ተግባር የሌለው የትልቅነት ምኞት መቀመቅ ነው:: በትናንት የሚያስኖር፣ ከታሪክ ሠሪነት አጉድሎ ታሪክ አውሪ የሚያደርግ የዝቅታ ቦታ ነው:: «ትልቅ ነበርን ትልቅም እንሆናለን» እንላለን:: ይሄን መፈክር ያልሰቀለ ግድግዳ፣ ያልተናገረ የመንግሥት አካልና ቢሮ የለም:: ተግባራችን ሲፈተሽ ለዚህ እውነት የሚሆን ብዙ ይቀረናል::
እውነት ነው እንደ ሀገር ትልቅ ነበርን:: ከራሳችን አልፈን ለዓለም የተረፈ የትልቅነት ሚና ነበርን:: በፖለቲካው፣ በዲፕሎማሲ ግንኙነት፣ በሠላሙ፣ በአስታራቂነት፣ በአንድነት፣ በወንድማማችነት የገነንን ሕዝቦች ነበርን:: ሥልጣኔና ዘመናዊነት መገኛቸው ከእኛ ዘንድ እስኪመስል ድረስ ምንም ለሆነችው ዓለም ፋናወጊዎች ነበርን::
አሁን ዘመን ተቀይሮ ከትልቅነት ወርደን ትልቅነትን የምንሽት ሆነን ተገኝተናል:: ትልቅ ነበርን እያልን ድሮን በማስታወስ በማይሠሩና በማያስቡ ወዲያ ወዲህ ማንነቶች ከከፍታችን ዝቅ ብለናል:: ትልቅ ያደረገንን ኢትዮጵያዊ ማንነት በብሔርና በዘር ሸንሽነን፣ ከፊት ያቆመንን የአብሮነት ኃይል በእኔነት መንዝረን ማንም ገፍትሮ የሚጥለው አቅመ ቢስ ልናደርገው እየተጋን ነው::
እንዴት ነበር ትልቅ ሀገርና ሕዝብ የሆንነው ብለን ብንጠይቅ፣ እንዴት ነበር ከዓለም ቀድመን ፊተኛ የሆንነው ብለን ብንመረምር በአንድነትና በወንድማማችነት ከፍ ሲልም በአንድ ገናና ስም የሚጠራ ኢትዮጵያዊነትን እናገኛለን:: አሁን ግን ይህ ትልቁ ስማችን ከብሔር ማንነታችን ቀጥሎ የሚጠራ ሆኗል::
ከብሔር ለጥቃ የምትጠራ ሀገር ትልቅ የመሆን ህልም እንጂ አቅም አይኖራትም:: ትርፉ ድካም ብቻ ነው:: ትልቅ መሆን አቅቶን በትልቅነት ምኞት አምናን እያስታወስን የምንዳክረው ተግባር በሌለው ህልም ነው:: ህልማችን ኢትዮጵያዊነትን ለብሶ፣ እኛነትን ተንተርሶ ወደመሆን እስካልመጣ ድረስ ትልቅነትን አንደርስበትም::
ምኞታችን ከብሔር ፖለቲካ ጸድቶ፣ ከአክራሪነት ነጥቶ ሁሉን አቃፊ እስካልሆነ ድረስ ግድግዳዎቻችን ምኞታችንን ከመስቀል፣ ፖለቲከኞቻችን ትልቅ ነበርን ትልቅም እንሆናለን ከሚል ትርክት የሚታደገው አይኖርም:: ትልቋ ኢትዮጵያ ዳግም ትልቅ ሆና እንድትመጣ በምኞታችን ውስጥ ለትልቅነት የሚያበቃ ሃሳብና ድርጊት፣ እርቅና ምክክር፣ ሠላምና ተግባቦት ያስፈልገናል::
አሁን አሁን አንዳንድ ድርጊቶቻችን ልጓም ለቆ ቼቼ ዓይነት ነው:: ልጓም ለቆ ቼቼ እንደምን ይቻላል? እርካብ ስቶ ግልቢያ፣ ፍቅርን ንቆ ጸጋ እንዴት ይሆናል? ሳንግባባ ትልቅነትን የምንመኝ፤ ሳንታረቅና አንድ ሳንሆን ትልቅ ነበርን ትልቅም እንሆናለን የምንል፤ ከጦርነትና ከጥላቻ እሳቤ ሳንወጣ እድገትና ብልግናን የምንሽት ሆነናል:: ትልቅነት በዚህ ውስጥ የለም:: ስለትልቅነት የተጸፉ አያሌ መጽሐፍት ትልቅነትን በዚህ መንገድ አልፈቱትም::
