በዘመናችን አልባሳት የሰው ልጅ መሰረታዊ ፍላጎት ከመሆን ከፍ ብለዋል:: “መጽሀፍን በሽፋኑ አትገምቱ” ቢባልም ሰዎች በለበሱት ልብስ፣ በተጫሙት ጫማ፣ በያዙት ቦርሳ፣ባደረጓቸው ጌጣ ጌጦች ይፈረጃሉ:: በአሁኑ ሰዓት በተለይ በከተሞች አካባቢ ያገኙትን ልብስ ካገኙት ጫማ ጋር አዋህዶ መልበስ እየቀረ ነው:: ‘ዘናጭ’ ወይም ‘ዘመናዊ’ ለመባል ልብስ ስላሞቀና ስላማረ ብቻ አይለበስም:: የዘመኑን ፋሽን (ትሬንድ) መከተል አለበት:: በጣም ዘናጭ ሲኮን ታዲያ የአልባሳት ምርጫዎች ከሀገር ውስጥ ያልፉና ያደጉት ሀገራት በወቅቱ ከሚለበሷቸው ልብሶች እኩል የሚራመዱ በርካቶች ናቸው::
ለዚህ ደግሞ በሀገራችን የሚገኙ የአልባሳት መሸጫ መደብሮች የሚይዟቸው እቃዎች ሙሉ በሙሉ ፍላጎታቸውን አያረካም:: ይህ ሲሆን ታዲያ አቅም ያላቸው በተወሰነ ጊዜ ከሀገር እየወጡ እንደምርጫቸው ሸምተው ይመለሳሉ:: ታዲያ ሀገር ውስጥ ላሉትም መላ አልጠፋም በርካታ የአልባሳት መደብሮች ዘመኑን የዋጁ ብለው ከሚይዟቸው አማራጮች በተጨማሪ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ የመገበያያ አማራጮች ደንበኞቻቸው የመረጡትን እቃ እንደሚያስመጡ መናገር ከጀመሩ ሰነበቱ::
በአዲስ አበባ ቦሌ የአልባሳት መሸጫ ሱቅ ያላት ወጣት ማህሌት ጌታቸው ከውጭ በተለይም ከሺን ደንበኞች ያዘዙትን እቃ ታስመጣለች:: በመደብሯ እሷ እራሷ ዘመኑን የዋጁ ናቸው ብላ ያስመጣቻቸው አልባሳት፣ ጫማዎች፣ መነጽሮች እንዲሁም ቦርሳዎች ይገኛሉ:: መደብሯ ለበርካታ ደንበኞች ያማከለ እንዲሆን በማሰብ በቦሌ ቢገኝም በርካታ ሰዎች በአካል በመሄድ ያሉትን እቃዎች ከመምረጥ ይልቅ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አይተው መምረጥና ማዘዝ ምርጫቸው መሆኑን ትናገራለች:: ለዚህም ይረዳ ዘንድ በቴሌግራም ግሎሲ ሾፒንግ (Glossy Shopping) በቲክቶክ ግሎሲ ሾፒንግኢቲ (glossyShoppinget) የተሰኙ ገጾችን ከፍታ ትእዛዝ ትቀበላለች፤ ያሏትን እቃዎች ለደንበኞች ታስተዋውቃለች::
በማህበራዊ ድረገጾች ያሏትን እቃዎች ስታስተዋውቅ የአልባሳቱን መጠን ትንሽ (ስሞል)፣ መካከለኛ (ሚዲየም)፣ ትልቅ (ላርጅ)፣ በጣም ትልቅ (ኤክስትራ ላርጅ)፣ በማለትና ያሏትን የጫማ ቁጥሮች ታስቀምጣለች:: ሆኖም ልካቸውን የማያውቁ ሰዎች እንደሚያጋጥሙና ለእነሱም ሁለት የተለያየ መጠን ተልኮላቸው ለክተው አንዱን የሚመልሱበት አሰራር እንዳላት ትገልጻለች:: የዴሊቨሪ ክፍያውን ከከፈሉ ባይሆናቸውም ቅያሪ የሚላክላቸው መሆኑን ትናገራልች:: የዴሊቨሪ አገልግሎት የሚሰጡ ቋሚ ደምበኞች ያላቸው መሆኑን በማንሳት እቃው ለደንበኛ በእነሱ በኩል ከተላከ ተመላሽ በሚኖርበት ወቅት እነሱ ጋር አቆይተው የሚመልሱበት አሰራር ዘርግተዋል::
አንዳንድ ገዢዎች መጠናቸውን (ሳይዛቸውን) ከመንገር ባሻገር “እኔ እንደዚህ አይነት ሰው ነኝ” በማለት ተክለ ሰውነታቸውን መለየት የሚያስችል ፎቶ በመላክ “የትኛውን ሳይዝ ባደርግ ይሻላል?” የሚለውን ይጠይቃሉ:: “እነሱም እንዲጎዱ አንፈልግም” የምትለው ማህሌት የመረጡት የልብስ አይነት አይሆናቸውም ብለን ካሰብን ሌላ አማራጭ እናሳያቸዋለን ትላለች:: ከተለያዩ የኦንላይን አማራጮችና ከተለያዩ ገበያዎች ገዝታ በመደብሯ እና በማህበራዊ ድረ-ገጾች ለሸማቾች ከምትለቃቸው የአልባሳትና የማጌጫ አማራጮች በተጨማሪ ሺን ከተሰኘው የመገበያያ አማራጭ ደንበኞች መርጠው አስመጪልን የሚሏትን እቃዎች ታስመጣለች::
ባደጉት ሀገራት የኦንላይን ገበያ ተለምዷል:: ገዢዎች እቤታቸው ሆነው ያዘዙት እቃ ቤታቸው ከደረሰ በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች ባይስማማቸው መመለስ ይችላሉ:: ለዚህ የሚጠበቅባቸው የሻጩን ድርጅት የመመለሻ ቀን ማክበርና ያዘዙበት ድረ-ገጽ ውስጥ በመግባት የሚመልሱበትን ምክንያት መጥቀስ፤ እቃው እንዳይበላሽ በጥንቃቄ መያዝና እንደ ገዙበት ድርጅቱ ሁኔታ የሚመለስበት ቦታ ወስዶ ማስቀመጥ ነው:: ሆኖም ከሺን እቃዎችን የምታስመጣው ማህሌት ደንበኞች ባይሆናቸው ኃላፊነቱን እንደማትወስድ ትገራለች:: ከሺን እቃ አዘዋት በመጣላቸው ያልተደሰቱ አንዳንድ ሰዎች የቅሬታ አስተያየታቸውን የማህበራዊ ድረ-ገጿ አስተያየት መስጫ ላይ የጻፉበት ገጠመኝም አላት::
እንደማህሌት ገለጻ፣ ሸማቾች በቀጥታ በውጭ የመገበያያ ድረ-ገጾች ያዩት እቃ እንዲመጣላቸው ሲጠይቁ የሚታዘዘው ገዢው ይሁንልኝ በሚለው ልኬት ነው:: ሸማቹ የሰጠው ልኬት ትክክለኛው ባይሆን ተጎጂ ይሆናል:: ጫማዎች ብዙ ጊዜ ሞደ ጠባብና ሞደ ሰፊ የሚባል እንዳላቸው በማንሳት ይሄ ግን በትእዛዙ ላይ እንደማይገለጽና ሰዎች በቁጥራቸው ይሆነኛል ብለው የሚያዙት ጫማ ሳይሆናቸው የሚቀርበት አጋጣሚ በርካታ መሆኑን ትናገራለች:: ከውጪ ድረ-ገጽ ሦስት ጫማ አዛ ያስመጣችላት ደንበኛዋ አንዱ ብቻ ልኳ እንደሆናት ታስታውሳለች:: በተመሳሳይ በውድ ዋጋ የሚሸጥ ቡትስ ጫማ በምርጫዋ የመጣላት ደንበኛዋ ልኳ ሳይሆን ቀርቷል:: በማህበራዊ ገጿ ላይ ብትለጥፍላትም ከዋጋው ውድነት የተነሳ ገዢ አልተገኘም:: ከዚ በመነሳት በተለይ ጫማ ከዚሁ ተለክቶ ቢገዛ ትላለች::
በእጇ የሚገኙትን እቃዎች በኦንላይን ያዘዘ ደንበኛ እቃውን ሳያበላሽ በፍጥነት እስከመለሰ ድረስ የምትቀይር መሆኑን የምትገልጸው ማህሌት፤ ሆኖም ቀጥታ ከውጪ የመገበያያ ድረ-ገጾች አይተው ይታዘዝልን የሚሏቸው እቃዎች ባይሆኗቸው ኪሳራው የገዢ ነው ትላለች:: ታዞላቸው የመጣ እቃ ሳይሆናቸው ሽጭልን በሚሏት ወቅት በትብብር በማህበራዊ ድረ-ገጿ ላይ በመለጠፍ እንዲሸጥ ትረዳቸዋለች::
ማህሌት ከልምዷ በመነሳት ሰዎች በተለይ ከውጪ ድረ-ገጾች እቃዎችን ከማዘዛቸው በፊት መመሪያውን (ዲስክሪብሽኑን) በደንብ ቢያነቡት ትላለች:: ከዛ በተጨማሪ ከውጭ ሀገራት የመገበያያ ድረ-ገጾች ከማዘዝ ይልቅ በእሷና በመሰል ሻጮች እጅ ላይ የሚገኙ እቃዎችን ቢያዙ ስለእቃው ባህሪ ጠይቀው መረዳት ከመቻላቸውም ባሻገር ከወሰዱትም በኋላ ስላልሆነኝ መጠኑን ጨምሩልኝ ወይ ቀንሱልኝ ማለት ይችላሉ:: እሷ እራሷ ሻጭ ብትሆንም በተለይ ሱሪና ጫማ ከድረ-ገጽ ከማዘዝ ሀገር ውስጥ ካስገቡ ሰዎች በአካል ተገኝታ መግዛት ምርጫዋ መሆኑን ትናገራለች:: ሰዎች በኦንላይን የሚለጠጡ (ስትረች የሚያደርጉ) ቀሚሶች፣ከላይ አላባሾች (ቶፖች)፣ ኮቶች በትእዛዝ ቢመጡ የተሻለ መሆኑን ትናገራች::
ቤዛ እሸቱ
አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም