ሀይለማርያም ወንድሙ
በሬና ገበሬ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸው፤ አይነጣጠሉም።በሬ ለገበሬ ሕይወቱ ሀብቱ የኑሮው መሠረቱ ነው።በተለይ ለእንደኛ ዓይነቱ እንደትራክተር በመሳሰሉ በዘመናዊ የግብርና መሣሪያዎች መጠቀም ዳገት ለሆነበት ገበሬ በሬ ወሳኝ ነው።
ከብቶቻቸው እና ልጆቻቸው እንዲቆጠሩ የማይፈልጉ ማህበረሰቦች ቢኖሩም ፣ ዱሮ የሰዎች ሀብት የሚለካው በከብቶቻቸው ብዛት ነበር ይባላል፤ ምን ጥንት ብቻ በአንዳንድ ከብት አርቢ አካባቢዎች አሁንም እንደዚያው ነው ይባላል።ብዙ ጥማዶች እና ጥገቶች (የምትታለቡ ላሞች) ያላቸው ከባለጸጋ ይመደባሉ፡፡
በሬ የገበሬውን ኑሮ በማቃናትም ሆነ በማጣመም ሁነኛ ሚና አለው።ገበሬ በበሮቹ ያርሳል፤ ሕይወቱን ያረሰርሳል።ጥሩ ሲያመርት ጥሩ ኖሮ መምራት ይችላል።የዚህ ፋይዳው ለሸማቹም ይተርፋል።በበሬው አርሶ የተሻለ ሲያመርት ከራሱ ተርፎ ምርቱን ለገበያ ስለሚያቀርብ ሸማቾች የተሻለ ሕይወት ይመሩበታል።በድርቅና በመሳሰለው ጥሩ ምርት ሳይገኝ ሲቀር ገበሬውም ሸማቹም ሀገሪቱም ችግር ውስጥ ይገባሉ ።
የበሬና ገበሬ ግንኙነት በብዕር ሲመነዘርና ሲዘረዘር ከዚህም በላይ ሊሆን ይችላል።በብዕር ሲመነዘርና ሲዘረዘር ያልኩት በብዕር መነፅር ሲታይ ለማለት ፈልጌ ነው።የብዕር መነፅር አለው ብትሉኝ ለዛሬ ጽሁፌ ቢኖረው ምን ችግር አለው? እላለሁ።በሰዎች አመለካከት ሲነካና ሲለካ ማለቴ መሆኑ ይታወቅልኝ።
በሬ አገልግሎቱ ዘርፈ ብዙ ነው፤ የከሳቴ ብርሃን ተሰማ የአማርኛ መዝገበ ቃላት በሬ የቀንድ ከብት ተባዕት የቤት እንስሳት ለእርሻ የሚሆን፣ ሥጋው የሚበላ፣ ቀንዱ ለጠጅ ለዋንጫ፣ ለቢላዋና ጎራዴ እጄታ፣ ለአረቄ መለኪያ የሚሆን፤ ቁርበቱ ተለፍቶ ለመኝታ፣ ተሰፍቶ ለጭልጌ፣ ለዘገባ፣ ለዳውላ፣ ለጫማና ለልዩ ልዩ ነገርም የሚሆን፤ ሞራው ለመብራትና ለሳሙና የሚሆን በሚል ይፈታዋል።መዝገበ ቃላቱ ገበሬ የሚለውን ቃል ደግሞ ጥማድ በሮችን ጠምዶ የሚያርስ ፣ዘርን የሚዘራ ይለዋል።ሙያው ደግሞ ግብርና በሚል እንደሚጠራ ሲያብራራ የእርሻና ከብት እርባታ ሥራ መሆኑን ያስረዳል።የደለበ ሰንጋ ፣ስናይ ስጋ የሚያምረን በገበሬው ልፋት ውጤት ነው።
በስነቃላችንም ገበሬው ፡ –
አሁን ማን አለና እንደ በሬ ወንድ
ሞፈር ቀንበር ይዞ መሬት የሚቀድ
አሁን ማን አለና በበሬ የማይኮራ
ወተቱ ከጓዳ ምርቱ ከጎተራ።በእርሻው ወቅት እያለ እንደሚያዜም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው በስነፅሁፍ መሠረታውያን መፃፋቸው ጠቅሰውታል፡፡
በሀገራችን በተለያዩ ጊዜያት ገበሬው ዝናም ጠፍቶ ድርቅ ተከስቶ የተወሰነ ወገኑም ከብቱም ሞቶ ራሱን ለማትረፍ አካባቢውን ትቶ ተሰድዷል፤ የከተሜውም ኑሮ ተንገዳግዷል።በ1977 ደርሶ በነበረው ድርቅ በሸገር / በአዲስ አበባ ማለቴ ነው/
ልመደው ልመደው ሆዴ፣ ልመደው ልመደው ሆዴ
ተወዷል ጤፍና ስንዴ፣ ሩዙን ብላው በዘዴ
እየተባለ በህፃናቱ ይዘፈን እንደነበር ትዝ ይለኛል።የዚያን ወቅቱን የድምጻዊ ኤፍሬም ታምሩን ዜማ ቀየስ በማድረግ ማለት ነው።ሩዝም ወደ ሀገራችን የመጣው በዚያን ዘመን ነው።
ገበሬ አዝመራውን ከሰበሰበ በኋላ ለዘር እና ለቀለብ የሚያስፈልገውን አስቀርቶ ፣ ሌሎች የሚያስፈልጉትን ለማሟላት እንዲያስችለው የተቀረውን ለገበያ ያቀርባል።በዚህም ሸማቹን ተጠቃሚ ያደርጋል።ሸማቹም የገበሬውንና የበሬውን ውለታ በሚገባ ይገነዘባል፡፡
በልጅነታን በሬዲዮ የግብርና ፕሮግራም ሲተላለፍ ሥራችን ብለን ባናዳጥም በወቅቱ አንድምታው ብዙም ያልገባን ስንጎለምስ የተገነዘብነው ደስ የሚለን ዘፈን ይታወሰኛል። ሸማቹም
ገበሬ ገበሬ ፣ ና ገበሬ
ገበሬ ገበሬ ፣ ና ገበሬ
በአንተ ነው ማማሬ
ገበሬ !
