ልጆች ሳለን መምህራኖቻችን ስለ ፍላጎታችን መዳረሻ አንድ በአንድ ይጠይቁን ነበር:: ‹‹ወደፊት ስታድጉ ምን መሆን ትፈልጋላችሁ?›› እያሉ:: የዛኔ ታዲያ ምድረ ተማሪን ማየት ነው:: ሁሉም እጁን እያወጣ የልቡን ምኞት ለመተንፈስ ይሽቀዳደማል:: ከትምህርቱ ማዶ፤ ከመልፋት መድከም ባሻገር የወደፊት ህልሙን ለመናገር የሚጣፈደው ብዙ ነው::
ይህ ጥያቄና የፍላጎት ስሜት የሚንጸባረቀው ታዲያ ከፍ ሲሉ አልነበረም::ገና በአንደኛ ደረጃ የመጀመሪያዎቹ ክፍሎች ላይ ሳሉ እንጂ:: አብዛኛው ተማሪ ይህ እውነት ሲነሳለት የምኞቱን፣ የፍላጎቱን ለመናገር ወደ ኋላ አይልም:: ከመምህሩ ጥያቄ በኋላ አንዱ ይነሳና ‹‹እኔ ሳድግ ዶክተር መሆን እፈልጋለሁ›› ይላል:: ተከታዩ ተማሪ ደግሞ ‹‹ፓይለት፣ሌላው አስተማሪ፣ኢንጂነር ወታደር፣ሳይንቲስት … እያለ ይቀጥላል::
ተማሪዎቹ ይህን ለመናገር ህልም የሆናቸው ከትምህርት የሚገኘው ጣፋጭ ፍሬ ስለገባቸው መሆኑ ግልጽ ነው::አስቀድመው የመማርን ጥቅም ባያውቁትና በጎ አርአያ የሚሆን ማሳያ ባይኖራቸው እንዲህ ለመናገር አይደፍሩም::በርትቶ ተምሮ በመለወጥ ብዘዎች የደረሱበትን የዕውቀት ማማ አሳምረው ያውቁታል:: በእነሱ ፈለግ ተከትለውም አርማቸውን ለማንሳት መድረሻቸውን ያስባሉ፣ያልማሉ:: አጋጣሚ ሆኖ ካሰቡት ሙያ ላይ የሚያርፉ ብዙ ናቸው::እነሱ ህልማቸው ዕውን ሆኗልና በያዙት ዘርፍ ስኬታማ ለመሆን አይዘገዩም::
ሌሎች ደግሞ በልጅነት ካረፉበት ህልም ርቀው ከሌላ ሙያ ይገኛሉ:: አንዳንዶች ከምኑም ሳይደርሱ ከትምህርት ዓለም ተናጥበው ህልማቸው ከዕቅድ ውጭ ይሆናል :: መገኛቸውም ካልታሰበው ጥግ ያርፋል:: እነዚህኞቹ እቅጣጫ መንገዳቸው ሌላ ቢሆንም ስለትምህርት እርም የሚሉ ናቸው ለማለት መረጃው አይገኝም::
ከሰሞኑ ከአንድ የማህበራዊ ገጽ ላይ አንድ መልዕክት ለዓይኖቼ ደረሰ::ሁሉንም ቃል በቃል አየሁት:: ያነበብኩት ሀሳብ እስከዛሬ በውስጤ የቆየውን የመማር ጥቅም ከእጅ የሚበትን መስሎ ተሰማኝ:: ‹‹ተምሬ የት ልደርስ? ይላል:: ዕውን የተማረ ፣የተመራመረ መድረሻ የለው ይሆን? ነገሩ ግራ እያጋባኝ ወደ ጽሁፉ ተመለስኩ::
