ራምፕ ሀርቫርድ ዓለም አቀፍ ተማሪዎችን እንዳይቀበል ያሳለፉት ውሳኔ በፍርድ ቤት ታገደ

ሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ዓለም አቀፍ ተማሪዎችን እንዳይቀበል ዶናልድ ትራምፕ ውሳኔ ቢያሳልፉም ውሳኔው ለጊዜው በፍርድ ቤት ታግዷል። የትራምፕን ውሳኔ ተከትሎ ሀርቫርድ ክስ ከመሠረተ በኋላ ነው ፍርድ ቤት ክልከላውን ያገደው።ዓለም አቀፍ ተማሪዎች ሀርቫርድ እንዳይገቡ ማገድ ሕግና የንግግር ነጻነትን የሚጻረር እንደሆነ ሀርቫርድ ገልጿል።

ሀርቫርድ ፀረ ሴማዊነትን ለማስቆም አልሞከረም በሚል ነው ትራምፕ በዩኒቨርሲቲው ላይ ክልከላ የጣሉት።ዩኒቨርሲቲው ይህንን ክስ አጣጥሏል።ዳኛ አሊሰን ቡሮህስ የትራምፕ ውሳኔ ለጊዜውም ቢሆን እንዲታገድ አድርገዋል።የሀገር ውስጥ ደኅንነት ቢሮ የሀርቫርድን የዓለም አቀፍ ተማሪዎች የመቀበል መብት እንዲነጥቅ ተወስኗል።ሀርቫርድ ለፍርድ ቤት ባቀረበው ክስ “መንግሥት በአንድ ትእዛዝ ግማሽ ሀርቫርድን ሊያጠፋ ነው። ዓለም አቀፍ ተማሪዎች ለዩኒቨርሲቲው ተልዕኮ ከፍተኛ ሚና አላቸው” ሲል ክልከላውን አጥብቆ ተቃውሟል።

የሀርቫርድ ፕሬዚዳንት አለን ጋርበር “ይሄንን ሕገ ወጥ ድርጊት እንቃወማለን” ብለዋል።“የማስተማር ነጻነታችንን ለመጋፋት መንግሥት ያደረገውን ሙከራ ባለማስተናገዳችን ነው ይሄ ርምጃ የተወሰደብን። የፌዴራል መንግሥት የትምህርት አሰጣጡን፣ ተማሪዎቻችንን እና የትምህርት ክፍሎችን እንዲቆጣጠር አንፈቅድም” ሲሉም ተናግረዋል።

የዋይት ሀውስ ምክትል ፕሬስ ሴክሬተሪ አቢጌል ጃክሰን “ሀርቫርድ ፀረ አሜሪካና ፀረ ሴማዊነት ንቅናቄን ለማቆምና ሽብርን ላለመደገፍ ቁርጠኛ መሆን ቢሆን ኖሮ ይሄ ሁሉ አይፈጠርም ነበር ብላለች።”ያልተመረጡት ዳኛ የትራምፕ ውሳኔ ማገድ አይችሉም” በማለትም የፍርድ ቤቱን ውሳኔ አጣጥላለች። በሀርቫርድ የትምህርት ዕድል ያገኙ ተማሪዎች ዕጣ ፈንታቸው ምን እንደሆነ ባለማወቅ ጭንቀት ውስጥ ገብተዋል። ወደ ሀገራቸው ሊመለሱ እንደሚችሉ በማሰብም ፈርተዋል።

የመንግሥት አስተዳደር ምሩቅ ኮርማክ ሳቬግ ከአየርላንድ ነው ሀርቫርድ የገባው። ዓለም አቀፍ ተማሪዎች ለቀጣይ 90 ቀናት አሜሪካ ከቆዩ ወደ አሜሪካ ተመልሰው ዲግሪያቸውን መጨረስ እንደሚችሉ ይናገራል። ከዩናይትድ ኪንግደም ሀርቫርድን የተቀላቀለው ሮሀን ባቱላ “ተመልሼ ትምህርቴን መጨረስ አልችል ይሆናል ብዬ ፈርቻለሁ” ብሏል። ተማሪዎቹ ፍርድ ቤት በትራምፕ ውሳኔ ላይ በሰጠው ጊዜያዊ ዕግድ ደስተኛ ቢሆኑም፤ በቀጣይ ምን ይፈጠራል ብለው መስጋታቸው አልቀረም።

በሀርቫርድ 6 ሺህ 800 ዓለም አቀፍ ተማሪዎች ያሉ ሲሆን” ከአጠቃላይ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች 27 በመቶ ናቸው። አንድ አምስተኛው ከቻይና ሲሆኑ፤ ከካናዳ፣ ከሕንድ፣ ከደቡብ ኮሪያ እና ዩናይትድ ኪንግደምም ተማሪዎች በብዛት ይገኛሉ።ነሐሴ ላይ ትምህርት ለመጀመር እየተዘጋጀ ያለው ሊዮ አክማን ሀርቫርድ መግባት “ሕልሜ ነበር” ይላል።“በጣም ጓጉቼ ነበር። ይሄንን ዕድል ከመነጠቅ በላይ የሚያሳዝን ነገር የለም” ብሏል።

ዓለም አቀፍ ተማሪዎችን ሀርቫርድ እንዳይቀበል ማድረግ ከዩኒቨርሲቲው በጀት ላይ ከፍተኛውን ድርሻ የሚያስቀር ነው። ዓለም አቀፍ ተማሪዎች የራሳቸውን የትምህርት ወጪ እንዲሸፍኑም የሚያስገድድ ሊሆን ይችላል።

በቀጣይ የትምህርት ዘመን የመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርት ብቻ በዓመት 59 ሺህ 320 ዶላር ያስከፍላል። ያለ መንግሥት ድጋፍ የዓመት ጠቅላላ ወጪ (ቤት፣ ክፍያ፣ መጻሕፍት፣ ምግብና የጤና መድኅንን ጨምሮ) 100 ሺህ ዶላር ይደርሳል።

ከሴራ ሊዮን ሀርቫርድ የገባው አይዛክ ባንጉራ ከባለቤቱና ሁለት ልጆቹ ጋር ይኖራል።“ልጆቼ ወደ ሀገራችን በግድ ልንመለስ ነው? ብለው እየጠየቁኝ ነው። አሜሪካውያን ችግር ሲገጥማቸው መፍትሔ አያጡም ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ” ብሏል። የአሜሪካ ዕውቅ ዩኒቨርሲቲዎችን በተለይም ለፍልስጤም ከተደረጉ የድጋፍ ሰልፍ ጋር በተያያዘ ከትራምፕ አስተዳደር ጋር ውዝግብ ውስጥ ከገቡ ቆይተዋል።

ትራምፕ ዩኒቨርሲቲዎቹ እንዲያደርጉ በሚፈልጉት ለውጥ ላይ ተቃውሞ ሲገጥማቸው በጀት እስከመቁረጥ ድረስ በመሄድ ዩኒቨርሲቲዎቹ ላይ ጫና ማሳደራቸውን ቀጥለዋል። ከወራት በፊት የሀርቫርድ 2 ነጥብ 2 ቢሊዮን በጀት ላይ ዕግድ መጣላቸው ይታወሳል። ዩኒቨርሲቲው ግብር እንዳይከፍል የተሰጠውን መብት እንደሚነጥቁም ዝተዋል ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው።

አዲስ ዘመን እሁድ ግንቦት 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You