ትክክል ነገር መገኛው ትክክል የሆነ ቦታ ነው:: ፖለቲካችንን ሳናጸዳ፣ ሃሳቦቻችንን ሳንገራ እንደአባቶቻችን ትልቅ መሆን አንችልም:: በወንድማማችነት ሳንተቃቀፍ፣ በምክክር ወደአንድነት ሳንመጣ ከምንመኘው እውነት መድረስ አንችልም:: ዘረኝነትና ብሔርተኝነትን ገድለን ሳንቀብር፣ በወንድም ሞት ደም የተቀቡ ጎራዴዎቻችንን ወደአፎታቸው ሳንመልስ፣ ለሠላምና ለእርቅ ሳናጎነብስ ከፍ ማለት የማይታሰብ ነው::
እስካሁን ከስረናል:: እየሄድንበት ያለው ነባራዊ ሁኔታ ትልቅነትን የሚሰጥ ሳይሆን ትልቅ እንዳንሆን መንገድ የሚዘጋ ነው:: መረቦቻችን ዓሣ እንዲይዙ፣ ሃሳቦቻችን እውነት እንዲጸንሱ ወደ ልክ የሚወስድ ልክ የሆነውን ጎዳና መከተል ግዴታችን ነው:: ሃሳብ ብቻውን አቅም የለውም:: ምኞት ብቻውን ሀገር አይፈጥርም::
ሀገር የምትፈጠረው ሀገር ለመፍጠር ብቁ በሆኑ ሃሳቦች ነው:: ትልቅነት የሚመጣው ለትልቅነት በተዘጋጁ አእምሮና ልቦች ነው:: ከድጡ ወደማጡ በሆነ ፖለቲካ፣ ሴራና መገፋፋትን ባነገበ የሥልጣን ሽኩቻ ሀገር የለችም:: የአቅጣጫ ለውጥ ያስፈልገናል:: ምኞታችን ጥሩ ሆኖ ሳለ ተግባራችን ግን ለምኞታችን የሚመጥን አይደለም:: ምኞታችንን የሚወልድ በእውቀትና በማስተዋል ከምንም በላይ ደግሞ በአንድነት የጎለመሰ ማንነት ያስፈልገናል::
በተለጠጠ የብሔር እሳቤ ውስጥ ሀገር ተፈጥራ አታውቅም:: የተለጠጠ የብሔር እሳቤ ሀገር የሚያኮስስ፣ ትውልድ የሚኮሰኩስ ነቀርሳ ነው:: ነገን የሚያጨልም፣ ተስፋን የሚያጠይም የዝቅታ ቦታ ነው:: መዳን አቅቶን ለግማሽ ክፍለ ዘመን የታመምነው በዚህ ነቀርሳ ነው:: ከዚህ ደዌ የሚፈውሰን እና ወደትልቅነት የሚወስደን በኢትዮጵያዊነት ስንታከም ነው::
የትኛውም ዓለም የሠለጠነው ሠልጥኖም ፊተኝነትን የተቀዳቸው በብሔር እሳቤ ሳይሆን በምክንያታዊነት ነው:: ምክንያታዊነት ደግሞ እውቀትን ተንተርሶ በሃሳብ የበላይነት ነፍስ የዘራ የምክክርና የውይይት ልማድ ነው:: እንድንግባባበት እና እንድንታረቅበት ከፊታችን ሰፊና ሁሉንም የማኅበረሰብ ክፍል የሚያሳትፍ የምክክር ጉባኤ አለ::
ይሄ ጉባኤ በምክንያታዊነት ወደትልቅነት ለመሄድ ጥሩ አጋጣሚያችን ነው:: ችግሮቻችንን ነቅሰን በመፍትሔ ሃሳብ አርቀንና ታርቀን ወደአንድነት፣ ወደኢትዮጵያዊነት የምንመለስበት የተሐድሶ መድረክ ነው:: ከልዩነት ወጥተን ስለሀገራችን አንድ ዓይነት ሃሳብ የምናስብበት የእርቅና የመተቃቀፍ ጉባኤ ነው::
