
ፖለቲከኛነት ትልቅ ማኅበራዊ እና ሀገራዊ ኃላፊነት ነው። ከሁሉም በላይ ከራስ ጋር እርቅን፤ ለማኅበረሰባዊ እሴቶች ታማኝ መሆንን፤ የማኅበረሰብን የለውጥ ፍላጎቶች አክብሮ መጓዝን፤ ትናንት፣ ከዛሬ፣ ዛሬ ከነገ የተሻለ ነው በሎ ማመንን፤ ለዚህ የሚሆን የአስተሳሰብ ልእልና እና የተግባር አርበኝነትን የሚጠይቅ ነው።
በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚገኝ ፖለቲከኛ የተልዕኮ ግቡ እወክለዋለሁ የሚለውን ማኅበረሰብ/ ሀገር ከአንድ የታሪክ ምዕራፍ ወደ ተሻለ ቀጣይ የታሪክ ምዕራፍ በስኬት ማሻገር ነው። የዛን ማኅበረሰብ ማኅበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ሕይወት ዘመኑን በሚዋጅ አስተሳሰብ በመግራት የተሻሉ ነገዎችን መፍጠር የሚያስችል የሀሳብ ከፍታ መፍጠር ነው።
የእኛን ሀገር ጨምሮ የተለያ የዓለም ሀገራት ታሪክ የሚያሳየው ይህንኑ ተጨባጭ እውነታ ነው። በየዘመኑ የነበሩ ፖለቲከኞቻችን ሀገርን እንደ ሀገር የሚያዩበት መነጽርም ሆነ ስለሀገር የነበራቸው እይታ ትናንት ሆነን ካለፍነው የታላቅነት ትርክት በቁጭት የሚቀዳ፤ ለሀገር የከፍታ ትንሳኤ እራስን ከመስጠት የሚነሳ ነው።
ይህ እውነታ ሀገራችን ብዙ አስቸጋሪ እና የመስዋዕትነት ገድል በጠየቁ የፍትህ እና የነጻነት አርበኝነት ውስጥ እንድታልፍ፤ በዚህም ነጻነቷን አስጠብቃ እንድትኖር አስችሏታል። በየዘመኑ ያጋጠሟትን፤ ሀገረ መንግሥቱን ሳይቀር የሚገዳደሩ ፈተናዎችን ተሻግራ ዛሬ ላይ ሉዓላዊነቷን ብቻ ሳይሆን ነገን በብዙ ተስፋ መጠበቅ በሚያስችል ሕዝባዊ መነሳሳት ውስጥ ነች።
ይህም ሆኖ፤ በተለይም ከ1960 ዎቹ የተማሪዎች እንቅስቃሴ የተስተዋሉ፤ ከማኅበረሰቡ መንፈሳዊ እና ማኅበራዊ እሴት ያፈነገጡ የፖለቲካ አስተሳሰቦች በቀደሙት ዘመናት በነበረ የፖለቲካ ስብራት ላይ ”በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” ሆነዋል። ሀገረ መንግሥቱን ሳይቀር የሕልውና አደጋ ውስጥ የከተቱበት ሁኔታ ተስተውሏል።
በጠላትነት እና ፍጹም በሆነ ተቃርኖ የተሟላው፤ ለመነጋገር እና ለመወያየት ዕድል የማይሰጠው የዘመኑ የፖለቲካ አስተሳሰብ፤ አንድ ቋንቋ የሚናገረውን የዘመኑን ትውልድ ቃታ አስቦ፤ መግደልን ሆነ መሞትን ያቀለለ ተጨማሪ የፖለቲካ ትርክት ይዞ መጥቷል። አስተሳሰቡ በነጻ አውጪ ስም ሀገር እና ሕዝብን ብዙ ያልተገባ ዋጋ ላስከፈለ የእርስ በርስ ግጭት ዳርጓል። ይህም አሁን ላይ ከግጭት ነጻ የሆነ የፖለቲካ አውድ ለመፍጠር የሚደረገውን ሀገራዊ ጥረት እየፈተነው ይገኛል።
ይህ መግደል እና መሞትን ያቀለለ የፖለቲካ ባሕል፤ አጠቃላይ የሆነውን የአዲሱን ትውልድ አስተሳሰብ እየመረዘ አሁን ላይ ያለው ነጻ አውጪ ነኝ ሳይቀር ለዜጎች ሕይወት ደንታ ቢስ እንዲሆን አድርጎታል። ባልተገባ የሕዝቦች መስዋእትነት ወደ ስልጣን መምጣት ኅሊናን የማይቆረቁር፤ መንፈስን የማይረብሽ አትራፊ የፖለቲካ ስትራቴጂም ተደርጎ እንዲወሰድ መደላደልንም ፈጥሯል።
ከሁሉም በላይ በጀግና ጀግና ጫወታ የብዙ ዜጎችን ደም ተረማምደው ወደ ሥልጣን የመጡ ኃይሎች፤ ትናንት በዚህ ያልተገባ ጫወታ ብዙዎችን በተጨባጭ ትርጉም ለሌለው መስዋእትነት መዳረጋቸው ሳያንስ፤ ይህንኑ ጨዋታ ሥትራቴጂክ የፖለቲካ አቅም አድርገው ዳግም ዜጎችን ለከፋ እልቂት የዳረጉበት ሁንታ ተፈጥሯል። ዛሬም ለተመሳሳይ እልቂት ፉከራና ቀረርቶ እንዲያሰሙ የልብ ድንዳኔ ፈጥሮባቸዋል።
ይህ መግደል እና መሞትን ያቀለለ፤ ለዜጎች ሕይወት ክብር የነፈገ፤ በሰላም የመኖር ፍጥረታዊ መብታቸውን የሚገዳደር፤ ለሕዝብ የመልማት ጥያቄ ደንታ ቢስ የሆነ፤ ሕዝብን እንደ ሕዝብ ፍላጎት አልባ የፖለቲካ መጠቀሚያ ዕቃ አድርጎ የሚወስድ የፖለቲካ አስተሳሰብ ዛሬም ሀገርን በብርቱ እየፈተነ ነው።
ከዩቲዩብ የግጭት ንግድ፤ ከሸኔ እና ፋኖ የጥፋት ትርክት እና ከፈጠረው የመገዳዳል ገድል፤ ከትናት ያለመማር የጦርነት ነጋሪት ጉሸማ በስተጀርባ ያለው አስተሳሰብ፤ በመሰረታዊነት መግደልን እና መሞትን ካቀለለው የፖለቲካ ባሕላችን የመነጨ፤ ከአስተሳሰቡ ለማትረፍ የሚደረግ የጥፋት ተልዕኮ አካል ነው።
አስተሳሰብ እና ከአስተሳሰቡ የሚመነጨውን ጥፋት፤ እስከዛሬዋ ቀን ድረስ ብዙ ወንድም እህቶቻችንን አሳጥቶናል፤ እንደ ሀገርም ለብዙ ቁሳዊ ውድመት ዳርጎናል፤ ማኅበራዊ እና መንፈሳዊ አሴቶቻችን አደብዝዟል፤ሀገረ መንግሥቱን ሕልውና ስጋት ላይ የጣለ ፈተና ውስጥ ከትቶናል፤ እንደ ሕዝብ አስተሳሰቡን በቃ ለማለት ወቅት አሁን ነው።
የምንፈልገው ለዜጎች ሕይወት ክብር የሚሰጥ፤ በሰላም የመኖር ፍጥረታዊ መብታቸውን የሚያከብር፤ የመልማት ጥያቄዎቻችንም ተቀብሎ ለመመለስ የሚያተጋ፤ ሕዝብን እንደ ሕዝብ የፖለቲካ ኃይል እና የሥልጣን ምንጭ አድርጎ የሚቀበል የፖለቲካ አስተሳሰብ እና ከዚህ የሚመነጭ የፖለቲካ ስብእና ያለው አሻጋሪ ፖለቲከኛ ነው!
አዲስ ዘመን እሁድ ግንቦት 17 ቀን 2017 ዓ.ም