ሰማይ ጠቀስ ሕንፃዎች ጎልተው ያስዋቧትን የዓለም ምርጧን ከተማ ማየት ከምንም በላይ ያስደስታል፡፡ በተንጣለሉት ፓርኮቿ መዝናናት ማንንም የሚማርክ ነው። በዓለም ያለ ሰው በሙሉ ሊመለከታት ይጓጓል፡፡ በዓለም ላይ ከሚገኙ ምርጥ ከተማዎች መካከል የአንደኝነት ደረጃን ተቆናጥጣለች። የአሜሪካዋ ኒዮርክ ከተማ (New York City)። ስምንት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሕዝብ ይኖርባታል። ነገር ግን የሰዎች ብዛት ሲያስጨንቃትና ሲተራመስባት ፈፅሞ አይታይም፡፡
የዓለም ትልልቅ ግብይቶች እና የፋይናንስ እንቅስቃሴዎችም ይደረጉባታል። አኗኗራቸው እጅግ ዘመናዊነትን የተላበሱ ሰዎች መቀመጫ ነች። ኒዮርክ እአአ በ1898 እንደተመሠረተች መረጃዎች ይጠቁማሉ ፡፡ ከኒዮርክ ቀጥሎ በዓለም ካሉ ምርጥ ከተማዎች ከሚጠቀሱት መካከል የምትመደበው ደግሞ የዩናይትድ አረብ ኤሜሬትሷ ዱባይ ነች። እአአ በ1971 ከብሪታኒያ ቅኝ ግዛት ተላቃ እንደተመሠረተች መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ከሁለቱ ከተማዎች በተጨማሪ ለንደን፣ ፓሪስ፣ ቶኪዮ እና ሌሎችም ከተሞችም በተለያየ መልኩ በምርጥ ከተማነት ተመራጭ ናቸው፡፡
በተቃራኒው የኢትዮጵያ ዋና ከተማና የአፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ ከተቆረቆረች አንድ ክፍለ ዘመን ተሻግራ ሁለተኛውን አጋምሳለች። ይሁን እንጂ ለዘመናት ባረጁና በዛጉ (በተለምዶ ቸኮሌት ቀለም የያዙ የሚል ስያሜ ያላቸው) ጥቋቁር ቆርቆሮዎች አናታቸውን የተሸፈኑ የጭቃ ደሳሳ ጎጆች ታጭቃ ዕድሜዋን ገፍታለች፡፡ ከፕላን ውጪ በተሠሩ መኖሪያዎች፣ ምቹ ባልሆኑ መሠረተ ልማቶች እንዲሁም በሌሎች ውስብስብ ጉዳዮች ለዘመናት ዘመናዊነትን ሳትላበስ ቆይታለች። በዚህ እና በሌሎች ምክንያቶች ሳቢያ ለጉብኝት የማትመች ከተማ ተብላ ተቀምጣለች፡፡ በመግቢያችን ላይ ካነሳናቸው ዘመናዊና ቅንጡ ከተሞች አንፃር አዲስ አበባ ብዙ ዘመናትን ወደኋላ እንደቀረች መገመት አይከብድም።
የዓለም ጎብኚዎች ለሚያካሂዱት ጉብኝት ቅድመ ዝግጅት ሲያደርጉ ያላቸው የገንዘብ መጠን ላይ ተመሥርተው ከተሞችን ሲመርጡ፤ አመራረጣቸው ምርጦቹን ከአስቀያሚዎቹ የሚለይ መረጃን በመሰብሰብ ሲሆን፤ ንጹሑን ከቆሻሻው፤ የሚያስደስተውን ከሚያስጨንቀው ለይተው ለጉብኝት ሲሰናዱ አስቀድመው አዲስ አበባን እንደሚሰርዙ ይነገራል፡፡
ምንም እንኳ በገንዘብ እጥረትም ሆነ በአጋጣሚ አዲስ አበባን መርጠው ቢመጡም ቆይተው ብዙ ቀናትን ለማጥፋት ፍላጎት የላቸውም፡፡ አስደሳች እና ውብ አካባቢን እንጂ አስቀያሚ እና የታጨቀ ልክ እንደ አዲስ አበባ የተጨናነቀ በየጥጋ ጥጉ ቆሻሻ የሚተኛበትን ከተማ ለመቆየት ቀርቶ ለማየት አለመምረጣቸው አያስወቅሳቸውም፡፡
ለመዝናናት የሚመች ጥራት ያለው ፓርክ እና የሚጎበኝ ሐይቅ፣ መሠረተ ልማት ሳይሟላ እና አስተማማኝ የጤና አገልግሎትም ሆነ ምቹ መንገድ ሳይኖር፤ ቀንም ሆነ ማታ የደህንነት ስጋት የሚያንዣብብበት ከተማ ምንም እንኳ የአየር ሁኔታው የተመቸ ቢሆንም ተመራጭ እንደማይሆን አያጠያይቅም፡፡
የእኛዋን አዲስ አበባ ከተቆረቆረች 139 ዓመታትን ማለትም ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ ብታስቆጥርም ከምርጦቹ ከተሞች ውስጥ መቆጠር ቀርቶ፤ ለመጎብኘት የምትበቃ ሳትሆን ቆይታለች፡፡ ዘመናትን ከማስቆጠር ባሻገር ምርጥ የአየር ሁኔታ ያላት እንደሌሎች ከተሞች አብዝታ የማትሞቅ አብዝታም የማትቀዘቅዝ ለሰው ልጅ የሚመች የአየር ሁኔታ ባለቤት የሆነችዋ አዲስ አበባ ለመጎብኘት እምብዛም የማትመረጥ ለነዋሪዎችም ምቾት የምትነሳ ከተማ ሆና ቆይታለች፡፡
ከሰሞኑን ግን አዲስ አበባ ቀን እየወጣላት ልትሞሸር መሆኑን የሚያመላክቱ መጠቆሚያዎች እየታዩ ናቸው፡፡ ለሦስት አስርት ዓመታት አካባቢ ያለምንም ሥራ በቆርቆሮ ታጥሮ የነበረው የአዲስ አበባ እምብርት አሁን ግን የአባት አርበኞችን ተጋድሎ የሚዘክር የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ተገንብቶበት ለጉብኝት በሚያመች መልኩ የአዲስ አበባ መገለጫ ለመሆን በቅቷል፡፡
ከሙዚየሙ በተጨማሪ በወንዝ ዳር ልማትም የአዲስ አበባ ከተማ ቆሽሾ እንዲታይ፤ ሰዎችም በቆሻሻ ቦታ ላይ በመኖር ሕይወታቸውን በበሽታ እየተሰቃዩ እንዲያሳልፉ የሚያስገድዱ አካባቢዎችም እየፀዱ ነዋሪዎቹም ወደ ፅዱ አካባቢዎች እንዲንቀሳቀሱ እየተሠራ ነው፡፡ ይህ አንዳንድ አካባቢን ብቻ ሳይሆን ከተማን የማፅዳት እና ውብ የማድረግ ሥራ የከተማው ሕዝብ ላይ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የሀገር ገፅታ ግንባታ ላይ የሚፈጥረው በጎ ተፅዕኖ ከፍተኛ ነው፡፡
የከተማዋ መሞሾርም ሆነ መዋብ በጎብኚዎች ተመራጭ እንድትሆን ማስቻሉ መንግሥትን ብቻ ሳይሆን በዋናነት የከተማዋን ነዋሪ ተጠቃሚ የሚደርግ ነው፡፡ ጎብኚዎች መጥተው ለእያንዳንዱ አገልግሎት ማለትም ሆቴል እና የእንግዳ ማረፊያ ማከራየትን ጨምሮ ምግብ እና መጠጥ የመሳሰሉትን አገልግሎት በከተማው ውስጥ መሸመታቸው፤ የትራንስፖርት አገልግሎት እና ሌሎችም የመዝናኛ አገልግሎቶችን የሚያቀርቡ የከተማዋ ነዋሪዎች ገንዘብ እንዲያገኝ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡
የገንዘብ መገኘት የከተማዋን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ለማሳደግ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል፡፡ ይህ የከተማው ሕዝብ ገቢ የማግኘት ሁኔታ የነዋሪው የሕይወት ደረጃ ከፍ እንዲል የሚያግዝ ይሆናል፡፡ ገቢው ያደገ ሕዝብ በምቹ ሁኔታ የመኖር ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡ በመሆኑም አሁን ላይ የከተማ አስተዳደሩም ሆነ የፌዴራል መንግሥት አዲስ አበባን ለማስዋብ እያደረገ ያለው ጥረት በነዋሪው ሕዝብ የሚደገፍ እንደሆነ አያጠያይቅም፡፡ የተዋበ እና ምቹ ገቢን የሚሳድግ እና ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ አካባቢን ማን ይጠላል?