በሁሉም ነገር ተፈጥሯዊ ብዝሃነታችን ጉዳት የለውም:: ሀገር በመፍጠር ረገድ የተሳካላቸው ሀገራት የተለያየ ባህልና ሥርዓት፣ ልማድና ወግ ያላቸው ማኅበረሰቦች ናቸው:: እኛ ደግሞ በዚህ ነገር የታደልን ነን:: የልዩነት ዋጋው ሲገባን ብቻ ነው የተሣለች ሀገር መፍጠር እና ለመጪዎቹ ትውልዶች ማስተላለፍ የምንችለው::
ሕንድ ብዙ ማንነት ያላት ሀገር ናት፣ ቻይና፣ ናይጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ ሌሎችም በርካታ ሀገራት በብዙ ልዩነት ውስጥ ሀገር የገነቡ ናቸው:: በዚያው ልክ ልዩነታቸውን ለኃይልና ለብርታት ያልተጠቀሙ ሀገራት ዕጣ ፈንታቸው እንደ ሩዋንዳና ዩጎዝላቪያ የከፋ ዋጋ ለመክፈል ይገደዳሉ::
ብሔር ከሀገር መቅደም የለበትም:: ብሔር ከሀገር ከቀደመ ልዩነት ጸጋ መሆኑ ቀርቶ መርገምት ሊሆን የሚችልበትን አደጋ ያስከትላል:: ከሀገር የቀደሙ ማንነቶች፣ አስተሳሰቦች፣ እምነቶች፣ ሥርዓቶች የኋላ ኋላ ዳፋቸው ለሁሉም የሚተርፍ ነው::
እዚህ ላይ የታዋቂውን አትሌት የቀነኒሳ በቀለን የአንድ ወቅት ንግግር ለመጥቀስ እገደዳለሁ:: ቀነኒሳ ስለብሔር ተጠይቆ ሲመልስ ልክ በሆነና ሁሉንም ባስማማ ሸጋ አገላለጽ ነበር:: ለእኔ አለ..‹ለእኔ ብሔር ማለት እንደ ጫማ እና ካልሲ፣ እንደ ልብስ እና ኮፍያ ተጨማሪዎች እንጂ ዋናዎች አይደሉም:: ዋናው ሀገር ነው› ሲል ነበር የተናገረው::
እውነት ነው ዋናው ሀገር ነው:: የብሔር እሳቤዎች ከሀገር ቀጥለው የሚመጡ ናቸው:: ሀገር ከብሔር ካልቀደመች፣ ኢትዮጵያዊነት ከእኔነት ካላለፈ ምኞታችን ሁሉ ውሃ ይበላዋል:: ወይም ደግሞ አሁን ላይ ትልቅ ነበርን ትልቅም እንሆናለን እያልን እንደምንመኛው ዓይነት ከንቱ ምኞት የማይደረስ ጉዞ ነው::
በሀገራችን በፖለቲካ ልዩነት የምንሰቃይበት፣ ወደጦርነት የምንገባበት የመገዳደል ልማድ ትልቁና ዋናው ትልቅነታችንን የሰወረብን ድርጊት ነው:: የማይገድል ፖለቲካ፣ የማይዋሽ ፖለቲከኛ እስካልተፈጠረ ድረስ ትልቅ መሆን አንችልም:: በነፃ መድረክ ስለሆነው እና እየሆነ ስላለው ጠያቂና ሞጋች ትውልድ እስካልፈጠርን ድረስ መታደስ አንችልም::
አባቶቻችን ትልቅ የነበሩት እኛ የሌለን እነሱ ያላቸው ወይም ደግሞ እኛ ያልገባን እነሱ የገባቸው እውነት ስላላቸው ነው:: ወደቀደመው ትልቅነታችን ለመመለስ ያልገባንን የአባቶቻችንን እውነት ፈልጎ ማግኘት አለብን:: ወደትልቅነት የሚወስዱ መሰላሎች በፍቅር የሚረገጡ፣ በአብሮነት የሚጀመሩ ናቸው:: ሁሉም የከፍታ ጎዳናዎች በመያያዝና በመደጋገፍ ጀምረው የሚያበቁ ናቸው::
የሌለን ምንድነው? አባቶቻችን ገብቷቸው እኛ ያልገባን የትልቅነት እውነት ምንድነው? ይሄ ጥያቄ ተግባር ከራቀው የትልቅነት ምኞት የሚያወጣን ወደአባቶቻችን የትልቅነት እውነት የሚያስጠጋን ነው:: ይሄ እውነት ከራቀንና ካልደረስንበት የከፍታ ምኞት የሚሰቅለን ነው:: የብዙዎቻችን ምኞት አንድ ዓይነት ነው:: ማደግ እንፈልጋለን፣ ሞትና ጉስቁልና የሌለባት ኢትዮጵያ እንድትፈጠር እንሻለን:: በፖለቲካው በማኅበራዊ ሕይወታችን የጥንቱን አብሮነት መልሰን በአንድ ስም መጠራት እንፈልጋለን::
ለዚህ ምኞታችን እውን መሆን የበኩላችንን ስንወጣ ግን አንታይም:: ጋን በጠጠር እንደሚደገፍ የኢትዮጵያ ተስፋና ህልም በእኛ ትንሽ መዋጮ ወደእውነትነት እንደሚቀየር ገና አልገባንም:: ማንን ነው የምንጠብቀው? ማን መጥቶ ከዝቅታ እንዲያነሳን ነው የምንጠብቀው? ሜዳውም ፈረሱም እጃችን ነው:: በፍቅርና በአብሮነት ተነስቶ መጋለብ የእኛ ፈንታ ነው::
አክሱምና ላሊበላን ያነጹ እጆች፣ የአፍሪካ እናት፣ የዓለም ምልክት..የፍጥረት ሁሉ በኩር ዛሬ ትልቅነት ርቋት በምኞት ስትዳክር ማየት ያሳዝናል:: የፉክክር ቤት ሳይዘጋ ያድራል እንደሚባለው በፉክክር ውስጥ ሀገራችንን እያጎሳቆልናት ነው:: የፉክክር ፖለቲካ ሀገር አይገነባም:: በዓለም ታሪክ የፈረሱ ሀገራት በፉክክር ፖለቲካ ውስጥ ያለፉ ናቸው:: የፉክክር ፖለቲካ የማንነት ፖለቲካ ነው:: ብሔርና ዘርን መሠረት አድርጎ የሚገነባ ነው::
ብሔርና ዘር የቀደመበት ፖለቲካ የጋራ እሴት፣ የጋራ እውነት ለመጸነስ አቅም አይኖረውም:: ያለፈን እያስታወሰ፣ መጪውን እያቀደ የአንድን ማንነት የበላይነት የሚያቀነቅን ነው:: ትልቅ ነበርን ትልቅም እንሆናለን ብለን ስንናገር ትልቅ የሚያደርገንን ፖለቲካና ማኅበራዊ አንድነት ይዘን ሊሆን ይገባል::
ለትልቅነት የሚያበቃ በሌለበት ሁኔታ ትልቅ ነበርን ትልቅም እንሆናለን ብለን ብንናገር ትርጉም አይኖረውም:: አባቶቻችን ትልቅ የነበሩት ለትልቅነት የሚያበቃ ፍቅርና አንድነትን ይዘው ነው:: እንደእኛ በብሔር ተቧድነው ሳይሆን ኢትዮጵያ በሚል የጋራ ስም ተጠርተው ነው::
እውነት መነሻው እውነት ብቻ ነው:: ትክክል የሆነ ነገር በትክክል የሚያበቃ ነው:: አሁን ባለው ፖለቲካ፣ አሁን ባለው ማኅበራዊ አረዳድ እንዳባቶቻችን ያለ ትልቅ ሀገር ለመገንባት ብቁዎች አይደለንም:: ከጦርነትና ከብሔር እሳቤ ነፃ መውጣት አለብን:: አፋችን ላይ ያለችውን፣ ሆና ማየት የምንሻትን፣ ድምጽ ማጉያ በያዝን ቁጥር የምንናገርላትን ኢትዮጵያ ለመፍጠር የአባቶቻችንን የአንድነት መንፈስ ያስፈልገናል::
ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን
የሚሰጡበት ነው።በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 28 ቀን 2016 ዓ.ም