ኢትዮጵያ የብዙ ባህሎች ባለቤት መሆኗ የበርካታ ባህላዊ ጨዋታዎችና ስፖርቶች ሀብታም እንድትሆን አድርጓታል:: በሀገሪቱ ጥናት 292 የሚሆኑ ባህላዊ የስፖርት ጨዋታዎች ቢኖሩም ሕግና ደንብ ወጥቶላቸው ውድድሮች የሚካሄዱት ግን በ11 የስፖርት ዓይነቶች ብቻ ነው:: እነዚህም በተለያዩ ክልልችና ከተማ አስተዳደሮች በፌዴሬሽን ደረጃ የሚመሩ ሲሆን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን አንዱ ነው።
ፌዴሬሽኑ በከተማዋ የባህል ስፖርቶችን ለማሳደግ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን የሚያደርግ ሲሆን ዓመታዊ ውድድሮችን ማካሄድ፣ የባለሙያዎች ሥልጠና እና የታዳጊ ፕሮጀክት ዋነኞቹ ናቸው:: ፌዴሬሽኑ ከሚያካሂዳቸው ውድድሮች መካከል የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ በክፍለ ከተሞች መካከል የሚካሄድ ባህላዊ ፌስቲቫልና ስፖርታዊ ጨዋታዎች፣ ከተማ አቀፍ የተማሪዎች፣ የታዳጊ ወጣቶች ፕሮጀክቶች እና ባህላዊ ሆቴሎች ውድድር ይገኙበታል። ፌዴሬሽኑ ስፖርቱን ለማሳደግ እነዚህንና ሌሎች የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ ሲሆን በትምህርት ቤቶችና ሆቴሎች ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራም ይገኛል::
የአዲስ አበባ ባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፈቃደ ጫካ፣ ፌዴሬሽኑ ሁለት ዋና ዋና ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልፀው፣ ከነዚህም መካከል የባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ሥልጠና (የዳኞችና አሠልጣኞች ሥልጠና)፣ በሁሉም ክፍለ ከተሞች የሚገኙ የታዳጊ ወጣቶች ፕሮጀክት ሥልጠና፣ የባህላዊ የስፖርት ውድድሮች መካሄዳቸውን ይናገራሉ:: በተጨማሪም ከተማአቀፍ የተማሪዎችና ሆቴሎች ውድድሮች በተለየ ትኩረት እንደሚካሄዱ ያስረዳሉ። ይህም ተተኪዎችን ለማፍራትና ስፖርቱን ለማሳደግ ትልቅ እገዛ ይኖረዋል ተብሎ ታምኖበታል።
የጽህፈት ቤት ኃላፊው እንደሚናገሩት፣ አምና በትምህርት ቤቶች ላይ የተጀመረውን ከተማአቀፍ የተማሪዎች ውድድር ዘንድሮም ለማስቀጠል ከአንድ ክፍለ ከተማ ሶስት ርዕሰ መምህራን እና የስፖርት መምህራን ተመርጠው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ተሰጥቷ:: በተያዘው ዓመትም በ 33 የከተማዋ ትምህርት ቤቶች መካከል የተማሪዎች ባህል ስፖርቶች ውድድር ለማድረግ ታቅዶ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል።
የባህል ምግብ ቤት ያላቸው አስር ሆቴሎች መካከል አምና መካሄድ የጀመረው የባህል ስፖርቶች ውድድር ዘንድሮም ለሁለተኛ ጊዜ ለማካሄድ ዝግጅቶች እየተደረጉ ይገኛሉ:: በአምናው ውድድር ቶቶት፣ ሶራምባ፣ ጊዮን፣ ዮድ አቢሲንያ፣ ካፒታል፣ ፍል ውሃ አገልግሎቶች ተሳትፈዋል:: የውድድሩ አሸናፊ የነበረው ቶቶት የባህል ምግብ አዳራሽ የዘንድሮውን ውድድር የሚያዘጋጅ ሲሆን ሌሎች ተጨማሪ ሆቴሎች ውድድሩን እንደሚቀላቀሉ ይጠበቃል።
የታዳጊ ስፖርተኞች ውድድር ፌዴሬሽኑ ተተኪ ስፖርተኞችን እያፈራበት የሚገኝ መሆኑን የሚያስረዱት የጽህፈት ቤት ኃላፊው፣ በሆቴሎች መካከል የሚካሄዱት ውድድሮች ከነዚህ ፕሮጀክቶች ስፖርተኞችን በመመልመል እንደሆነም ተናግረዋል። ይህም ታዳጊዎች ከየፕሮጀክቱ ተመርጠው ሆቴሎችን በመወከል የውድድር እድሎችን እንዲያገኙ ያስችላል። ሆቴሎችና ትምህርት ቤቶች ላይ እየተከናወኑ በሚገኙት ሥራዎች ስፖርተኞች የተሻለ አቅምን እየገነቡ ከተማውን በሀገር አቀፍ ደረጃ ተፎካካሪና ውጤታማ ማድረጉንም ይናገራሉ:: ፕሮጀክቶች ትምህርት ቤቶችና ሆቴሎች ላይ ለሚከናወነው የባህል ስፖርቶች እንቅስቃሴ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበረከታቸውንም አክለዋል።
በክፍለ ከተሞች ሁለት ዓይነት የባህል ስፖርቶች ፕሮጀክት ሥልጠና ተግባራዊ እየተደረገ ሲሆን፣ በከተማው ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ሥልጠና ዳይሬክቶሬት ድጋፍ የሚንቀሳቀሱ ስድስት ፕሮጀክቶች እና ክፍለ ከተሞች በራሳቸው አቅም በአምስት ትምህርት ቤቶች ላይ እየሠሩ ነው:: ከነዚህም መካከል ተጨማሪ ሶስት ፕሮጀክቶች በከተማው ሥልጠና ዳይሬክቶሬት እንዲደገፍ ለማድረግ ታቅዶ እየተሠራ እንደሚገኝ ይጠቁማሉ:: በዚህም መሠረት በ 11ዱም ክፍለ ከተሞች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የታዳጊ ወጣቶች ፕሮጀክት ተቀርፆ እየተሠራበት ነው።
ሆቴሎች ፕሮጀክቶችን በመያዝ ቡድን እንዲመሠርቱ ለማድረግ እቅዶች ተቀርጸው ተግባራዊ እንዲሆኑ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ የጽህፈት ቤት ኃላፊው ገልፀዋል። የባህል ስፖርቶች ከፍተኛ ጠቀሜታ ስላላቸው ማስፋፋት፣ ጠብቆ ማቆየትና ለተተኪው ትውልድ ማስተላለፍ የፌዴሬሽኑ ኃላፊነት በመሆኑ፣ በዚያ መሠረት እየተሠራ መሆኑንም አብራርተዋል። ለዚህም በአዲስ አበባ ከተማ ባህል ቱሪዝምና ኪነ-ጥበብ ቢሮ አማካኝነት ከከተማዋ ሆቴሎች ጋር በቅንጅት እየተሠራ ይገኛል:: በተጨማሪም ከትምርት ቢሮ ጋር ተማሪዎችንና መምህራንን ለማሠልጠን በቅንጅት እየተሠራ ነው።
ከዚህ በፊት ጥቂት ውድድሮች ብቻ የነበሩ ቢሆንም አሁን ግን የሆቴሎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ የታዲጊ ወጣቶች ውድድር እንዲኖር ሰፊ ሥራ ተሠርቷል:: ፌዴሬሽኑ ሕዝባዊ መሠረት ይዞ የራሱን የገቢ ምንጭ እንዲፈጥር አጋር አካላትን በማግባባት እቅድ ተያይዞ እየሠራ ነው:: አቅም ግንባታ ላይ አጋር አካላት የሚያደርጉትን ድጋፍ ከማነሱ ውጪ ፌዴሬሽኑ በውጤትም ሆነ በሌሎች ነገሮች የተሻለ ደረጃና እንቅስቃሴ ላይ መሆኑንም የጽህፈት ቤት ኃላፊው ጠቅሰዋል።
በመጪው ታህሳስ ወር በክፍለ ከተሞች መካከል ለሚካሄደው ዓመታዊው የባህል ፌስቲቫልና ባህል ስፖርቶች ውድድር በክፍለ ከተማና ከተማ ደረጃ ከክረምት ጀምሮ ዝግጅቶች እየተደረጉ ሲሆን፣ ከታህሳስ አጋማሽ ጀምሮ ውድድሮቹን በማካሄድ ከገና በዓል በፊት ለማጠናቀቅ መታቀዱን ኃላፊው ያስረዳሉ::
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም