በ2019 ካሜሩን ለምታስተናግደው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ በተለያዩ ምድቦች ከትናንት ጀምሮ ሦስተኛ የማጣሪያ ጨዋታዎች ተከናውነዋል። በምድብ ስድስት የተደለደለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ትናንት አስር ሰዓት ላይ የኬንያ አቻውን አስተናግዶም ዜሮ ለዜሮ በሆነ አቻ ውጤት ተለያይቷል።
በጨዋታው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋልያዎቹ ኳስን ተቆጣጥረው ጫና በመፍጠር የተሻለ የበላይነት የነበራቸው ቢሆንም ኳስና መረብን ማገናኘት አልሆነላቸውም። በሁለተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ዋልያዎቹ ወደ ኬንያ የግብ ክልል በተደጋጋሚ ለመድረስ ያደረጉት ሙከራ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ቢችልም ወደ ውጤት አልተቀየረም። በተለይም ሁለት ኳሶች ከመረብ ተገናኝተው ጋምቢያዊው የአፍሪካ ኮከብ ዳኛ ባካሪ ፓፓ ጋሳማ ከጨዋታ ውጪ ነው ብለው መሻራቸው ከመቶ ሺ በላይ የሚሆነውን የባህርዳር ስቴድየም ውብ ተመልካች ቅስም ሰብሯል።
በአንፃሩ የኬንያ ብሔራዊ ቡድን የሃራምቤ ኮከቦች ከጨዋታው የሚፈልጉትን ውጤት ይዘው ለመመለስ የተፈጠረባቸውን ጫና ተቋቁመው በፍፁም መረጋጋት ያሰቡትን አሳክተዋል። ይህም ፈረንሳዊው አሰልጣኝ ሴባስቲያን ሚኜ ከሃራምቤ ኮከቦች ጋር ወደ አፍሪካ ዋንጫ የሚያደርጉትን ጉዞ በተስፋ የተሞላ አድርጎታል። ከዋልያዎቹ ጋር ገና ሁለተኛ ጨዋታቸውን ያደረጉት አሰልጣኝ አብረሃም መብራቱ ቡድኑን የተሻለ እንዲንቀሳቀስ ቢያስችሉም ከትናንቱ ጨዋታ ሙሉ ሦስት ነጥብ አለማግ ኘታቸው ወደ አፍሪካ ዋንጫ የሚያደርጉትን ቀጣይ ጉዞ ፈታኝ አድርጎባቸዋል።
በምድቡ ከጋና እና ሴራሊዮን ብሔራዊ ቡድኖች ጋር የተደለደሉት ኢትዮጵያና ኬንያ የትናንቱን የጨዋታ ውጤት ተከትሎ አራት አራት ነጥብ በመያዝ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ይመራሉ። በዚህ መንገድ አሰልጣኝ አብረሃም መብራቱ ቡድኑን ወደ አፍሪካ ዋንጫ ለማድረስ ተስፋ ያላቸው ቢመስልም የሴራሊዮን ብሔራዊ ቡድን በፊፋ ከየትኛውም ጨዋታ መታገዱን ተከትሎ ኢትዮጵያ ቀደም ሲል የነበራት ሦስት ነጥብ እንዳይሻር ስጋት ፈጥሯል።
ፊፋ በሳምንቱ መጀመሪያ የሴራሊዮን መንግሥት የአገሪቱን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ኃላፊዎች በሙስና ወንጀል ጠርጥሮ ከኃላፊነታቸው ማንሳቱን ተከትሎ አገሪቱ በየትኛውም የእግር ኳስ ውድድር እንዳትሳተፍ ማገዱ ይታወሳል። ከትናንት በስቲያ ይህ እገዳ እንደተነሳ ቢሰማም ፊፋ ዳግም አፅንቶታል። ይህም ሴራሊዮን በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያው ያደረገቻቸው ጨዋታ ውጤቶች የሚሰረዙ ይሆናል። በዚህ ደግሞ ዋነኛዋ ተጎጂ ኢትዮጵያ ትሆናለች።
