በቁምላቸው አበበ ይማም(ሞሼ ዳያን)
(ክፍል ሁለት)
በሀገራችን በመጭው ግንቦት ማብቂያ ለሚካሄድ ምርጫ ቢያግዝ በሚል ዕምነት በአለማችን ከ1980ዎች ጀምሮ ከተካሄዱ ምርጫዎች ከተቀመሩ ዋና ዋና ስትራቴጂካዊ ትምዕርቶች ሁለቱን እንመልከት ። የመጀመሪያውን “ዝቅተኛ መስፈርቶች፤”ማለትም አስተማማኝ ደህንነት ፤ የአስተዳደርና የኮሙንኬሽን መዋቅሮችና መሰረተ ልማቶች እና በምርጫ ሂደቱም ሆነ ከምርጫው በኋላ የሚከሰቱ እንደ ድምፅ ማጭበርበር እና ነፃነቱና ፍትሐዊነቱ ላይ የሚነሱ ቅሬታዎች ካሉ በገለልተኛነት የሚመለከት የፍትሕና የዳኝነት አካል ሊኖር ይገባል የሚሉትን በዚሁ ጋዜጣ በክፍል አንድ መጣጥፍ የተመለከትን ሲሆን በክፍል ሁለት ደግሞ “የምርጫ ጊዜ ውርክብን” እንዲህ እንቀጽላለን።
2ኛ . የምርጫ ጊዜ ውርክብ፤
ከላይ የተዘረዘሩ ዝቅተኛ መስፈርቶችን ለማሟላት ምርጫው በጥድፊያ እንዳይካሄድ አለም ዓቀፍ የምርጫ ልሒቃን ይመክራሉ ። በተለይ የመድብለ ፓርቲ ምርጫ በሚካሄድበት ውድድሩ ፣ ፉክክሩ በጎሳ ፓለቲካ የሚራገብ ከሆነ ዘሎ ወደ ምርጫ ከመግባት በፊት አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ እና ቆም ብሎ ማሰብ እንደሚገባ ይዘከራሉ ። በተፈጥሮዬ ጨለምተኛ ሰው ባልሆንም ይህ ምርጫ ቅድመ ሁኔታዎችን ከ ሀ እስከ ፐ ሙሉ በሙሉ አሟልቷል የሚል ቅዠት የለኝም ። ሆኖም በቀደመው መጣጥፌ እንዳልሁት ሕልም ተፈርቶ ሳይተኛ አይታደርምና ሀገሪቱ ባለችበት ነባራዊ ሁኔታ ቀዬውንና መልካውን እየተፈታተኑን ካሉ ሰይጣናት ቀለል ያለውን ሰይጣን(lesser evil)ማለትም ቀጣዩን “ምርጫ” በተቻለ መጠን በአሉት ውስን አስቻይ ሁኔታዎች ማካሄድ ተመርጧል ። ለሁለተኛ ጊዜ እናራዝመው ብንል ነገ ከዛሬ የተሻለ ስለመሆኑ እርግጠኞች መሆን አንችልም ። ሆኖም በጎረቤት ሀገር ኬኒያ አይነት የቅድመና ድህረ ምርጫ ቀውሶች እንዳይገጥሙን ከወዲሁ መጠንቀቅ አለብን ። በ1998 ዓ.ም በጎረቤታችንና ወዳጃችን ኬኒያ የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ የተፈጠረውን የዜጎች ሞት መፈናቀል እና ሀገራዊ ቀውስ በሀገራችን እንዳይከሰት አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ላይ በትጋት አበክሮ መስራት ይጠይቃል ። የግጭት ቀጣና ሊሆኑ ይችላሉ ተብለው የሚሰጉ አካባቢዎችን አበክሮ ለመለየትና ቅድመ ጥንቃቄ ለመቀየስ የሚያስችል መላ ማበጀት ያሻል ።
