለያዩ ስፖርታዊ ዝግጅቶች ቀርበዋል።

ዓድዋን እና ኢትዮጵያዊነትን የሚያስታውሰው ጥልቅ ሙዚቃ ከሰብዐዊነት፣ ከነጻነት፣ ከእኩልነት፣ ከጥቁርነት እና ከመሰል ጅጋኔ አኳያ ላቅ ያለ ትርጉም ነበረው። በክራር፣ መስንቆ፣ ከበሮ፣ ጡሩንባ እንዲሁም በመሰል ሀገር በቀል መሳሪያዎች የታጀበው ዝግጅት በዓይነቱ የተለየ፣ ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊነትን በማስተዋወቅ ረገድም ትልቅ ሚና እንዳለው ማስገንዘብ የተቻለበት ነው።

በመቀጠል የመሀሙድ አሕመድ ‹ሰላም› የሚለው ሙዚቃ በመሳሪያ በተቀነባበረ (በክላሲካል) እና በድምጽ ተስተጋብቷል። ሙዚቃው ሰላም ለሰው ልጅ ያለውን ዋጋ ከመግለጽ አኳያ ጠንካራ መልዕክት የተላለፈበትም ነው። ሰላም ወዳድነታችን ከሀገር አልፎ ዓለም አቀፍ ምኞታችን መሆኑንም በሙዚቃው ውስጥ ለመታዘብ ችለናል።

በሁነቱ ላይ የተላለፈው ዝግጅት ከያኒያኑ ተዘጋጅተው እና ጊዜ ወስደው በተቀናጀ መልኩ የሠሩት ስለመሆኑ ከገቢረ ትዕይንቱ ይታወቅ ነበር።

ብዙዎች ያደነቁት፣ ያጨበጨቡለት ይህ መድረክ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎን የመዝጊያ ንግግር ተቋጭቷል። ለልኡክ ቡድኑ እና ለተገኙት እንግዶች ልባዊ ምስጋና በማቅረብ ንግግራቸውን የጀመሩት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ የኢትዮጵያን የብዙሀነት ከፍታ በኪነ ቡድኑ በኩል የማየት ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል።

እንደ አፈ ጉባኤው ገለጻ፤ ኢትዮጵያ የረጅም ዘመን የሀገረ መንግሥት እና የማኅበረሰብ ትስስር ያላት ሀገር ናት። ቱባ ባኅሎቿ፣ ሥርዓት እና እሴቶቿ፣ ከድንቅ ተፈጥሮዎቿ ጋር የከበቧት መሆኗ ከሌላው ሀገር ልዩ ያደርጋታል። በፈጠራ ጥበብ እና በመሰል ሁነቶች የታደልነውን የተፈጥሮም ሆነ ሰው ሰራሽ ጸጋዎቻችንን ማስተዋወቅ የሁላችንም ኃላፊነት ነው ሲሉ ጠቁመዋል።

ዛሬ ላይ በኢኮኖሚ እና በቴክኖሎጂ የበላይነት ስልጡን የምንላቸው ሀገራት እንደሙዚቃና ፊልም ያሉ የኪነጥበብ ዘርፎቻቸውን ለሚገባው ዓላማ በሚገባው መንገድ ተጠቅመዋል ሲሉ ጠቅሰው፣ ያላቸውን እምቅ ሀብት ሌላውም እንዲያውቅላቸው የሚፈልጉትን ሁሉ በፊልም እና በሙዚቃቸው ለዓለም ሀገራት ማስተዋወቃቸውን ጠቅሰዋል።

እኛም ኪነጥበብን በመጠቀም ያለንን እምቅ የተፈጥሮ ትሩፋት በተገቢው መንገድ ለተገቢው ዓላማ ለመጠቀም ሰፊ እድል አለን። ድንግል የተፈጥሮ ሀብቶቻችን፣ ቱባ የሕብረ ብሄራዊነት ውበቶቻችን የማንነት ስያሜዎቻችን ሆነው ዘመናትን ተሻግረዋል ሲሉም ጠቅሰው፣ እነዚህን ውበቶቻችንን ከመጠበቅ፣ ከማስቀጠል ጎን ለጎን ኪነ ጥበብን በመጠቀም ለተቀረው ዓለም የማስተዋወቅ ሥራ አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸዋል።

በቱሪዝሙ ዘርፍ እያደረግን ያለው እንቅስቃሴ ለብዙ ሀገራዊ ዕድሎች በር የሚከፍት ነው። ይህ በኪነጥበብ መታገዝ ከቻለ ደግሞ የበለጠ አትራፊ እና ፍሬያማ የሚሆንበት ዕድል የሰፋ ነው ሲሉ አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገልጸዋል። በርትተን ከሠራን እና ለአንድነት ከተጋን በኪነ ጥበብ እገዛ ታሪካቸውን እንደቀየሩ ሀገራት በፊተኝነት የምንጠራበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም ብለዋል።

