በአሜሪካ ጦር መንደር አካባቢ ባለቤትነታቸው የማይታወቁ ድሮኖች ታዩ

በሚገኙ ሶስት የዩናይትድ ስቴትስ የጦር መንደሮች አካባቢ ባለቤትነታቸው ያልታወቁ ድሮኖች እንደታዩ የአሜሪካ አየር ኃይል አስታወቀ። ከረቡዕ እስከ አርብ ባሉት ቀናት “አነስተኛ ሰው አልባ በራሪዎች” ሰፎክ፣ ፌልትዌል እና ኖርፎክ በተባሉ የጦር መንደሮች አካባቢ መታየታቸውን አየር ኃይሉ ገልጿል።

አየር ኃይሉ በሶስቱ የአሜሪካ ጦር መንደሮች የታዩት ድሮኖች ጥቃት ለማድረስ የመጡ ስለመሆናቸው እስካሁን የሚታወቅ ነገር የለም ብሏል። የአሜሪካ አየር ኃይል ድሮኖቹን ለመከላከል የተወሰደ ርምጃ ይኖር እንደሁ ከመለግፅ የተቆጠበ ቢሆንም “ራስን ለመከላከል” የሚያስፈልጉ ጥንቃቄዎች ማድረጉን አስታውቋል።

በአውሮፓ የዩናይትድ ስቴትስ አየር ኃይል ቃል አቀባይ “አነስተኛ ሰው አልባ በራሪዎች ብሪታኒያ በሚገኙ ሶስት የአሜሪካ አየር ኃይል ጣቢያዎች መታየታቸውን አረጋግጠናል” ብለዋል። “በተለያየ ጊዜ የመጡት እኒህ ድሮኖች ቁጥራቸው እና ግዝፈታቸው የተለያየ ነበር” ሲሉ ገልጸዋል።

“ወታደራዊ ደህንነታችንን ለመጠበቅ ሲባል ምን ዓይነት ርምጃ እንደወሰድን አንገልፅም። ነገር ግን ራሳችንን ለመከላከል አስፈላጊውን ሁሉ እንደምናደርግ እንሳውቃለን” ብለዋል ቃል አቀባዩ። የጦር መንደሮችን አባላት እና ቁሳቁሶች ደህንነት ለመጠበቅ ለማረጋገጥ ሲባል የአሜሪካ አየር ኃይል አካባቢውን እየቃኘ እንዳለ እና ከብሪታኒያ መንግሥት ጋር ተባብሮ እየሠራ እንደሆነም በመግለጫቸው አውስተዋል።

ሶስቱ የዩናይትድ ስቴትስ አየር ኃይል ጣቢያዎች በርካታ ዘመናዊ የጦር ጄቶችን የያዙ ናቸው። አልፎም የአሜሪካ ወታደሮች መኖሪያ መንደሮች አሏቸው። የብሪታኒያ መከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ “መሰል ጉዳዮችን በአትኩሮት ነው የምናያቸው። የጦር መንደሮቻችን ለመጠበቅ ርምጃ እንወስዳለን” ብለው ተጨማሪ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።

ሱፎክ ሚድንሆል የሚገኘው የአሜሪካ አየር ኃይል ጣቢያ በአውሮፓውያኑ 1934 የተገነባ ሲሆን በ2015 ይዘጋል የሚባል ጭምጭምታ ተሰምቶ ነበር። አሜሪካ በአውሮፓ ሀገራት በርካታ የጦር መንደሮች እንዳሏት ቢቢሲ ዘገባ ያመለክታል።

አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You