ምርጫ ከሀገርና ከሕዝብ በታች ሆኖ የሚከውን ሁነት መሆኑን መተንተንና መተርጎም ግድ ይላል ። ምርጫ ይመጣል ። ይሄዳል ። ሕዝብና ሀገር ግን ይኖራል ። ለሚያልፍ ምርጫ የማያልፍ ሕዝብና ሀገር ዋጋ እንዳይከፍሉ ገዢው ፣ ተፎካካሪ ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ፣ ሕዝብና ሲቪክ ማህበራት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት ይጠበቅባቸዋል ። እነዚህን ተዋንያንና ባለድርሻ አካላት ጎረቤታችንና ወዳጃችን ኬኒያ በአግባቡ ባለማሳተፏ የከፈለችውን ዋጋ ያስታውሷል ። ከፍ ብዬ በጠቀስሁት አመት በኬኒያ በተካሄደ ምርጫ ከተቃዋሚው ጎራ ዋናው ተፎካካሪ የነበረው ራይላ ኦዲንጋ የጎሳውን የሎው መብትና ጥቅም ለማስከበር በሚል ሽፋን ሎው እንደተገፋ የበይ ተመልካች እንደሆነ በመቀስቀሱ ፤ ኡሁሩ ኬኒያታ በተመሳሳይ ሁኔታ ለስልጣን ሳይሆን ለጎሳው ለኪኩዩ ጥቅም መብት የቆመ መስሎ ልዩነት ፍርሃትን በመስበኩ የምርጫው ውጤት ይፋ ሲሆን በተፈጠረ ግጭት በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከሁለቱም ጎሳዎች ሲሞቱ በአስር ሺህዎች የሚገመቱ ደግሞ ለዘመናት ከኖሩበት ቀዬ ተፈናቅለዋል ። በሁለቱ ጎሳዎች መካከልም ዛሬ ድረስ ቂም ፣ መጠራጠር ፣ ጥላቻ ሰፍኖ ይገኛል ። በኋላ ላይ የወጡ ጥናቶች እንዳረጋገጡት ፓለቲካው ከፓሊሲ ከፕሮግራም ይልቅ በጎሳ ላይ የተመሰረተ መሆኑና ሚዲያዎችም ሁለቱን ጎሳዎች ተገን አድርገው የተቋቋሙ እና ልዩነትንና ጥላቻን ይለፍፉ ስለነበር ግጭቱን ቤንዚን ሆነው በፍጥነት እንዳቀጣጠሉት ተደጋግሞ ይነሳል ። የፓለቲካ መሪዎች የየጎሳዎችን ድምፅ ለማግኘት እነዚሁን ሚዲያዎች መጠቀማቸው በእንቅርት ላይ— እንዲሉ ሆኗል ። በመጨረሻ ፓለቲካውም ፣ ሚዲያውም ዘውጌአዊ ሆኖ አረፈውና ጎረቤታችን ኬኒያ ማጣፊያው ሲያጥራት ከአንድ ሁለት ሶስቴ በላይ ተመልክተናል ። በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት የጎሳ ፓለቲካ የክርክሩ ፣ የሀቲቱ ማዳወሪያ በሆኑባቸው የአፍሪካ ሀገራት ለመራጭነት ከተመዘገበው ሕዝብ 98 በመቶ የሚሆነው ድምፁን የሚሰጠው ጎሳውን ወክሎ ለሚወዳደር ፓርቲ ወይም ግለሰብ ነው ። ይህ ጎሳ ዘውግ ላይ የተንጠለጠለ ፓለቲካ ምን ያህል ፓለቲካዊ ምህዳሩን እንደተቆጣጠረው ጥሩ ማሳያ ነው ። ስለሆነም ምርጫ ብሶትን ፣ የፈጠራ ትርክትንና የማንነት ፓለቲካን ከመጋለብ ተቆጥቦ እንዲካሄድ የቀሩንን ከሰባት ሳምንታት ያነሰ ጊዜያት በአግባቡ ልንጠቀምባቸው ይገባል።
የድሬዳዋና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደሮች ምርጫ ቆይቶ እንዲካሄድ መወሰኑ ተገቢ ሆኖ ሳለ በደቡብ ክልል የደቡብ ምዕራብ የክልልነት ሕዝበ ውሳኔ ከምርጫው ጋር ተዳብሎ መካሄዱ በውጥረት ላይ ውጥረት የሚፈጥር ሆኖ ይሰማኛል ። ሀገር አቀፍ ምርጫው ላይ ጥላውን እንዳያጠላበትም እሰጋለሁ ። የአካባቢ እና ሀገር አቀፍ ምርጫዎችን በአንድ ላይ በተመሳሳይ ጊዜ ከማድረግ ይልቅ የአካባቢ ምርጫዎችን አስቀድሞ ሀገር አቀፍ ምርጫዎችን ማስከተል ይመከራል ። ከፍተኛ ወጭና ሎጂስቲክ የሚጠይቅ ቢሆንም ውጥረትን ለማርግብና በምርጫ አስፈፃሚዎች ላይ ጫና እንዳይፈጥር ያግዛል ተብሎ ስለሚመከር በቀጣይ ሊታሰብበት ይገባል ። በተለይ አንደኛ ባሉ እስከ 80 በመቶ የሚሆነው ዜጋ በገጠር ለሚኖርባቸው ሀገራት የአካባቢ ምርጫ ለሕዝቡ ይበልጥ ትርጉም ያለውና ቅርብ ስለሆነ ቅድሚያ ለአካባቢ ምርጫ ሊሰጥ ይገባል የሚለው መከራከሪያ ውሃ የሚያነሳ ይመስላል ።
ከዚህ በመለስ የለውጥ ኃይሉ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ መሠረት ስለጣለና እርሾ በሆነ በልኩ እውቅና መስጠት ያስፈልጋል ። የለውጥ ኃይሉ የዴሞክራሲያዊ ተቋማት ግንባታ መሠረት የጣለው ለዴሞክራሲ ፣ ለሰብዓዊ መብትና ለፍትሕ ዋጋ የከፈሉና የታመኑ ታዋቂና በግራም በቀኝ ተቀባይነት ያላቸውን እንደ ክብርት ብርቱካን ሚደቅሳ ፣ መዓዛ አሸናፊና ዳንኤል በቀለ (ፒኤችዲ) ያሉ አመራሮችን ወደፊት በማምጣት ነው ። በምርጫ ቦርድና በሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የመጣው ለውጥም ይሄንኑ ያረጋገጠ ነው ። ለውጡም ሆነ ቀጣዩ ምርጫ ያደረ ፣ ተመርጎ የከረመ ፣ የቦካ ፣ የበሰለ ፣ የቆመጨረ እዳ አለባቸው ። እንግዲህ እኔ አንደኛ ፣ ምርጫ ቦርድና ሌላው ተዋናይ ደግሞ ስድስተኛ የሚሉት ምርጫ የሚከፍለው እዳና መፍታት የሚጀምረው የተንከባለለና ያደረ ችግር እንዳለ አምኖ ነው ወደስራ የገባው ። ይሄን ከባድ ኃላፊነት ለመወጣት የሚያግዝ ቅድመ ዝግጅት ለማድረግ የተጓዘበትን እርቀት ይበል የሚያሰኝ ነው ። ይሄን ተስፋ አሰናቂ የቦርዱን ጉዞ በሌላ መጣጥፍ እመለስበታለሁ ።
እንደ መውጫ
በተለይ በማንነት ላይ የተዋቀረ ፓለቲካ ስርዓትን ላነበረች ሀገር ሀቀኛ ፣ ነፃ ፣ ተአማኒ ፣ ፍትሐዊ ፣ ግልፅ እና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማካሄድ ልዩ ጥንቃቄን ይጠይቃል ። ከሁሉም በላይ ከቀውስ አገግማ በሁለት እግሯ ለመቆም በምትፍገመገም እና ሽግግር ላይ ላለች ሀገር ምርጫ መዳኛም መጥፊያም ነው ። ከሶስት አመት በላይ በጎሳ ግጭት ስትናጥ በሴራ ፓለቲካ ስትታመስ ለከረመች ሀገር ምርጫ ከኮሮጆው ፣ ከሳጥኑ ባሻገር መመልከትን ይጠይቃል ። ጥላቻ ፣ ልዩነት ከሩብ ክፍለ ዘመን በላይ ሲሰበክባት ለኖረች ሀገር ምርጫ ባለሁለት አፍ (ስለት ) ሰይፍ ነው ። ዜጎቿ ወደ ዘውግ ወደ ጎሳ ፈለፈል በተጠቀለሉበት ወቅት የሚካሄድ ምርጫ ከምርጫ በላይ ነው ። ስለሆነም በሚቀጥሉት ሳምንታት የሀገሪቱ ደህንነት ፣ ፀጥታ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መረጋገጥ አለበት ። በመቀጠል የሕግ የበላይነት ለድርድር ሳይቀርብ ተግባራዊ ሊደረግ ይገባል ። የቅድመ እና ድህረ ምርጫ ስርዓቶችም ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ባሳተፈ መልኩ መከበር አለባቸው ።
የምርጫ ቦርድ በአዲሱ የማቋቋሚያ አዋጅ መሠረት ወደስራ መገባቱ ፤ የቦርዱ ሰብሳቢዋን ጨምሮ ሌሎች አባላት ከገለልተኛ ወገን መሰየማቸው ተስፋ የሚጣልበት እርምጃ ነው ። በተለይ ነፃና ተአማኒ ምርጫ ለማካሄድ የዳኝነት አካሉ እንዲሁም የደህንነትና የፀጥታ መዋቅሩን ከፓለቲካዊ ወገንተኝነት ተላቆ እንዲደራጅ መደረጉ ፤ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ገለልተኛ ሆኑ መዋቀር ፤ አፋኝ አዋጆች ሕጎች ገለልተኛ የባለሙያዎች ምክር ቤት ተቋቁሞ መሻሻላቸው እንደ እኔ ላለ ተስፈኛ መጭው ጊዜ ከምርጫውም ባሻገር ብሩህ እንደሚሆን ቀብድ የሚያሲዝ ነው ። ይሁንና ከተስፋዎቻችን ፊት የተደቀኑ ስጋቶችን በመላ ፣ በጥበብና በማስተዋል ካልተሻገርናቸው ለውጡን ከመገዳደር አልፈው ዋጋ ሊያስከፍሉን ይችላሉ ። ይህ እንዳይሆን የቀሩ የቤት ስራዎችን በጊዜ ማጠናቀቅ አለብን ። ከእነዚህ ያደሩ የቤት ስራዎች ቀዳሚው ግጭቶች ከመከሰታቸው በፊት መከላከልና የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ነው ። ከዚያም አስተማማኝ ሰላም የማስፈን ፤ በዜጎች መካከል የተፈጠረውን ክፍተት የማጥበብ ፤ ልዩነቶችን በኃይል በመንጋ ፍርድ ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ በመነጋገር በውይይት ለመፍታት የሚያግዙ ተከታታይ መድረኮችን ማመቻቸት ይበልጥ ተጠናክሮ ሊሰራበት ይገባል ። ገዥው ፓርቲም ሆነ ተቃዋሚዎች ከፓርቲያቸው ይልቅ ሀገርንና ሕዝብን በማስቀደም ቀጣዩ ምርጫ ነፃ ፣ ግልፅ ፣ ተአማኒ ፣ ፍትሐዊ ፣ አሳታፊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የሚያግዙ ቁልፍ የምርጫ አላባውያንን በጋራ መለየት አለባቸው ። ከወዲሁ የመራጩን ፣ የእጩውን ፣ የተቃዋሚ ፓለቲካ ፓርቲዎችንና የሕዝቡን በራስ መተማመን መገንባት ትኩረት ይሻል ። የዚህ ምርጫ ስኬትም ሆነ ውድቀት የሁላችንም ስኬትና ውድቀት እንደሆነ ተገንዝበን በጋራ ልንቆም ይገባል ። የሀገራችንን መጻኢ እድል የምንወስንበትና የምንተረጉምበት ታሪካዊ አጋጣሚ መሆኑን ተገንዝበን በንቃት ፣ በማስተዋልና በጥበብ ስለ 1ኛው / 6ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ እንትጋ ።
ፈጣሪ ሀገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን አብዝቶ ይባርክ !አሜን።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 7/2013