አዳማ፡- ጠንካራ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ባይኖር ኖሮ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በሚነሱ አለመረጋጋትና ግጭቶች ኢትዮጵያ የመፈራረስ ዕጣ ይገጥማት እንደነበር የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ ገለጹ።፡
7ኛውን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ መከላከያ ሠራዊት ቀን አስመልክቶ “ሕገ መንግሥታዊ ታማኝነታችንን እና ህዝባዊ ባህሪያችንን ጠብቀን የተጀመረውን ለውጥ እናስቀጥላለን” በሚል መሪ ሀሳብ በትላንትናው ዕለት በአዳማ ከተማ ገልማ አባገዳ የፓናል ውይይት ተካሂዷል፡፡
በመድረኩ “መከላከያ ሠራዊት በለውጥ ሂደት” በሚል በመከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ሰዓረ መኮንን ሰነድ ቀርቧል፡፡ በተያያዘም “የኢትዮጵያ አየር ኃይል ታሪካዊ ጉዞ ከትላንት እስከዛሬ” በሚል ሌላ ሰነድ የአየር ኃይል ጠቅላይ መምሪያ ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ይልማ መርጋሳ አቅርበዋል፡፡
በቀረቡት ሰነዶች ላይ መከላከያ ከመንግሥት ጋር ተለዋዋጭ ሳይሆን ቋሚ መሆን እንዳለበት ከተሳታፊዎች ለተነሳው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ፣ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋሉአለመረጋጋቶች እንዲሁም ግጭቶች ወደ ከፋ ደረጃ እንዳይሸጋገሩ የመከላከያ ሠራዊቱ አባላት እስከ ህይወት መስዋዕትነት እየከፈሉ መሆናቸው ለሀገር ደህንነትና አንድነትን ለማጎልበት መቆሙን ማሳያ እንደሆነ አንስተዋል፡፡
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ብሔርና ጎሳ የሌለው ኢትዮጵያዊ ሠራዊት መሆኑንና በአለመረጋጋቶችና ግጭቶች ሀገር የመፍረስ አደጋ እንዳይገጥማት ማድረጉ ጠቅሰው፣ ሠራዊቱ የተላበሰው ጠንካራ ሰብዕና ከሀገሪቱ አልፎ የመላው አህጉሪቱ ኩራት እንዳደረገው አቶ ለማ ገልጸዋል፡፡
ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ግለሰቦች የሚፈጥሩትን ስህተት በመንቀስ የፖለቲካ ማወራረጃ ማድረግ አግባብነት የጎደለው ድርጊት ነው ያሉት አቶ ለማ፣ ይልቁንም ሠራዊቱ መስዋእትነት እየከፈለ በመሆኑ የጋራ ጠንካራ የብረት አጥር የሆነ መከላከያ ሠራዊት ለመገንባት ሁሉም በሞራልና ተገቢውን ክብር በመስጠት ሊደግፈው እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ አያይዘውም መከላከያ ሠራዊቱ የድርጅትም ሆነ የብሔር ሳይሆን የሀገር ምሽግ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ሀገሪቱ የባህር በር ሳይኖራት የባህር ኃይል ማቋቋም አስፈላጊነቱ ምኑ ላይ ነው ለሚለው ጥያቄ ርዕሰ መስተዳድሩ ሲመልሱ፣ በሁለት ዋነኛ ምክንያት ማቋቋሙ አስፈላጊ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ በዚህም የቀጣናው ጂኦፖለቲክስ አንዱ ሲሆን ሌላኛው ምክንያት ደግሞ ማንኛውም ጠንካራ መከላከያ ኃይል ያለው ሀገር የባህር በር ባይኖረውም የባህር ኃይል እንዳለው ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ ባሻገርም የንግድ መርከቦች እንዲጠበቁ በማድረግ በኩል የሚኖረው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳም ከፍተኛ እንደሚሆን አመላክተዋል፡፡
በመድረኩ የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጅነር አይሻ መሀመድን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮችና በየደረጃው ያሉ የመዋቅሩ አባላት፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ፣ የቀድሞ የሠራዊቱ አባላት፣ የሀገር ሽማግሌዎችና አባ ገዳዎች ፣ አርበኞች እንዲሁም ከ 2 ሺህ በላይ ተጋባዥ እንግዶች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
በ2007 ዓ.ም በምዕራብ እዝና በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አዘጋጅነት በባህር ዳር ከተማ ተካሂዶ በነበረው መድረክ ሠራዊቱ ከህዝቡ ገንቢ ሀሳቦችን ያገኘ ሲሆን የዘንድሮ በዓልም ሠራዊቱን ለተሻለ ተልዕኮ የሚያዘጋጀው እንደሆነ ታስቦ ሲሠራ የቆየ ነው፡፡ ከጥቅምት 2011ዓ.ም ጀምሮ በየክልሉ በተለያዩ ፓናል ውይቶች እንዲሁም በስፖርታዊ ትዕይንቶች ሲከበር የቆየው ሰባተኛው የመከላከያ ሠራዊት ቀን በዛሬው ዕለት በአዳማ ከተማ በሚገኘው አበበ ቢቂላ ስታዲየም የመዝጊያ መርሃ ግብሩ ይከናወናል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 7/2011
ፊዮሪ ተወልደ