ኢትዮጵያ ከዓመት በፊት የመጀመሪያውን የማጣሪያ ጨዋታ ከጋና ብሔራዊ ቡድን ጋር አድርጋ በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ የሚመራው ስብስብ አምስት ለዜሮ መረታቱ ይታወሳል። ከወር በፊት ደግሞ በሁለተኛው የማጣሪያ ጨዋታ በሐዋሳ ላይ ኢትዮጵያ ሴራሊዮንን አስተናግዳ አንድ ለዜሮ ማሸነፏ አይዘነጋም። በመጀመሪያው የማጣሪያ ጨዋታ ኬንያ በሴራሊዮን የተሸነፈች ሲሆን በሁለተኛው የማጣሪያ ጨዋታ ጋናን አንድ ለዜሮ መርታት ችላለች። ይህም በምድቡ የሚገኙ አራቱም አገራት ከትናንቱ ጨዋታ በፊት እኩል ሦስት ነጥብ እንዲይዙ አስችሏቸዋል።
ፊፋ ሴራሊዮን ላይ የጣለው እገዳ ከፀናና ካፍ አገሪቱ በማጣሪያ ጨዋታዎች የሰበሰበችውን ነጥብ የሚሰረዝ ከሆነ ኬንያ በሴራሊዮን የደረሰባት ሽንፈት ይሻራል። ኢትዮጵያ ደግሞ ሴራሊዮንን በማሸነፏ የነበራትን ሦስት ነጥብ ታጣለች ማለት ነው። በዚህም ሴራሊዮን ከማጣሪያ ውጪ ከሆነች ኢትዮጵያ፤ ኬንያና ጋና በምድቡ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ለማለፍ የሚፋለሙ ይሆናል። በዚህ አካሄድ ኢትዮጵያ የሚኖራት ከትናንቱ ጨዋታ ያገኘችው አንድ ነጥብ ሲሆን ኬንያ አራት ነጥብ ይዛ ምድቡን የመምራት አጋጣሚ ይፈጠርላታል። ጋና ከሴራሊዮን ጋር ጨዋታ ባለማድረጓ የነበራት ሦስት ነጥብ ቀጣዮቹን የማጣሪያ ጨዋታዎች ውጤት ሳያካትት በሁለተኛነት ከምድቡ የማለፍ ዕድል ይኖራታል።
ዋልያዎቹ ምናልባትም ከትናንቱ ጨዋታ ሙሉ ነጥብ አግኝተው ቢሆን የሴራሊዮን ጉዳይ ሳያሳስባቸው በምድቡ ተፎካካሪ ሆነው በተሻለ የማለፍ ዕድል ይፈጥሩ ነበር። ከሴራሊዮን ጋር በተያያዘ ያለውን ጉዳይ ወደ ጎን ብንተወውም ዋልያዎቹ ትናንት የጣሉት ወሳኝ ነጥብ ከቀሪ ጨዋታዎች ክብደት አኳያ ትልቅ ዋጋ ሊያስከፍላቸው ይችላል። ዋልያዎቹ የምድቡን አራተኛ የማጣሪያ ጨዋታ ከቀናት በኋላ ጥቅምት 4 ቀን ወደ ኬንያ አቅንተው በናይሮቢው ካሳራኒ ስታዲየም የሚጫወቱ ይሆናል። እዚህ በሜዳቸውና በደጋፊያቸው ፊት ያመለጣቸው ሙሉ ሦስት ነጥብ ደግሞ ከሜዳቸው ውጪ በቀላሉ ይገኛል ማለት ከባድ ነው።
ከቀሪ ጨዋታዎች አኳያ ዋልያዎቹ በሜዳቸው የሚገጥሙት በመጀመሪያው ማጣሪያ ጨዋታ አምስት ለዜሮ ማሸነፍ የቻለችውና የምድቡ ጠንካራ የሆነችውን ጋናን እንደመሆኑ መጠን ከጥቁር ከዋክብቱ ሦስት ነጥብ እንደዋዛ ይገኛል ማለት ዘበት ነው። ሴራሊዮን ቅጣቱ ተነስቶላት ወደ ጨዋታ የምትገባ ከሆነ ዋልያዎቹ ከሜዳቸው ውጪ የሚገጥሙ ይሆናል። የሴራሊዮን ብሔራዊ ቡድን ሐዋሳ ላይ ሽንፈት ይግጠመው እንጂ በበርካታ ፕሮፌሽናል ተጫዋቾች የተሞላ ከጋና ቀጥሎ በምድቡ ጠንካራ ስብስብ ያለው በመሆኑ ለዋልያዎቹ ቀላል አይሆንም። ይህ ሲታሰብ ትናንት ዋልያዎቹ ዋጋ የሚያስከ ፍላቸውን ነጥብ ለሃራምቤ ኮከቦች አሳልፈው ሰጥተዋል ማለት ይቻላል።
ቦጋለ አበበ