በአንተ ነው ማማሬ ገበሬ ሲል ገበሬውን እንደሚያመሰግነው በዜማ ተገልጿል፡፡
አሁን ሳስበው ምንም ከተሜ ብሆን ቆሜ የሄድኩት በገበሬው ልፋትና ድካም ነው ለካ።ሀገሬ ኢትዮጵያ እንኳ ትልቁን የውጪ ምንዛሪ የምታገኘው በገበሬው ምርት ነው።ቡና፣ የቅባት እህሎች፣ ጫት፣ የቁም ከብት፣ አሁን ገበያ እያጣ የመጣው ቆዳና ሌጦ ሁሉ የገበሬው ውጤቶች ናቸው፡፡
ገበሬዎቹ አቅማቸው እንዲጎለብት የእርሻና የከብት እርባታውን እንዲያዘምኑ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።የግብርናው ምርት ለውጪ ገበያ ሲቀርብ ከሚገኘው ገቢ ግብርናውን ለሚያነቃቃ ስራ መመደብ ይኖርበታል። አለበለዚያ የበሬውን ውለታ ወሰደው ፈረሱ እንደሚባለው ብሂል ይሆናል።ግብርና ሌላውን የኢኮኖሚ ዘርፍ እያነቃቃ እሱ የማይነቃ ከሆነ ባለህበት ሂድ ብቻ ሳይሆን ከመስመር መውጣትም ሊከትል ይችላል።የግብርና ምርት እየተወደደ ባለበት ሁኔታ ግብርና እንዲዘመን ካልተደረገ ችግር ይገጥመናል፡፡
ነጋዴው ትርፋማ መሆን እንዳለበት ይታመናል፤ እንደ ሀገር ከምርቱ ሽያጭ የሚገኘው ገቢ ገበሬውን የሚያነቃቃ እና ለቀጣይ የበለጠ ምርታማ ሊያደርገው እንዲችል መስራት ያስፈልጋል። አርሶ አደሩ ከነጋዴው ይልቅ ተጠቃሚ የሚሆንበት ስርአት መበጀት ይኖርበታል።
ገበሬ አፈር መስሎ እየሠራ ህዝቡን ጌታ አድርጎ ያኖረዋል ፤ የገበሬ ውለታ ይህ ሆኖ ሳለ ትኩረት የሰጠው ማነው ብትሉኝ ማንም ነው መልሴ።በእርግጥ በደርግ ዘመን በኅብረተሰብአዊነት (socializim) ርዕዮተ ዓለም መሬት ላራሹ አርሶ አደሩን መሬቱን የመጠቀም መብት ሰጥቶታል።ኃላ ላይ የጭቃ ጅራፉ መጣ እንጂ።ኃላ ላይ እርሻ ሰብል የሚባል ድርጅት ተቋቁሞ ያመረቱትን ለእሱ እንዲያስረክቡ መደረጋቸው ችግር አመጣ። በንጉሡ ዘመን የነበረው ደግሞ በእጅጉ የከፋ ነበር፤ መሬቱ ሁሉ በከበርቴዎች የተያዘበት ገበሬዎች ጭሰኞች የነበሩበት።በዚያ ዘመን ገበሬዎች ያልደረሰባቸው ግፍ አልነበረም።የዚያ አብዮት አንዱ ምክንያትስ ይሄው ግፍ አልነበር፡፡
አሁን አሁን በኩታ ገጠም እርሻ፣ በመስኖ ስንዴ እርሻ አርሶ አደሩ በዘመናዊ መንገድ እንዲያለማ እየተደረገ ነው።ባለፈው ዓመት በኦሮሚያ ለገበሬዎች ዘመናዊ የማረሻና መከስከሻ መሣሪያዎች ሲሰጥ አይቻለሁ።ለግብርናው የተሰጣቸውን ትኩረት የሚሳይ ነው።ሌሎች ክልሎችም ከዚህ በጎ ነገር ይማሩ፡፡
ትራክተሩ ኮምባይነሩ ቀስ በቀስ የበሬውን ሃላፊነት ሊቀንሰው ይችላል።በእርግጥም በዘመናዊ ግብርና የበሬ ሚና እያነሰ ይመጣል።ያ ግን ብዙ ጊዜን ይጠይቃል።አሁንም ለብዙ ግዜ ገበሬው ከበሬው ጋር ይቆያል፡፡
ገበሬው በትራክተር መጠቀም ጀመረ ማለት ከበሬ ተፋታ ማለት አይደለም።ከበሬው ጫንቃ ቀንበር ይወርድና በሬ ለስጋ ብቻ የሚለማ ይሆናል።የከብት እርባታው ለብቻው ትኩረት ይሰጠዋል፤ አርሶ አደሩ በከብት እርባታው ይበልጥ ተጠቃሚ መሆን ውስጥ ይገባል።አንድ ሰንጋ ስንት እንደሚሸጥ ቢያንስ በየበአላቱ ወቅት ሳንገዘብ አልቀረም።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 7/2013