
የእግር ኳስን ሕይወት አንድ ብሎ የጀመረው እንደማንኛውም አፍሪካዊ ታዳጊ ተጫዋች በአካባቢው በሚገኙ አቧራማ ሜዳዎች ከእኩዮቹ ጋር የጨርቅ ኳስ በማንከባለል ነው። ይህ በመንደር ውስጥ የተጀመረ የእግር ኳስ መንገድ ከፍ ብሎም የአሁኑ የሲዳማ ቡና ክለብ አሠልጣኝ አዲሴ ካሳ፤ የታዳጊዎች ፕሮጀክት ተቀላቅሎ ወደ ትልቅ ደረጃ እንዲያማትር መሸጋገሪያ ሆኖታል።
በኋላም ወደ አንጋፋው የሀዋሳ ከነማ ስፖርት ክለብ በመቀላቀል በግብ ጠባቂነት ለሰባት ዓመታት ያህል እንዲጫወት አስችሎታል። የሐይቆቹ የግብ ዘብ ሆኖ ባገለገለባቸው ዓመታት እንደ ኮከብ መድመቅ የቻለ አይረሴ የእግር ኳስ ተጫዋች መሆን የቻለበትን ድንቅ ብቃት እንዳሳየ በወቅቱ የነበሩ የስፖርት ቤተሰቦች ይመሰክራሉ። ከሀዋሳ ከተማ በመቀጠል ወንጂ እና ዲላ ከተማም ተጫውቶ ያሳለፈባቸው ክለቦች ናቸው።
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ድንቅ ብቃት ያሳዩና ምስጉን ስም ያተረፉት ሙሉጌታ ምህረት፣ ሽመልስ በቀለ ፣ በሀይሉ አሰፋ (ቱሳ ) ፣ አንዷለም ነጋ (ቢጣ) ፣ ግርማ በቀለ እና ሌሎችም በሀዋሳ እግር ኳስ ውስጥ ስማቸው ሁሌም ከሚነሳ ኮከብ ተጫዋቾች ጋር በመሆን ሐይቆቹን በኢትዮጵያ እግር ኳስ ጠንካራ ተፎካካሪ ማድረግ የቻለም ምርጥ ግብ ጠባቂ ነበረ፤ ፍቃዱ ዘውዴ (ደያስ)።
በአንድ ወቅት ድንቅ ግብ ጠባቂ ሆኖ በተለይም በሀዋሳ ከተማ እግር ኳስ ታሪክ ደማቅ አሻራውን ያኖረው ደያስ፤ አሁን ላይ ከባድ የሕይወት ፈተናን ለመጋፈጥ ተገዷል። የቀድሞው ግብ ጠባቂ ዛሬ ላይ በዲላ ከተማ እጅግ ከባድ የሆነውን የጎዳና ሕይወት እያሳለፈ ይገኛል። በርካታ የስፖርት ቤተሰቦችም “ፍቃዱ ዘውዴን በመደገፍ የበኩላችንን በመወጣትና ወደ ተሻለ የቀድሞው ኑሮው እንዲመለስ አለንልህ እንበለው።” በማለት የቀድሞውን ግብ ጠባቂ ሕይወት ለመታደግ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ በቅርቡ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች በጎዳና ላይ ሕይወቱን እየገፋ እንዳለ የተነገረውን የቀድሞ ግብ ጠባቂ ደያስ ምን እንደገጠመው አነጋግሮት ነበር። “ከእግር ኳስ ዓለም የወጣሁት ሳልወድ ሁኔታዎች አስገድደውኝ ነው” ይላል ፍቃዱ ዘውዴ ያለበትን አስከፊ ሕይወት በተሰበረ ድምፅ ሲያስታውስ።