የተምሬ የት ልደርስ ፍሬ ሀሳብ መነሻ ገንዘብ ይሉት ጉዳይ ነው::ይህን አስፈላጊ ፤ ለዛውም ወሳኝ የሆነ ነገር የሚዘውረው ትምህርት ሳይሆን ቢዝነስ /ንግድ / ብቻ ስለመሆኑ ሀሳቡ ይጠቁማል:: አብዛኞች በዘመናችን እየተማረኩበት ያለው እውነትም ፈጣንና አቋራጩን የንግድ ልውውጥ ይመስላል:: ይህን ሀቅ በተግባር ሞክረን አይተነዋል የሚሉቱ ደግሞ ከትምህርት ልፋት ድካም ባነሰ መልኩ የቢዝነሱ ጸጋና ጉልበት እንደሚገዝፍባቸው ያምናሉ::
ወደ ጽሁፉ መለስ ብዬ በግርምታ ማንበቤን ቀጠልኩ ::የተምሬ የት ልደርስን ሀሳብ እንደመነሻ ያሳየው ገጽ ሀሳቡን በግልጽ እየተቃወመ መሆኑን አስተዋልኩ:: ጸሀፊው ይህ አይነቱ ሀሳብ የእነሱ ይሆናል ብሎ ከማይጠብቃቸው ሰዎች ጭምር እየመነጨ መሆኑ አሳስቦታል::
አሁን ላይ ብቸኛው የችግር መፍቻ ቁልፍ ትምህርት ሳይሆን ገንዘብ እንደልብ የሚዘወርበት የንግዱ ዘርፍ ብቻ ተደርጎ እየታሰበ ነው::ዓለም በእግሯ የምትቆመው በቢዝነሱ የደም ዝውውር የሆነ እስኪመስል ተጽዕኖው ከፍ ማለት ይዟል::
በትኩረት ወደ ጽሁፉ መስመሮች ተመለስኩ:: በታላላቅ ሃይማኖቶች አስተምህሮ የፈጣሪ ስጦታዎች የተለያዩ ስለመሆናቸው ይጠቁማል::ንግድ ጥበብ ስለመሆኑ ቢታመንም ሁሉም ግን ነጋዴ መሆን እንደማይቸል ግልጽ ነው::ምርጥ ነጋዴ መሆን የቻለው ደግሞ ከፈጣሪ የትምህርት ስጦታና ዕውቀት ሲሰጠው መሆኑን ማመን ይኖርበታል::ይህ ምሳሌ ደግሞ ማንም ያለ በቂ ትምህርትና ዕውቀት የትም መድረስ እንደማይቻለው አመላካች ይሆናል::
በፅሁፉ ላይ አንድ የማይሸሽ እውነታ በግልፅ ተመላክቷል::አንድ በቢዝነስ ብቻ አምናለሁ የሚል ነጋዴ ዕጣፈንታው ወዴት እንደሚያደርሰው ይጠቁማል:: ጽሁፉ ደጋግሞ ጠያቂ ነው::ከሚመለከተው አካል ፈጣን ምላሽ ባያገኝም እንዲህ እያለ ጥያቄውን ይደረድራል::
አንተ ልጅህን ማስተማር ብትሻ የምትልከው ወዴት ነው? ወደ መርካቶ ነውን? በድንገት የስኳር ህመምህ ተነስቶ መታከም ብትፈልግስ መደረሻህ የት ይሆን? ንብረትህን የሚነጥቅ፣ ዕድሜህን የሚያሳጥር ችግር ገጥሞህ የህግ ድጋፍን ብትሻ ጠበቃ ዳኛህ ማነው?ሚስትህ ምጥ ብትያዝ፣ልጆችህ ቢታመሙ ወዴት ልትሄድ ነው?ታክስ አናትህ ላይ ቢቆለል፣ ገንዘብ ኖሮህ ህንጻ ማሰራት ብትሻ አማካሪህን ከየት ታመጣለህ?