ቀደም ሲል አዲስ አበባ በተለይም አራት ኪሎ አካባቢ ምን ይመስል እንደነበር የኖረበት ብቻ ሳይሆን ሲያልፍ የጎበኘ ሰውም ብዙ ሊል ይችላል፡፡ ምቹ የሆነ መፀዳጃ ቤት እንኳ በቅጡ የማይገኝበት፤ በአንድ ክፍል ቤት ውስጥ ቆጥ ተሠርቶ አምስት እና አሥር ሰው ታጭቆ የሚኖርበት፤ መራመጃ መላወሻ ያልነበረበት አካባቢ ነበር።
አሁን ግን አብርኆትን የመሰለ ትልቅ ቤተ መጽሐፍት እና ወዳጅነትን የመሰለ ፓርክ ተገንብቶበት የድሮው ቦታ ፍፁም ተቀይሯል። በተጨማሪም የልጆች መጫወቻን ያካተተ አካባቢ ሆኖ ለከተማዋ ውበትም ለነዋሪው ምቾት ሆኗል። እንደቀድሞ አካባቢውን አይቶ መጨነቅ ሳይሆን መንፈስን ማደስ ከተጀማመረ ቆይቷል፡፡
ሰሞኑን ደግሞ ፒያሳ ዶሮ ማነቂያ አካባቢን ጨምሮ፣ አራት ኪሎ አካባቢ እና ሌሎችም በወንዝ ዳርቻ አካባቢዎች ያሉ መንደሮችን በማፅዳት በአዲስ መልክ የማስዋብ ሥራ እየተከናወነ ነው፡፡ ይህ ሥራ ምንም እንኳ ያለምንም እንከን እየተከናወነ ነው ብሎ በድፍረት ለመናገር ቢያስቸግርም፤ በከፍተኛ ጥረት እና ቅንጅት ሃያ አራት ሰዓት የሥራ ዘመቻ በማካሔድ በፍጥነት አካባቢዎቹ እጅግ የተዋቡ እንዲሆኑ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ በእዚህ ሒደት የከተማ አስተዳደሩ በቻለው አቅም ከአካባቢው ላይ የሚነሱ ነዋሪዎችን ምትክ ለመስጠት እያደረገ ያለው ጥረት በተመለከተ ብዙዎች መልካም መሆኑን በመግለፅ ላይ ይገኛሉ፡፡
ለውጥ ለአንዳንዶች ደስታ ለአንዳንዶች ደግሞ ጊዜያዊ ጭንቀት ቢኖረውም ጊዜው የሚመጥነውን ለውጥ ተከትሎ ራስን ማዘጋጀት ደግሞ የግድ ነው፡፡ ጊዜያዊ ጭንቀትን በመፍራት ሁሉም ነገር ዘለዓለም እንደነበረ እንዲቀጥል መፈለግ፤ መመኘትም ሆነ ባለፈ ጊዜ ላይ ተጣብቆ መታደስ የለበትም ማለት ሞኝነት ነው፡፡
መንግሥት ከዓለም ጋር ተወዳዳሪ ሆኖ የዓለምን ትርፍ በቱሪዝምም ሆነ በሌላ መንገድ ለማግኘት የሚደርገውን ጥረት ለማደናቀፍ መሞከርም ‹‹ኢትዮጵያዊ ነኝ ሀገሬን እወዳለሁ ›› ከሚል ዜጋ የሚጠበቅ አይደለም፡፡ በእኔ በኩል አሁን የተጀመረው የልማት ሥራ ሲገባደድ ከተማችን እጅግ ያማረችና በጎብኚዎች ተመራጭ የሚያደርጋት ገፅታን እንደሚያላብሳት አምናለሁ። ሰላም!
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 14 ቀን 2016 ዓ.ም