ፍቃዱ ትውልድና እድገቱ በርካታ የእግር ኳስ ተጫዋቾችን ባፈራችው ሀዋሳ ከተማ ሲሆን፤ ገና በልጅነቱ በእግር ኳስ ልቡ እንደተነደፈ ይናገራል። በሰፈር ውስጥ በጨርቅ ኳስ የጀመረው የእግር ኳስ ሕይወቱ በፕሮጀክት አልፎ በሀዋሳ ከነማ ከሰባት ዓመታት በላይ በዋና ግብ ጠባቂነት እስከ ማገልገል እንደደረሰ ያስታውሳል።
“ጭምትነቴ ጎድቶኛል” የሚለው ፍቃዱ በተለያዩ አሠልጣኞች በነበሩ ጫናዎች ሀዋሳ ከነማን በመልቀቅ ወደ መተሀራ ያቀና ሲሆን፤ አንድ ዓመት ተጫውቶ ወደ ሀዋሳ ተመልሷል። ቀጥሎም የቀድሞውን ዲላ ከነማ ተቀላቅሎ ከተጫወተ በኋላ በአሁኑ ይርጋጨፌ ቡና ሴቶች ቡድን በበረኛ አሠልጣኝነት መሥራት ይጀምራል።
የሕይወቱ አስከፊው አጋጣሚ ይህ ወቅት እንደሆነ የሚናገረው ፍቃዱ “ፈግቼ እያሠለጠንኩ ደመወዝ የሚበላ ሌላ አሠልጣኝ ነበረ፤ይህ ሁኔታ ቀስ በቀስ ሕይወቴን አመሰቃቅሎታል” ሲል ይናገራል።
“ደመወዝ ማጣት ለድህነት ዳርጎኝ ቀን ሥራ ወደ መሥራት ገብቼ ነበር” የሚለው ደያስ “ኑሮ ፊቷን አዙራብኝ ሚስቴ ልጄን ይዛ ከሄደች በኋላ ነገሮች ተመስቃቅለውብኝ ለጎዳና ሕይወት ተዳረኩኝ” በማለት የገጠመውን ተናግሯል።
“ራሴን ጥዬ ጎዳና ባየኝ በአንድ የሚያውቀኝ ሰው አማካኝነት አሁን ላይ የገንዘብ ድጋፍ እየተሰባሰበልኝ፤የሥነ ልቦና ምክርም እያገኘሁኝ ነው” የሚለው ፍቃዱ ዘውዴ፣ አሁን ላይ በዲላ ከተማ ሆኖ ድጋፍ እየተሰባሰበለት ይገኛል። ከቲክቫህ ኢትዮጵያ ጋር በነበረው ቆይታም ወደ እግር ኳስ ሕይወቱ በግብ ጠባቂ አሠልጣኝነት መመለስ እንደሚፈልግ ገልጿል።
ፍቃዱን ለመደገፍ የተዋቀረው አስተባባሪ ኮሚቴ በስሙ የተከፈተውን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቁጥር (1000226570407) ይፋ አድርጓል። የስፖርት ቤተሰቡም የቀድሞውን ግብ ጠባቂ ከወደቀበት ለማንሳት ጥሪ ቀርቦለታል። የተለያዩ ክለቦችም ይህን ጥሪ እየተቀበሉ ይገኛሉ። ፋሲል ከነማ ስፖርት ክለብ የበኩላቸውን ድጋፍ ለማድረግ የቡድኑ አባል በሆነው በጌታነህ ከበደ በኩል የተዘጋጀውን የድጋፍ ደብዳቤ ተቀብለዋል። በተመሳሳይ የመቻል ስፖርት ክለብም የበኩላቸውን ድጋፍ ለማድረግ የቡድኑ አባል በሆነውና የልብ ጓደኛው በነበረው በአንጋፋው የእግር ኳስ ተጫዋች በሽመልስ በቀለ በኩል የተዘጋጀውን የድጋፍ ደብዳቤ ተቀብለው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን እሁድ ግንቦት 17 ቀን 2017 ዓ.ም