ጠያቂው ብዙ መልስ የሚሹ ጉዳዮችን ደጋግሞ ያነሳል::እንደሱ ዕምነት እነዚህ ዝርዝር ጉዳዮች በሙሉ የቁልፍ መፍቻቸው ገንዘብ/ቢዝነስ / ብቻ ሳይሆን መሰረቱ በትምህርት የተደገፈ ዕውቀት ነው:: ከጠያቂው ባለፈ ሌሎቻችን ጭምር የራሳችን ጥያቄና ሀሳቦች ሊኖሩን ይችላሉ::
ወደ እውነታው መለስ ብለን ስንገመግም ደግሞ አሁን ላይ በርካቶች መሰረታዊ ለሚባለው ትምህርትና ዕውቀት ትኩረታቸው አናሳ መሆን ይዟል::እንደእነሱ ዕምነት ዓለማችን መመንደግ፣ማደግ የያዘችው ቢዝነሱን መሰረት አድርጋ ነው::እንዲህ ከሆነ ደግሞ ዕድሜ ዘመን ሙሉ መማር፣ለዕውቀት መትጋት አስፈላጊ አይሆንም::
እንደውም አንዳንዶቹ ይህን ምክንያት መነሻ አድርገው ተምሬ የት ልደርስ? ሲሉ ይደመጣሉ:: ለዚህ ማሳያቸው የተለመደው ቢዝነስና ቢዝነስ ብቻ ነው:: አልገባቸው ይሆናል እንጂ ቢዝነሱም ቢሆን በወጉ ሊቀላጠፍ የሚችለው በዕውቀትና በጥሩ ትምህርት ሲታገዝ ነው::ያልተማረ ነጋዴ ለስራው ስኬታማነት ሊቀጥር የሚችለው በቢዚነሱ በቂ ዕወቅት ያለውን ባለሙያ ስለሚሆን ::
የአባባል አባዜ ሆኖ እንጂ ዘመናችን ባለ ቢዝነሱን ብቻ ሳይሆን ባለ ዕውቀቱ ሊቅ እንደሚያስፈልጋት ግልጽ ነው:: እንዲያማ ባይሆን ይህ ሁሉ ቴክኖሎጂ ሲስፋፋ ተማረው፣ የተመራመረው ሀይል ባላስፈለገ ነበር::አንድ ምሳሌ ላንሳ ሁሌም ባይሆን አንዳንዴ ደጋግመው የቆሙባትን መሬት የሚያሙ፣ የሚያማርሩ አንዳንዶች ይኖራሉ::
ይህን ሀሜትና ምሬታቸውን የሰሙ ሌሎች ታዲያ ለእነሱ የሚሆን መልስ ሲሰጡ አርግተኝነትን አክለው ነው ‹‹በማን ላይ ቆመሽ ምድርን ታሚያለሽ››የሚለውን ተረት አስቀድመው ::
የዕውቀትና የቢዝነሱም ጉዳይ እንዲሁው:: ቢዝነስ ራሱን የቻለ ጥበብ ይጠይቃል:: በሙያው የገቡ ብርቱዎችም አሰራር፣ አያያዙን ያውቁበታል:: ሙያውን ሲኖሩበት ለመልካም ፍሬ ነውና የድካም ዋጋቸውን፣ የላባቸውን ጠብታ ያህል አያጡበትም::
ይህ የቢዝነስ ዓለም ታዲያ ያለአንዳች የዕውቀት መሰረት የተገነባ አይደለም:: ከመነሻ እስከ መድረሻው ይፈተሽ ቢባል በዕውቀት እጆችና አዕምሮዎች የተዳሰሰ፣የተዳበሰ ነው:: ቢዝነሱ ያለዕውቀት ለብቻው ፈጽሞ ሊቆምና ሊተነፍስ አይቻለውም::
ይህ አይነቱ በርካታ እውነታ ባለበት ዓለም ታዲያ ‹‹ትምህርት ለምኔ ቢዝነስ መድህኔ›› ብሎ መተረቱ የሚያዋጣ አይሆንም::እንዲህ አስቦ ብቻ ልራመድ ፣አርቄ ልጓዝ የሚል ቢኖር ደግሞ ‹‹በማን ላይ ቆመሽ ምድርን ታሚያለሽ›› ይሉት አባባል ሊተረክበት ግድ ይሆናል::
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም