በሀገር ላይ ሌብነት ሁሉን አቀፍ ክስረት ነው

አንዳንድ ኩነቶች እንደብርቱ መነሻቸው ብርቱ መውደቂያም አላቸው። ሀገር በታሪክ፣ በሥራ፣ በትጋት፣ በአብሮነት እንደምትጸና ሁሉ የሚጥላትም እንደሙስና ያሉ ራስ ተኮር አስተሳሰቦች ናቸው። አብዛኞቹ ሀገራት በብልሹ አሠራር በተከፈተ የሙሰኞች አመል ወድቀዋል ለመውደቅም እየተንገዳገዱ ናቸው።

በዚህ ዓውድ ውስጥ መውደቅ ማለት ከታሪክ መጥፋት አሊያም ደግሞ አለመኖር አይደለም። መውደቅ ማለት በእድገትና በብልጽግና ወደ ኋላ መቅረት ማለት ነው። ብዙኃኑን የረሳ፣ መሐሉን የዘነጋ ተጠያቂነት የሌለው ሕገ ወጥ ቅብብሎሽ ማለት ነው። ሕግና መርሕን ባልተከተለ ራስወዳድነት የሀገርን ሀብት ለግል ጥቅም በማዋል ብዙኃኑ ላይ መከራን ማወጅ ማለት ነው።

በሀገር ላይ ሌብነት ሁሉን አቀፍ ክስረት መሆኑን ለማመን በሙስናና በብልሹ አሠራር የደረሰብንንና እየደረሰብን ያለውን ስርቆትና ውድመት ማሰቡ በቂ ነው። የሰው ልጅ በእንቅፋት ተመቶ ይወድቃል አሊያም ይደነቃቀፋል። የሀገር መደነቃቀፍ በሙሰኞች አመል ውስጥ ያለ ነው። መደነቃቀፍ ጸንተን እንዳንቆምና ወደፊት እንዳንሄድ የሚያደርግ ነው።

ሙስና መነሻው የተለያየ ቢሆንም የስብዕና ግድፈት የሚለው ግን ጥሩ አድርጎ ይገልጸዋል። በስብዕናቸው የተመሰገኑ ሰዎች የሌላን ለመንካት የሞራል ልዕልና የላቸውም። ሀገር በማገልገል ጊዜና ጉልበታቸውን የሚሰዉ ናቸው። በተቃራኒው በስብዕናቸው ጤነኛ ያልሆኑ ግለሰቦች በስርቆትና በሌብነት በሌላም መልካም ባልሆነ ተግባር በሀገር ላይ መከራ ለማዝነብ የሚቀድማቸው የለም።

በብልሹ አሠራር እየተመዘበረ ያለው የሕዝብ ሀብትም በነዚህ ግለሰቦችና ቡድኖች መሪነት የሆነ ነው። ንቅናቄአችን መጀመር ያለበት ስለሀገር ሲሉ ታማኝ የሆኑትን በማመስገን እና ነውረኞችን በመቅጣትና በማጋለጥ ነው። ታማኝ አገልጋዮች ካልተመሰገኑ በሕዝብ ስም የሚነግዱ አስመሳዮች ከጥፋታቸው አይታረሙም።

ሙስና በብልሹ አሠራር ተጀምሮ እንደ ሀገር ብዙ ዋጋ የሚያስከፍል ሲሆን በተጨማሪ ከየትኛውም አደገኛ ሁኔታ በላይ ጎጂ መሆኑን ለመገንዘብ ጠቢብ መሆን አይጠይቅም። ሥልጣንና ኃላፊነታቸውን ወደጎን ብለው በማን አለብኝነት ከድሀ ሕዝብ ላይ የሚሰርቁ ብዙ ባለሥልጣናት አሉ።

ማይክ በጨበጡ ቁጥር ሙስና ጎጂ ነው፣ አዋራጅ ነው የሚሉ በተግባራቸው ግን የቀለሉ የመንግሥት ባለሥልጣናት ለሕዝብ በተከፈተ በራፋቸው ብዙ መሰል ነውረኞችን አመላልሰዋል። ከፌዴራል እስከ ወረዳና ቀበሌ ድረስ ለምንም ነገር እጅ መንሻ የሚጠይቁ ተበራክተዋል። አንዳንዶቹ ከተጠያቂነት ወደእውቅና ወርደው ነውርነታቸው ቀርቶ ገሀድ ወጥተው በግልጽ ወደመሆን የመጡ ናቸው።

ሙስና በጭቃ ሲለወስ መልኩ እንደሚጠፋ አንድ ፀዓዳ ቁስ ልናስበው እንችላለን። የፀዓዳውን ቁስ ውበት ጭቃው ሸፍኖታል። ጭቃው እስካልጠራ ድረስ የቁሱ ውበት አይታይም። ሀገርም እንዲህ ናት..ሙሰኞች እስካልጠፉ ድረስ እድገቷ ብልጽግናዋ አይታይም። ግልጸኝነትና ተጠያቂነት እስካልሰፈነ ድረስ ሕልምና ራዕዮቻችን አይሰምሩም። ጥቂቶች ጠግበው ብዙኃኑ በተራበባት ሀገር ላይ፣ ጥቂቶች ደልቷቸው የተቀረው በተከፋበት ሁኔታ ሁሉን አቀፍ ውድቀት ካልሆነ በስተቀር ሁሉን አቀፍ ለውጥ አይመጣም።

ሁሉን አቀፍ ለውጥ የሚመጣው ሁሉን አቀፍ በሆነ ሚዛናዊ አስተሳሰብና ትግባሬ ነው። ሁሉን አቀፍ ውድቀት ለመፍጠር ቀላል ነው ሙስና ብቻውን በቂ ነው። የሙስናን አደገኛነት ለመግለጽ ብዙ የቅርብና የሩቅ ታሪኮችን ማስታወስ ይቻላል። ብዙ መብራትና ውሀ፣ ሆስፒታልና ትምህርት ቤት የሚገነባ ገንዘብ ወደአንድ ሰው ኪስ ሲገባ፣ ብዙ ድሃዎችን የሚታደግ የሕዝብ ንብረት ወደሆኑ ቡድኖች ካዝና ሲገባ፣ የተለያዩ የሕዝብ መገልገያ መሠረተ ልማቶችን የሚሠራ ረብጣ በሆኑ ሰዎች እጅ ሲገባ አይተናል፤ ለዚህ እንግዶች አይደለንም።

እንደመንግሥት እና እንደዜጋ ትልቁ ትግላችን ሊሆን የሚገባው የሙሰኞችን ሰንሰለት መበጠስ ላይ ነው። በእኩል ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ አስተዳደራዊም ሆነ ተገልጋይነትን ለማስፈን ትልቁ መነሻችን ሊሆን የሚችለው ግልጽነት የሰፈነበት የተጠያቂነት አሠራር ነው። ሙሰኞችን ማጋለጥና ለሕግ የማቅረብ አሠራር ድሀና ኋላ ቀር በሆነች ሀገር ላይ እንዲሁም ራሱን በምግብ ለመቻል ደፋ ቀና በሚል ሕዝብ ውስጥ ዐበይት ጉዳይ ነው።

ተግዳሮቶቻችንን ወደ በረከት ለመቀየር ሀገር የቀደመችበት የአመራር ጥበብ ያስፈልገናል። ራሳችንን አስቀድመን ትውልዱን በማስከተል የምንመራው ፖለቲካ፣ የምንወደው ሕዝብ፣ የምናልመው ሕልም ትርጉም አልባ ነው። ከእንዲህ አይነቱ መሠረታዊ ችግር ስንወጣ ነው ለአዲስ ለውጥ በር የምንከፍተው።

በሥርዓት ካላደግን ሕዝብ በማገልገል ረገድ በበጎ የሚጠቀስ ስም አይኖረንም። በግብረገብነት አድገን ከሆነም በእኩይ ምግባር ሀገር ለማዋረድ እድል ፈንታ አናገኝም። ለኢትዮጵያ መከራ የሆኑባት ከአስተዳደግ ጀምሮ ባለው ታሪካቸው ላይ አግድም ያደጉ ከእምነትና ከሥርዓት ያፈነገጡ ናቸው። ድምፅ ማጉያ ሲይዙ አፋቸው የሚያወራ በተግባር ሲፈቱ ግን እዚህ ግባ የማይባሉ ዱባና ቅሎች።

ሙስና ዓለም አቀፍ ችግር ቢሆንም ጎልቶ የሚገኘው እንደእኛ ባሉ በአስተሳሰብና በሥልጣኔ ባልዳበሩ ሀገራት ውስጥ ነው። ሥልጡኖቹ ሀገራት ሀገር ማለት ምን ማለት እንደሆነ ስለገባቸው ከራሳቸው ላይ ለሀገር ይሰጣሉ እንጂ ማንም አላየኝም ወይም አያየኝም ብለው ከሀገራቸው ላይ ለራሳቸው አይሰርቁም።

ይሄ የሀገር ፍቅር ጽንሰ ሀሳብ ነው በሥልጣኔም በዘመናዊነትም ላይና ታች ያስቀመጠን። ሀገር ማለት ምን እንደሆነ ሲገባን እንደሥልጡኖቹ ከሕዝብ ላይ አንሰርቅም። ካልገባን ግን በመስረቅና በማሰረቅ ከበር ከፋቾቹ እንደአንዱ በመሆን ሀገር እናራቁታለን።

ሙስናና ሙሰኞች ሀገር በመለወጥ ትግል ውስጥ ሁሉም የድርሻውን እየተወጣ ባለበት ሁኔታ ውስጥ ተጋድሎን የሚያደናቅፉ፣ ተስፋን የሚያደበዝዙ የብርሀን ጽልመቶች ናቸው። እኚህ ጽልመቶች ሲገፈፉ ብቻ ነው እንደ ሀገር ብርሀን የሚወጣልን። በሥልጣንና በአለቅነት ብርሃናችንን ጋርደው ቆመዋል። በተጠያቂነት መርሕ ገለል እንዲሉ ስናስገድዳቸው ያኔ ሁሉም ነገር አዲስ ይሆናል።

ዓለም ስለሙስና መክራና ዘክራ ታውቃለች። እየቀጣችና እያስጠነቀቀች፣ እየሸለመችና እያወደሰች ዓመታትን ዘልቃለች። ሰሞኑን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ20ኛ ጊዜ ‹ሙስና የጋራ ጠላታችን ነው በኅብረት እንታገለው› በሚል መሪ ሀሳብ የፀረ ሙስና ቀን ተከብሯል።

በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር በኩልም ፕሮግራሙን በሚዘክሩ የተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሮ ውሏል። በመዝጊያ ፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አበቤ ‹ሙስናና ሙሰኞች ላይ የሚደረገው ትግል የታይታ መሆን የለበትም እንደሀገር ተጨባጭ ለውጥ የሚያመጣ መሆን አለበት› ሲሉ አጽንኦት የሰጡበትን ንግግር ማስታወስ ያስፈልጋል።

ከዚህ ጋር አያይዘውም ‹ሙስና የሀገርን እድገት በእጅጉ እንደሚጎዳና ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እንዳይኖር በማድረግ በእውነት ላይ ያልቆመ የድህነትና የሀብት ልዩነትን የሚፈጥር በተጨማሪም ሀገር ገቢዋን እንዳትሰበስብ እክል የሚፈጥር ነው› ሲሉ ጥቁምታ አስቀምጠዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን ሀገራዊ ስጋቱን በመመልከት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማ ደረጃ የፀረ ሙስና ኮሚሽን በማቋቋም የፀረ ሙስና ትግሉን ከሆነ ስፍራ አውጥቶ ተቋማዊና ሀገራዊ ለማድረግ ይሁንታ የሚያሳይ ሥራ እየሠራ እንደሆነ በክቡር ከንቲባዋ በኩል መገለጹ ትግሉን የሚያበረታና ይበል የሚያሰኝ እንደሆነ ያመላክታል። በመስተዳድር ደረጃ እንዲህ ያለ የትግል ንቅናቄ ለዛውም ተቋማዊ በሆነ አሠራር መጀመሩ መጪውን ጊዜ በበጎ እንድንቃኝ የሚያደርግ ነው።

ከዚህ ቀደም ስለሙስና የተለያዩ ሀሳቦችን የተለዋወጥንባቸው የተለያዩ መድረኮችን አስተናግደናል። ሀሳቦቻችን ለውጥን ሲያመጡልን ግን አልታዩም። ይሄ ማለት ከንግግር ባለፈ ወደተግባር የሚወስድ ብርታትና ቁርጠኝነት አላዳበርንም ማለት ነው። ከዚህ ረገድ የተነጋገርንባቸውን ሀሳቦች መለስ ብሎ በማጤን ለትግበራ ቁርጠኛ መሆን ሙሰኞችን ለመዋጋት ቀዳሚው ነገር ነው።

ሙስናን ከመከላከል ረገድ እንደዋና መፍትሔ ከተጠቀሱ ሀሳቦች ውስጥ ቀዳሚዎቹ ግልጸኝነትና ተጠያቂነት ናቸው። አሁን ባለው የአገልጋይና የተገልጋይ መስተጋብር ውስጥ የተባለውን ያክል ግልጸኝነትና ተጠያቂነት እንደሌለ ብዙዎች ይስማሙበታል። ይሄ አይነቱ አካሄድ ብልሹ አሠራርን በማበረታታት ሥልጣንን ያለአግባብ ወደመጠቀም መርቶናል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ሌላው የመፍትሔ አካል አሠራርን ማዘመን የሚለው ነው። አሠራርን ማዘመን ማለት ከአስተሳሰብ ጀምሮ፣ ተገልጋይ ተኮር የሆነ እንቅስቃሴን እንደመርሕ በመውሰድ በቴክኖሎጂና በሀገር ፍቅር በታገዘ ሃላዊነት መመራት ማለት ነው።

ግልጸኝነትና ተጠያቂነት ከዘመነ አሠራር እና በሥርዓት ከተቃኘ ኃላፊነት ጋር ተዋሕደው ሲቀርቡ ነው ሙሰኞችን በማጋለጥ ሀገር የምንታደገው። ይህ በእንዲህ እንዳለ ትውልዱን እንደአዲስ የሚቀርጹ የሥርዓትና የግብረገብነት አካላት መኖራቸው የሚያጠያይቅ ባይሆንም የመጣንበት ‹ያበላል እንዴ? እና ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል› አይነት እኩይ አመለካከቶች የዛሬዋን በሁሉ ነገሯ ስንኩል የሆነችን ሀገር እንድንፈጥር አስተዋፅዖ አዋጥተዋል ብዬ አስባለሁ።

ከእንዲህ አይነቱ ማንንም በኩራት ካላራመደ አስተሳሰብ ወጥተን ሀገር ተኮር እና ማኅበረሰብ መር በሆነ የሥርዓት አቅጣጫ ብንመራ የተሻለ ነው ባይ ነኝ። በዚህ ረገድ የሃይማኖት ተቋማት፣ ሲቪክ ማህበራት፣ ትምህርት ቤቶች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ኃላፊነት አለባቸሁ።

በሞራል የተገነባ፣ በተጠያቂነት የጎለመሰ ትውልድ በሥራው ምስጋና ይቸረዋል እንጂ ማንም ጣት አይጠቋቆምበትም። ሙስንና የሚያጋልጥ እና ለምን ብሎ የሚጠይቅ ትውልድ በሌለባት ሀገር ላይ ለውጥ የማይታሰብ ነው። የሆነ አካል ሲሰርቅና ሲያሰርቅ ስናይ መጠቆም ኃላፊነትን ከመወጣት ጎን ለጎን ሙስናን ለማድረቅ እየሄድንበት ያለውን ንቅናቄ የሚያሳልጥም ነው።

ሙስና በአንድ ሀገር ላይ እንደ እከክ ነው። እከክ በወቅቱ ካልታከመ ሰውነትን የሚወርስ ከዛም ወደቁምጥና የሚወስድ ደዌ ነው። ሙስናንም ከዚህ ለይተን ልናየው አንችልም። አነሳሱ ቀላል ቢመስልም መሐሉና ዳሩ ሀገርን አቆርቁዞ፣ ትውልድን አደህይቶ ከድጥ ወደማጥ የሚያስገባ እኩይ ተግባር ነው።

እንደሀገር ብዙ ማኅበራዊ ተግዳሮቶች ቢኖሩብንም የሙስናን ያክል እየጎዳንና እያራቆተን ያለ ችግር ግን የለም። ሙስና ብዙኃን የሚጠቀሙበት ሳይሆን ጥቂቶች ኪሳቸውንና ሆዳቸውን የሚያደልቡበት ነው። ችግሩን ሕዝባዊ ያደረገው ደግሞ ወደአንድ ግለሰብ ኪስ ወይም ካዝና የሚገባው ሀብት የሀገር ንብረት የሕዝብ ላብ እና ድካም መሆኑ ነው። በዚህ ረገድ ሙስናን ለመከላከል ቁርጠኞች እንሁን።

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 8 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You