አዲስ አበባ፤- በታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ ተሸርሽሮ የነበረው የህዝቡ አመኔታ መነሳሳት ማሳየቱን የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ገለጸ።
ከብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ድረገጽ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በህዳሴ ግድብ ግንባታ የህዝቡ ተሳትፎ መነቃቃት ጀምሯል። ግድቡ ባጋጠመው የሃይድሮ ስቲል ስትራክቸር ግንባታ መዘግየት ጋር ተያይዞ የመጀመሪያ ሙከራ ምርት አለመጀመሩን ተከትሎ ህዝባዊ ተሳትፎው መቀነሱን ያመላከተው ድረገጹ፤ መንግሥት በግድቡ ግንባታ ላይ ያጋጠሙ ችግሮችን ፈትሾ በመለየት ያስተላለፈው ውሳኔ ተከትሎ መነቃቃቱ ሊመጣ መቻሉን አመላክቷል።
የዘገየውን ግንባታ ለማፋጠን ሥራው በውጭ ካምፓኒዎች እንዲከናወን የማሻሻያ እና የማስተካከያ ተግባራት እየተከናወነ ነው። ከዚህ በተጨማሪም ግልጽና ወቅታዊ መረጃ በማድረስ አመኔታ በማትረፍ የህዝቡ ተሳትፎ ወደ ነበረበት እንዲመለስ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን መረጃው ያመለክታል።
እስካሁን በተከናወነው ተግባርም ከኢትዮ ጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ባለፉት ስድስት ወራት 484 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ተደርጓል። ይህም ህዝቡ ግድቡን ለማጠናቀቅ ቁርጠኛ መሆኑን ያሳየበት ነው። ባለፉት ሰባት ዓመታት ከ12 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ በቦንድ ግዢ እና በልገሳ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ መደረጉንም መረጃው ያመለክታል።
ህዝባዊ ተሳትፎውን ለማጠናከር በብሄራዊ ምክር ቤቱ ሥራ አስፈፃሚ ደረጃ ትኩረት ሰጥቶ መሥራትና የህዝቡን አመኔታ ለመመለስ የሚያስችሉ ተግባራት ማከናወን ያስፈልጋል። የቦንድ ስርጭትና ቅንጅታዊ አሰራርን በየደረጃው ያሉ አደረጃጀቶች እንዲጠናከሩ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሠራም አቅጣጫ ተቀምጧል። ጽሕፈት ቤቱ በተለያዩ ቦታዎች የሕዝብ መድረኮች በመክፈትና ተከታታይ ውይይት በማካሄድ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች በስፋት መረጃ ለማድረስ እንደሚሠራ የድረገጹ መረጃ ያመለክታል።
አዲስ ዘመን የካቲት 6/2011