ሰፊ እና ሀገር ሊጠቅሙ የሚችሉ የቱሪስት መዳረሻዎች አሉን፤ ነገር ግን በኪነ ጥበብ ባለመታገዛቸው እምብዛም ጥቅም ላይ አይታይም ያሉት አፈ ጉባኤው፣ በዚህ በኩል መንግሥት የጀመረው መልካም እንቅስቃሴ አድጎ እና በብዙዎች ዘንድ ተደራሽ ሆኖ በርካታ ለውጦችን እያስተናገደ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል። የኪነጥበብ ባለሙያዎች ኃላፊነታቸውን በመወጣት ዘርፉ ላይ አሻራቸውን ማሳረፍ ከቻሉ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንዲሉ ዘርፉም የበለጠ እንዲነቃቃ ዕድል እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

እንደ አፈጉባዔው ማብራሪያ፤ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ፣ በሌማት ትሩፋት፣ በቱሪስት መዳረሻዎች፣ በፓርኮች እና መሰረተ ልማቶች፣ በኮሪደር ልማት፣ በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በቴክኖሎጂ ለውጥ እያመጣች ትገኛለች፤ ለውጡም የሚታይ እና የሚዳሰስ ነው።

ይሄ መንግሥታዊ ጥረት በግለሰቦች እና በከያኒያን መታገዝ ከቻለ ለውጡ ይበልጥ አመርቂ መሆን ይችላል፤ ለተጀመረው የለውጥ እና የእድገት ርምጃ ኪነጥበብ ወሳኝ ሚና ይጫወታል ሲሉ አመልክተው፣ ሁሉም በሙያው ለኢትዮጵያ እንዲተጋ እና የበኩሉን እንዲያደርግ የአደራ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ያሉንን መጠቀም ከቻልን ወደሌሎች ሳናይ ሌሎች ወደ እኛ እንዲያዩ ማድረግ እንችላለን ያሉት አፈ ጉባኤው፣ ቀጣዩ ጊዜ የኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያውያን እንዲሆን የምናሳርፋት እያንዳንዷ አሻራ ዋጋ አላት፤ የተሰጠን ከማንም ይበልጣል፤ ግን አልተጠቀምንበትም፤ ለመጠቀም በሙያችን በትጋት መሥራት ወሳኝ ነው ብለዋል።

የልኡክ ቡድኑ ኢትዮጵያን በመግለጥ፣ በማስተዋወቅ እና በማስቀጠል ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለበት አስገንዝበው፣ ከሕዝብ የተቀበለውን አደራ በታማኝነት፣ በቁርጠኝነት፣ በፍጹም ትጋት እንዲወጣ አደራ በማለት ባንዲራ በመስጠት ሸኝተውታል።

በኢትዮጵያዊነት ወዝ የደመቀው የባንዲራ ርክክብ በምስጋና እና በቸር ያድርሳችሁ ተቋጭቶ በስተመጨረሻም በአንጋፋው ድምጻዊ የክብር ዶክተር ጥላሁን ገሰሰ ‹ኢትዮጵያ› ሙዚቃ ዝግጅቱ ፍጻሜውን አድርጓል። ሁሉም ታዳሚ ከመቀመጫው ተነስቶ በልዩ ሀገራዊ መንፈስ ኢትዮጵያን ተቀኝቷል።

በመድረኩ ላይ ተሳታፊ የሆነውና አዲስ ዘመን ጋዜጣ በጉዳዩ ላይ ያነጋገረው አርቲስት አብረሀም ግዛው የዝግጅቱን ግዝፈት አንስቶ ኢትዮጵያ የቡና መገኛ ሀገር ከመሆኗ ጋር በተያያዘ የቡድኑ ተልዕኮ አንድምታም የላቀ መሆኑን ጠቁሟል። ከብሪክስ ሀገራት ባለፈ መላው ዓለም አትኩሮት እንዲሰጠው ሆኖ የተሰናዳ መሆኑንም ጠቅሶ፣ ባሕሏን፣ ማንነቷን በአጠቃላይ የተፈጥሮ ሀብቷን እንድታስተዋውቅ ጥሩ ዕድል እንደሆነ ገልጿል። ከጥቅሙ አኳያ ሲታይ እንደዘገየ በማንሳትም ወደፊት ነገሮች ተስተካክለው ቀጣይነት ያለው ቢሆን የተሻለ እምርታ እንደሚያመጣ አንስቷል።

ኢትዮጵያ ያሏት የቱሪዝም መስህቦች በበቂ ሁኔታ እንዳልተተዋወቁ አርቲስት አብርሃም ጠቅሶ፣ ይህ የኪን መድረክ የውጪ ቱሪስቶችን ከመሳብ ባለፈ የውጪ ባለሀብቶች ሀገር ውስጥ በመምጣት ኢንቨስት እንዲያደርጉ ትልቅ አቅም እንዳለውም አስታውቋል። ምዕራባውያን ሀገራችንን በጦርነት፣ በርሀብ፣ በኋላ ቀርነት የማሰብ አመለካከታቸውን በበጎ ለመቀየር የገጽታ ግንባታ በማድረግ ረገድ ምቹ ሁኔታ የተፈጠረበት መሆኑንም አመላክቷል።

ዘላለም ተሾመ

አዲስ ዘመን እሁድ ግንቦት 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You